ከማዘጋጃ ቤት እንደወጣሁ ቀጥታ ስፖርት ቤት ገባሁ። ምናልባት ለመነቃቃትና ያሳለፍኩትን ውጥረት ለመርሳት መላ ማበጀቴ ነው። የካቲትና መጋቢት 1992 ዓ.ም ያለ ሥራ አሳለፍኩ፡፡ በጊዜው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ተጀምራ ስለነበር፣ ዋና አዘጋጁ ነቢይ መኮንን ዘንድ በመሄድ ፅሁፎችን እሰጠው ነበር፡፡ ነቢይም ፅሁፎቼን ስለወደዳቸው ጋዜጣው ላይ እንዲወጡ አደረገ። በሂደት ቤተሰብ ሆንኩ። ለመቀጠርም ባለቤቱ አሰፋ ጎሳዬ ዘንድ ሄድኩ፡፡ አሰፋ ደስ በሚል ፈገግታ አስተናገደኝ፡፡ መገናኛ ሴንትራል ሸዋ ሆቴል አካባቢ የሚገኘው የአሰፋ ቢሮ በብዙ ወረቀቶች ተሞልቶ ነበር፡፡ አሰፋ ገና የተዋወቅን ዕለት በጥሩ ስሜት ነው ያወራኝ፡፡
" ጋዜጣችን ላይ እየተሳተፍክ እንደሆነ ነቢይ ነግሮኛል፡፡ አሪፍ ነው" አለ አሰፋ ኮምፒውተሩን በእጆቹ እየነካካ። ”አሪፍ” አሴ ሁሌ የሚያዘወትራት ቃሉ ነች።
"…መቀጠር እፈልጋለሁ "አልኩት በራስ መተማመን መንፈስ ተሞልቼ።
" የት ሰርተሻል ? ማለቴ የሥራ ልምድ አለህ?"ሲል አሴ ጠየቀኝ፡፡
ማዘጋጃ ቤት ስሠራ የተፃፈብኝን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አሳየሁት፡፡ ወረቀቱን አገላብጦ ካየው በኋላ በታማኝነቴ ተገርሞ፤
"ጎበዝ ትመስለኛለህ" ሲል ልዩ ብርታት ሰጠኝ።
በመቀጠልም ጠቃሚ ምክር ለገሰኝ፡፡ ሱስ ውስጥ መውደቅ እንደሌለብኝ፣ መማርና ማንበብ እንዳለብኝ፣ 30 አመት እድሜዬ ላይ መጽሐፍ ለማሳተም መጣር እንደሚኖርብኝ መከረኝ፡፡ ምክሩን ልብ ብዬ ሳጤነው ከማዘጋጃ ቤቱ ነብዩ ተካልኝ ጋር ተመሳሰለብኝ፡፡ ተማክረው ነው እንዴ የሚመክሩኝ ? አልኩኝ በሆዴ። ብቻ በምክር ታጅቤ በ400 ብር ደሞዝ የአዲስ አድማስ ቋሚ ባልደረባ ሆንኩ። ባላሰብኩት መንገድ ከታላላቅ ሰዎች መሀል ተገኘሁ፡፡ አሰፋ ቢሮዬን አሳየኝ፡፡ ከባልደረቦች ጋርም አስተዋወቀኝ፡፡ ተፈሪ መኮንን (ቀደም ሲልም እንተዋወቅ ነበር) ሰለሞን ገብረእግዚአብሄር፣ መስፍን ሀብተማሪያም( ሰዐሊ,)፣ ሰለሞን ጎሳዬ፣ ዮብዳር በቀለ፣ኤፍሬም እንዳለ፣ ሰለሞን ካሣ፣ እሸቴ ጎሳዬ ወዘተ-- ማንም የቀረው የለም፤ ሁሉንም አስተዋወቀኝ። በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥራ ነፃነት የሰፈነበት፣ ግምገማ የሌለበት፣ አንባቢ ሰዎች የሞሉበት ታዛ ስር ገባሁ።
አዲስ አድማስ ለመግባቴ ቀዳሚው ተመስጋኝ ነቢይ መኰንን ነው፡፡ የእኔና የነቢይ ትውውቅ 1989 ላይ ይጀምራል፡፡ እናም ነቢይ የቅርብ ክትትል እያደረገልኝ፣ የአዲስ አድማስ ቤተሰብነቴ ተጠናክሮ ቀጠለ። ነቢይ ፤ በትርጉም ሥራ ወደር አይገኝለትም፡፡ የትርጉም ፅሁፍን ኢትዮጵያዊ ቅርፅና ለዛ አላብሶ፣ ብሎም አዋህዶ ማቅረብን ከነቢይ ተምሬአለሁ፡፡ ለአዲስ አድማስ በጊዜው ብዙ መጣጥፎች ይላካሉ። ጋዜጣው ሁሉንም ፅሁፎች ለማስተናገድ ክፍት ነበረ። በመሆኑም ፣ አልፎ አልፎም ቢሆን ፅሁፍ የመምረጥ ሥራዎችንም አከናውን ነበር፡፡ ታዲያ ሰዎች ፅሁፍ ለመስጠት አሰፋ ጋ ሲመጡ፣ ነቢይ ጋ ለጨዋታ ብቅ ሲሉ በዕውነቱ ብዙ ነገር ተምሬአለሁ፡፡ እነ ተፈሪ አለሙን፣ ተስፋዬ ማሞን ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳየኋቸው ትዝ ይለኛል።
አንድ ቀን ነቢይ የሚሚ ስብሀቱን አባት፣ አቶ ስብሀቱ ገብረየሱስን ኢንተርቪው ለማድረግ ሲሄድ እኔንም ይዞኝ ሄደ። መቼም ነቢይ ቃለ ምልልስ ማድረጉን ተክኖበታል፡፡ ፅሁፉ ጋዜጣ ላይ ሲወጣ ደግሞ እንዴት ግሩም እንደነበር አልዘነጋውም።
አሴ ነፍሱን ይማረውና ወርቅ ሰው ነበር፡፡ ሰርቪስ ቤት ውስጥ ከምትገኘው ቢሮው ሆኖ ፦
"… ሰለሞን!!!!!! " ጮክ ብሎ ይጣራል፡፡ ሌይአውት ዲዛይነሩ ሰለሞን ጎሳዬ አቤት፣ ብሎ አሴ ጋ ይሄዳል፡፡ ሰሌ የአሴ ታናሽ ወንድም ነው፡፡ ለኔ ደግሞ ቶሎ የተግባባሁት ጓደኛዬ። ከሰለሞን ጋር አብሬ ፅሁፍ ስመርጥ ከርሜአለሁ። አዲስ አድማስ ውስጥ እንደ አለቃ ወይም እንደ ኤዲተር የማያቸው፣ ተፈሪ መኮንንና ሰለሞን ገ፣ ፈፅሞ አይረሱኝም፡፡ ያኔ ገና 30ዎቹ መጀመሪያ ላይ ቢሆኑ ነው። ነገር ግን የሚያነቧቸው መፅሀፎችና የሚወያዪባቸው ርዕሰ- ጉዳዬች ዛሬ ሳስባቸው ድንቅ ይሉኛል። ተፌ ዛሬም ወዳጄ ነው- ድንቅ አሰላሳይና ጎበዝ ፀሀፊ። አንዳንድ የአዲስ አድማስ ዜናዎቼን ምርጥ አድርጎ ኤዲት የሚያደርግልኝ ተፌ ነበር፡፡ ትዝ ይልህ ይሆን ተፌ?
አንድ ቀን አሰፋ በነጯ ዳትሰን መኪና ወደ ቤት እያደረሰኝ ውስጤ ሲብላላ የኖረ አንድ ጥያቄ ጠየቅኩት፤ "… አሴ ፣ አዲስ አድማሶች ለምንድነው ስብሰባ የማይኖረን? ማለቴ በሳምንት ምን እንደምንሠራ፣ ያለፈውን ድክመትና ጥንካሬ የምንፈትሽበት መድረክ ያስፈልገናል፡፡ እዚህ ቤት ከተቀጠርኩ አንስቶ ስብሰባ የሚባል ነገር አላየሁም። ምን ይመስልሀል?" አልኩት፡፡
አሴም፣ሀሳቤን በደንብ ከተረዳኝ በኋላ፦"… ጥሩ ብለሀል። በስብሰባ ስኬታማ የሆነ ተቋም አለ ብለህ ነው? ሊኖር ይችላል፡፡ የአዲስ አድማስ ስታፍ ግን ለዚህ የስብሰባ ባህል የሚመች አይመስለኝም። እንደ ሀሳብ ግን ጥሩ ነጥብ እንዳነሳህ አስባለሁ" በማለት መልስ እንደሰጠኝ አስታውሳለሁ።
አንድ ጊዜ ደግሞ ሰኔ 1992 ዓ.ም ይመስለኛል፡፡ በዶ/ር ፍሰሀ እሸቱ የተመሠረተ በየቀኑ ለህትመት የሚበቃ "ዕለታዊ አዲስ "የተባለ ጋዜጣ ሊጀመር እንደሆነ ተሰማ፡፡ የሚቀጥሩበትም ደሞዝ ከነባሩ የጋዜጠኛ ደሞዝ 3 እጥፍ ነበር፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው ያለ ምንም ልምድ ከ800 ብር እስከ 1000 ብር ይቀጠራል ማለት ነው። በጊዜው ብዙ ጋዜጠኞች በደሞዙ ተማረኩ፡፡ የዕለታዊ አዲስ መጀመር ወቅታዊ አጀንዳ እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡ የመንግስትና የግል ሚዲያ ጋዜጠኞች ሳይቀሩ ወደ ዕለታዊ አዲስ የተመሙበት ጊዜ ነበር። ከእነዚህም መካከል ታምራት ሀይሉ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ፣መንግስቱ አበበ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ሄለን መሀመድ ከሬድዮ ፋና፣ኤርሚያስ ስዩምና ነፃነት ሰለሞን ከእፎይታ፣ መታሰቢያ ተሾመና ተድባበ ጥላሁን ከሪፖርተር፣ ማንም የቀረ የለም። 150 ጋዜጠኛ ገርጂ ከሚገኘው ዩኒቲ ኮሌጅ ህንፃ ውስጥ ተሰበሰበ፡፡ ብዙ የሚዲያ ተቋማት ዕለታዊ አዲስን የገበያ ብልጫ ይይዛል በሚል ፈርተውት ነበር፡፡ የሚከፍሉት ደሞዝም ያጓጓ ስለነበር ሠራተኞቻቸውን በሙሉ እንዳይወስዱባቸው ይሰጉ ነበር። አንዳንዶች ደግሞ 'የትም አይደርስም። በቅርቡ መዘጋቱ አይቀሬ ነው' እያሉ ይናገሩ ነበር። ከእኛ መስሪያ ቤት የጋዜጣ ሌይአውት ዲዛይነሯ የውብዳር በቀለ በእጥፍ ደሞዝ ዕለታዊ አዲስን ተቀላቅላለች። እነ አሴም ቢሮ አልፎ አልፎ ስለ ጋዜጣው መነሳቱ አልቀረም፡፡
እኔን በተመለከተ፣ መረጃው ስለነበረኝ የዩኒቨርሲቲ የክፍል ጓደኛዬን ማርታ እንድርያስን ማስቀጠሬን አልዘነጋውም፡፡ ለራሴ ግን አላሰብኩትም ነበር፡፡ አዲስ አድማስ ልፋቴን ተመልክቶ ደሞዜን ያሳድጋል የሚል ተስፋ ሰንቄ ስለነበር፣ ዕለታዊ አዲስ ማመልከቱን ለጊዜው አላመንኩበትም፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋር ማደጉ ይበጀኛል ብዬ አሴ ጋር ቀረሁ፡፡ የጓደኞቼ ግፊት ግን ሊያስቀምጠኝ አልቻለም፡፡ ብዙዎቹ እኔ ከማገኘው በ3 እጥፍ ደሞዝ ያገኙ ስለነበር ቀልቤ መሳቡ አልቀረም፡፡ ቀልቤን እየተቆጣጠርኩ ጥቂት ወራት ቆየሁ። የጋዜጣው ዋና አዘጋጆች ሰሎሞን አባተ፣ደረጄ ደስታና ጌታቸው ማንጉዳይ ነበሩ፡፡ መስከረም 1993 ዓ.ም ሲመጣ ዕለታዊ አዲስ ከጋዜጣ አዟሪዎች እጅ ገባ፡፡ ይዘቱም ጥሩ ነበር።
ለእኔ ደሞዝ መጨመሩ ግን የታሰበበት አይመስልም። በዚያ ላይ የተቀጠርኩበት ጋዜጣ አዲስ አድማስ ላይ ፅሁፎቼ ወረፋ ይጠብቁ ተብሎ ቶሎ ቶሎ አይወጡም፡፡ ፅሁፌም ሳይወጣ ደሞዜም ሳይጨመርልኝ እያልኩ ምሬት አሰማ ነበር፡፡ ዕለታዊ አዲስ ላመለክት ስፈልግ ቦታ የለም ተባልኩ፡፡ ይህም ሌላ ንዴት ውስጥ ከተተኝ። ስለዚህ፣ ዕለታዊ አዲስ ላይ በብዕር ስሜ ለመፃፍ ወሰንኩ፡፡ ጓደኛዬ ታምራት ሀይሉ ዕለታዊ ላይ ኤዲተር ነበር፤ ዐምድም ነበረው፡፡ ለእርሱ መፃፍ ጀመርኩ፡፡ በሳምንት 3 ቀናት የእኔ ፅሁፍ ዕለታዊ አዲስ ላይ ይወጣ ጀመር። ደሞዝ የሚከፍለኝ አዲስ አድማስ፣ ፅሁፌ የሚወጣዉ ድምቡሎ በማይከፍለኝ ዕለታዊ አዲስ፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም።
አሴም፣ ሌላ ጋዜጣ ላይ እየፃፍኩ መሆኑን የሰማ ይመስለኛል። አንስቶብኝ ግን አያውቅም። እኔ ግን ልቤ ወደ ዕለታዊ ሸፍቷል፡፡ የማተኩርባቸው ጉዳዮችም ምቾት ሰጥተውኛል፡፡ ዕለታዊ አዲስ ላይ ታትመው ከወጡልኝ ፅሁፎች መካከል፡- ስለ መቶ አለቃ ክፍሌ አቦቸር፣ስለ አቤ ጉበኛ፣ ስለ ህያው ፍቅር መፅሀፍ፣ የሥነ ፅሁፍ ኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ታሪክ ይጠቀሳሉ፡፡ ለአንድ የ22 ዐመት ወጣት ከዚህ በላይ ደስታ ከወደየት ይገኛል?
ጊዜው እየነጎደ ሲሄድ እኔም ለዕለታዊ መፃፌን አጠናከርኩት፡፡ አንድ ቀን ልቀጠር እንደምችል ጌታቸው ማንጉዳይ ተስፋ ሰጠኝ፡፡ በመሀል ለአዲስ አድማስ አንድ ፅሁፍ ፃፍኩ፡፡ ፅሁፉም የክቡር አቶ ሐዲስ አለማየሁ ገፀ ባህሪያትና የሩስያዊው ደራሲ የፊዬዶር ደስታዬቭስኪ ገፀ ባህሪያት ንፅፅር ላይ ያተኩራል። ይህ ፅሁፍ በጥሩ መልኩ የተሰናዳ ስለነበር አዲስ አድማስ ላይ ይወጣል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ግን አልሆነም። ፅሁፉን ከነቢይ ተቀብዬ በአብርሀም ረታ ዓለሙ ለሚዘጋጀውና አርብ አርብ ለሚታተመው ሩህ ጋዜጣ ሰጠሁት፡፡ አብርሀምም ዕዝራ እጅጉ በሚለው የመዝገብ ስሜ ፅሁፉን አተመው። አርብ ዕለት ፅሁፉ የወጣ ቀን ወደ አዲስ አድማስ ቢሮ ሳቀና የልብ ትርታዬ ጨምሮ ነበር። የሆነ ነገር ክብድ ብሎኛል። ገና አዲስ አድማስ ከመግባቴ እንደምፈለግ ተነግሮኝ፣ እኔም በፍርሀት እየራድኩ ራሴን አሴ ቢሮ ውስጥ አገኘሁት፡፡ የድሮው ፈገግታ የለም፡፡ ቅይም እንዳለ ያስታውቅበታል።
"…ይህን የመሰለ ፅሁፍ ምናለ አዲስ አድማስ ላይ ብታወጣው?" በማለት በቁጭት ተናገረ።
ብዙ ላስረዳው ሞከርኩ፡፡ ተረዳኝ፡፡ ግን ለተወሰኑ ቀናት ዕረፍት እንድወጣ መከረኝ፡፡ እኔ ግን መልቀቁን መርጬ በዚያው ወደ ቤት አቀናሁ፡፡ በኋላ በ600 ብር ደሞዝ ሩህ ጋዜጣ ላይ ተቀጥሬ ራሴን አገኘሁት። የካቲት 1993 ዓ.ም ሦስተኛ መስሪያ ቤቴንና ስድስተኛዬን አለቃዬን ተዋወቅኩ። አብርሀም ረታ ዓለሙ።
ከዚያ በኋላ ከአሰፋ ጎሳዬና ነቢይ ጋር ለመገናኘት 36 ወራት ወይም 3 ዓመታት መታገስ ነበረብኝ። ተወዳጅ ሚዲያን መስርቼ፣ ተወዳጅ የማስታወቂያ ጋዜጣን አሳትሜ፣ የመጀመሪያ መፅሐፌን አካፑልኮ ቤይን በመያዝ ከአዲስ አድማስ ቢሮ ተገኘሁ። ሚያዝያ 1996።
አሴ ስኬቴን ሲመለከት ፊቱ በሀሴት ተሞልቶ አየሁት፡፡
"…ይኸው አርፌ ተመልሻለሁ፡፡" አልኩት
"…መፅሐፍም ፅፈህ ተመለስክ፡፡ ግሩም ድንቅ ነው" አለኝ
"… ግን እኮ አሴ ሠላሳ ዐመት ሳይሞላኝ ነው የፃፍኹት፡፡" አልኩት፤ ከ36 ወራት በፊት ያለኝን ለማስታወስ፡፡ ከልቡ ኮራብኝ፡፡ ቀጥሎ መኪና መግዛት እንዳለብኝ አሳሰበኝ፡፡ መረቀኝ፡፡ ከ9 ወራት በኋላ ግን አሴ ማረፉን ወዳጄ ፍቅሩ ካሣ አረዳኝ።
አለቆቼ ነቢይና አሴ ዛሬ በህይወት ባይኖሩም፣ አብረን ባልሠራንባቸው ጊዜያት እንጠያየቅ ነበር፡፡ ለቅሶ ሲገጥማቸው እሄዳለሁ፡፡ በደስታ በሀዘናቸውም እገኝ ነበር፡፡ ታላላቅ አለቆቼ እነ ነቢይ በዕውቀትና በሀሣብ ለማደጌ ምክንያት በመሆናቸው ደስ ይለኛል። በልጅነት ወይም በጊዜያዊ ስሜት ተናድጄባቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ያ ስሜት ጊዜያዊ እንጂ ቋሚ አይደለም፡፡ “እንዳይሳካልኝ የጠመመው አለቃዬ ነው” ብለው አለቃቸውን 47 ዓመት ያኮረፉ ሰዎች ያስቁኛል፡፡
ወዳጄ ሆይ፤ ዕድል ፈንታህ የሚወሰነው በአለቃህ ሳይሆን በእግዚአብሄር ነው፡፡ ስለዚህ ከአለቃህ ጋር ቢቻልህ ምንጊዜም በሰላም ኑር፡፡
እኔ ሁለቱ ለወግ መዐረግ ያበቁኝ አለቆቼ ካለፉ በኋላ፣ ህይወታቸውን እንድዘክር የእነርሱ ሰነድ እኔ ዘንድ የተገኘው ለምን ይመስላችኋል?
በህይወት ለሌሉት የአዲስ አድማስ ባልደረቦቼና አለቆቼ ሁሉ ነፍስ ይማር፡፡