Sunday, 05 January 2025 00:00

ልክ ልካችንን ነገሩን!

Written by  በፍቃድ የሻነህ (MD,MA)
Rate this item
(0 votes)

ምክንያቱን ሳላውቀዉ ጋዜጣ ማንበብ ካቆምኩ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ያሳዝናል! በ19/4/2017 ግን ወደ ቶሞካ ቡና ጎራ ብዬ በዕለቱ የወጣዉን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ሳገላብጥ የማረከኝ ርዕስ አየሁ፡-‹‹አወዛጋቢዉ የነፃ ፈቃድ ግንዛቤ በስንኝ ዳብሮ ሲፈተሽ›› ይላል፡፡ የተፃፈዉ በኤመረተስ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ነዉ፡፡ ፀሐፊዉን በአካልም ይሁን በሥራዎቻቸዉ አላዉቃቸዉም፡፡ ይህም ያሳዝናል፡፡ እርሳቸዉ ማን እንደሆኑ ባለመዋቄ አትፈርዱብኝም ብዬ አስባለሁ፡፡
መቼም ቲክቶከሮች ደግሞ ፕሮፌስሩን አላዉቃቸዉም ስል ‹‹ቴዴ አፍሮን ታዉቀዋለህ፣ጎሳዬ ተስፋየን ታዉቀዋለህ፣ ኤፍሬም ታምሩን ታዉቀዋለህ፣ ጥላሁን ገሰሰ የሚባል ሯጭ ታዉቃለህ፣ ሃይሌ ገ/ሥላሴ የምትባል ሞዴሊስት ታዉቃለህ›› እያላችሁ እንደማትሳለቁብኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ፕሮፌሰር ሽብሩ ‹ነፃ ፈቃድን /Free will/› ከተለያዩ ሰዎች እይታ ደስ በሚሉ ቃላት ከሽነዉ፣ አሳጥረዉ፣ ለአንባቢ አቅልለዉና ዉበት አላብሰዉ አቅርበዉታል፡፡ በዚህም ምክንያት በሚቀጥለዉም ቀን ተመልሼ በመሄድ ይህንኑ ርዕስ በድጋሚ አነበብሁት፡፡ አበሻዎች ምን አሉ? በእዉቀቱ ስዩም፣ ፀጋዬ ገብረ መድህንንና፣ መንግስቱ ለማ በግጥሞቻቸዉ ዉስጥ ‹ነፃ ፈቃድ› ለሰዉ ልጅ እንደሌለዉ ያሳዩባቸዉን የግጥም ስንኞች አስቀምጠዋል፡፡ ‹ነፃ ፍቃድ› እንደሌለ ለማሳየት ማህበረሰብ የገጠማቸዉንም ግጥሞች ስንኞች በአጭሩ አስቀምጠዋል፡፡ ከአበሻዎች ወጥተዉ ታዋቂ ፈላስፎችን ሁለት ጠቅሰዋል፤ ስፒኖዛንና አንስታይነን፡፡ ሁለቱም ታዋቂ ፈላስፎች ‹ነፃ ፈቃድ› እንደሌለ ማሳየታቸዉን ጠቅሰዋል፡፡ (የእርሳቸዉን ፅሁፍ ማንበብ የበለጠ ግልፅ ያደርገዋል)፡፡
የፕሮፌሰሩ አስተሳሰብስ ‹በነፃ ፈቃድ› ላይ ከየትኛዉ ጎራ ነዉ? በአጭሩ ለመጥቀስ ‹በነፃ ፈቃድ› ዙሪያ ሦስት ሊባሉ የሚችሉ ጎራዎች አሉ፡፡ አንደኛዉ፤ ሰዎች ለድርጊቶቻቸዉ በሙሉ ‹ነፃ ፈቃድ አላቸዉ› የሚል ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ‹ማንኛዉም የህይወታችን ክስተትና ዉጤት ቀደም ብሎ የተወሰነ /predestined/ ነዉ፣ ነፃ ፈቃድ የሚባል ነገር የለም› የሚል ነዉ፡፡ ሦስተኛዉ ደግሞ ‹ነፃ ፈቃድም ሆነ አስቀድሞ መወሰን በአፅናፈ ዓለሙም ሆነ በግል ህይወታችን ዉስጥ አብረዉ የሚሰሩ ናቸዉ፣ ሁለቱም አሉ› የሚል ነዉ፡፡ ፕሮፌሰር ሽብሩ በአሸብራቂ የአማርኛ ስንኞች ያንሸራሸሩት ሁለተኛዉን አስተሳሰብ ነዉ፡፡
ፕሮፌሰር ሽብሩ፤ ‹ነፃ ፈቃድ የለም› ከሚሉ ፀሐፊዎችና ፈላስፎች ጎን እንደሆኑ የሚያሳይ አንድ ግሩም ምሳሌ አንስተዋል፡- የወሊድና የወላድ ጉዳይ፡፡
‹‹አንዲት እናት ስትወልድ የሚሰማት የምጥ ህመም እጅግ ከፍተኛ ነዉ፡፡ በዚህ ህመምና ስቃይ ዉስጥ እያለች ዳግመኛ ‹እወልዳለሁ፣ ከባሌም ጋር ፍቅር እሰራለሁ› ብላ ለማሰብ ይከብዳታል፡፡ ከወለደች ከጥቂት ቀናት በሁዋላ ግን በደሟ ዉስጥ ሁለት ዓይነት ሆርሞኖች ይለቀቃሉ፡፡ አንደኛዉ ሆርሞን የነበረባትን ህመም የሚያስረሳ ሲሆን፤ሁለተኛ ደግሞ ደስታ የሚሰጥ ናቸዉ፡፡ ዳግመኛም የመዉለድ ሀሳብ ከጥቂት ቀናቶች በሁዋላ ይመጣል!!! ይህ የሚያመለክተዉ ወላድ የምትወልደዉም ሆነ ልጇን የምትወደዉ በራሷ ነፃ ፈቃድ ሳይሆን ተፈጥሮ በሚያስቀምጥላት የበራሂ፣ ሆርሞንና ኒሮን ቅንብር መመሪያ መሰረት ነዉ፡፡ ›› ድርጊቶቻችን በሙሉ የሚወሰኑት በበራሂ፣ ሆርሞንና ኒሮን እንዲሁም ከእነዚህም ዉጭ በሆነ ሃይል እንጅ በእኛ ነፃ ፈቃድ እንዳይደለ ግልፅ የሆነ ጉዳይ ይመስላል፡፡
ማናችንም የራሳችንን ማንነት በራሳችን ፈቃድ አልሰራነዉም፡፡ ድርጊቶቻችንም በተለያዩ ሃይሎች ተጽኖ ስር ያሉ ናቸዉ፡፡ አንስታይን እንዳለዉ ማንኛዉም እንቅስቃሴ በዩኒቨርሱ ዉስጥ በተዘረጋዉ ሥርዓት ዉስጥ ያለና የሚደረግ እንጅ ከዚህ ዉጭ እኛ በነፃ ፈቃድ የምናደርገዉ ጉዳይ የለም፡፡
ብዙዎቹ የክርስትና ሃይማኖት አስተማሪዎች ‹የሰዉ ነፃ ፈቃድ አለዉ› ብለዉ ያስተምራሉ፡፡ ይህን ካሉ በሁዋላ ‹ትንቢቶች ሊፈፀሙ ግድ ነዉ› ይሉሃል፡፡ ‹ጌታ ከተከታዮቹ በአንዱ ሊካድና በመስቀል ላይ ሊሰቀል ግድ ነበር› ይሉህና፣ እነዚሁ ሰዎች ‹ይሁዳ ጌታዉን ያለመካድ ነፃ ፈቃድ ነበረዉ› ይሉሀል፡፡ የዓለም የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ ኑሮና የፖለቲካ ምስቅልቅል እየባሰ እንደሚመጣ በትንቢት ያለ እዉነት በመሆኑ እንደማይቀር ይነግሩህና፣ እነርሱ ግን ፍቅር እንዲኖር፣ አንድነት እንዲኖር፣ መተሳሰብ እንዲኖር፣ ጦርነት እንዲጠፋ፣ ፍትህ እንዲሰፋ እንሰራለን ይሉሀል፡፡ ‹እግዚአብሔር ካልፈቀደ በቀር ወደ እርሱ የሚቀርብ የለም› ይሉህና፣ እነርሱ ሁሉንም ወደ ‹እግዚአብሔር ቅረቡ› ብለዉ ያስተምሩሀል፡፡ የቸገረ ነገር!
አሁን ገባኝ! ሁሉም ነገር አስቀድሞ በተወሰነ ነገር ዉስጥ እንዳለ፣ ‹ነፃ ፈቃድ› የሚባል ነገር እንደሌለ ሳይንሱም፣ ፈላስፎችም፣ ፕሮፌሰር ሽብሩም፣ ገጣሚዎችም ነገረዉናል፡፡ አንዳንድ ሰዎችና የእምነት አስተማሪዎች ደግሞ (ከክርስትና ዉጭም ያሉ አሉ) ‹የሰዎች ነፃ ፈቃድ አላቸዉ› ብለዉ ያስተምራሉ፡፡
ህይወት ደግሞ ደጋግማ የምታሳየዉ የእያንዳንዳችን ጉዞ አስቀድሞ የተወሰነ መሆኑን ነዉ፡፡ ታዲያ የገባኝ ነገር ምንድን ነዉ ካላችሁ፣ እነዚህ ‹የሰዉ ነፃ ፈቃድ አለዉ› ብለዉ የሚያስተምሩ ሰዎች፤ ይህን እንዲያስተምሩ አስቀድሞ ተወስኖባቸዋል፡፡ አዎ በራሳቸዉ ነፃነት ዉስጥ ሆነዉ ይህንን ማለት የሚችሉ አይመስለኝም፡፡
ጠለቅ ወዳለዉ የነፃ ፈቃድና አስቀድሞ ዉሳኔ /Free will and Predistination/ መላምቶች ዉዝግብ ሳይገቡ፣ ለእኛ ለአንባቢያን በሚገባ መንገድ ነፃ ፈቃድ የሚባል ነገር እንደሌለ ነግረዉናል፤ ያዉም ሰዎች እንዳይበሳጩ አዋዝተዉ፣ አለስልሰዉ!
ህዝቤ መልፋትህን ቀጥል፤ የተወሰነብህ ነገር ነዋ! ፅድቅ መሥራትህንም ሆነ ኃጢኣት መስራትህን፣ ሀብታም መሆንህንም ሆነ ድሀ መሆንህን፣ ቆንጆ መሆንህምን ሆነ ፉንጋ መሆንህን፣ መገዳደልህንም ሆነ ሰላም መሆንህን፣ መዋደድህን ሆነ መጣላትህን የወሰነልህ የዓፅናፈ ዓለሙ ሥርዓት ዘርጊ ፈጣሪ እንጅ አንተ አይደለህም፡፡ አንተ ግን በዚህ ዉጣ ዉረድ እንድታልፍ በሥርዓቱ ዉስጥ ትንቀሳቀስ ዘንድ ተወስኗል፤ ቀጥል፣ተንቀሳሰቀስ!፡፡
የዘላለም ፅድቅ ለማግኘት አንተ ‹ማመን፣ መስራት ወዘተ.› እያልህ ልፋ፤ የሚሆነዉ ግን ቀደም ብሎ የተወሰነልህ ነዉ፡፡
ወይ ወደ ዘላለም ህይወት ወይም ወደ ዘላለም ጥፋት እንደምትሄድ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ የተወሰነልህ እንጅ አንተ አንዲትም ነጥብ ጨምረህ የምትለዉጠዉ ነገር የለም፡፡ ዳይ ወደ መኳተንህ!
ፕሮፌሰሩ ግን ጨካኝ ነዎት! እኛ እኮ ልክ ልካችንን የሚነግረን ሰዉ አንወድም! ይህ አዉነትን አለመዉደድም አስቀድሞ የተወሰነብን ነዉ፣ የእርስዎም ጨካኝነት እንዲሁ!! ይህን የፃፍሁት ግን በነፃ ፈቃዴ ነዉ?
ፕሮፌሰሩግንጨካኝነዎት! እኛእኮልክልካችንንየሚነግረንሰዉአንወድም! ይህአዉነትንአለመዉደድምአስቀድሞየተወሰነብንነዉ፣ የእርስዎምጨካኝነትእንዲሁ!!ይህንየፃፍሁትግንበነፃፈቃዴነዉ?

Read 209 times