የአክሱም ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት የከተማዋ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ የጣለውን ዕግድ ለማስነሳት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱን የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት አስታውቋል። ቀደም ሲል ምክር ቤቱ ዕግዱን ለማስነሳት በተለያዩ መንገዶች ያደረጋቸው ጥረቶች እንዳልተሳኩ ገልጿል።
ባለፈው ረቡዕ ታሕሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ም/ቤቱ ባወጣው መግለጫ፣ “የክልሉ ትምህርት ቢሮ ችግሩን በመፍታት ረገድ ደብዳቤ ከመጻፍ ያለፈ ውጤታማ ሚና አልተጫወተም” ብሏል። አክሎም፣ በሂጃብ ምክንያት የ12ኛ ክፍል ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የመቀመጥ ዕድል እንደተነፈጋቸው አስታውቋል።ምክር ቤቱ በማብራርያው፣ የአክሱም ከተማ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃባቸውን ለብሰው እንዳይማሩ የተደረገው ክልከላ ሃይማኖታዊና ዓለማዊ የሰው ልጆችን መብት የሚጋፋ መሆኑን አንስቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ችግሩን ለመፍታት ብዙ አማራጮች መሞከራቸውም ተጠቅሷል።
“ክልከላው እንዲነሳ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ያልተሳካ ሽምግልና እና መተግበር የማይችል ደብዳቤ ከመፃፍ የዘለለ ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ የለም” ሲል ምክር ቤቱ ስሞታውን አትቷል። በአክሱም ከተማ የሚገኘው ትምሕርት ቤት አንዳንድ አመራሮች ከራሳቸው የሃይማኖት ፍላጎትና የትምህርት መብት አተያይ በመነሳት ተማሪዎች ወደ ትምሕርት ገበታቸው እንዳይመለሱ ማድረጋቸውን ምክር ቤቱ ጠቁሟል።በሂጃብ ምክንያት የ12ኛ ክፍል ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የመቀመጥ ዕድል እንደተነፈጋቸው የከሰሰው ከፍተኛው ምክር ቤት፤ ዕገዳው የሙስሊም ተማሪዎችን መብት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት የጣስ ድርጊት ነው በማለትም ምክር ቤቱ ዕገዳውን አውግዞታል። ምክር ቤቱ ጉዳዩን ሁሉም ትግራዋይ እንዲያወግዘው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ “ከቀናት በፊት በአቋም መግለጫችን እንደጠቀስነው ‘ክልከላው በአፋጣኝ ዕልባት ካልተሰጠው፣ በሕግ እንጠይቃለን’ ባልነው መሰረት ጉዳዩን ወደ ሕግ ወስደነዋል” ብሏል።
የትምህርት ቢሮው ችግሩን በጥቂት ቀናት ውስጥ ካልፈታ፣ ቀጣይ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት አስጠንቅቆ እንደነበር ይታወሳል።በተያያዘ ዜና፣ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች የተሰኘው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት፣ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በአክሱም ከተማ ትምሕርት እንዲቋረጥ ባደረጉ አካላት፣ ትዕዛዝ የሰጡና ወደ ግቢው እንዳይገቡ የከለከሉ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ድርጅቱ ባለፈው ዓርብ ታሕሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ለአዲስ አድማስ በላከው አጭር ሪፖርት፣ በተማሪዎቹ ላይ የተጣለውን ዕግድ ተከትሎ፣ የክልሉ ትምሕርት ቢሮ ለአክሱም ከተማ አስተዳደር ትምሕርት ጽሕፈት ቤት የጻፈው ደብዳቤ ለችግሩ ግልጽ መፍትሔ የሚሰጥ አለመሆኑን ጠቅሶ፣ “ችግሩ እስከ አሁን እንዲቀጥል አስተዋጽዖ አድርጓል” በማለት ነቅፏል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 25 ላይ የተደነገገውን የዕኩልነት መብት፣ የሃይማኖት፣ የዕምነትና የአመለካከት ነጻነት መብት አንቀጽ 27ን ጨምሮ፣ ልዩ ልዩ መመሪያዎች መጣሳቸውን አትቷል። ድርጅቱ፣ የትግራይ ክልል ትምሕርት ቢሮ በአክሱም ከተማ ትምሕርት እንዲቋረጥ ባደረጉ አካላት፣ ትዕዛዝ የሰጡና ወደ ግቢው እንዳይገቡ የከለከሉ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ የጠየቀ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ወደ ትምሕርት ገበታ በአፋጣኝ እንዲመለሱ በማድረግ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፎርም እንዲሞሉ እንዲደረግም ጥሪ አቅርቧል።
Saturday, 11 January 2025 12:13
“የአክሱም ሴት ሙስሊም ተማሪዎችን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ወስጄዋለሁ”
Written by Administrator
Published in
ዜና