Saturday, 11 January 2025 13:24

የትዳርና የፍልስፍና ጋብቻ

Written by  ሙሉጌታ ቢያዝን
Rate this item
(1 Vote)

በሳይንስ ዘርፍ ስሙ ቀድሞ የሚነሳው፣ የተፈጥሮ ፈላስፋ(natural philosopher) የሚባለው አይዛክ ኒውተን ‘ድንግልናውን እንደያዘ በ84 ዓመቱ, ይቺን ዓለም ተሰናበተ፤ የሚለውን ታሪክ ባነበብኩ ጊዜ እጅግ አዘንኩ፡፡ ስሙን የሚያስጠራ ልጅ ባይኖረውም፣ ስሙን የሚያስጠሩ በርካታ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለዓለም ማበርከቱን በሰማሁ ጊዜ ግን ከኃዘኔ ፈጥኜ ተጽናናሁ፡፡
ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት በጋርድያን ጋዜጣ የፍልስምና ፕሮፌሰሩ ጆናታን ወልፍ (Jonathan Wolff) “why do philosophers make unsuitable life partners? በሚል ርእስ የጻፈውን መጣጥፍ ሳነብ፣ እሱ ይገርምሃል? “…ፕሌቶ፣ ሆብስ (Thomas Hobbes)፣ ሎክ (John Lock)፣ ሁሜ (David Hume)፣ አዳም ስሚዝ(Adam Smith)፣ ዴካርት (Descartes)፣ ስፒኖዛ(Benedict de Spinoza)፣ ሌይቢንዝ (Leibniz)፣ ካንት (Immanuel Kant)፣ ሾፐን አወር (Arthur Schopenhauer)፣ኪርከጋርድ (Soren Kierkegaard)፣ ቮልቴር (François-Marie Arouet)፣ አኪውነስ (Thomas Aquinas)፣ ሳርት (Jean-Paul Sartre) እና ቤንታምን (Jeremy Bentham) ወዘተ ሁሉም አላገቡም፤አልወለዱም…” አለኝ፡፡
 “ሴት የእግዚአብሔር ሁለተኛ ስሕተት ናት” የሚለው ኒቼ (የመጀመሪያው ስሕተት አዳም መኾኑ ነው፡፡ የአዳም ሲገርመን ሔዋንን ደገመ ዓይነት!) ከነዚህ መደብ ነው፡፡  ይህ ተጋፊ አስተያየቱ ‘ፍልስፍናው ከሴት ጥላቻ የመነጨ ይኾን?’ የሚል ጥያቄ እንዲነሣበት ምክንያት ኾኗል፡፡ ለምን ቢሉ እንደ ብዙዎቹ ላጤ ፈላስፎች ከጋብቻ 40 ክንድ መራቅ ፈልጎ ሳይኾን፣ ካንድም ሁለት ጊዜ የጋብቻ ጥያቄው ውድቅ ስለተደረገበት ነው፡፡  
ከሴት ፈላስፎች ሲሞን ደበቯር (Simone de Beauvoir)፣ ሃና ኤህረንት (Hannah Arendt)፣ ሲሞን ዌል (Simone Weil)፣ አሪስ ሙርዶክ (Iris Murdoch) ሁሉም ልጆች አልነበራቸውም፡፡ ጃክ ሩሶ(Jean-Jacques Rousseau) አግብቶ አምስት ልጆች ቢያፈራም (ለልጆቹ መልካም ስለኾነ ነው ብሎ ቢያስተባብልም)፤ ዕጣቸው ለሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅት መሰጠት ነበር፡፡ ጆርጅ በርክሌይ (Bishop Berkeley) እና ጆን ስቱዋርት ሚል ዘግይተው ቢያገቡም ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ኤፒክታይተስ በስተርጅና የወዳጁን ልጅ በጉዱፈቻ ልጅ አድርጎ የኢፒኩረስን ፈላስፎች ልጅ ማሳደግ የለባቸውም የሚለውን ድምዳሜ ፉርሽ ቢያደርግም ከአብራኩ የወጣ ልጅ አልነበረውም፡፡
እንደሌይተር ሪፖርትስ (Leiter Reports) የምንጊዜም ጉምቱና ተፅዕኖ ፈጣሪ ከተባሉ የዓለማችን 20 ፈላስፋዎች ውስጥ ቢያንስ 13 ከአብራካቸው የተከፈለ፣ከወገባቸው የወጣ ልጅ አልነበራቸውም፡፡
ሜሪ ወልስቶንክራፍት (Mary Wollstonecraft)ን ብንወስድ አንጋፋ ሥራዎቿን ያበረከተችውም ልጅ ከመውለዷ በፊት ነበር፡፡ ካርል ማርክስ ፍልስፍናን ትቶ ፊቱን ወደ ኢኮኖሚክስና ፖለቲካ ያዞረው ልጅ ከወለደ በኋላ መኾኑን ስናጤን፣ “አወይ ልጅ ማሰሪያው አወይ ልጅ ገመዱ፣ጎጆማ ባዳ ነው ጥለውት ቢሔዱ” የሚለውን ሀገርኛ ተረት ያስታውሰናል፡፡ ከዚህ ተነሥተን ‘ሳትወልድ ብላ’ እንደሚባለው፣ ‘ሳትወልድ ተፈላሰፍ’ ብንልስ አያስኬድ ይኾን?  የሕፃናት ተረት ለመጻፍ አልሞ ከመምህር (እንዲያ መባሉ ደስ ስለሚለው ነው) ኃይለመለኮት መዋዕል ጋ ማጀቴ የሔደው ስብሐት ለአብ፣ ‘ጻፍ እንጂ’ ሲባል “ለምን ብየ ነው የምጽፈው? እዚህ እኮ እያንዳንዱ ሰው ‘ኖብል’ ነው” እንዳለው’ ከልጅ ወዲያ ፍልስፍና የለም’ ብለው ይኾን?
ምክንያቱ ምን ይኾን? ‘የአጋጣሚ ወይስ ምን?...’  ሲል ወልፍ ይጠይቅና ሦስት መላምቶችን እንዲህ ሲል ይዘረዝራል፡፡  ቤተሰብ መመሥረት ፍልስፍናን ስለሚያፍናት?  ፈላስፎች ባሕርያቸው ወጣ ያለ /ከሰው የማይገጥም/ ስለኾኑ? ወይስ በጥልቅ ማሰላሰል/ፍልስፍና ብህትውናን በእጅጉ ስለምትሻ?
ሶቅራጥስ “አግባ፣ጥሩ ሚስት ከገጠመህ ደስተኛ፣ ካልገጠመህ ደግሞ ፈላስፋ ትኾናለህ” ሲል ይመክራል፡፡ እና ከላይ የተጠቀሱት ፈላስፎች በሞላ ትዳር ቢይዙ ኖሮ ፈላስፋ አይኾኑም ነበር?  
በቴክኖሎጂ ስሟ በፊት አውራሪነት የምትጠቀሰዋ ጃፓን፤ ዜጎቼ ‘መውለድ፣ መዋለድ አቆሙ’ ብላ ተጨንቃለች፡፡ በ2023 ብቻ የሕዝብ ብዛቷ በግማሽ ሚሊዮን አሽቆልቁሏል፡፡ ለአንድ ሕዝብ አነስተኛው የመውለድ መዋለድ ምጣኔ (low fertility rate) 2.1 ሲኾን፤ የጃፓን ግን 1.3 ነው፡፡ ይህ የሕዝብ መሳሳት ሀገሪቷን ‘ማን ሊረከበኝ ነው’ የሚል ብቻ ሳይኾን ‘ቴክኖሎጂውን ማን ሊያስቀጥል ነው?’ የሚል ስጋት ቢንጣት የተገባ ነው፡፡
የአልበርት አነስታይን አባት ለሳይንስ ቅርብ (ኤሌክትሪካል ኢንጂነር) ነበር፡፡ የአቶሚክ ፊዚስቱ ሲቦርግ አባት ማሽኒስት ነበር…የባዮ ኬሚስቱ ሌይነስ ፓውሊንግ አባት ፋርማሲስት ነበር፡፡ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከስንት አንድ  “Like father Like son” የሚለው ሊሠራ ይችላል፡፡ በቅርቡ የተደረገው ጥናት ግን “የሀሳብ ልህቀት የሚያጎናጽፈው ጂን (gene) በአያሌው የሚገኘው ከኤክስ (X) ክሮሞዞም ነው” ይለናል፡፡ ስለዚህ የላቀ አእምሮ ልጆችን ወደ ትውልድ የማሸጋገሩን ሥራ ተፈጥሮ ለእናቶች ስላደለች፣ ‘ፈላስፎች ልጅ ካልወለዱ ፈላስፋ ልናጣ አይደለም?’ የሚለውን ስጋት አዘል ጥያቄ ውድቅ ያደርገዋል፡፡
ወደ ነጥቤ ስመለስ “ከጋብቻ፣ ከልጅና ከቤተሰብ ኃላፊነት ያፈገፈጉበት ምክንያት ምንድር ነው?” ብለን ጠይቀን ሳናበቃ፤ “ያገቡትም፣የወለዱትም አባትነታቸውን በወጉ ለመወጣት ብቁ ናቸው” ማለት እንደማይቻል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ወደ ሕፃናት ሥነ ጽሑፍ የሚያዘንብለው ዋልተር ቤንጃሚን (Walter  Benjamin)፤ ብቸኛ ወንድ ልጁ ሲፈልገው የሚያገኘው አባት አልነበረም፡፡ የበርትራንድ ሩሰል ሴት ልጅ ካትሪን ቴይት በአውደ ዕለቷ ላይ ባሰፈረችው መልእክት፤ “በኅሊናዬ ተቀርጾ የቀረው የአባቴ ቀጥ ያለ ጀርባና እንዳንተያይ በመካከላችን የከለለን ስውር ግድግዳ ነበር” ትላለች፡፡ የኦክስፎርዱ ፈላስፋ ኤ.ጄ አየር (A. J. Ayer) ወንድ ልጅ፣ ኒክ አየር  (Nick Ayer) ደግሞ ቃል በቃል “አባቴ በጣም ያፈቅረኛል፤ ነገር ግን አባቴ ፈላስፋ ቢኾንልኝ ብለው ለሚመኙቱ አትመኙት (“My father loved me very much, but I would still say to anyone who might be considering getting a philosopher as a father, don’t do it!”) ሲል ይመክራል፡፡ ‘ምነው?’ ሲባል “…ምክንያቱም በቤት አይኖርም፤ከስንት አንዴ ቢመጣ እንኳ በጥልቅ ሀሳብ እንደሰመጠና አንገቱን ቀብሮ እንደጻፈ ነው” ይላል፡፡
በተቃራኒው አሜሪካዊው ፈላስፋ ጆን ዴዊ (John Dewey) በስተርጅና በጉዲፈቻ ለ’ወለዳቸው’ ሁለት ልጆቹና ለቤተሰቡ የማይኾነው አልነበረም፡፡ የሕይወት ታሪኩን የጻፈው ጄይ ማርቲን እንዳለው፤ “…እንደ ጆን ዴዊ ያለ በሕይወት ዘመኑ ከቤተሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ጉምቱ ፈላስፋ ዐላየሁም..በሥራዎቹም በግልጽ ይታይ ነበር” ካለ በኋላ “ስለ ልጆች ትምህርት በሰፊው ሲጽፍ ስለአባትነት ግን እንደሌሎች ፈላስፎች ገድፎታል” ይላል፡፡ የ “The Happiness Fantasy” ደራሲ (Carl Cederstrom) በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ “ታላቅ የሚባሉ የዓለማችን ፈላስፋዎች ስለብዙ ርእሰ ጉዳዮች ሲፈላሰፉ ስለአባትነት ባላየ የሚያልፉት ስለምን ነው?” ለሚለው ጥያቄ ”ልምድ ስለሌላቸው ነው” ይላል፡፡ “እና ስለሞት የጻፉት  ሞተው ነው እንዴ?” ብለን ብንጠይቅስ፡፡ አንዳንድ ሕይወት ሲኖሩት እንጂ ሲጽፉት አይመጣም ይኾን? ወይስ ከሥጋና ደም የሚፈልቅ ምሥጢር ይኖር ይኾን? አይታወቅም፡፡ ከጥቂቶች በቀር የዘመኑ ፈላስፎችም በአባትነት ዙሪያ ብዙ አላሉም፡፡ ወይም ለማውራት ፍላጎት አያሳዩም፡፡
ቁጥራቸው ጥቂት ቢኾንም ፈላስፋ ኾነው አባትነትን ካጣጣሙት መካከል ከቀዳሚዎቹ ሶቅራጥስና አሪስቶትልን፣ ከቅርቦቹ ሄግልን፣ ከሃገራችን ዘርአ ያዕቆብን ማንሣት ይቻላል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ግን ፈላስፎች ፍልስፍናን በማግባታቸው ወይም በመወሸማቸው ምክንያት እልል ያለ የቤተሰብ ሕይወት ያሳለፉ አልነበሩም፡፡ ለምን? ጆናታን ወልፍ ከላይ ከጠቃቀሳቸው ሦስት መላምቶች ሌላ ሳያስፈልግ አይቀርም፤ ሲል አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ እኛም በቀደደልን የአስተያየት ቦይ እንዲህ እንፈሳለን፡፡
የብዙ ፈላስፎች በዓለም እየኖሩ መመነን  የመካከለኛው ዘመን ፈላስፎች ሁሉም ካህናት (ከቤተክርስቲያን አካባቢ) ስለነበሩ?  ወሲብን፣ ጋብቻንና ልጅ ማሳደግን አጥብቆ የሚከለክለው ኢፒኩረስ(Epicurus) ይኾን? በጉዲፈቻ ልጅ በማሳደግ በብስጭት ለኢፒኩሪየስ ምላሽ የሰጠው የስቶይክ (stoic) ፈላስፋው ኢፒክታይተስ (ከቤተሰብ ሕይወት እራስን ነጥሎ ልጅ ማሳደግ እንዴት እንደኾነ ግራ ቢገባም) ‘ምርጥ መምህር ያላገባና ከቤተሰብ ሕይወት እራሱን የነጠለ ነው’ ማለቱ??  ከክርስቶስ ልደት በፊት ፓይታጎረስ አትክልት ተመጋቢነትንና ከወሲብ መታቀብን ‘ሃይማኖቱ’ ያደረገ ማሕበረሰብ ፈጥሮ ነበርና ከእሱ በኋላ የበቀሉት ፈላስፎች ‘ከወሲብ መራቅ ጥበብ ይገልጣል’ ብለው ያምኑ ስለነበር? ሜንከን (H.L Mencken) እንዳለው ‘ካገቡ ወንዶች ይልቅ ወንደ ላጤዎች ሴቶችን በደንብ ስለሚያውቁ?’ ወይስ ወሲብን በጠቅላላ እንደ ሃጢአት የሚቆጥረው በ3ኛው ክፍለ ዘመን ብቅ ያለው የማኑኪ (Manichee) የሃይማኖት አስተምህሮ ጫና አሳርፎ ይኾን?
‘ምርጥ ሥራዎች በእርግጠኝነት የተወለዱት ካላገቡ ወይም ካልወለዱ ወንዶች ነው’ የሚለው  ፍራንሲስ ቤከን ይኾን?…best of all not to have been born, because life contains far more suffering than good ያለው ሶፎክለስ ይኾን?
በዓሉ ግርማ ‘ደራሲው’ን ከጻፈ በኋላ ‘ግዴለሽነት’ የደራሲ መለያ እንደኾነው ያለ የቀደሙ ላጤ ፈላስፎች በኋለኞቹ ፈላስፎች ተፅዕኗቸው ብርቱ ነበር ይኾን? ምነው ቢሉ ሳርት የኒቼ፣ሲሞን ዲበቯር የሳርት፣ ፕሌቶ የፓይታጎረስ የተፅዕኖ ሰለባ (greatly influenced) ነበሩ፡፡
 በተመሳሳይ ኒቼ፣ ካንት፣ ኪርከጋርድና ቪትገንሽቲን (Wittgenstein) የአርተር ሾፐንአወር ተፅዕኖ ነበረባቸውና፡፡
ጨዋታን ጨዋታ ያነሣዋልና የጥንቱ የእንግሊዝኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት የወንድ ዘር ፈሳሽ ወዘተ በማለት ፈንታ ለእንግሊዝኛው ስፐርም (sperm) የሰጠው አንዱ የአማርኛ አቻ ፍቺ ‘ሃጢአት’ መባሉ ለዛ ይኾን? ለዐቅመ መዝገበ ቃላት ማንበብ በደረሰው ዜጋ ላይ ጥላውን ስላለማጥላቱ ምን ማረጋገጫ አለ? ‘ብዙ ተባዙ’ን ባያስታጉል ‘ሃጢአት እየሠራሁ ነው’ የሚለው ሃሳብ ወደ ልቦናው ሽው ስላለማለቱስ ደረቱን ነፍቶ ማን ሊነግረን ይችላል?
ለመኾኑ በዘመናቸው ትዳርን ሲሸሹ የኖሩት ፈላስፎች ‘ወልዶ መሳም፣ዘርቶ መቃም የደስታ ምንጭ ነው’ ለሚሏቸው ቤተሰብና ዘመድ ምን ይሉ ነበር?  ‘የማነህ ይሉኛል፣የማን ልበላቸው፣ ብቻየን ብቆይስ ምን አስጨነቃቸው…’ የሚል ተስፋና ብሶት ያረገዘ ምላሽ የሚሰጡ፣ አለያም አጠር አድርገው …that is the life we chose የሚሉ አይመስለኝም፡፡ children are natural philosophers የጻፈችው Jana Mohr Lone ‘ማን ፈጠረን? ከየት መጣን?’ ብለው በድፍረት የሚጠይቁ ሕፃናት በተፈጥሮ ፈላስፋ ናቸው” ብላለችና ‘ምሽት አግባ እንጂ፤ አግባና ውለድ’  ለሚላቸው ወዳጅ ዘመድ ‘ገና ልጅ ነኝ ጋሜ‘ ይሉ ይኾን? መጀመሪያ ግን ሁሉም ባንድነት ‘ደስታ እራሱ ምንድን ነው?’ ማለታቸው አይቀርም፡፡
ከዛስ?
በዘመናቸው እናንት ጠቢባን ‘ስለምን ሚስት አላገባችሁም?’ ሲባሉ እንዲህ ያሉ ይመስለኛል፡፡
ከፈላስፋነቴ ጋር ደርቤ ንጉሥ እስክኾን ድረስ አላገባም -ፕሌቶ፡፡
ጋብቻ ያስፈልጋል በምትለው ነገር አልስማማም፡፡ ነገር ግን የማግባት መብትህን ለማስከበር እስከሞት ድረስ አብሬህ እታገላለሁ፡፡ ወሲብን እግዚአብሔር ፈጠረ፤ ጋብቻን ደግሞ ቄሶች፡፡ ጋብቻ መልካም ቢኾን እንኳ ቄሶችን ስለማላምናቸው አላገባም- ቮልቴር፡፡
ነፃ እንድንኾን ተረግመናል እና ምነው በጋብቻ ልታሰር? - ሳርት፡፡
ባገባም ባለገባም መጸጸቴ ካልቀረ ለምን ብየ…? -ኪርከጋርድ፡፡
ማግባት  እኮ ምርጫ ነው፡፡ ግዴታ አስመሰላችሁትሳ? ቅዱስ ጳውሎስ ‘ላስቻለው እንደ እኔ መኖር ይሻለዋል’ ብሎ የለም? - አኪውናስ፡፡
የቤቱን ሥራ እሷ፣ የውጩን ሥራ ለኔ የምትተው ሴት አልገጠመችኝም- አዳም ስሚዝ፡፡
ወድጃት ሳበቃ ‘ላግባሽ’ ስላት የማትግደረደር ሴት ካለች ዐይኔን አላሽም ነበር-ሊብኒዝ፡፡
ከወደድኩት ጆርጅንስ ባገባ ምን አገባችሁ? - ሎክ፡፡
እኔ የቤቱ እራስ መኾኔን በሙሉ ልቧ ተቀብላ፣ በሙሉ ኃይሏ የምትተጋ ሴት ሳገኝ አገባለሁ - ሆብስ፡፡
ጭራሽ ሔዋንን አግብቼ የእግዚአብሔርን ስሕተት ልድገም?-ኒቼ፡፡
መብቴን አስርቤ ግዴታየን አላጠግብም፡፡ ምን በወጣኝ?- ሾፐን አወር፡፡
ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርአ ያዕቆብን “ይሄ ሁሉ ፈላስፋ አላገባም፡፡ አንተ እንዴት አገባህ? ትዳር በጥልቅ ማሰብን እንደሚከለክል አታውቅምን?” ሲሉት ምላሹ አጭር ነበር፤ ‘ልቦናዬ አልተቀበለውም’፡፡
ልቦና ይስጠን!
ምንጭ፡-
ለአርታኢ ወይም አዘጋጅ /ዋና አዘጋጅ ብቻ …. i.e not to be published publicly)

England, Charlotte. (2019, December 23). Children inherit their intelligence from their mother not their father, say scientists. INDEPENDENT. https://www.independent.com
Wolff, Jonathan. (15 march 2016). Why do philosophers make unsuitable life partners? The Guardian. https://www.google.com/amp/s/amp.theguardian.com/education/2016/mar/15/why - philosophers- make- unsuitable- life- partners?
Outis, Nemo.(n.d).The Philosophers’ Magazine
https://www.philosophersmag.com
Cederstrom,  Carl. (2018, June 11). The Philosopher as Bad Dad. The New York Times.
https://www.nytimes.com/2018/06/11/opinion/philosophy-fatherhood.html

Read 285 times