Saturday, 11 January 2025 12:03

ጊዜው እንዴት ይሮጣል ጃል ‹‹አዲስ አድማስ ይታየኛል››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

በ‹‹አዲስ አድማስ›› ልደት ለመገኘት፤ በኮከቡ አሰፋ እየተመሩ ከተጓዙ ‹‹ሰብአ ሰገሎች›› መካከል፤ ነቢይ
መኮንን፣ ሰለሞን ገ/እግዚአብሔር፣ ብርሃኑ ነጋሽ እና የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ማርቆስ ረታን
ጨምሮ፤ ነቢይ፣ ሰለሞን፣ ብርሃኑ ኦርማ ጋራዥ አካባቢ በነበረው የ‹‹አዲስ አድማስ›› ቢሮ፤ Backlog
እየሰሩ ጥቂት ወራት እንደ ቆዩ ነበር እኔ የተቀላቀልኳቸው፡፡ ወዲያው ቢሮ ቀየርን፡፡ ከኦርማ ጋራዥ ወደ
‹‹ሴንትራል ሸዋ›› አካባቢ ተዛወርን፡፡ የ‹‹አዲስ አድማስ›› የመጀመሪያ ዕትም ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም
ለገበያ ቀረበ፡፡ የ25 ዓመታቱም ጉዞ ተጀመረ፡፡



በአሰፋ ጎሳዬ ህሊና ተጸንሳ ቆየች፡፡ ከ25 ዓመት በፊት ኦርማ ጋራዥ አካባቢ ምጡ አፋፋማት፡፡ በመጨረሻም ሃያ ሁለት አካባቢ ‹‹ሴንትራል ሸዋ ሆቴል›› አቅራቢያ በታህሳስ ወር ተወለደች፡፡ ‹‹የእርስዎና የቤተሰብዎ ጋዜጣ›› ይኸው ለሩብ ምዕተ ዓመት ተጓዘች፡፡  ‹‹አዲስ አድማስ›› እንደ ናዝሬቱ ኢየሱስ በታህሳስ ወር ተወለደች፡፡ በመርካቶው ባለራዕይ አሰፋ ጎሳዬ ማህጸነ ህሊና የተጸነሰችው ‹‹አዲስ አድማስ››፤ በናዝራዊው ነቢይ መኮንን ዋና አዘጋጅነት 25 ዓመታትን ዘለለቃለች፡፡
በ‹‹አዲስ አድማስ›› ልደት ለመገኘት፤ በኮከቡ አሰፋ እየተመሩ ከተጓዙ ‹‹ሰብአ ሰገሎች›› መካከል፤ ነቢይ መኮንን፣ ሰለሞን ገ/እግዚአብሔር፣ ብርሃኑ ነጋሽ እና የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ማርቆስ ረታን ጨምሮ፤ ነቢይ፣ ሰለሞን፣ ብርሃኑ ኦርማ ጋራዥ አካባቢ በነበረው የ‹‹አዲስ አድማስ›› ቢሮ፤ Backlog እየሰሩ ጥቂት ወራት እንደ ቆዩ ነበር እኔ የተቀላቀልኳቸው፡፡ ወዲያው ቢሮ ቀየርን፡፡ ከኦርማ ጋራዥ ወደ ‹‹ሴንትራል ሸዋ›› አካባቢ ተዛወርን፡፡ የ‹‹አዲስ አድማስ›› የመጀመሪያ ዕትም ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም  ለገበያ ቀረበ፡፡ የ25 ዓመታቱም ጉዞ ተጀመረ፡፡
ናዝራዊው ነቢይ፣ መወለዷንና በሰለሞን ስፖርት፣ ኤፍሬም እንዳለ፣ ኤልሳቤት ዕቁባይ፣ አልአዛር ኬ.፣ ሌሊሳ ግርማ፣ ከበደ ደበሌ፣ግሩም ሰይፉ ወዘተ ትጋት ማደጓን አይቷልና፤ አረጋዊው ስምዖን ‹‹ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም አሰናብተው›› እንዳለ፤ ነቢይም ከወራት በፊት ‹‹አዲስ አድማስ››ን መልካም መዐዛ ባለው ሥሙ ባርኳት ተሰናብቷል፡፡ ሆኖም በልደቷ ማግስት በተቀላቀለው፤ በወዳጄ ኢዮብ ካሣ ቅን ልብና ትጋት ራዕዩ አሁንም ቀጥሏል፡፡
‹‹አዲስ አድማስ›› የባለ ራዕዩ የአሰፋ ልጅ ነች፡፡ ‹‹የአዲስ አድማስ›› የዓይን አባት ልለው የምወደውና የጋዜጣዋ ታማኝ ቤተሰብ የሆነው ባልንጀራዬ ዘነበ ወላ፤ አሰፋ ጎሳዬን ዘወትር በአድናቆት ያነሳዋል፡፡ ‹‹አሰፋ ሀሳብ ዋጋ እንዳለው የሚያምን ሰው ነው›› ይለኛል፡፡ ‹‹አሰፋ ረብ ያለው ሀሳብ ስታወራ ከሰማህ፤ ‹ወዳጄ ገንዘብ አያስፈልግህም? ይቺን ጨዋታህን በወረቀት አስፍረህ አምጣልኝ፡፡ እኔም ኪሴን ለመዳበስ ዝግጁ ነኝ ይልሃል›› ይል እንደነበር በማውሳት ይደነቃል፡፡ እኔም ምስክር ነኝ፡፡ ጊዜ የገደፋቸው ሀሳቦችን እንድንፈትሽ፤ እንደ ባሴ ሀብቴ፣ መስፍን ሀብተ ማርያም ባሉ ዝነኛ ፀሀፊዎች የተጻፉ መጣጥፎችን እንድናርም ይሰጠን ነበር፡፡
አሁን የትዝታ ዶፍ እየወረደ አስቸግሮኛል፡፡ የጊዜ ነገር ይገርማል፡፡ ጊዜው እንዴት ይሮጣል ጃል! ‹‹ኧረ ባባ ጃሌው›› እያልኩ እንደ ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ፤ ‹‹ጊዜ በረርክ በረርክ፤ ግና ምን አተረፍክ?›› እያልኩ እቀጥላለሁ፡፡   
አሰፋ፣ ‹‹ህይወት ፖለቲካ ብቻ አይደለም፡፡ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ ሳይንስ ፍልስፍና ወዘተ ያስፈልገናል፡፡ እኔ የምፈልገው ማዶ ለማዶ የቆሙ ፖለቲከኞች የሚዘላለፉበት ጋዜጣ አይደለም፡፡ ከልጆቻችን ጋር ተጋርተን ሀሳብ የምንሸምትበት የቤተሰብ ጋዜጣ ነው›› የሚል ሰው ነበር፡፡ ስለዚህ ‹‹አዲስ አድማስ›› አዲስ የአስተሳሰብ አድማስ ከፋች ነበረች፡፡
‹‹አዲስ አድማስ›› የአዲስ ሀሳብ ጋዜጣ ነበረች፡፡ በመጀመሪያው እትሟ የፊት ገጽ፤ አለቃ አያሌውን ዋቢ አድርጋ ‹‹ሰብአ ሰገሎች ኢትዮጵያውያን ናቸው›› የሚል ዜና ማተሟን አስታውሳለሁ፡፡ በወቅቱ እንዲህ ያለ ዜና በግል ጋዜጣ ይዞ መውጣት የተለመደ ነገር አልነበረም፡፡ ‹‹በተቃዋሚ ቅኝት፤ እንደ ኮሶ የመረረ የፖለቲካ ዜና ሳይሰሩ በገበያ መቆየት አይቻልም›› የሚል እምነት ነበር፡፡ ስለዚህ ብዙዎች የአሰፋን አቋም ‹‹ሳይወለዱ የመሞት ውሳኔ›› አድርገው ተመለከቱት፡፡ ግን እንደ ግምታቸው አልሆነም፡፡ ‹‹አዲስ አድማስ›› በአጭር ጊዜ ተወዳጅ ሆነች፡፡ እንደ ሰአቸ (ሰለሞን አበበ ቸኮል) ያሉ ወዳጆች አፈራች፡፡
አዲስ አድማስ የሀሳብ ገበያ ነበረች፡፡ የተሰተረ፣ የታሰበበትና ለዛ ያለው ማናቸውም ሀሳብ በጋዜጣዋ ሊስተናገድ ይችላል፡፡ ‹‹አዲስ አድማስ›› መዐዛው የሚያውድ የሀሳብ የአትክልት ስፍራ ሆነች፡፡
በተለይ የጋዜጣው ‹‹ኮር ቲም›› የሀሳብ ጓደኞች ነበርን፡፡ በቡና ጨዋታ እንኳን ሀሳብን በቸልታ የማያሳልፍ ክበብ ነበር፡፡ በጓደኝነትና በጨዋታ ስሌት ቸል ተብሎ የሚታለፍ ሀሳብ አልነበረም፡፡ በመካከላችን ብዙ የሚያግባቡ ጉዳዮች እንዳሉን፤ በርካታ የሚያለያዩን ነገሮችም ነበሩን፡፡ ‹‹በተለያየ ጎዳና እውነትን ፍለጋ የወጡ ወጣቶች›› ልንባል እንችላለን፡፡
ይህ የጋራ ሁኔታ የመከባበር መንፈስ የፈጠረልን ይመስለኛል፡፡ በሀሳብ ለማደግም ጠቅሞናል፡፡ ከሀሳብ ተቃርኖው የሚፈጠር ብልጭታም አንዳንድ ነገሮችን ወገግ እያደረገ ያሳየናል፡፡ በጣም የተለያየን ሆነን፤ በጣም ተመሳሳይ ነን ማለት ይቻላል፡፡ በሀሳብ የሚፋለሙ ወዳጆች አድርጎናል፡፡ ሀሳብ እና ልማድ፤ የፖለቲከኞች እና  የምሁራን ንግግር ጭምር በጥንቃቄ ይመዘናል፡፡ በሎጂክ እና በመርህ ይበለታል፡፡ እንኳን የሌላን ሰው ሀሳብ፤ ልማድ ያሸከመንን የራሳችን ሀሳቦች ጭምር በጥንቃቄ እንፈትሻለን፡፡ ጥሩ ራስን የመብለጥ ጥረት አድርገናል፡፡
አንዱ የሰራው ሥራ፤ በጉዳዩ ተቃራኒ አቋም እንዳለው በሚታሰብ ጓደኛ አስተያየት ይመዘናል፡፡ የሚታረመው ታርሞ፤ መሠረታዊ ልዩነታችን ይቀጥላል፡፡ ክርክራችን ልማድ ከሰወረው እና ከተዘነጋ የሀሳብ መፋለስ እና ከውሽልሽል ሀሳቦች ጠብቆናል፡፡ የመታረም ዕድልም ይሰጠናል፡፡ ይሁንና አንዳንዴ ክርክራችን ሰሚን ያስደነግጣል፡፡ አሰፋ ገና ብዙ በማያውቀን ጊዜ ክርክራችን ወደ ጸብ እንዳያመራ ይጨነቅ እንደ ነበር ነግሮኛል፡፡ ‹‹እኔ እኮ አንዳንዴ እንደዛ ስትከራከሩ የምትታጣሉ እየመሰለኝ እጨነቃለሁ፡፡ ከዚያ ለምሳ አብራችሁ ስትወጡ እገረማለሁ›› ብሎኛል፡፡
በእኔ እይታ፣ አዲስ አድማስ መረጃ የምናቀርብባት ገበታ ብቻ አልነበረችም፡፡ በአደባባይ የማሰብ ልምምድ ያደረግንባት ት/ቤት ጭምር ነበረች፡፡ ከግብዝነት ካልተቆጠረብኝ፣ የአዲስ አድማስ ባልደረባ የነበረው እዝራ እጅጉ ከሰሞኑ ‹‹እኔና 28ቱ አለቆቼ›› በሚል በፃፈው አንድ ጽሁፍ የጠቀሰውን አንድ ሀሳብ ማንሳት እሻለሁ፡፡
‹‹…ተፈሪና ሰለሞን ገ. ፈጽሞ አይረሱኝም፡፡ …የሚያነቧቸው መጽሐፎች እና የሚወያዩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዛሬ ሳስባቸው ድንቅ ይሉኛል….›› የሚለው ለጋስ አስተያየቱ ወደ ኋላ ዞሮ የማስታወስ ዕድልን መፍጠር ብቻ ሳይሆን፤ ‹‹አዲስ አድማስ›› እንደ አቴና ሰዎች ‹‹አጎራ›› ሆና እንዳስተማረችንም አስታውሶኛል፡፡
‹‹አዲስ አድማስ›› ምክንያታዊ አስተሳሰብ እንዲጠናከር፤ የግለሰብ መብቶችና ነጻነቶች እንዲከበሩ ለማድረግ የተሻለ ሥራ እንደሰራች አስባለሁ፡፡ በአንዳንድ ሚዛን ሳየው፣ ‹‹አዲስ አድማስ›› የላቀ የኤዲቶሪያል መመሪያ ነበራት፡፡ እንደ ‹‹አዲስ አድማስ››  የብሔር ፖለቲካን የተገዳደረ ጋዜጣ ያለ አይመስለኝም፡፡ ለዴሞክራሲ ስርዓት የሚበጅ የውይይትና የሀሳብ አበርክቶ አድርጋለች፡፡ የባህል እና የሥነ ጽሁፍ ልማቱን አግዛለች፡፡ ግን ከተሰራው ሊሰራ የሚገባው ነገር የበዛ መሆኑን አሁን የምንገኝበት ሀገራዊ ሁኔታ ያስረዳናል፡፡ ስለዚህ ‹‹አዲስ አድማስ›› ገና ብዙ የቤት ሥራ አለባት፡፡   
‹‹አዲስ አድማስ›› በሀሳብ ክፍ ብላ ‹‹የዘመኑን መንፈስ›› (Zeitgeist) መመርመር አለባት፡፡ በስውር የሚገዛንን ‹‹የዘመኑን መንፈስ›› መፈተሽ እና በባህል፣ በሀይማኖት እና በምሁራዊ አምባዎች እየተሸመነ ያለውን ነገር ማሳየት አለባት፡፡ ይህ ዘመን ፈጣን ነው፡፡ የፈጣን ለውጥ ዘመን ነው፡፡ ቀድም ሲል በ100 ዓመት ሂደት የሚከናወኑ ነገሮች፤ ዛሬ ከ25 ዓመት ባነሰ የጊዜ አውድ ታጭቀው ይከወናሉ፡፡ የከበደ ሚካኤልን ‹‹ሥልጣኔ ምንድናት?›› እንደገና ማንበብ ይኖርብናል፡፡
‹‹አዲስ አድማስ›› ስትወለድ የነበረው ዓለማዊ እና ሀገራዊ ሁኔታ በጣም ተቀይሯል፡፡ ቴክኖሎጂው፣ አስተሳሰቡ እና ፖለቲካው ሁሉ ብዙ ተለውጧል፡፡ ‹‹አዲስ አድማስ››፤ ሀገራችን በዚህ አዲስ ዓለም  ለምታደርገው ጉዞ አቅጣጫ አመላካች ፋና  ቤት መሆን ይገባታል፡፡ እንደ ሀገር ወይም እንደ ህዝብ ለምናደርገው ጉዞ አቅጣጫ አመላካች ሀሳቦች የሚስተናገዱባት መድረክ ሆና ማየትን እመኛለሁ፡፡
ምሁራን ዘመናችንን የ‹‹ድህረ እውነት›› ዘመን በሚል ይገልጡታል፡፡ የ‹‹ድህረ እውነት›› ዘመን (‹‹post-truth››) ሲሉ፤ ተጨባጭ ሀቆች የህዝብ አስተያየትን በመቅረጽ ረገድ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ የተዳከመበትና የህዝብ አስተያየትን በመቅረጽ ሂደት ግላዊ እምነት እና ስሜት ከፍተኛ ጫና የሚያሳድሩበት ዘመን መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡
በመገኛ ቋንቋው ‹‹Post-truth፡ relating to or denoting circumstances in which objective facts are less influential in shaping public opinion than appeals to emotion and personal belief.›› ይላል፡፡
እንዲህ ያለ ሀሳብ የሚያነሱ አንዳንዶች፤ መጪው ጊዜ ለሰው ልጆች በጣም ፈታኝ ጊዜ እንደሚሆን ያስባሉ፡፡ የትውልዱ አስተሳሰብ በጣም ተቀይሯል፡፡ በእኛ እና በልጆቻችን መካከል እጅግ ሰፊ የአስተሳሰብ ልዩነት ይታያል፡፡ ልጆች ከወላጆች ጋር ያላቸው የአስተሳሰብ ልዩነት አስፈሪ ነው፡፡ ቀደም ሲል ወላጆቻችን በእኛ በልጆቻቸው ላይ የነበራቸው ሥልጣን፤ ዛሬ እኛ በልጆቻችን ላይ የለንም፡፡
በእኛ ዘመን ‹‹አባት›› እውነት ነበር፡፡ በልጆቻችን ዘመን ‹‹እውነት ነው›› አባት፡፡ ‹‹Authorities are no more truth. Truth is the authorities››፡፡ እኛ ሌሎች ባሰቡልን ለመኖር ፈቃደኞች ነበርን፡፡ ነገር ግን ልጆቻችን በሌሎች ሀሳብ ተመስርተው ለመኖር ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ሁሉም ሰው በራሱ አስተሳሰብ ሊመራ ይወድዳል፡፡ የዛሬው ትውልድ በየራሱ አስተሳሰብ እየተመራ መኖርን የሚሻ ነው፡፡ ስለዚህ ዓለማችን እንደ ቁጥራችን በበዛ እውነት ተወጥራለች፡፡
ምድራችን በራሱ አስተሳሰብ እየተመራ ለመኖር በሚፈልግ ትውልድ ፈተና ተጋርጦባታል፡፡ በምድሪቱ ላይ ከባድ መከራ እንዣብቧል፡፡ ሰው ከራሱ ጋር ተጣልቷል፡፡ ሰው ከመንደሩ ወጥቶ የባከነ እና የባዘነ ፍጡር ሆኗል፡፡ ግራ መጋባት ሰፍኗል፡፡ ይህም እንደ ህብረተሰብ የመኖር ችሎታችንን አዳክሞታል፡፡ ብዙ እውነቶችን ይዘን፤ ተጣጥሞ እና ሰምሮ መኖር አቅቶናል፡፡ በጋራ ለመኖር የሚያግዙ ነገሮች ሁሉ፤ የነፃነት ጸር ተደርገው መታየት ጀምረዋል፡፡ ሁሉም ወደ slab city መሰደድ ይከጅላል፡፡ አሜሪካኖች slab city የሚሉት አላቸው፡፡ slab city ምንም ዓይነት የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ወይም የጤና ተቋማት፣ የዳኝነት እና የፖሊስ አካላት የማይገኙበት ደረቅ ጣቢያ ነው፡፡
በሀገረ በአሜሪካ፣ በካሊፎርንያ ግዛት፣ በኢምፔሪያል ካውንቲ (ወረዳ) የሚገኝ ሳኖራን የተባለ ጭው ያለ በረሃ አለ፡፡ የአሜሪካ ባህር ኃይል ይህን በረሃ፣በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት   የሥልጠና ካምፕ አድርጎት ነበር፡፡ ጦርነቱ ሲያበቃ፣ ሠራዊቱ የገነባውን ነገር ነቃቅሎ፤ የጣለውን ጥሎ ወጣ፡፡
እና በሳኖራን በረሃ ተገለል፤ ምንም ዓይነት የተደራጀ ስርዓት በሌለበት፤ የመብራት፣ የመፀዳጃ እና የውሃ አገልግሎት በማይገኝበት በዚያ በረሃ ለመኖር የሚሹ አንዳንድ ሰዎች የከተሙባት ቦታ ‹‹slab city›› ተባለች፡፡ ብዙ ‹‹ስላብ›› አግኝተውባት መሰለኝ፡፡ በህብረተሰብ የኑሮ ዘይቤ ተጨቆንን ያሉ ነፃነት ፈላጊ ሰዎች ይሄዱባታል፡፡ በslab city ለመኖር የሚመጡ ሰዎች፤ የበረሃውን ዋዕይ ተቋቁመው፤ የህግ አስከባሪ አካላት በሌሉበት አደገኛ አካባቢ ለመኖር ወስነው የሚመጡ ናቸው፡፡ ነፃነትን ፍለጋ አደገኛ  ነገሮችን እና ፈተናዎችን ተጋፍጠው ለመኖር ይመጣሉ፡፡ ‹‹ነፃነት ወይም ሞት›› ባዮች ናቸው፡፡
የልጆቻችን ዘመን እንዲህ ዓይነት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ መጓዝ የሚያስከትለውን አደጋ የሚናገሩ  ሰዎች እየሰማን ነው፡፡ ‹‹አደገኛ ጊዜ እየመጣ ነው›› እያሉም ነው፡፡ ሰው ከተፈጥሮ እና ከማህበረሰብ እየተነጠለ የግል መሻቱን ተከትሎ እየነጎደ ነው፡፡ የ‹‹slab city›› ነዋሪዎች ማህበራዊ ስርዓቱን የጭቆና አውራጃ አድርገው ይመለከቱታል፡፡
ታዲያ በዚህ አስተሳሰብ የታነጸ አዲስ ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ፤ በርካታ ሰዎች በራሳቸው አመለካከት ለመሄድ የሚፈልጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ጉዳዩ አስተሳሰባቸው ትክክል ነው - አይደለም የሚለው አይደለም፡፡ ዋናው ነገር አስተሳሰብ የተቀየረ መሆኑ ነው፡፡ ይሁንና ትውልዱ ገነትን በመሬት የመፍጠር ተምኔቱ፤ ምናልባት በመጪዎቹ 40 ወይም 20 ዓመታት ውስጥ ፈራርሶ አናቱ ላይ ሊከመርበት ይችላል፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ ቅዱስ መጻሕፍት ያስቡልን ነበር፡፡ ሽማግሌዎች ያስቡልን ነበር፡፡ በሰፈራችን ያሉ ደጋግ ሰዎች ያስቡልን ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም ሰው ለራሱ የሚያስብበት ዓለም ውስጥ ገብተናል፡፡ ሁሉም በየራሱ እይታ መዝኖ ምክንያታዊ ያልመሰለውን ነገር አሽቀንጥሮ ይጥላል፡፡ በግድ ተቀበል የሚለው የለም፡፡ ከተባለም በአመጽ ይነሳል፡፡ እንዲያ ሲሆን ወደ ራሱ slab city ይሰደዳል፡፡ ልጆቻችን እንዲህ ናቸው፡፡ ወይም በመሆን ሂደት ውስጥ ናቸው፡፡ እንኳን ሰው ራሱ ፈጣሪ ወርዶ ቢያናግራቸው በሀሳቡ ካላመኑ አይቀበሉም፡፡ በቅርቡ ኮሜዲያን እሸቱ ‹‹ሁላችንም የራሳችንን መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ ጀምረናል›› ያለው ቃል፤ ዘመናችንን ይገልጸዋል፡፡
የሀይማኖት መምህሩ ለሰንበት ተማሪዎቹ ‹‹ገነት ለመግባት ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ የተለያዩ ህጻናት የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ በመጨረሻም አንዱ ህፃን፤ ‹‹ወደ ገነት ለመግባት መጀመሪያ መሞት አለብን›› ብሎ መለሰ፡፡ ‹‹Die before you die›› ነው፡፡
ከተፈጥሮ እና ከማህበራዊ ህይወት ህግጋት ጋር ተጣልቶ፤ ወደ ገሃነም እንጂ ወደ ገነት መግባት አይቻልም፡፡ አጠቃላይ የህይወትን ምስጢር በመረዳት ለመኖር ካልሞከርን ገነት በአናታችን ላይ እንደ አሮጌ ቤት ይፈራርስብናል፡፡ እንዲሁ በየፊናችን ለመሄድ ከሞከርን፣ ዓይናችን እያየ ገነታችን ይፈራርሳል፡፡ ሰው ነፃነትን ፍለጋ የሚያደርገው ጥረት ባርነትን እየጎተተበት ነው፡፡ አንዳንዴ፣ ዣን ፖል ሳርትር፤ “ሰው ነጻ ሊሆን ተረግሟል” (Man is condemned to be free) የማለቱ ፍቺ ይኸ ይሆን?›› እላለሁ፡፡
ሰው የነፃነት ባርያ ሆኗል፡፡ ነፃነትን ሲመኝ፣ ባርነት ይወርሰዋል፡፡ የጠላው ነገር እየወረሰው የህሊና እረፍት አጥቶ ከራሱ ጋር ተጣልቷል፡፡ ይህን ፀብ እና ጩኽት በኬሚካል ድጋፍ ፀጥ ለማድረግ ይሞክራል፡፡ ከአሜሪካ ህዝብ 70 በመቶው በሐኪም በታዘዘ መድኃኒት ተደግፎ የሚኖር ነው፡፡ ምናልባት 30 በመቶው በራሱ ውሳኔ መድኃኒት ከጎዳና እየሸመተ የሚኖር ይሆናል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በርካቶች የአልኮል መጠጥ እና የዕጽ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ቁጥራቸው በ10 ሺህ ፐርሰንት ጨምሯል፡፡ ምናልባት በጥቂት ዓመታት ውስጥ 90 በመቶው የዓለም ህዝብ በኬሚካል ተደግፎ ለመኖር የሚገደድ ይሆናል፡፡ ‹‹ይህ ለምን?›› ከተባለ፤ ገነታቸው እየፈራረሰ ነው፡፡
ልጆቻችን ከራሳቸው እና ከማህበረሰባቸው ጋር ሰላም ፈጥሮ መኖር አቅቷቸዋል፡፡ እናም ልጆቻችን ከራሳቸው እና ከወንድማቸው ጋር በሰላም ለመኖር የሚያስችል ጥበብ እንዲማሩ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ስዊድኖች፣ በዓለም ደስተኛ የሚባሉ ህዝቦች መሆናቸውን እንሰማለን፡፡ ግን ራስን በማጥፋት እነርሱን የሚተካከል የለም፡፡ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ነገር በቀላሉ የሚያገኙት ስዊድኖች ከሞት በኋላ ህይወት በመኖሩ አያምኑም፡፡ ስለዚህ ጡረታ ሲወጡ፤ የተፈጥሮ ሞትን መጠበቅ እየሰለቻቸው ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡ ችግሩ ቁስ አይደለም፡፡ ሀሳብ እና አስተሳሰብ ነው፡፡
ይህ ትውልድ አስተሳሰቡን አስተካክሎ፤ ከቀዳሚው ትውልድ የተረከብናትን ዓለም ወይም ሀገር በመጠኑ የተሻለች ዓለም አድርጎ፤ ለተረካቢው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ  እንዳለበት ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ ትውልድ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መኖር እና ከተፈጥሮ ጋርም መታረቅ አለበት፡፡ ባለፉት ዓመታት ምድርን በብዙ አጎሳቁሏታል፡፡ አፈር ህይወት መሆኑን ዘንግቶ፤ ወርቅ ለማውጣት፣ መሬት አምካኝ መርዝ ይደፋል፡፡ ተራሮችን አራቁቷቸዋል፡፡ በጦርነት ብዙ ዘመናት አሳልፏል፡፡ አሁንም ጦርነት ማድረግ ቀጥሏል፡፡ ልጆቻችን በጦርነት ውስጥ ተወልደው፤ በጦርነት አድገዋል፡፡ ሰላም ምን እንደሆነ ጠፍቶባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እና እንደ አንድ ሀገር  ኃላፊነት ወስደን ይህን ሁኔታ በመቀየር ትውልዱን መታደግ ይኖርብናል፡፡ ልጆቻችን ከራሳቸው እና ከወንድማቸው ጋር በሰላም ለመኖር የሚያስችል አስተሳሰብ እንዲይዙ ማስተማር ያስፈልገናል፡፡ ሰዎች እንዴት መኖር እንደሚገባቸው ማስተማር ከፍተኛ አገልግሎት ነው፡፡ መልካም የሰው ልጅ ወይም መልካም ህብረተሰብ ወይም መልካም ሀገር ለመፍጠር የሚቻለው የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች በመፍጠር ነው፡፡ ‹‹አዲስ አድማስ›› በዚህ ረገድ የጎላ ድርሻ እንዲኖራት እመኛለሁ፡፡ አሁንም ‹‹አዲስ አድማስ ይታየኛል!››



Read 259 times