Saturday, 04 January 2025 00:00

ከባዶ ላይ እንዲህ የሆነ ፥ ከሙላትማ እንዴታ!

Written by  ዙፋን ክፍሌ
Rate this item
(2 votes)

“አልበላሽምን ምን አመጣው..?”
ይኸ “ ‘ምላሸ አንባቢ’ (Reflection?) ነው “ በማለት እንጀምራለን። ዘሪሁን አስፋው (ነፍስ ኄር) እንደ አንድ የስነ ጽሁፋዊ ሂስ ዓይነት ጠቅሶታል - ‘ምላሸ አንባቢ’ ን። ይህ ሂስ (Reflection) የአንባቢው የሃይማኖት፥ የንባብ ልምድ፥ የግል ዕይታ፥ ዕድሜ..ወዘተ ላይ ጥገኛ በመሆኑ እንደ ሌሎቹ የሂስ አሰጣጥ ቴክኒኮች ስነ ጽሑፍን በምልዓትና ጥልቀት የማይመራመርና የላላ ሊሆን ይችላል።
ስለ’ሱ ላወራለት/በት የተነሳሁለት/በት መጽሐፍም የጥልቅ ሂስና ተምሰልስሎት ውጤት ነውና - ‘ሂስ’ ራሱን እያሄስኩ አይደለም ለማለት ነው መሰል መውተርተሬ። አጓጉል ትሕትና ቢጤ። የጮሌ ትሕትና። “አልበላሽምን ምን አመጣው..?” ይለኛል መጽሐፉ። እንዝለቅ በሉ...
” ከባዶ ላይ መዝገን “
ከባዶ ላይ መዝገን በ ፳፻፩፬ ዓ.ም የታተመ የደራሲ ያዕቆብ ብርሃኑ [ከ ‘ሠለስቱ ጣዖታት’ እና ከ ‘የካህሊል አማልክት’ ቀጥሎ] ሦስተኛ መጽሐፍ ሲሆን፤ ፳ ማለፊያና ሁነኛ መጣጥፎችን በ፻፵፮ ገጾች ውስጥ የቀነበበ ምጥንና እምቅ ሥራ ነው።
፩. ርዕስ ፥ የሽፋን ስዕል፥ የውስጥ ቅንብር
ርዕስ:
ያዕቆብ ርዕሶቹን ይሁነኝ ብሎ(intentionally) እና ጥቂት እንግዳ (a bit strange) እንዲሆኑ አስቦ የሚመርጥ ይመስለኛል። ርዕሶቹ ጎርባጭ ቢጤ (somewhat odd) ኢመደበኛና የከረሩ (extraordinary) ናቸው። በመጽሐፉ ውስጥ ከተካተቱ መጣጥፎች መካከል “ከዲያብሎስ ጋር መደነስ”፥ “ከክብና ከአጽም ጋር የመቆዘም ጣጣ“፥ “ጥበብና የጠየመች ሀዘን“፥ “የደራሲነት እብደቶች“፥ “የሌሊት የእግር ጉዞ የእብደት ለዛዎች“፥ “የዚያ ትውልድ መርገምት“፥ “የስብሐት ለአብ የአርባ ዓመታት ቁዘማ“፥ “በራስ ቀብር ላይ መደነስ” ወዘተ የሚሉት ጎንተል፥ ሸንቆጥ፥ ነቃ የሚያደርጉና ‘Odd’ ቃላት ያሉባቸው ርዕሶች ማሳያ ናቸው። “ከባዶ ላይ መዝገን" የሚለውም የመጽሐፉ መጠርያ ርዕስ ‘Odd’ ነው ለእኔ። መሰል ርዕሶችን መጠቀም አንባቢን ከመንገዱ ሰንክሎ “ደሞ ይኸ ምን ያለ ርዕስ ነው?” ፥ “የማነህ መጽሐፍ በል?” ብሎ መጽሐፉን እንዲያነሳ ሊያደርገው ወይም ‘ገር’ አንባቢን ሊያሸሸው ይችላል። እኔን በግሌ “የማነህ መጽሐፍ በል?” እንድል አድርጎኛል።
የሽፋን ስዕል እና የውስጥ ገጽ ቅንብር፡
“የጋቭሬል ጉየሮ መነሻ ሃሳብና የመርኀጽዮን ጌታቸው እጅ አበጅተውኛል” የሚለው የሽፋን ገጽና የኅብር ዲዛይን ሥራ የሆነው የውስጥ ገጽ ቅንብር - ባጭሩ ማለፊያ ናቸው ።
፪. ይዘት(Content) ፥ ጭብጥ (theme?) ፥ ቅርጽና ውበት(aesthetics)
ይዘት (Content)፡
መጽሐፉ በዋናነት የሂስና የተምሰልስሎት ውጤት የሆኑ መጣጥፎች ስብስብ ነው። ከተሄሱ ያገር ውስጥና የውጭ ሃገር የኪነጥበብ ሰዎችና ስራዎች መካከል ፦
ስንዱ አበበ - “የኔ ማስታወሻ” - ውበት፣ ሴትነትና ውበት፣ ውበትና መለኮት፥ ውበትና አምልኮ ተፍታ`ተውበታል። ወንድነት ወንዴነት፥ ሴትነትና ሴቴነት፥ ሰውነትና ጾታ ታርሰዋል። ለስልሰዋል።
አለማየሁ ገላጋይ - “በእምነት ስም” - ስለ እግዚአብሔር እና ስለ እምነት በአሉታ (በአሉባልታም ለማለት እንችል ይሆን? ምናልባት በሆዳችን እንያዝ። ይኸ ራሱ አሉባልታ ሊሆን ይችላልና።)፥ እና መሰል ጭብጦች ተበርብረዋል።
ሳሙኤል ቤኬት - “Waiting for Godot” ስለ ሕይወት ወለፈንድነት (absurdity) እና ከንቱ ጥበቃ፥ አሁንም ስለ እግዚአብሔር በአሉታ እና መሰል ሃሳቦችና ጥያቄና መልሶች..።
ገብረክርስቶስ ደስታ ነገዎ - ስለ ክብ፤ ክብነትና ገብሬ፥ ክብነትና ሕይወት፥ ክብነትና መለኮት ወዘተ ተነስተውበታል።
ስብሐት ለአብ ገ/እግዚአብሔር - ራሱ ጋሽ ስብሐትም ይሁን ወዳጆቹ ያልነገሩን ከተለመደው ታሪክ ወጣ ባለ እይታ ታይቷል - ጋሽ ስብሐት። መሞገት ይቻላል። ምናልባት የስብሐት እጅግ የቅርብ ሰው ከተገኘ መላምቱን[ከሀና ይልማ ጥላው መጥፋት ጋር በተገናኘ] በተጨባጭ መረጃና ትንታኔ (analysis) ማሻሻል፥ ማጽናት፥ ውድቅ ማድረግ ይቻላል።
ጭብጥ (theme?)
በመጽሐፉ የተነሱትን ጭብጦች (themes) ከሞላ ጎደል በ፫ ምድብ ማየት ይቻላል። (ከምጠቅሳቸው ምድቦች ባንዱም ሳይካተቱ የሚቀሩ ይኖሩ ይሆናል)
ምድብ ሀ: ድርሰት፥ ደራሲ፤ ኪነት፥ ከያኒ ፤ ጥበብ፥ ጠቢብ ተነስተውበታል። ተተንትነዋል። ተተችተዋል። ተሞግሰዋል። የደራሲን እዳ እና ፍዳ፤ የድርሰትን ዳገት ቁልቁለት አሳይቷል። ለጥበብ የሚከፈልን ዋጋ፣ እንዴት ያበጁት ትጥቅ፣ ከምን የቀመሙት ስንቅ እውነተኛን ደራሲ ከሐሳዊው (Pseudo) እንደሚለየው በብእር ስል፥ በነገር ብስል ነግሮቶናል።
ምድብ ለ: ጉዞ እና ፍለጋ(ተኀሥሦ - Wandering)፣ ተፈጥሮ እና በተፈጥሮ መደነቅ (ተደሞ - Wondering) ብቸኝነት እና ግለሰብነት። ስለ ጉዞ። ከጉዞም ስለ ፍለጋ። ከጉዞም የእግር ጉዞ። ከጉዞም የሌሊት ጉዞ። ሌሊት ራሱ። ከጉዞም የተራራ ጉዞ። ተራራ ራሱ። ከጉዞም የብቻ ጉዞ። ገና በመግቢያው “..ከሰው ይልቅ ሰዎች ሲበልጡባችሁ ዐይቻለሁና..” የሚለው ደራሲ፤ እንዴት “ሰው”ነትን (ግለሰብነትን) እንዳጎሰቆልነውና “ሰዎች”(Crowd) መሆን ያልቻሉትን እንዴት ዕሩቃን ነዳያን እንዳደረግናቸው፤ ብቸኝነት፣ ብቻ መቆም፣ ብቻ በመሆን ሙሉ መሆን። ግለሰባዊነት እና መሰል ጭብጦችን አትቷል። እነዚህ እንደ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር እና እንደ አንድ ደራሲ ምን ማለት ናቸው? ሂድና አንብብ እንጂ፤ እኔ ሁሉን እነግርሃለሁን? አልነግርህም!
ምድብ ሐ - ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት
የፈረደበት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ተነስቷል። ተተችቷል። ጥምብ እርኩሱ ወጥቷል። የሚያወያይ ነገር አለው። እውነት አለው። ሀሰትም። ስሜትም። ምናልባት Nihilism። ምናልባት መራር እውነታ። ያዝ የሚያደርገንን የመጽሐፉን የመጀመሪያ መጣጥፍ እናንሳ ፦
አንድን ደራሲ “በዚህ ርዕስ፥ በዚህ ጉዳይ ላይ ወይም በዚህ አኳኋን አትጻፍ፣ እኛ የምንነግርህን ብቻ ጻፍ” ማለት የሞኝ ምኞት ነው። ደራሲ የነገሥታትና የስብስብ ዘመነኞች ጸሐፌ ትዕዛዝ አይደለም። ከጉባኤው (Crowd) ርዕስ ጠይቃ መልሳ ለጀምዓው የራሱን የተቀባባ ቃልና ሃሳብ የምትጀባ ብእር ጸያፍ ናት። በበዓሉ ቃል “አድር ባይ” ናት። በያዕቆብም ቁጣ ተሰንዝሮባታል። ልክ ነው።
ነገር ግን “እውን ኢትዮጵያ ሥልጡን ሃገር ነበረችን?” የሚለው መጣጥፍ ከእርሱ[ያዕቆብ] በፊት በሌሎች[በተለይ በፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ‘መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ’ በዝቅተኛ ድምጸት (tone) እና በብሩህ ዓለምነህ ‘የኢትዮጵያ ፍልስፍና’ በከፍተኛ ድምጸት] የተነሳው ክርስትና (በተለይም ምንኩስና) ኢትዮጵያን ከአክሱማዊ [ዓለማዊ፣ ሄሌናዊ፣ ሃያል፣ ሥልጡን] ገናናነት ወደ ላሊበላዊ [መንፈሳዊ፣ ዕብራዊ፣ ትሑት፣ ኋላቀር] ወደ ሆነ መተናነስ ወስዷታል የሚል አተያይ እና አተናተን ላይ በደራሲው የተጨመረ ሐተታ፣ ጠንካራ መከራከሪያ ወይም እዚህ ግባ የሚባል ማጠናከሪያ (Emphasis) እምብዛም ጎልቶ አይታይም። ምናልባት ፊደሉን - “የሰካራም ደብተሮች” እና ምናምኖች ምናምን፤ ላሊበላን - “ገልቱ ሕንጻ” ወዘተ የሚሉ ስድቦችን ከመመረቁ በቀር ያሻሻለው ነገር የለም።
[*] ደራሲው “...ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብቸኛው የፊደል ገበታ ባለቤት ብትሆንም ቅሉ የሚራቀቁበት ጥቂት የሰከሩ ደብተራዎች ብቻ እንደነበሩ መናገር ለቀባሪ ማርዳት አይሆንብኝ ይሆን?” ይላል ገጽ 15 ላይ። ጌታዬ የያኔውን የሜሶፖታሚያውን ‘Cuneiform’ ሆነ የግብጹን ‘Hieroglyphs’ ፊደልስ ቢሆን የነዚህ ክፍለ ዓለማት ‘ጥቂት የሰከሩ ደብተራዎች’ እንጂ ገበሬው አይራቀቅበት እንደነበር ለርሶ ብናገርስ፣ ‘ለቀባሪ ማርዳት አይሆንብኝ ይሆን?’
[*] “..ላሊበላን ጨምሮ የፋሲል ግንብ የመሳሰሉ ‘ገልቱ ሕንጻዎች’ አንድም ለነገሥታቱ ክብር አሊያም ለአምልኳቸው እጅ መንሻ የተሰሩ ናቸው።” ገጽ 21
የግብጹ ፒራሚድ ለማን ክብር ስለተሰራ ነው ሥልጣኔ የሆነው በል? ወይስ ለምን ዓላማ ተብለው ቢሰሩ ነበር “ገልቱ” ከመሆን ይተርፉ የነበር?
[*] “..የጥበብ(ቅኔ) ነገር ተነሳም አይደል። በእርግጥ ቅኔው፣ ዝማሬው፣ ዝማሜው፣ የሥዕልና የጽህፈት ጥበቡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምናልባት ከሺኅ ለሚልቁ ዘመናት ሲከወን፣ ሲከናወን ነበር። ሆኖም ክዋኔው ሁሉ ከሃይማኖታዊ ተግባራት ውጭ የሆነውን የሕይወት ፈርጅ ለመዳሰስ የማይችል ስንኩል ሆኖ አልፏል።” ገጽ 21። አንድ ጥበብና ሥልጣኔ ክብረት ለማግኘት ጭብጡ ዓለማዊና ግሪካዊ [Hellenistic] የመሆን ግዴታን ማን እንደጣለበት መጠየቁን እናቆየውና፣ ደራሲው በዚህን ያህል ኩራት ለመናገር እንዴት ያለ ጥልቅ ጥናትና ምርምር አድርጎ ይሆን ብለን እንገረማለን። ኢትዮጵያ ፥
“በተነ ጊሜ ረቂቅ ዘያአቁሮ ለማይ
ያዐርጎ እምቀላይ ወያወርዶ እምኑኀ ሰማይ” ብላ የተሟላ የ ‘Hydrological Cycle’ ድርሰት ስትደርስ አውሮፓውያን አልቀደሟትም። ኢትዮጵያ ስለ አዕዋፍ፣ ስለ አራዊት፣ እጸዋት እና ከዋክብት ..ወዘተ የጻፈችው ድርሰት፣ የነደፈችው ሥዕል ደራሲውን አልገጠመው ሆኖ ወይም ቢገጥመውም አቀራረቡ ዕብራዊ/ላሊበላዊ [ክርስትና ዘመም፣ አምላክ ዘመም] ብለው ወደሚሸሹት ስለጋደለበት አውቆ ትቶት እንደሆነ አላውቅም።
ደራሲው በዚህ መጣጥፍ ውስጥ ያለው ሁነኛ ዓላማ ምን እንደሆነም አይለይም። የዛሬዎቹን ፋሲል ግንብና ላሊበላ አካባቢ ያሉ ገበሬዎችን ምንዳቤ በማውሳት እነዚህን ቅርሶች ለማጣጣል ይዳዳል። ዓላማው “እውን ኢትዮጵያ ሥልጡን ሃገር ነበረችን?” የሚል መነሻውን “አዎ/አይደለም” ብሎ በማስረጃ ማሳየት ነው ወይስ “ሥልጡን ነበርን ግን መማሰን (Declination) ገጠመን” የሚለውን ቁጭት መግለጥ እንደሆነ ያምታታል። ይደባለቃል። ከአንገት በላይ ‘ሥልጡን ነበርን እሱስ’ ይላል። መልሶ ይሰድበዋል። ደሞ ስድቡን ይጥለዋል። አንዳንዱ ሥልጣኔያችን [ለምሳሌ ሸክላ ስራችን፣ የኮንሶ ኑሮና ፍልስፍና..ወዘተ] ባለመዘከሩና ተገቢ ክብር ባለማግኘቱ ይቆጫል። እና እውን የመጣጥፉ ዓላማ ምን ነበር? በግሌ እንጃ።
ሌላው “እውን ኢትዮጵያ ሥልጡን ሃገር ነበረችን?” እና መሰል ርዕሶች ላይ ሊጽፍ የሚነሳ አንድ ጸሐፊ የሚያደርገውን በቂ ዝግጅት ያደረገ አይመስለኝም። ያለውን ቀዳሚ ሐተታ (thesis) ከምንም ዓይነት አውቆና ሳያውቁ ከሚደረግ ማንጋደድ፣ መቆንጸል፣ መመረዝ፣ መሰረዝ፣ መበረዝ ወዘተ ጸድቶ በቅንና ታማኝ ልቡና በሚገባ መመርመር፥ መረዳት፤ ቀጥሎ አውቆና ሳያውቁ ከሚደረግ ያንድ ወገን ድጋፍ (Partiality)፣ የራስን ሃሳብና ምኞት መጫን፣ እና ሌሎች ጥመቶች በጸዳ መልኩ ለእውነት እንጂ ለራስ እንኳ ሳይራሩ መድፍነ ሐተታ (antithesis) መንደፍና እና እጅግ ልባዌ (Consciousness) እና ጥበብ በሰፈነበት ሁኔታ እርቁን(Synthesis) ማዘጋጀትን ይጠይቃል። የተጠና መፍትሔ መጠቆምም - ከማሁ። ይኸ ደግሞ ሰፊ ገጽ ብቻ ሳይሆን ሰፊ ጥናትና ዝግጅት ይፈልጋል።
አይ ያዕቆብ በዚህ መጣጥፍ ሰፊ ገጽና ጥናት ሳያስፈልገው፣ በዚህች አጭር መጣጥፍ መቆስቆሻ (provocation) እና ማንቂያ ጉንተላ መጎንተል ነው ሃሳቡ እንዳንል በመጣጥፉ ውስጥ የተነሳው ሃሳብ፣ ከላይ እንዳልነው የቆየ እንጂ አዲስ በእርሱ የተነሳ እና ጎንታይ አይደለም።
“የለም አንተም አበዛህ በአንዲት መጣጥፍ እንዲህ ችክ አልክሳ?” ያላችሁኝ እንደሆነ አዎን ጌቶቼ ልክ አላችሁ። ደራሲ ቢሉህ እንዲህ እንጂ ያነጋግርሃል።
ቅርጽና ውበት፡
የአዘቦት የማሄሻ(ሂስ መስጫ) ሙያዊ ቃላት(technical terms) እና የቸኩ (Usual) ቅርጾችን በመከተል አያታክተንም፥ አይዘበዝበንም። አንዱን መጣጥፍ አንብባችሁ እንደጨረሳችሁ የስነ ጽሑፍ ዛራችሁ ከቸች ትላለች። ትልሳችኋለች። ጋል፥ ጋል ይላችኋል። ሞቅ፥ ሞቅ ይላችኋል። አንድ ቲያትር፥ አንድ ልቦለድ፥ ቢቀር አንድ መጣጥፍ፥ ቢቀር ቅንብብ ያለች ግጥም ታስጽፋችኋለች - ያዕቆብ የጠራት ዛራችሁ።
ዛራችሁ አልገባም ብትልስ? ኧረ ከቴም ዛር ባይኖራችሁስ? ሙግት የምትገጥሙበት መጣጥፍ አታጡም። ትወያያላችሁ። ሃሳቡን በሃሳብ ትጥላላችሁ። ለዚያም ባትበቁ ታጣጥላላችሁ። ‘ አንተን ብሎ..’ ትላላችሁ። ነገር ግን ምንም አለማለት አትችሉም። ሙልጭ፥ ፉት አድርጋችሁ የምትወጡት፥ የማትሰድቡት፥ የማትቆዝሙበት፥ የማታጣጥሉት የልጆች መጽሐፍ አይደለም ይሄ። እሱን ሂዱና የነ እገሌ “አድርባይ ብእር” ጫፍ ላይ ፈልጉት። ያች “አድርባይ ብእር” የኔና የእናንተ አፍ ነች። በልባችን ያለውን ትልልናለችና። እንጂ እውን ብእር፥ እውን ድርሰት አይደለችም። ‘ውብ ነው’ ነው የምልህ ባጭሩ። ቅንብብ ያለ።
ድረታ፡
አንድ ቃል በልዩነት ት`ክት አድርጎኛል - ‘ሃቲት’ የሚል ቃል።
ስንብት
ደራሲው ፍሬ ልጅ ነው። ብኩርና የገዛ ልጅ ነው - ያዕቆብ! ስለ ምስር ወጥ፥ ስለ መ`ጀመል፥ ስለ ‘ፍሉስ’፥ ስለ ‘እዩኝ፥ እዩኝ’፥ ስለዚህ እና ስለዛ ብለው ብዕር ብኩርናቸውን ከሸጡት ከእነ ደራሲ ‘ኤሳው’ ብኩርና የገዛ ልጅ ነው - ያዕቆብ! የእርሱ ዘመን የኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ላይ አንዳች ንቅሳት እንደሚነቅስ ጥርጥር የለኝም።
“ከባዶ ላይ መዝገን” ብሎ እንዲህ እንቅብ ሙሉ ስላሳፈሰን አመስግነን እና “ከባዶ ላይ እንዲህ የሆነ፥ ከሙላትማ እንዴታ!" ብለን እንፈጽማለን። ቸር እንሰንብት!!

 

Read 99 times