“የመሬት መንቀጥቀጥ እና የእሳተ ጎመራ ክስተት የሚያሰጋው የጂቡቲ መንገድ፣ አንዳች ነገር ቢገጥመው ኢትዮጵያ መፈናፈኛ አይኖራትም”… (የዛሬ ዓመት በአዲስ አድማስ ከወጣ ጽሑፍ የተወሰደ ነው። እውነትም ኢትዮጵያ ተጨማሪ የመውጫና የመግቢያ አማራጭ መስመሮች ያስፈልጓታል፤ የባህር በር ማግኘት ይኖርባታል ያስብላል)።
በአዋሽ አካባቢ ነዋሪዎች ላይ የሚያስከትለው የሕይወትና የንብረት አደጋስ? ከመሬት መንቀጥቀጥ ጋር የተዳበለ የእሳተ ጎመራ አደጋ ባለሙያዎችን በእጅጉ ያሳስባቸዋል። 80 ሺ ነዋሪዎች ከአደጋ አካባቢ ተነሥተው በሌላ ቦታ እንዲጠለሉ አድርጌያለሁ ብሏል - መንግሥት።
የአዲስ አበባ እና የሌሎች ከተሞች ስጋትስ? በርከት ያሉ ሕንጻዎችና ብዙ ነዋሪዎች የያዙ ከተሞች ላይ ስጋት ቢበረታ አይገርምም። ነገር ግን፣ የተጋነነ የስጋት ስሜትም ጥሩ አይደለም።
ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ባለፉት 300 ዓመታት እንዳልተመዘገበ የታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አፍሪካ “ለከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት” የተጋለጠች አይደለችም።
አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት “ይህ ነው” የሚባል የመሬት ንዝረት አያጋጥማቸውም - ከሌሎች ክፍለ ዓለማት ጋር ሲነጻጸር። አፍሪካን ብቻ ካየን ግን፣ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ እነ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ታንዛኒያ… ዋነኛ የስጋት ቦታዎች ናቸው።
ቢሆንም፣ “ያልተረጋጋ ነው” ተብሎ የሚጠቀሰው የስምጥ ሸለቆ አካባቢም ቢሆን፣ የከርሰ ምድር መዋቅሩ በአመዛኙ ለክፉ የሚሰጥ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
መቼም፣ አዲስ አበባ ውስጥ የመሬት ርዕደት ሳይነካቸው በፊት ብዙ ቤቶች ፈርሰዋል። ለኮሪደር ልማት። የፈረሱት ቤቶች በአብዛኛው… ከጥቂቶቹ በስተቀር፣ በጣም ያረጁ ቤቶች ናቸው። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ፣ ጥገናና እድሳት የማያውቃቸው የቀበሌ ቤቶች ናቸው በብዛት የፈረሱት።
በእርግጥ “ከምንም ይሻላሉ” ማለት ይቻላል። ከባዶ እጅ፣ ያረጀ ቤት ይሻላል። እውነት ነው። ነገር ግን በርካታ ነዋሪዎች፣ ደህና ምትክ ቤት ማግኘታቸውን ለመርሳት አይደለም። አዲስ ሰፊ ኮንዶምኒዬም ቤት ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም። እንደ ዕድል ቢቆጠር አይገርምም።
እንዲያም ሆኖ ግን፣ የብዙ ሰዎች ኑሮ ተናግቷል። የመተዳደሪያ ሥራቸውን አጥተዋል። ከመንገድ ዳር የነበሩ በጣም ብዙ የገበያ ሱቆች ፈርሰዋል። እንዘርዝረው ቢባል ማለቂያ የለውም። ዘርዝረን ብንጨርሰው እንኳ፣ “ደርሶብን ካላየነው በቀር” የሰዎችን ጉዳትና ጭንቀት ሙሉ ለሙሉ መረዳት ይከብዳል።
መንግሥት ይህን ይህን ማሰብ አለበት።
ደግሞም የነዋሪዎች ጉዳት ማሰብና ችግሮችን ማቃለል እንደሚቻል፣ ከራሱ ከመንግሥት ተግባር መረዳት ይቻላል። ምትክ የሥራ ቦታዎችን በማዘጋጀትና የማካካሻ ድጋፎችን በመስጠት፣ ነዋሪዎች ችግሮቻቸውን ታግለው እንዲያንሰራሩ ማነሣሣት ይቻላል። እንደሚቻልም በተወሰኑ ቦታዎች በተግባር ታይቷል። ከልብ ቀረብ ብሎ የነዋሪዎችን ችግር መታዘብና መገንዘብ፣ ብዙ ችግሮችንና ጭንቀቶችን ለማቃለል፣ አላስፈላጊ ንትርኮችንና ቅሬታዎችን ከመነሻው ለማስቀረት ይጠቅማል። መኖሪያና የሥራ ቦታ የፈረሰባቸውን ነዋሪዎች፣ በጥገኝነት ይኖሩ የነበሩትንም ጭምር በተቻለ መጠን ማካካሻ እንዲያገኙ፣ እግራቸውን እንዲተክሉ፣ ኑሯቸውን የሚያሻሽሉበት ዕድል እንዲፈጥሩ ማገዝ ተገቢ ነው። እንደዚያ ከሆነ፣ ያረጁና እጅግ የተጎሳቆሉ ቤቶች ቢፈርሱ ብዙም ችግር የለውም። የመሬት መንቀጥቀጥ ስጋት ለመቀነስ ባይረዳም እንኳ። ግን ሊረዳም ይችላል።
የስራና የመኖሪያ ቤት ያልፈረሰባቸው ነዋሪዎች ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም ማለት አይደለም። የከተማው መስተዳደር ባዘዘው ጊዜና መንገድ ሕንጻዎችን በፍጥነት ለማደስና ለማስዋብ፣ ብዙ ነዋሪዎች ተቸግረዋል። ነዋሪዎች ኪስ ውስጥ ሁልጊዜ በቂ ገንዘብ ይገኛል እንዴ? አይገኝም።
የእያንዳንዱን ሰው ኪስ ማወቅ ያስቸግራል። እዳ ያለበት ነዋሪ አለ። ገበያ የቀዘቀዘበት አለ። ያልተጠበቀ ወጪዎች የመጡበት አለ። ጥሪቱን ለአዲስ የሥራ ማስፋፊያ ያዋለ ሰውም ይኖራል። የእያንዳንዱ ሰው ችግር በዝርዝር ማወቅ ይከብዳል።
የራሱን መኖሪያና የራሱን ሕንጻ አድሶ ማሳመር ጠልቶ ሳይሆን፣ ትዕዛዝ በመጣበት ወቅት ምንም የገንዘብ ዓቅም ላይኖረው ይችላል። አንዳንድ ባለሥልጣናት ግን፣ ይህን ከማገናዘብ ይልቅ፣ “ሊያስወቅሰን ነው” በሚል ስሜት ወደ እልህና ወደ ቅጣት ውሳኔ ይቸኩላሉ። አንዳንዱ ደግሞ ሥልጣኑን የማሳየት ጥሩ አጋጣሚ ያገኘ ይመስለዋል።
የከተማው መስተዳድር እንዲህ ዓይነቱን የነዋሪዎች ችግር በበጎ መንፈስ ቢያገናዝብ መልካም ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። ለእግረኞች መንገድ መክፈት አለባችሁ ተብለው፣ የሕንጻዎች የመጀመሪያ ፎቅ ላይ ግድግዳዎች እንዲፈርሱ ተደርጓል። ያለ ጥርጥር ለባለሕንጻዎች ትልቅ ገቢ ያሳጣቸዋል። ከመንገድ ዳር የሚገኝ ለዚያውም የሕንጻው የመጀመሪያ ፎቅ፣ ለንግድ ሥራ በጣም ተመራጭ ነው። የእግረኛ መተላለፊያ እንዲሆን አድርጉ ሲባል፣ በየወሩ ከ50 ሺ እስከ መቶ ሺ ብር የኪራይ ገቢ ሊያሳጣቸው ይችላል። በእርግጥ፣ እስካሁን እንደምንሰማው፣ የከተማው መስተዳድር ይህን የነዋሪዎችና የሕንጻ ባለቤቶች ችግር ሳይገነዘብ የቀረ አይመስልም። በየጊዜው ምስጋና ሲገልጹ እንሰማለንና። ቢሆንም ግን፣ ከምስጋና ባሻገር፣ ወጪዎችን የሚያካክስ የሆነ ዘዴ ቢፈጠር መልካም ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። አንዳንድ ሕንጻዎች ለእግረኞች መንገድ ለመክፈት አይመቹም። እንደ ምሶሶ የሚያገለግሉ ግድግዳዎችን መነካካት፣ ሕንጻዎችን ሊያናጋ ይችላል። የሕንጻው ጥቂት አምዶች ያለ ተጨማሪ ድጋፍ ከቀሩ፣ ሕንጻውን የመሸከም ዓቅማቸው ይቀንሳል። ያለ ድጋፍ መቅረት የሌለባቸውን አምዶችን በብረት ማገሮች ለማጠናከር የሚሞክሩ አይታችሁ ይሆናል። የግድ ቢሆንባቸው ነው።
በተለይ አሁን የመሬት መንቀጥቀጥ በየዕለቱ በሚያጋጥምበት ወቅት፣ ሕንጻዎች ላይ ተጨማሪ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።
እስካሁን በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ አደጋ የደረሰበት ሕንጻ አለመኖሩ በጎ ነው። በእርግጥም፣ በብረትና በኮንክሪት የተሰሩ የአዲስ አባባ መኖሪያ ቤቶችና ሕንጻዎች፣ ብዙም ለአደጋ የተጋለጡ አይደሉም ብለው የሚናገሩ ባለሙያዎች አሉ።
ሁሉም ሕንጻዎች ባይሆኑም፣ ብዙዎቹ በቀላሉ የሚፈርሱ አይደሉም። በወፋፍራም አምዶች የመገንባት ልማድ፣ ለዚህ ለዚህ ይጠቅማል ይላሉ - ባለሙያዎች።
ደግሞስ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ለኢትዮጵያ ያን ያህል ያሰጋታል ወይ?
በእርግጥ በአፍሪካ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከሚያጋጥማቸው ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች።
ነገር ግን፣ ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነጻጸር፣ አፍሪካ ውስጥ ያን ያህልም የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አይደርስም ማለት ይቻላል።
ባለፉት 120 ዓመታት ውስጥ፣ በሬክተር መለኪያ ከ8 ነጥብ በላይ የተመዘገበባቸው 95 የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች በዓለም ዙሪያ ተከስተዋል። አፍሪካ ውስጥ ግን እንዲህ ዓይነት ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አንዴም አልተከሰተም።
በ120 ዓመታት ውስጥ ከ8 ነጥብ በላይ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የደረሰባቸው ክፍለ ዓለማት
በኤስያ 44
ደቡብ አሜሪካ 20
አውስትራሊያ ዙሪያ 15
ሰሜን አሜሪካ 13
አውሮፓ 2
አንታርክቲካ 1
አፍሪካ 0
ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ 7 ነጥብ የደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በታሪክ አልተመዘገበም - ባለፉት 300 ዓመታት።
ባለፉት 150 ዓመታት ውስጥከ5 እስከ 6.5 ነጥብ የተመዘገበባቸው ጥቂት አደጋዎች ተከስተዋል። ግን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። በአማካይ በ10 ዓመት አንዴ ቢከሰት እንደማለት ነው።
ቢሆንም ግን የአደጋ ትንሽ የለውም። ኢትዮጵያ በ10 ዓመት ውስጥ አንዴ የሚያጋጥማት ዓይነት አደጋ፣ በብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ላይ አይከሰትም። በመቶ ዓመት ውስጥ አንድም ጊዜ አላጋጠማቸውም።
ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ማሊ፣ ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን የመሳሰሉ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ላይ ነው አደጋ የሚበረታው። አዎ ይበረታባቸዋል።
ነገር ግን፣ ከሌሎች ክፍለ ዓለማት ጋር ሲነጻጸር፣ ከቁጥር የሚገባ አይደለም።
የጂኦሎጂ አጥኚዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ በአፍሪካ ውስጥ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ብዙም የማይከሰተው፣ በከርሰ ምድር አወቃቀሩ ምክንያት ነው። የአፍሪካ ከርሰ ምድር ከሞላ ጎደል አንድ ወጥ ንጣፍ ነው ይላሉ። ትንሽ ለየት የሚለው የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ላይ ነው።
ከኢትዮጵያ አፋር ክልል ጀምሮ፣ በኬንያናና በታንዛኒያ በኩል እስከ ሞዛምፒክ ድረስ የሚዘልቀው የስምጥ ሸለቆ፣ የአፍሪካ ከርሰ ምድር ለሁለት ተሰንጥቋል - ከበርካታ ሚሊዮን ዓመታት በፊት።
እናም፣ የአፋር ክልል፣ ሦስት የከርሰ ምድር ንጣፎች የሚሳሳሙበት አካባቢ ነው ይሉታል።
ከሰሜን በኩል ያለው ትልቁ የአፍሪካ ንጣፍ…
ከደቡብ በኩል ወደ ሶማሊያ አቅጣጫ የተዘረጋው ንጣፍ… እንዲሁም
የቀይ ባህር መስመርን ተከትሎ ወደ ምስራቅ በኩል የተነጠፈው የአረቢያ ንጣፍ ብለው ይዘረዝሯቸዋል።
አህጉር የሚያካክሉ የከርሰ ምድር ንጣፎች እርስ በርስ የሚሳሳሙበት አካባቢ፣ ለመሬት መንቀጥቀጥ መነሻ ይሆናል። እንዲያውም የመሬት መንቀጥቀጥ ዋነኛ መንስኤ፣ የንጣፎቹ እንቅስቃሴ ነው ይባላል።
የከርሰ ምድር የአለት ንጣፎች ሲንቀሳቀሱ፣ እርስ በርስ መነካካት፣ መፋተግ፣ መገፋፋት ይኖራል። ከባባዶቹ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሚከሰቱት በዚህ ምክንያት ነው - ተጠጋግተው በሚፋተጉ የምድር ንጣፎች ሳቢያ።
ደግነቱ፣ በአፋር ክልል እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ የስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚከሰተው የከርሰ ምድር ንጣፎች እንቅስቃሴ፣ ከዚህ ይለያል። እርስ በርስ እየተጠጋጉ የመገፋፋት ሳይሆን እየተለያዩ የመራራቅ ነው - የንጣፎቹ እንቅስቃሴ።
በመቶ ዓመት ውስጥ በአማካይ አንድ ሜትር ያህል ይራራቃሉ ይባላል። በዚህ ከቀጠለ፣ ከሚሊዮን ዓመታት በኋላ፣ የአፍሪካ አህጉር ለሁለት ተሰንጥቆ ከመሃል ባሕር ሊፈጠር ይችላል ተብሎም ይተነበያል።
በሌላ አነጋገር፣ ዓይነቱ ምንም ሆነ ምን፣ የከርሰ ምድር ንጣፎች እንቅስቀሴ፣ የመሬት መንቀጥቀጥን ያስከትላል። ነገር ግን፣ በአፍሪካ አህጉር ንጣፎች ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ፣ “እየተጠጋጉ የመፋተግና የመገፋፋት እንቅስቃሴ” ስላልሆነ፣ አህጉራችን ክፉኛ አይንቀጠቀጥም።
በእርግጥ፣ ከዚህ ጎን ለጎን ነገሮችን ሊያወሳስብና ሊያባብስ የሚችል ሌላ የአደጋ መንስኤ አለ - የእሳተ ጎመራ አደጋ።
የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ፣ ለእሳተ ጎመራ አደጋ የተጋለጠ ነው። ከከርሰ ምድር ንጣፍ እንቅስቃሴ ጋር ሲደማመር፣ የቀለጠ አለት ፈንድቶ ሊወጣ ይችላል። በርካታ ባለሙያዎችን በእጅጉ የሚያሳስባቸውም ይሄው ነው። ከመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችል የእሳተ ጎመራ አደጋ፣ በአዋሽ አካባቢ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ይሰጋሉ።
አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞችስ?
ከስምጥ ሸለቆ አካባቢ እየራቅን በሄድን ቁጥር፣ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በአማካይ እየቀነሰ ይሄዳል። በአመዛኙ አደጋው ይቀንሳል ለማለት እንጂ፣ ሁልጊዜ አደጋው ትንሽ ይሆናል ለማለት አይደለም። እንደየ አካባቢው መልክዓ ምድርና የአፈር ሁኔታ አደጋው ሊለያይ ይችላል።
በዚያ ላይ የመንገዶችና የሕንጻዎች ግንባታ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት፣ እንደ ግንባታዎቹ ዓይነት፣ ብዛትና ርዝመት ይለያያል። የግድቦች ዲዛይንና ግንባታ ላይ ብዙ ጥንቃቄ ይደረጋል። በየጊዜውም ቅኝትና ፍተሻ ይካሄዳል። ሕንጻዎች፣ ድልድዮችና መንገዶች ላይም ተመሳሳይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
የጂቡቲ መስመር፣ የኢትዮጵያ የደም ሥር
በአፋር አካባቢ የሚከሰት የመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ የእሳተ ጎመራ አደጋ፣ በአስፋልት መንገዶች ላይ የሚያደርሰው አደጋ በጣም አስጊ መሆን አልነበረበትም።
ነገር ግን፣ የኢትዮጵያ መውጫና መግቢያ መንገድ፣ የጂቡቲ መስመር ብቻ ነው ማለት ይቻላል። አንድ ሳምንት ሁለት ሳምንት የጂቡቲ መስመር ቢቋረጥ፣ ለኢትዮጵያ ትልቅ አደጋ ነው። “ኢትዮጵያ ተጨማሪ የመውጫና የመግቢያ አማራጭ መስመሮች ያስፈልጓታል፤ የባህር በር ማግኘት ይኖርባታል” የሚለው ሐሳብ ቀላል ጉዳይ እንዳልሆነ ከዚህ አጋጣሚ መረዳት ይቻላል።
የዛሬ ዓመት በአዲስ አድማስ የታተመ ዘገባ እንዲህ ይላል።
“የመሬት መንቀጥቀጥ እና የእሳተ ጎመራ ክስተት የሚያሰጋው የጂቡቲ መንገድ፣ አንዳች ነገር ቢገጥመው ኢትዮጵያ መፈናፈኛ አይኖራትም”።
እውነት ነው። ነገር ግን፣ ለጊዜው አሁን አማራጭ መስመር መፍጠር አይቻልም። በአንድ ጀምበር የሚሆን ነገር አይደለም። ለዘለቄታው ግን፣ አማራጭ መንገዶችና አስተማማኝ የባሕር በር ለአገራችን ያስፈልጋሉ።
እስከዚያው፣ በእጅ ያለውን የጂቡቲ መስመር በጥንቃቄ ከመጠበቅ ውጭ ሌላ መፈናፈኛ የለም። በመሬት መንቀጥቀጥ ወይም በእሳተ ጎመራ ሳቢያ ጉዳት እንዳይደርስበት ዕለት በዕለት መከታተልና የመከላከያ ዘዴ ማበጀት የመንግሥትና የባለሙያዎች ኃላፊነት ነው።
ምናልባት ጉዳት ከደረሰበትም፣ ሳይውል ሳያድር በፍጥነት ለመጠገንና መፍትሔ ለመፍጠር ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል።
በአቅራቢያና በአመቺ ቦታዎች የግንባታ መሣሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ከባለሙያዎች ጋር ማሰናዳት፣ ለነገ የማይባል ሥራ ነው። “አንዴ አሰናድቻለሁ” ብሎ ለመቀመጥ አይደለም። የተሰናዱ ቁሳቁሶችንና መሣሪያዎችን በየጊዜው እያዩ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
አደጋ ካልደረሰ፣ መልካም! አደጋ ከደረሰስ?
ሳንሰናዳ ከጠበቅን፣ የአገርን ኢኮኖሚ የሚያቃውስ ከባድ ችግር ፈጠርን ማለት ነው። የነዳጅ፣ የመለዋወጫ ዕቃና የማዳበሪያ እጥረት፣ በአገሪቱ የእርሻና የኢንዱስትሪ ምርት ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለማሰብ ያስፈራል።
የፍጆታ ሸቀጦች ዕጥረትም ቀላል አይሆንም።
በዚያ ላይ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች መንገድ ተዘግቶባቸው እዚሁ ሲቀሩ የአገሪቱ የዶላር ዕጥረት ክፉኛ ይባባሳል።
ምናለፋችሁ! እርስ በርስ ተያይዞ እንደሚወርድ ናዳ ነው የሚመስለው። ነገር ግን፣ ከወዲሁ በመጠንቀቅና በቀላል ዝግጅት አማካኝነት ለአደጋዎች ፈጣን መፍትሔ ማበጀት እንችላለን - በኋላ ከመቆጨት፣ በኋላ ከመወነጃጀል።