Sunday, 05 January 2025 00:00

ብዕርና ጎራዴ

Written by  -ሙሉጌታ ቢያዝን
Rate this item
(0 votes)

“Birds of the same feather flock together” የሚል የቆየ የእንግሊዛውያን አባባል አለ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያንም “ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር ፈስ ተምራ መጣች” እንላለን፡፡ ይህን ለማለት ያስቻለኝ ለሌላ ሥራ መረጃ ሳገላብጥ አንድ ዘመን የሚጋሩ የሁለት አወዛጋቢ ግለሰቦች ተዛምዶ እጅግ ስላስገረመኝ ነው፡፡ የቃረምኩትን አጠር አድርጌ ባካፍላችሁስ?
ፍሬድሪክ ኒቼና አዶልፍ ሂትለር፡፡
ሂትለር በ1889 ፤ ኒቼ ደግሞ 1844 ተወለዱ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የከንፈር ጢም አንድምታው ከጦርነት ጋር ሲቆራኝ፣ የጥንቷ ግሪካውያንና ሮማውያን ከወንድነት ጋር ያያይዙታል፡፡ የሂትለር የከንፈር ጢም አነስ ቢልም ሁለቱም በከንፈር ጢማቸው (moustache) ይታወቃሉ፡፡ ሁለቱም በ19ኛው ክፍለ ዘመን በዘመናዊ ትምህርት ዘርፍ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መሪ በነበረችው ጀርመን የተወለዱ ናቸው፡፡
ሁለቱም በፈጠራ የላቀ፣ ሰው ለፈጠረውም ለፈጣሪም ሕግ የማይገዛ፣ ከሰው ሁሉ መላቅን በሚሰብከው በ’ልእለ-ሰብ /Superman or overman/ያምኑ ነበር፡፡ የሚገርመው ሁለቱም ከአጥባቂ የክርስቲያን እናት ተወልደው፣ በክርስትና የሚሳለቁ፣ፀረ ክርስትና ነበሩ፡፡ ሁለቱም በልጅነታቸው ካህን ለመኾን ያለሙ ወይም የታለመላቸው ነበሩ፡፡ ሂትለር በራሱ ፤ኒቼ ደግሞ በወላጅ እናቱ በኩል ካህን ይኾናሉ ተብለው ሲጠበቁ፣ ኢአማኚ ኾነው እርፍ!
ሁለቱም ታናሽ ወንድሞቻቸውን በልጅነታቸው ሞት ነጥቋባቸዋል፡፡
ሁለቱም በግብረ ሰዶምነት ይታማሉ፡፡
ሁለቱም የቂጥኝ ደዌ አቅላቸውን እንዳሳታቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ሁለቱም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ተሳትፎ ነበራቸው፤ ኒቼ በህክምና፣ሂትለር በውትድርና፡፡
ሁለቱም በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተወለዱ ናቸው፡፡ ሁለቱም ጨለምተኝነት (Pessimist) የተጠናወታቸው፣ ሁለቱም በዲሞክራሲ የማያምኑ ነበሩ፡፡
ኒቼ “ከወንድም ፍቅር ይልቅ ነውጥን አጥብቅ” ሲል ሂትለር “ሰብአዊነት የደደቦችና ቦቅቧቆች መገለጫ ነው” ሲል ያከፋዋል፡፡ ሁለቱም ጦርነትን/ኃይልን እንደ ለውጥ መሳሪያ የሚቆጥሩ ነበሩ፡፡
ስለ እናት “Usually a mother loves herself in her son more than she loves the son himself” ሲል ቢደመጥም፣ እናቱን አጥብቆ ያፈቅር እንደነበር ድርሳናት ያወሳሉ፤ ሂትለርም እንደዚሁ፡፡ ሁለቱም እናታቸውን አጥብቀው የሚወዱ ቢኾኑም (አጥብቀው የሚለው ይሰመርበት)፣ ሁለቱም ከወላጅ እናታቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ውስብስብ ነበር፡፡ሁለቱም ወላጅ እናታቸውን የምትመስል ሴት በመፈለግ ዕድሜያቸውን የፈጁ ነበሩ፡፡ ሂትለር ነገ መሞቱን ሲያውቅ ዛሬ ሚስት ሲያገባ፤ “ሴት የእግዚአብሔር ሁለተኛ ስሕተት ናት” የሚለው ኒቼ ደግሞ ዕድሜ ዘመኑን ወንደላጤ ኾኖ ያለፈ ነበር፡፡ (የመጀመሪያው ስሕተት አዳም መኾኑ ነው፡፡ የአዳም ሲገርመን ሔዋንን ደገመ ዓይነት!)
ይሄን ስናይ በሴትና ወሲብ ዙሪያ የኒቼ ሻፈፍ ማለቱ ሳይልቅ አይቀርም፡፡ ምናልባት እንዲህ ዓይነቱን ነገር ደፍሮ መናገሩ /ለpolitical correctness አለመጨነቁ/ወይም የሕዝብ መሪ አለመኾኑ አግዞት ይኾናል፡፡ ሁለቱም ዓለምን ያነጋገሩ ተፅዕኗቸው የጎላ ነበሩ፡፡ (ሂትለር በጎራዴው፣ኒቼ በብዕሩ፤አንዱ በገቢር ሌላኛው በነቢብ)፡፡ ሞት አይቀርምና ሁለቱም ስድሳን ሳይደፍኑ ያለፉ ነበሩ፡፡
እንደ መውጫ፡-
ሃሳብ የሁሉ ነገር መነሻ ነው፡፡ ተግባር ሃሳብን ሊቀድመው አይችልም፡፡ እንዲያ ከኾነ ‘ኒቼ ሂትለርን መርቶታል ወይስ?...’ ብለን መጠራጠር የምንችል አይመስለኝም፡፡ ሃሳብ የሁሉ ነገር መቅድም ከኾነ፣ ቀድሞ የተወለደ (ኒቼ)፣ በኋላ ለተወለደው (ሂትለር) ሃሳብ አቀብሎ ቢኾንስ?
ማድነቅ ለማይወደው ሂትለር ይሄ ስድብ ሊሆን ይችላል፡፡
እውነታው ግን ይሄ ይመስለኛል፡፡ ነቢብ ገቢርን ይቀድመዋል፡፡ ከ50 ሚሊዮን በላይ እንደ ቅጠል ላረገፈው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት የኾነው ሂትለር፣ ‘ጦርነት የሥልጣኔ ምንጭ ነው’ ብሎ የጻፈው ኒቼ ‘አስተዋጽዖ አላደረግም’ ማለት የምንችል አይመስለኝም፡፡ በልእለ ሰብ የሚያምነው ኒቼ፣ከኋላው ለተወለደው ሂትለር፣ ምርጡ የዓለም ዘር/የአራያን ዘር/ ‘ንጹህ ጀርመናውያን ናቸው’ ብሎ እንዲነሣና በጥቂቱ ስድስት ሚሊዮን አይሁዲዎችን በጅምላ ለመፍጀቱ እርሾ አልተወም ማለት እንችላለን? “ብዕር ከጎራዴ ይበረታል” (A pen is mightier than a sword) ሲባል ሰምተናል፡፡ እውነት ነው፡፡
“ብዕር ጎራዴን ይበልጠዋል፡፡ ከሁለቱም ግን ምላስ ይልቃል” እንዲል ማርከስ ጋርቬይ፣ በንግግር ክህሎቱ መንጋውን በስሜት ነድቶ ሚሊዮኖችን በጎራዴ የበላው የሂትለር ምላስ ግን ይበልጥ ያስፈራል፡፡ ያሰንብተን!

 

Read 176 times