፨ በጠዋት ተነስቶ ፈረሴን ማብላትና ማጠጣት የዘወትር ሥራዬ ኾኗል። ለውድድሩ ብቁ እንድትኾን ከአባይ ወንዝ ማዶ ያለችዋ ሜዳ ላይ፤ ጸሃይ ከአናታችን ትይዩ እስክትኾን፣ ሳለማምዳት እውላለኹ። ማደሪያዋ አስገብቻት የምትበላውን እሰጣትና እረፍት እንድታደርግ እተዋታለኹ - ሊመሽ ሲል አኹንም ልምምድ።
፨ ውድድሩ በጣም አጓጊ ነው። ኹሉም ህዝብ በተሰበሰበበት ነው የሚከናወነው። ልጁ ተወዳዳሪ ስለኾነ መንግሥቱም ሳይቀር ይመጣል። እስከዛሬ አንድም ውድድር ተሸንፌ ባላውቅም የበፊቶቹ መንግሥታት ልጃቸው ሲቀደም የቀደመውን ሰው ስለሚቀጡ የነሱን ልጅ ለማሸነፍ የሚሞክር አልነበረም። እኔም ባለሥልጣናት ካሉበት አልወዳደርም - ግን ከሌሎች ጋር ስወዳደር አልሸነፍም። አኹን ያለው መንግሥት ጥሩ ይመሥለኛል። እኔ ስለ ፈረሶች እንጂ ስለ መንግሥቶች ባያገባኝም የእናቴ ታላቅ እህት ቤታችን የመጣች ቀን የነገረችንን አልረሳም።
፨ አያቴ ሲሞት ለልጆቹ ባወረሳቸው ቤት ውስጥ ነው የምንኖረው። ለአክስቴም እዚያ ከከተማዋ መሃል ላይ ያለችውን ቤት አውርሷት ነበር። ይሄ አዲስ የመጣው መንግሥትም የሷ ቤት ጋር መሥጂድ ሊሰራ ፈለገና ሌላ ቦታ ቤት እንደሚሰጣት ነገራት።
አክስቴም በኹለት ምክንያቶች ቤቷን መልቀቅ አልፈለገችም። አንደኛ ክርስትያን ናት፤ እሷም እኛም ክርስትያኖች ነን - ስለዚህ ቤቷ ፈርሶ መሥጂድ እንዲሰራ አልፈለገችም። ኹለተኛ አባቷ ነው ያወረሳት፤ አባቷን በጣም ስለምትወደው የሱን ነገሮች በስስት ነው የምታየው። ስለዚህ እንቢ አለች። መንግሥቱ ቢለምናት ‹‹ሌላ ቤት ልስጥሽ፣ ያሻሽን ብርም ልጨምርልሽ›› ቢላት ‹አሻፈረኝ› አለች። እሱም በጣም ተናዶ ‹‹ስትፈልግ መሬትና ገንዘብ መጥታ ትጠይቀኝ›› ብሎ አፈረሰባት። አክስቴም ክፉኛ አዝና ለሱ አለቃ ለኾነው መሪ ደብዳቤ አስጽፋ ታላቅ ወንድሜን ላከችው። ወንድሜም ፈረሴን ይዞ ባህር አቋርጦ(ግን ፈረስ ይዞ ባህሩን እንዴት አቋረጠው? ለምን አልጠየኩትም?).. ደብዳቤውን አደረሰ። (ፈረሴ ያኔ ተጎድታብኝ ነበር። አኹን በደንብ የምንከባከባት ውድድሩ ላይ እንዳትሰንፍብኝ ነው።)
እዚያ ያለው መሪ ይኽን ሲሰማ ተናዶ በመጣለት ደብዳቤ ጀርባ ላይ፤ ‹‹አሁኑኑ መሥጂዱን አፍርሰህ ቤቷን ገንባላት!›› ብሎ አዘዘው። መንግሥቱም ደብዳቤውን ሲያይ ወዲያውኑ መሥጂዱን አፍርሶ ቤቷን ሰራላት።
፨ በጊዜ የውድድሩ ቦታ ተገኝቻለሁ። ፈረሴም ለመወዳደር ዝግጁ ነች። የግብጽ ህዝብ ጠቅላላ የመጣ ነው የሚመስለው። ሁሉም ያፏጫል፤ ያበረታታል። ግን አብዛኛዎቹ ለመንግሥቱ ልጅ ነው የሚደግፉት። ቤተሰቦቼን ከሩቅ አየኋቸው። ደስ ብሏቸዋል። ለነሱ ባላሸንፍ እንኳ መወዳደሬ በቂ ነው።
. . .ተጀመረ። ጋለብን። ብዙዎቹ ወደ ኋላ ቀሩ። እኔ እና የመንግሥቱ ልጅ እስከ መጨረሻው ተያይዘን ቀጠልን። ጥሩ ጋላቢ ነው። ግን ፈረሴ አላሳፈረቺኝም፤ አንደኛ ወጣሁ። ደስ አለኝ። ህዝቡም ለኔ መጮህ ጀመረ። የበፊት መንግሥታት ቢሆኑ ወላጅ እንኳ ለልጁ አይደግፍም ነበር። ወደ መንግሥቱ ልጅ ሄጄ’ም ‹‹ጎበዝ ተፎካካሪ ነበርክ!›› አልኩት። እሱ ግን ወዲያው ፊቱን አጥቁሮ ወገቡ ላይ ይዞት የነበረውን አለንጋ አንስቶ ‹‹እንዴት ትቀድመኛለህ? የንጉሥ ልጅ መሆኔን አታውቅም!›› ብሎ ጭንቅላቴን መታኝ። ደነገጥኩ፤ አዘንኩ። ከውድድሩ ቦታ ቶሎ ወጣሁ። ቤተሰቦቼ ፈረሴን ጥዬ መሄዴን ሲያዩ፣ እሷን ይዘው ተከተሉኝ። የአባይ ወንዝ ጋር ሄጄ አለቀስኩ። አክስቴ ናት ቀድማ የደረሰችው። እያለቀስኩ መሆኔን ሲያውቁ ደንግጠው ምን እንደኾንኩ ጠየቁኝ። ነገርኳቸው። ‹‹በል ተነስ ዛሬውኑ መዲና ሂድና ለመንግሥቱ - አለቃ ለዑመር ንገረው›› አለች አክስቴ። ‹‹እንዴ! እሱን ምን አገባው? ነገሥታት ናቸው። መወዳደራችንም አንድ ነገር ነው። አንተ ነህ ጥፋተኛ.፤ መቅደም አልነበረብህም።›› አለ አባቴ።
‹‹ለምን? እኔ ነኝ ያልኩህ ምንም አይፈጠርም››
‹‹አይኾንም፤ እዚያ ሄዶ ቢያስሩትስ? ምን ማለት ነው ሄዶ ‘የመንግሥት ልጅ ለምን ቀደምከኝ ብሎ መታኝ’ ብሎ ለንጉሥ መክሰስ? ቢያስሩትስ? ‘ስላልገደለህ ነው ወይ?’ ቢሉትስ..››
‹‹እሱ እንደዚያ አይልም። ለምን አትሰሙኝም እኔን?›› ተቆጣች አክስቴ። ‹‹ውድድር ነው ተሸነፈ። አበቃ! የምን መማታት ነው!››
፨ በጠዋት ፈረሴን ይዤ ወጣሁ። ምን ባህር ነበር የሚሉት? ጠፋኝ። ብቻ አባይ አይደለም። ከአክሱም የሚመጣ የአክሱማውያኖች መርከብ አለ፤ እሱን ጠብቄ እንድሄድ ነው የተነገረኝ። ሌሎች መርከቡን የሚጠብቁ ሰዎች ነበሩ፤ ትንሽ እንደቆምን መጣ። ስንት ቀንና ስንት ሌሊት እንደተጓዝኩ አላውቅም - ደረስኩ።
፨ ህዝቦቹ እንግዳ መሆኔን አውቀዋል። ግንባሬ ላይ ባለው መስቀልም ሙስሊም አለመሆኔን ተገንዝበዋል። አንዱ ወደኔ መጥቶ
‹‹ከግብጽ ነህ?›› አለኝ።
‹‹አዎ››
‹‹ምን ፈልገህ ነው? ምን ልርዳህ?››
‹‹ዑመርን ፈልጌ ነው።››
‹‹ዑመር ያው እዚያ ዛፉ ሥር›› አለኝ። ሄድኩ። ቤተ-መንግሥቱን እየፈለኩ ነው የሄድኩት፤ ግን አጣሁ። ዛፉ ሥር ሁለት ጫማዎቹን ትራስ አርጎ፣ ብዙ ቦታ የተጣፈ ልብስ የለበሰ ረዥም ሰው ተኝቶ አየሁ። ፊትለፊቱ ስቆም ጸሃዩዋን ከለልኩበት መሰለኝ ነቃ። ‹‹አቤት ምን ልርዳህ?›› አለኝ። ‹‹ዑመርን ፈልጌ ነው። ሰዎች ዛፉ ሥር ነበር ብለውኝ ነበር።›› አልኩት።
‹‹እኔ ነኝ ዑመር።››
‹‹ምን?›› አልኩ ደንግጬ። የምድርን አንድ ሶስተኛ እያስተዳደረ ያለው ሰው ተቀዳዶ የተሰፋ ልብስ ለብሶ ሳይ። ‹‹ምን ልርዳህ?›› አለ።
‹‹አይ እኔማ ከግብጽ ስሞታ ላሰማ ነው የመጣሁት››
‹‹እሺ ንገረኝ››
‹‹የፈረስ ውድድር ነበረንና አንተ የሾምከው መንግሥት ልጅ’ም አብሮን ይወዳደር ነበር። ውድድሩን እኔ ሳሸንፍ ‘የመንግሥት ልጅ መሆኔን እያወቅክ እንዴት አሸነፍከኝ!’ ብሎ ልጁ ጭንቅላቴን መታኝ›› አልኩ፤ አክስቴ እንዳለቺኝ ምንም ሳልፈራ። ፊቱ ሲለዋወጥ አስተዋልኩ። ተቆጣ። ፈራሁት። ‹‹ና›› አለኝና ከፊትለፊቴ ሄደ። ረዥም ነው። አንዲት በጭቃ የተለሰነች ቤት ውስጥ ገባን። ውስጥ ቆመው ከነበሩት አንዱን ‹‹ዐሊ እስኪ ወረቀት አምጣ›› አለ። ተሰጠው። እኔ አጠገቡ ቆሜያለሁ።
‹‹ከዑመር ለግብጽ መንግሥት አምር የተጻፈ። ይህ ደብዳቤ ማታ ከደረሰህ ጠዋቱን፤ ጠዋት ከደረሰህ ማታውን ልጅህን አስከትለህ መዲና እንድትመጣ!›› ብሎ ጻፈና ቤቱ ውስጥ ከነበሩት አንደኛውን ጠርቶት ግብጽ ይዞ እንዲሄድ ነገረው። ወደ’ኔ ዞሮም ‹‹ምግብ በልተሃል?›› አለኝ። ‹‹አልበላሁም›› ስል ሰዎቹን ጠርቶ የማድረበትንና የምበላውን ለኔም ለፈረሴም እንዲሰጠን አዘዘ። አንዱ መጥቶ ወደ ማድርበት ይዞኝ ሄደ። ኋላ እንደተረዳሁት ቤተ-መንግሥት ሳይኾን ያለው፣ ይቺ ጭቃ ቤት ናት።
፨ ከቀናት በኋላ ተጠራሁ። ህዝብ በተሰበሰበበት፤ ዑመር አለንጋ ሰጥቶች የልጁን ጭንቅላት እንድመታ ነገረኝ። መታሁት፤ ደስ አለኝ። ‹‹አባቱንም ምታው!›› አለ ዑመር የባለፈው ንዴት አልለቀቀውም።
‹‹ለምን እሱ እኮ ምንም አላለኝም››
‹‹ልጁ የመታህ የአባቱን ሥልጣን ተመክቶ አይደል››
‹‹አይ እኔ ልጁን ብቻ ነው መምታት የፈለኩት›› አልኩ። ከዚያም ወደ ግብጹ መንግሥት ዞሮ ‹‹ከመቼ ጀምሮ ነው ከእናቶቻቸው ሆድ ሲወጡ ነጻ የሆኑ ግለሰቦችን ባሪያ አድርጋችሁ መያዝ የጀመራችሁት!›› አለ። አባትም ልጅም ዝም አሉ። ለኔ ስንቅ አስጫነልኝና የሚሸኘኝን ሰው መድቦልኝ ወደ ቤቴ ጉዞ ጀመርኩ።
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በቴሌግራም አድራሻው፡- @NEBILADU ማግኘት ይቻላል፡፡