Saturday, 04 January 2025 00:00

ሆድዬ

Written by  ሙሉጌታ ቢያዝን
Rate this item
(5 votes)

ከዕለታት ባንዱ ቀን ባንድ ቁርጥ ቤት ቁጭ ብለን ፍርፍርና ላላ አዝዘን እየበላን ስልኳ ጠራ፡፡ ስልኳ ሲጠራ ብልጭ የሚለው ነገር (flash ) አለው፡፡ ከማንሣቷ በፊት ፈገግ ብላ “እቴቴ ናት” አለችኝ፡፡ እናቷን “እቴቴ ነው” የምትላት፡፡ ምን እሷ ብቻ መላ ቤተሰቡ እንዲያ ነው የሚላት፡፡ ስልኩ ከሚረጨው መብራት ለመከለል እጄን እየጋረድኩ “እኮ አንሺዋ” አልኩኝ፡፡ ተበሳጨሁ እንዴ?
“ደረቅ እንደሱ አይባልም! አይደረግም!” ብላ ክንዴን ከቆነጠጠችኝ በኋላ ወደ ‘ሬስት ሩም’ ተጣደፈች፡፡ ስልኩን ጨርሳ ስትመለስ “ክፈልና እንሒድ!” አለች፡፡
“ምን መጣ?”
“ክፈልና እንሒድ አልኩኮ ‘ከተማ ውስጥ ረብሻ አለ’ አሉ፡፡”
“መች ሰላም ውሎ ያውቃል?”
“ሆሆሆ…ቀልዱን ተውና ባጃጅ ጥራ…” ብላ ውብ ዐይኗን ስታጉረጠርጥብኝ አስተናጋጁን ተጣራሁ፡፡
የኔ ውድ ማናት? መቅዲ ማናት? እንዴት ተዋወቅን?
ከዕለታት ባንዱ ቀን (እንዲያ ማለት ትወዳለህ ይሉኛል ፎታች ወዳጆቼ)… ከፒያሳ 33 ቁጥርን አውቶብስ ይዤ ወደ ኮተቤ (የታክሲ ረዳቶቹ ‘ኩተቤ’ የሚሉት) መሳለሚያ እየሔድኩ ነበር፡፡ ዐራት ኪሎ ላይ አንዲት ልጅ ገባች፡፡ እንደምን ያለች ናት? ዳሌዋ ኩሩ ነው? መቀመጫዋ ያምራል? እኔ እንጃ! ‘በደንብ አልገለጻትም’ ብለው ሐያሲያን ይውገሩኝ እንጂ አልናገርም፡፡ የእራስን ሰው እንዲያ ማለት ይቻላል? ልክ አይመጣም እኮ!
ብዙ ገጠመኝ ግን አለኝ፡፡ ሸጋ ጠባይ ካላችሁ አንዱን አሁን እነግራችኋለሁ፡፡ ዝግጁ?
ከዕለታት ባንዱ ቀን የምትወደውን ደረጃ 1 ማስቲካ ‘ፖፖቲን’ የተሰኘ (አሁን ‘ትሪደንት’ ተክቶታል መሰል?) ልገዛ ወደ ኋላ ቀረት ብዬ ነበር፡፡ አንድ ወጣት “እናቱ መቀመጫሽ እንዴት ያምራል! የት ነው የማውቀው? እርግጠኛ ነኝ የኾነ የአማርኛ ፊልም ላይማ ዐይቸዋለሁ፡፡” ፈገግ እያለ “ከምር ግን የእራስሽ ነው?” የኔ እናት! ከማፈሯ የተነሣ ‘ረዥም ምላሱን ቢሰበስብልኝ ’ብላ የቀላ ፊቷን ወደሱ አዞረች፡፡ መቀመጫዋን ከዐይኑ ማሸሽዋ ነበር፡፡ አጅሬ ሊተው ነው?
“እንዴ! ከኋላም ከፊትም ማማር እንዴት ነው ነገሩ ጎበዝ? እረ ‘ፌር (fair)’ አይደለም? ምንም ለሌለው እናካፍል እንጂ!”
ሆዴን ይዤ ስስቅ ዞር ብሎ ዐየኝና ድንግጥ ብሎ ጠጉሩን እያፍተለተለ “እረ ብሮ (bro) ሰው አለ አይባልም እንዴ? እ?…ከምር ‘ፌር’ አይደለም”፡፡
መቅዲ ይህ ሳቄ አናዷታል መሰል፡፡ ፊቷ ፍም መስሎ “እረ በደንብ ሳቅ! አንተ ምናለብህ!” አስከትላም ግራ በተጋባ ግን ደግሞ ለማወቅ በመሻት ድምፀት፤ “እኔ የምልህ ያንተ የኾነችን ሴት ሌላ ወንድ ሲለክፋት ምላሽህ ሳቅ ነው?”
እንዲህ ዓይነት ቦምብ ጥያቄዋን ለምጀዋለሁ፡፡ ንጹህ ልብ የሚጠይቀውን ጥያቄ በብቃት የሚመልስ እርሱ ብጹእ ነው፡፡
“ማን ቆንጆ ሁኚ አለሽ?”
ክንዴን ጨምድዳ “አትቀልድ የምሬን ነው”
“ብቻሽን ነበርሽ እኮ ማሬ፡፡ ሴት ብቻዋን ትኾን ዘንድ መልካም አይደለም፡፡ ሴት ብቻዋን ከኾነች ባትደፈርም አልተደፈረችም አይባልም” አልኩ ውድነሽ በጣሙን የነፍስ አባት አፍ ተውሼ፡፡
“የቀረብኩህ ሲመስለኝ ትርቅብኛለህ፣ ያወቅኩህ ሲመስለኝ ይበልጥ ትርቅብኛለህ” አለችና ይበልጥ ደረቴ ላይ ተለጥፋ ከንፈሬን ታየኝ ጀመር፡፡ … ያለ ቃል፣ ያለ ንክኪ በዐይኗ ከንፈሬን ስትስመኝ ታወቀኝ፡፡ /እራሴን አዋደድኩ እንዴ?/
… ዐራት ኪሎ ላይ አንዲት ጠይም ልጅ ገባች፡፡ መገናኛን እንዳለፍን ቲንጥየ የምሳ ዕቃ በቲንጥየ ቦርሳ በትክሻው ያንጠለጠለ ሰው ከኋላዋ ይጠጋታል፡፡ …ይጠጋታል…ይጠጋታል… ይጠጋታል፡፡ ይጠጋታል ብቻ ሳይኾን ከፊት ከቆሙት ሰዎች ጋር ያጠጋጋታል፡፡ ምን ያጠጋጋታል ያላትማታል ማለቱ ሳይሻል ይቀራል? ! ልጅቱ ቢጨንቃት ምንም ፍሬቻ ሳታበራ መሬት ላይ ዝርፍጥ አለች፡፡
ለክፋቱ ደግሞ ጂጂ ታዜማለች፡፡ እንዲህ እያለች “…ተው ሽሸኝ አልሸሽም ተው ሽሸኝ አልሸሽም እንዲያ ስንባባል አለብኝ ጭልምልም…” ይሄኔ ከወንበሬ ብድግ አልኩና ከጎኔ ላለው ጎልማሳ ሰው እንኳ ወንበሬን አደራ ማለት አልደፈርኩም፡፡ የዛሬ ጊዜ ሰው ለአደራ ይበቃል እንዴ? እናም ባንድ እጄ ወንበሩን፣ በሌላኛው እጄ ልጅቱን ክንዷን ጨምድጄ ወንበሬን አስረከብኳት፡፡ (ወንበር ማስረከብ እንዲህ እንደ ዘበት! ሆሆሆ…የኛ ሀገር ፖለቲከኞች ሳይናደዱብኝ ይቀራሉ?) ከኋላዋ ‘ግፋ አባቴ’ ሲል የነበረው ሰው በጎሸ ዐይኑ አጉረጠረጠብኝ፡፡ የቆመ ቀንዱን ወጥሮ “…‘ልውጋ፣ልስረቅ’ እያለ ሲቅበዘበዝ እጅ ከፍንጅ የያዝኩት እኔ ምን ያስፈራኛል?” ስል እራሴን አጀገንኩት መሰል ዐይኑን ከኔ ላይ አሸሸ፡፡ ተመስገን!
አንገቱን አቀርቅሮ ዐይኔን ሲሸሽ… ሲሸሽ… ሲሸሽ… ቆይቶ መውረጃው ሲደርስ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ምቀኛ!
ከትናንቷ ‘ልጅቱ’ ከዛሬዋ ‘መቅዲ’ ጋር የተዋወቅነው በዚህ መልኩ ነበር፡፡
ከኋላም ከፊትም የምታምረዋን ሴት የሰጠኝን የአንበሳ አውቶብስን ውለታ፣ ዛሬ ባቡር መጣ ብዬ የምረሳ ሰው አይደለሁም፡፡ ከቶዉኑም! እንድያውም የአንበሳ አውቶብስ ቀን እንዲታወጅ በግሌ እፈልጋለሁ፡፡
መቅዲና እኔ ባጃጅ ጠርተን እንደገባን “ውዴ አትወጂኝም?” የባጃጁ ሹፌር በ’ስፖኬ’ው ሲሾፈን ዐየዋለሁ፡፡ ምን ማየት ብቻ ጆሮውን እዚች ወሳኝ ምላሽ ላይ እንደተመሰጠ ያወቅኩት ከኋላ የመኪና ጥሩንባ ሲያንባርቅብን ነው፡፡
“አንተ እኮ ነህ! የሥራህን ይስጥህ” ብላ ስቃ የማታውቀውን ሳቅ (ወይም ሰምቼው የማላውቀውን ብለው ይሻላል መሰል?) ሳቀች፡፡ የባጃጁ ሹፌር እንደተናደደ ከአነዳዱ መገመት ይቻላል፡፡
“እኮ ንገሪኛ ውዴ አትወጂኝም?”
ክንዴን እየቆነጠጠች “ደረቅ! መጀመሪያ ሲጃራና ጫትህን ተው!” የባጃጁ ሹፌር ድምፅ አውጥቶ ‘እርፍ’ አላለም?! ይሄ ክፉ! እኛ ለጥላቻ ጊዜ የለንም፡፡ ፍቅር ብቻ! ፊቷ ቅጭም ብሎ የቀላው ጉንጬን ሳመችኝ፡፡ እራሷ ትወግረኝ ይኾናል እንጂ በፍጹም ከሚወግሩኝ ወገን ቆማ አትገኝም፡፡ በጭራሽ!
እንዲህ ናት እሷ፡፡
የእቴቴ ልጅ ቁጥብ ናት! የእቴቴ ልጅ ሐቀኛ ናት! የእቴቴ ልጅ ሆደ ቡቡ ናት!
የእቴቴ ልጅ የዋህ ናት! ከሁሉ አብልጬ የምወደው ይሄን የዋህነቷን ነው፡፡ አንድ ቀን ሳጨስና ስቅም ዐይታኝ አታውቅም፡፡ ማንም እንዲያ ሲያደርግ ‘ዐየነው’ ያላትም ከቶ የለም፡፡ አንድስ እንኳ! ሊነግሯትም አይችሉም፤ቢነግሯትም አታምንም፡፡ ከኔ በቀር ማንንም አታምንም! ማንንም!
እኔ ነኝ ለቀልድ ብዬ የነገርኳት፡፡ እኔ ነኝ በእራሴ ላይ ያሟረትኩት፡፡ ወዲያውም ፈተና መኾኑ ነው መሰል? ሰው እራሱን ፈትኖ ሳይጨርስ ሌላ ይፈትናል? አያሌ ‘April the fool’ ነገሮች በሕይወታችን ይገጥሙናል፡፡ “ይሄን እንደ አንዱ ቁጠሩት” ብለን ማለፍ ግን የምንችል አይመስለኝም፡፡
የውዴን የተደበቀ ውበት አሳየኝ እንጂ፡፡ “ትምባሆ እምጋለሁ፣ ጫትም እበላለሁ” አልኳት፡፡ የነገርኳትን አመነች፡፡ እምነት ፍቅርን ይቀድመዋል ወይስ ይከተላል? አምናም አልቀረች፡፡ አዘነችልኝ ወይም አዘነችብኝ፡፡ ለዚህ ነው ይበልጥ የምወዳት! ለዚህ ነው እንደ ነፍሴ የምወዳት! “ትምባሆ እምጋለሁ፣ ጫትም እበላለሁ” ማለቴን “እውነተኛ ፍቅር አይዋሽም…፡፡ ለዛ ነው ገመናህን ገልጠህ ያሳየኸኝ” ነበር ያለችው፡፡ ይቺ በተሳሳተ ዘመን የተፈጠረች ትክክለኛ ሴት ናት፡፡ (She is the right person but born at the wrong time የሚባልላት) እሷ ደብዝዛ ብዙ አስመሳዮችን የምታጋልጥ ንጹሕ ነፍስ!
***
ስልኳን እያቀበለችኝ፤ “ስወድህ ይሄን መብራት አጥፋልኝ፡፡ ዐይኔን ሊያጠፋው ነው’፡፡ የሰውንም ግልምጫ አልቻልኩትም፡፡”
“እዚች ላይ ከሳምሽኝ ብቻ” ብዬ ከንፈሬን በሌባ ጣቴ እየተመተምኩ አሳየኋት፡፡
“እኮ እዚሁ? ሰ…ው ፊት?” አለች ዐዩኝ አላዩኝ ብላ እየተገላመጠች፡፡ የኔ ውብ!
“አዎ” ብዬ ድርቅ!
“ደረቅ! ጉንጭህን እስማለሁ” ብላ ከመቅጽበት ጉንጬን ሳመችኝ፡፡ ምኔን እንደምትነካው እንጃ እንኳን ስማኝ በጇ ስትነካኝ፣ ጊዜ የቆመ ይመስለኛል፡፡ ወዲያው ስልኳን ተቀብዬ ካስተካከልኩ በኋላ መሥራትና አለመሥራቱን ለማረጋገጥ በኔ የስልክ ቁጥር ስደውልላት ማን ብሎ ቢወጣ ጥሩ ነው?- ‘my love’
የጣሉትን ነገር ሲያገኙ ወይስ አዲስ ነገር ማግኘት--የቱ ያጓጓል? የቱ ይበልጥ ልብን ያሞቃል? የያዙትን ወይስ ተስፋ ያደረጉበትን ነገር ማጣት---የቱ ይበልጥ ያሳዝናል? የትኛው ይበልጥ ልብ ይሰብራል?
ካህሊል ጂብራን “ለሷ ከተፈጠረው ከእውነተኛ አፍቃሪዋ በቀር የሴትን ልብ ማን ያገኘዋል?” ብሎ የለ፡፡ እናም ይሄን (‘my love’) መልእክት ካነበብኩ በኋላ ልቧን ‘በርብሬያለሁ’ና ምድር ጠበበችኝ፡፡ /የክንድን መቆንጠጥ መልእክት የማይስት ሰው ይሄ እንዴት ይጠፋዋል? የሚል ባይጠፋም ንጉሥ የሆንኩ ያህል ተሰማኝ፡፡ ጨነቀኝ፤እንቅልፍ አጣሁ፡፡ ንጉሥነት ያስጨንቃል? ታድያ አሁን ድንገት ተነሥቼ ‘አላጨስም አልቅምም ነበር እኮ!’ ብላት ዳግም የምነግራትን ታምነኛለች? እውነተኛ ፍቅር አይዋሽም ትል የለ? ለምን ዋሸኋት? ከንጉሥነት ወደ ሕዝብነት፣ ከሸክላነት ወደ ገልነት እንዲህ እንደዋዛ?! አይደረግም፡፡
እናስ እንደ ከዚህ በፊቱ ከባጃጅ ስትወርድ “ውዴ አትወጅኝም?” ስላት፣ ምን ትለኛለች?
“ደረቅ መጀመሪያ ሲጃራና ጫትክን ተው!” ከሚለው ምላሽዋ ጋር እኮ የቤተሰብ ያህል ተላምደናል፡፡
“ውዴ አትወጅኝም ?” ስላት ምን ልትለኝ ትችላለች?
“ ዋሾ! መጀመሪያ ታማኝ ሁን!”
በስመ አብ አይኾንም!
እናስ እንደከዚህ በፊቱ ከባጃጅ ልትወርድ ስትል “ውዴ እኔ ግን ምንሽ ነኝ?” ስላት፤ ምን ትለኛለች?
ዐይንዋ እምባ እንዳቀረረ ቃሉ እየተናነቃት “ንጹህ ወንድሜ!”
በስመ አብ አይኾንም! ከዚህ ከዚህማ ሲጃራና ጫት ብጀምር ይሻላል! (ቂቂቂቂ…)

Read 172 times
More in this category: « ህልምና እውን