Friday, 10 January 2025 20:28

“ሁሉም አምዶች ሳምንቱን ሙሉ የሚነበቡ ናቸው”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ወይዘሮ ፈለቀች ለማ እባላለሁ፡፡ የቤተሰብ አስተዳዳሪና የአስራ አንድ ልጆች እናት ነኝ፡፡ በጥሩ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግሁት፡፡ ትምህርት የጀመርኩት በቄስ ትምህርት ቤት ነው፤ ከዚያም በመንግሥት ትምህርት ቤት ገብቼ እስከ ስድስተኛ ክፍል ከተማርኩ በኋላ በሀገሩ ባህልና ወግ መሠረት በጣም በልጅነቴ ተዳርኩ፡፡ ሆኖም ያኔ ሲንጀር ካምፓኒ የሚሰጠውን የዲዛይን ትምህርት ጨርሼ ከተመረቅሁ በኋላ፣ በጅማ የሴቶች በጎ አድራጎት ድርጅት፣ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን፣ ሴቶች ራሳቸውን እንዲችሉ፣ የልብስ ስፌትና ጥልፍ ስልጠና በመስጠት እናስመርቅ ነበር።

አዲስ አድማስ ከመጀመሩ በፊት ባለቤቴ ሁሌም ጋዜጣና መፅሔት እንዲሁም መጻሕፍት እየገዛ ያመጣ ስለነበር፣ ንባብ የቤታችን ባህል ሆኗል፡፡ በኋላም አዲስ አድማስ ቅዳሜ መውጣት ሲጀምር ልጆቹም በዚያው ቀጠሉበት፡፡ እኔም ጋዜጣውን ማምጣት እንዳይረሱ ሁሌም አስታውሳቸዋለሁ፤ በጣም የሚወደድ ጋዜጣ ስለሆነ ምንጊዜም እንዲያልፈኝ አልፈልግም፡፡

አዲስ አድማስን ለብዙ ዓመታት አንብቤአለሁ፤ ወደፊትም አነባለሁ፡፡ ጋዜጣውን እንዳገኘሁ መጀመሪያ የማነበው የነቢይ መኮንንን (ነፍሱን ይማረውና) ርዕስ አንቀጽ ነው፤ ሁለተኛ የማነበው ደግሞ የዮሐንስ ሰ.ን ጽሁፍ ነው፡፡ እኔ ከልጆቹ ቀድሜ ካነበብኩ ጥሩ የምላቸውን ጽሁፎች እንዲያነቡ እጠቁማቸዋለሁ፡፡ ሁሉም አምዶች ሳምንቱን ሙሉ የሚነበቡ ናቸው፡፡ በእኔ በኩል፣ አዲስ አድማስን በድረ ገፅ አላነብም፤ለዕድሜዬ አይሆንም፤ በዚያ ላይ ጋዜጣው ሁሌም በእጄ ነው።

በአዲስ አድማስ ላይ በርካታ አስገራሚና አስደማሚ ታሪኮችን አንብቤአለሁ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ሁሌም የማይረሳኝ፣ ኮፊ አናን ኢትዮጵያ በነበሩ ጊዜ የቤት ውስጥ ረዳታቸው የነበሩትን ሴት ተመልሰው ሲመጡ ሊያገኟቸው ፈልገው፣ ሴትየዋ በቀጠሮው ሰዓት ባለመድረሳቸው ሳይገናኙ መቅረታቸውን የሚያትተው ታሪክ ነው፡፡ የቀጠሮ ሰዓት የማያከብር ሰው ስለሚገርመኝ ይሆናል፣ ይሄ ታሪክ ሁሌም ትዝ የሚለኝ፡፡

በእርግጥ የማነበው ጋዜጣ ብቻ አይደለም፤ መፅሔቶች የታሪክና የሀይማኖት መጻሕፍትንም አነባለሁ፡፡ ዜናም አያመልጠኝም፡፡ ማንበብ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዕውቀትን ያስታጥቃል፡፡ መረጃን ከሰው አፍ ከመስማት አንብቦ መረዳት የተሻለ ነው፡፡

የአዲስ አድማስ ፀሐፊዎችና አዘጋጆች፣ ከአንባቢዎቻቸው ቀድመው መገኘት አለባቸው፤ በሁሉም ረገድ ሊበረቱ ይገባል፡፡ ጋዜጣው አምዶቹን መጨመር እንጂ መቀነስ የለበትም፤ የተቀነሱ አምዶች ስላሉ የጎደሉትን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ በመጨረሻ እንኳንም ለአዲስ አድማስ 25ኛ ዓመት አደረሳችሁ እላለሁ፡፡ መልካም የሥራ ዘመን ይሁንላችሁ።

Read 257 times