Saturday, 11 January 2025 12:15

የ25 ዓመት የሃሳብና የዕውቀት ጉዞ!!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የመጀመሪያው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ታትሞ ለንባብ የበቃው ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር - የዛሬ 25 ዓመት በዕለተ ቅዳሜ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ያለ አንድ ቅዳሜ በስተቀር ጋዜጣው ያልታተመበት ጊዜ  የለም፡፡ ያም ቢሆን የተከሰተው በ97 ምርጫ ማግስት በተፈጠረው  ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ነበር፡፡
የዛሬ 20 ዓመት፣ የአዲስ አድማስ ጠንሳሽ፣ መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ (አሴ) በድንገተኛ ህመም ህይወቱ ባለፈበት ወቅት እንኳን ጋዜጣው ሳይታተም አልቀረም፡፡ ረቡዕ ከቀብር በኋላ ቢሮ ገብተን የቅዳሜውን ጋዜጣ ስናዘጋጅ ነበር፡፡ ከሃዘናችን ጋር እየታገልንም ቢሆን የቅዳሜውን ሳምንታዊ ጋዜጣ በጉጉት ለሚጠብቁን ውድ አንባቢያን  አድርሰናል፡፡ በዚህም ኩራትና ክብር ይሰማናል፡፡ የጋዜጣው መሥራች አሰፋ ጎሳዬም ቢሆን፣ ከምንም በፊት ቅድሚያና ትኩረት የሚሰጠው ለአንባቢያን ነበርና፡፡   
እነሆ አዲስ አድማስ  ከዚያም በኋላ ሁለት አሰርት ዓመታትን አስቆጥራ፣ በብዙ ውጣ ውረዶችና ተግዳሮቶች አልፍ፣ እነሆ ለ25ኛ ዓመቷ በቅታለች፡፡ ኮረኮንች በበዛበት የአገራችን የግል ፕሬስ፣ ሩብ ክፍለዘመን ቀላል ዕድሜ አይደለም፡፡ ረዥም ዕድሜ ነው፡፡ ትልቅ ስኬትም ነው ማለት ያስደፍራል፡፡   
ለዚህ የደረስነው ግን  በውድ አንባቢያን ገንቢ አስተያየትና ድጋፍ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ አጋጣሚ ልባዊ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ ለአዲስ አድማስ ህልውናና በስኬት መቀጠል ከእኛ ከአዘጋጆቹ እኩል የሚጨነቁና የሚጠበቡት የረዥም ጊዜ ጽሁፍ አቅራቢዎችም ሌሎቹ ትልቅ ምስጋና የምንቸራቸው ባለውለታዎች ናቸው፡፡
ማስታወቂያቸውን በጋዜጣችን ላይ የሚያወጡ የንግድ ድርጅቶችና የመንግሥት ተቋማትም ሁነኛ  አጋሮቻችን  ናቸውና ከልብ ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡
መጪው ጊዜም ነጻ ሃሳብ በነጻነት የሚንሸራሸርበት፣ ዕውቀትና ሥልጡንነት የሚያብብበት፣ የንባብ ባህል የሚዳብርበት  እንዲሆን እንመኛለን፤ ለዚያም በትጋት መሥራታችንን እንቀጥላለን፡፡
እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን!!

Read 320 times