Saturday, 11 January 2025 13:40

“ወረቀትን መቅረጥ ዕውቀትን መቅረጥ ነው!”

Written by  ዘነበ ወላ
Rate this item
(0 votes)

“ትንሽ፣ ትንሽ ማንበብ መዳን ነው” ይላሉ በአያሌው ከመጻሕፍት ጋር ተፋቅረው በቅጡ የዘለቁበት አንባቢያን። እነዚህ ድንቅ የመጻሕፍት አፍቃሪያን “ዓለማችን ድንቅ ድንቅ ደራሲያንን ፈጥራልናለች፤
እነሱም ከልብ ተጠበውልን ነበር። የሚያሳዝነው ሁሉንም ለማንበብ በቂ እድሜ የለንም” ሲሉ ይቆጫሉ። አንደመታደል ይህንን በመረዳት በዚህች አጭር እድሜ፣ የተቻላቸውን ያህል አውቀው
እንዲያልፉ ከሆነም ውጤቱ የሚያጽናና ነው።


ሰሞኑን ኢንተርኔት ስበረብር “አጃኢብ !” ያሰኘኝን መረጃ ተመለከትኩ፡፡ “በዓለማችን ላይ 130 ሚሊዮን  መጻሕፍት ለህትመት በቅተዋል። አንድ ብርቱ የተቀባ አንባቢ ከዚህ ውስጥ 6000 መጻሕፍት በህይወት ዘመኑ ያነባል። ማንኛውም መጻሕፍት አፍቃሪ ሥራዬ ብሎ ማንበብ በጀመረ 30ኛ ኮፒ ላይ ራሱን ተሰጥኦውን ዝንባሌውን ያውቃል” አለኝ። ብዙዎቻችን ስራዬ ብለን የምንጥረው ተሰጥኦዋችንን ለማወቅ ይመስለኛል ወይም እገምታለሁ። አልያም ማንበቡ ላይ ሳንተጋ ቀርተን ጋርዶብን በብርሃንም ቢሆን ጨልሞብን የምንይዘው የምንለቀው እየጠፋን ይሆናል። አለበለዚያም መጋረዳችንንም ሳናውቀው ደንዝዘን፤ በተገረዝንበት አልጋ ላይ ልንገነዝ እየጠበቅን ይሆናል።
 “ትንሽ፣ ትንሽ ማንበብ መዳን ነው” ይላሉ በአያሌው ከመጻሕፍት ጋር ተፋቅረው በቅጡ የዘለቁበት አንባቢያን። እነዚህ ድንቅ የመጻሕፍት አፍቃሪያን “ዓለማችን ድንቅ ድንቅ ደራሲያንን ፈጥራልናለች፤  እነሱም ከልብ  ተጠበውልን ነበር። የሚያሳዝነው ሁሉንም ለማንበብ በቂ እድሜ የለንም” ሲሉ ይቆጫሉ። አንደመታደል ይህንን በመረዳት በዚህች አጭር እድሜ፣ የተቻላቸውን ያህል አውቀው እንዲያልፉ ከሆነም ውጤቱ የሚያጽናና ነው።
ዜጎቻቸው በቅጡ አንብበው የበኩላቸውን አንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ባህላቸው ያደረጉ አገሮች አሉ።  ከእነዚህ አገሮች ውስጥ ለዛሬ በምሳሌነት በመጀመሪያ የማነሳት ህንድን ነው። ህንድ በአሁኑ ጊዜ 1.4 ቢሊዮን ህዝብ አላት። በሌላ አባባል ከስምንት የአለማችን ሰዎች መካከል አንዱ ህንዳዊ ነው። ይህ ህዝብ በእኔ የልጅነት ጊዜ፣ በ1960ዎቹ ተጠቃሽ የሆነ ችጋርና ችግር የበዛበት፣ ጎርፍ፣ ርእደ መሬት የሚያስጨንቀው፤ በመጥፎ ዜና የሚወሳ ነበር፡፡ አሁንስ? “የእለት ጉርስ፣ የአመት ልብስ” የሰማያተ ሰማይን ያህል ያልራቀው ህዝብ ሆኗል።
ለምን ማለታችን “ሳይታለም የተፈታ ነው”፡፡ አንደኛው ሰላም ነው። ልብ አድርጉልኝ፤ 1.4 ቢሊዮን ህዝብ በሰላም ወጥቶ ይገባባታል። በሚችለውና በተካነው መስክ ይሰራል። ባህር ማዶ ተሻግሮም ቢሰራ እጁ ከገባው ሲሳይ አገሩን አይረሳም። በመጻሕፍት አቅርቦት ረገድ የማንበብ ፍቅር ላለው ህንድ ምቹ አገር ናት፡፡ ምን አልባትም በአለማችን ላይ የመጻሕፍትን ጉዳይ የሚከታተል፣ የሚያስፈጽምና የጎደለውን የሚሞላ ወዘተ--ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያላት አገር ህንድ ብቻ ትመስለኛለች። አዎን ህንድ የመጻሕፍት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አላት።
ልብ አድርጉልኝ፤ የትኛውም ዩኒቨርስቲ ገብተን ብንማር የአንድ ሙያ ባለቤት ብቻ ነው የሚያደርገን፤ አዋቂ ለመሆን የምንሻ ከሆነ ግን ማንበብ  የግድ ነው፡፡ አልያ ከተካነው ሙያ ውጪ ምንም እማናውቅ ነው የምንሆነው፡፡ ይህ የገባት ህንድ የመጻሕፍት ሚኒስቴር ያቋቋመችው በዚህ ምክንያት አይመስላችሁም? በዚህ ስሌት ዜጎች መጻሕፍት እንደ ልብ  እንዲያገኙ  አድርጋለች፡፡
ህንድ ውስጥ በመላው ዓለም ለህትመት የበቁ መጻሕፍት ወደ አገሪቱ እንዲገቡ በሯ ክፍት ነው። በርካታ አሳታሚያን አሉ። ሸማች ሊገዛቸው በሚችለው ወረቀት እንደ አቅሙ ያሳትሙለታል። ጭብጡ አንድ አይነት ሆኖ በርካሽ ወረቀት ወይም በምርጥ ወረቀት ይታተማል። በዚህም ምክንያት ሁሉም እንደ አቅሙ ሸምቶ እውቀቱን ይገበያል። ህንድ ዓለም አቀፍ የኮፒራይት ስምምነት ስላልፈረመች፣ ማንኛውም መጻሕፍት ያለከልካይ የማሳተም መብቷን በብልህነት ትጠቀምበታለች፡፡ በዚህ መብት አማካኝነት የአገሪቱ ተርጓሚዎች ያለማንም ከልካይ ለህዝባቸው ይረባል ብለው ያሰቡትን መጻሕፍት ተርጉሙው በየቋንቋቸው ያስነብቡታል። በዓለም ላይ በመጻሕፍት ህትመት የልብ አድርስና በርካሽ ዋጋ  በማቅረብ ህንድ ተጠቃሽ  ነች። በየትኛውም ቋንቋ ይታተም ከሌላ ዓለም ህንድ ለህትመት የሚገባ ደራሲ 25% ቅናሽ ይደረግለታል።
ህንድ የዜጎች አባት የሆነው የማህተመ ጋንዲሂ አገር መሆንዋን ልብ በሉልኝ። ጋንዲሂ በድንቅ አንባቢነቱ ተጠቃሽና  መጻሕፍት ከልብ አፍቃሪ እንደሆነ ይነገርለታል። man of letter ስለነበር ከታላቁ ሩሲያዊ ደራሲ ሊዮ ቶልስቶይ ጋር ደብዳቤ በመጻጻፍ በቀሰመው ጥበብ፣  በሰላማዊ አመጽ አገሩን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ አውጥቷል። መጻሕፍትን ካነበባቸው በኋላ books for all በሚለው መርሁ ሊያነበው ለሚሻ ማንኛውም ወገን ይሰጣል። ይህ መርህ ነው አድጎና ጎልብቶ የህንድ መጻሕፍት ሚኒስቴርን የፈጠረው። እርሱን ተከትለው ህንድን የመሩ ታላላቅ ሰዎችን አስቡ፤ ማንበብ አቅጣጫ የመራቸው አይመስላችሁም?
ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ ህንድ በዘግናኝ ታሪክ ተጠቃሽ ነበረች። ያ የመከራው ጊዜም አለፈ፣ አንድ ቤተሰብም መራር መስዋዕትነት ከፍሏል። ጁሀራ ኔህሩ ህይወቱን ለህንድ ሲሰጥ፤ ተከትላ አመራሩ ላይ የተቀመጠችው ልጁ ኢንድራ ጋንዲሂ፣ ልጅዋ ራጂብ ጋንዲሂ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ መቼም ሀዘን ባለበት መጽናኛ  ሙዚቃ አለና በእነ ራጂሽ ካህን፣ በእነ ሂማማሊ አና ላታ ማንግሽካር  እንጉርጉሮ እየተጽናናን የህንድን ህዝብ ታላቅነት እንመሰክራለን።
በመቀጠል የምናደንቀው የጎረቤታችንን የኬንያን  የመጻሕፍት ሥርአት ይሆናል። ኬንያን በህትመት ልሳን ብንመዝናት፣ በጋዜጣ ህትመት ታስከነዳናለች። ነብሱን ይማረውና ከወዳጄ አሰፋ ጎሳዬ ጋር ከ23 ዓመታት በፊት በወረቀት ዋጋ ዙሪያ ቃለምልልስ አድርገን ነበር። አሴ፤ “ሩቅ አትሂድ፤ እዚህ ጎረቤት አገር ኬንያ ‘ኔሽን’ የሚባል ጋዜጣ አላቸው። ይህ ጋዜጣ 500 ሺ ኮፒ በየሳምንቱ ያሳትማል። ይህ ማለት እኛ አገር የመንግስት፣ የፓርቲ፣ የግልና የሃይማኖት ልሳናት ሁሉ ተደምሮ የአንድ ቀን ህትመቱን አይሆንም። ቸር ሆነን ብናስብ ምን አልባት የእኛ የሁሉም ህትመት ተሰባስቦ 100 ሺ ከደረሰ መታደል ነው” ያለኝን ምንጊዜም አልረሳውም።
ወደ መጻሕፍት ስንመጣ፣ የኬንያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቋሚነት አንድ ወንበር ለመጻሕፍት ተወካይ አለው። እዚህ ወንበር ላይ የሚቀመጥ ሰው ዋና ሥራው፣ መጻሕፍት በኬንያ እንዴት ውለው እንዳደሩ መመርመርና ለፓርላማ አባላቱ ሪፖርት ማድረግ ነው፡፡  የተከበሩት እንደራሴዎችም መክረው ዘክረው የጋራ መፍትሄ ያስቀምጣሉ።...ይህ ተወካይ በስድስቱም ክፍለ ሀገራት 17 ጽህፈት ቤቶች ሲኖሩት፣ መጻሕፍትን በተመለከተ ያላቸውን መረጃ ናይሮቢ ለሚገኘው ተወካያቸው እንዲደርስ ያደርጋሉ። በአገሪቱ ተወካዮች ምክር ቤት አጀንዳው ስራዬ ብሎ  ይመከርበትና ተወስኖ ወደ ተግባር ይገባል። በወረቀት ተወደደ፣ ቀለም ወይም ኬሚካል ጠፋ ወዘተ... ዙሪያ ማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ ይህንን ከላይ ያወጋኋችሁን መረጃ ሬዲዮ ወይም ቴሌቪዥን ላይ የምተርከው ቢሆን ኖሮ፣ ከጀርባ እንዲሰማ የማደርገው ሙዚቃ የአለማየሁ እሸቴ “ተማር ልጄ” ይሆን ነበር።
አሁን ደግሞ የማወጋችሁ ስለ ግብጽ ህትመት ነው። ይህንን ቀጣይ ታሪክ ያጫወተኝ ነብሱን ይማረውና አብደላ እዝራ ነበር። አብደላ በጡረታ እስከተገለለ ድረስ የሰራው የመን አየር መንገድ ነው። በአመት አመት ነጻ የአየር ትኬት አየር መንገዱ ይሰጠዋል። በዚህ ችሮታው እርሱም የእረፍት ጊዜውን አመቻችቶ  ዓለምን ይዞራል። በተደጋጋሚ ካያቸው አገሮች ግብጽ አንደኛዋ ነች። ይህቺ  አገር ሃሳብን ተረድቶ ደራሲያንን የማጻፍ ትጋቷ ይበል የሚሰኝላት ነው። አብደላ እንዳጫወተኝ፤ አንድ ግብጻዊ ጥብስቅ ያለ እውቀት ካለው እንዲጽፈው ያበረታቱታል። ለምሳሌ ግብጻውያን ምንጊዜም ቀልባቸውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚስበው የአባይ ጉዳይ ነው። አንድ ሀሰን ሁሴን የተባለ ሰው፣ ለወዳጆቹ በየእለቱ ስለ ህዳሴው ግድብ ያወራል እንበል፤ ወሬው አርቲ ቡርቲ ሳይሆን በተጨባጭ ተአማኒ የሆኑ የዜና ምንጮችንና የምርምር ውጤቶችን  እየጠቀሰ ይሆናል፤ ይህን ጊዜም  ይህንን ሃሳብ እንዲጽፈው ያግባቡታል።
“ምን ማለታችሁ ነው መደበኛ ሥራዬስ ?” ይላል ሀሰን።
“ለእርሱ መላ አለን፤ ይህንን መጽሐፍ ጽፈህ ለመጨረስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድብሃል?”
“ሁለት አመታት እሻለሁ”
“መልካም፤ ልክ የዛሬ ሁለት አመት አንተ ይህንን መጽሐፍ ጽፈህ ልታስረክበን እንስማማ። እኛ ለመስሪያ ቤትህ ነግረን በየወሩ እየሄድክ ደሞዝህን ትቀበላለህ። ማንኛውም ጥቅማ ጥቅም የተጠበቀልህ ይሆናል” ይሉትና ከሀሰን ጋር ስምምነት ይፈጽማሉ። ደራሲውም በውሉ መሰረት መጻፍ ጀምሮ ባለው ጊዜ አጠናቆ አስረከበ እንበል። ይህንን ስራ እንዲሰራ የሰጠው ክፍል ድርሰቱን ይቀበልና በባለሙያዎች ያስገመግማል፤ ጎደለ የሚለውን ያሟላል ወይም የመጀመሪያ ሥራው አንጀት አርስ ይሆናል። ይህንን በቅጡ ካስተዋለ በኋላ ደጉመው ለህትመት ያበቁታል። ተደራሲያን እጅ በፍጥነት እንዲደርስ በርካሽ ዋጋ ያቀርቡለታል። አንባቢያን እየሸመቱ ያነቡታል፤ መጅሊሳቸውም ፣ ሺሻቸውም በአዲስ ወግ ይደምቃል፤ ሲል ወዳጄ አብደላ አጫውቶኛል።
በዚህ ሃሳብ ምን ያህል እንደምጎመጅ ልብ በሉልኝ። ይህን ሃሳብ አገራችን ላይ መንግስት ልሞክረው ቢል በሙስና የሚበከል አይመስላችሁም ? እኔ እንደሚታየኝ በፊደላውያን ሥራው ይወረወራል። ሃሳብ አለው ብለን ያሰብነው ሰው፣ ድንቅ መጻሕፍት አንባቢም ቢሆን፣ ለዚህ ፕሮጀክት እንደማይመጥን ተደርጎ ይብጠለጠልና ሥራውን በአንድ ሙያ ከተመረቀ ጊዜ  ጀምሮ መጻሕፍት ዝር ባሉበት ዝር ብሎ የማያውቅ “ምሁር” እንዲሰራው ይደረግና አይን ፣ ጆሮ ወዘተ የሌለው ሥራ ሰርቶ ይሰጠናል። ያንን እንጨት እንጨት የሚለውን ሥራ፤ “ፐ ! ብራቮ !” እየተባለ በኮክቴል ጋዜጠኞች ተአምር ሲባልለት እንሰማለን። ይህንን ያስባለኝ በተለይ ባለፉት ግማሽ ምእተ አመታት በአገራችን  ሙሰኛ ያልገባበት ሥፍራ ባለመኖሩ ነው፡፡  
ግብጾችም ከእኛ ሊብሱ ይችላሉ ብለን እናስብ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ጉዳዩ የሚያገባውን ሰው አጥርተው የማየት አቅማቸው ከእኛ  የተሻለ ይመስለኛል። ምንም አንጠራጠር፤ ይህ ሃሳብ ለእኛ አገር አሁንም አዲስ ነው። አይደለም በአዲስ ሃሳብ በገዛ ሙያቸው አንዲት ወግ ሳይተውልን ይህቺን ዓለም በሞት የተሰናበቱ ብዙ ናቸው።
አብደላ እዝራ  ልሳነ ብዙ ነው። ልምዱም ያንን ያህል ጥብስቅ ያለ ነው። እኔ እንኳን ከማውቀው አረብኛን፣ እንግሊዝኛንና አማርኛን አሳምሮ ይጠበብበታል፡፡ “አረብኛን ለማሳደግ ግብጽ ትጉህ ነች። አንድ ደራሲ በዓለም ላይ በሥነ ጽሁፍ ለኖቤል ሽልማት ከበቃ በሚቀጥሉት ጊዜያት  በአገሪቱ ሊቃውንት  ወደ አረብኛ ተተርጉሞ  ለህትመት በማብቃት፣ ለንባብ ይቀርባል፡፡” ብሎ አብደላ አጫውቶኛል።
የእድሜ ልክ ደመኛ አገር እንዴት እንዲህ ታወድሳለህ የሚለኝ አንድ የዋህ አንባቢ አይጠፋም፡፡ እንደሚያስብ ሰው፣ እውነቱን አውቆ የእኛንስ  እንዴት እንግራው ነው እኔን የሚያስጨንቀኝ። “ኢትዮጵያን ከቻልን በቁጥጥር ስር ማድረግ፣ ካልተቻለም ለዘለአለሙ እንድትተራመስ መስራት አለብን!” ይለናል የአንድ ዘመን ገዢያቸው ሙን  ሲንጀር፡፡ እንዳሉትም እቅዳቸውን እውን ለማድረግ ከአንድም ሁለቴ በጦርነት ሊያንበረክኩን ጥረዋል። በጉራንና ጉንደት አፄ ዮሐንስ ልክ አስገብተው ሸኝተዋቸዋል። ከዚያ በኋላ በጦር መከጀሉ የማያዋጣ መሆኑ ገብቷቸዋል። ማተራመሱን ግን የቀናቸው መሆኑን ከኤርትራ አማጺያን ጋር ያደረግነው የ30 ዓመታት መራር ጦርነት ህያው የታሪክ ምስክር ነው። በነገራችን ላይ በዚህ ጦርነት በአንዱ አውደ ግንባር ላይ ተካፍያለሁ። ሲደመደምም የአይን ምስክር ሆኛለሁ። ውጤቱ ሁለት የምር ደሀ አገር መፍጠር መሆኑን ስመለከት፣ በሁለቱም አቅጣጫ በመሩን መሪዎች አፍሬያለሁ።
ይህንን ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን ጋር ላያይዘው። ወጣቱ ደራሲ ይታገሱ ጌትነት ገበየሁ፣ ዚምባቡዌ ሀራሬ ድረስ ዘልቆ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማሪያምን አናግሮ በቅርቡ ለጥራዝ ያበቃው መጽሐፍ አለ። እዚያ ላይ ወጣቱና አዛውንቱ ሲያወጉ፤ “ሆስኒ ሙባረክ ጎጃምን መቼ ነው የምታስጎበኘኝ ይለኝ ነበር። እኔንም  ካይሮን እንድጎበኝ ጋበዘኝ። ግብዣውን ተቀብዬ ግብጽ ዘለቅሁ፤የሚገርመው ከሚቀጥለው ቀን ጀምሮ ያስጎበኙን የነበረው የመድፍ ፋብሪካዎቻቸውን ነበር። እኛም ሃሳባቸው ምን እንደሆነ ስለገባን ከጓዶች ጋር እየተጠቃቀስን እንሳሳቅ ነበር” ብለውታል። በዚህ መጽሐፍ ላይ ኮሎኔሉ ለይታገሱ እንዳወጉት፤ በእርሳቸው መንግሥት ውጥን አባይን አይደለም በእውን በህልማቸውም አይነኩትም። ይሁን እንጂ ማስፈራራቱን አልተዉትም፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በቅርብ ምስራቅ ባሉት አገራት ላይ የሚሰጡን መረጃ ድንቅ ነው፤ እኔ ስራዬ ብዬ ነው የምከታተላቸው። የህዳሴው ግድብን እኛ መገንባት ከጀመርን በኋላ ግብጾች 660 ኮንፍረንሶችን አካሂደው ፤ 1500 የምርምር ውጤቶች ቀርበውባቸዋል። 222 መጻሕፍት ለህትመት በቅተዋል” ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ  ያወጉናል።  በአባይ ጉዳይ ላይ ተመራማሪና ተደራዳሪ ከሆነው ፕሮፌሰር ዘሪሁን ወልዴ ጋር በቅርቡ ተገናኝተን በነበረበት ወቅት  የአደም ካሚልን ሃሳብ አነሳሁበት፡፡ “መጻሕፍት የተባሉት አጀብ የሚያሰኝና  ውሃ የሚያነሳ ሃሳብ ያለው እንዳይመስልህ። ለፕሮፓጋንዳ  ፍጆታ እንዲሆናቸው  ያሳተሙትን ሁሉ አክለው ነው ቁጥሩን ያበዙልህ” አለኝ።
“በዚህ ምን ይጠቀማሉ ?” አልኩ እኔ ።
“ህዝባቸውን ያረጋጉበታላ!”
“ወንዙንስ የሚንሰፈሰፉለትን ያህል ይሰሩበታል?”
“አባይ  ሱዳንን እንደተሻገረ ይበከላል፤ ካይሮ ሲደርስ  ብክለቱ ብሶበት ሜዲትራንያን ባህር ይገባል” ብሎኛል ፕሮፌሰር ዘሪሁን።
ሰሞኑን ምን አልባትም በዘመናችን ባልተከሰተ ሁኔታ፣ የመሬት ርዕደት አገራችን ውስጥ እየተከሰተ ነው። ይህንን ርዕደት የግብጽ ምሁራን ከህዳሴው ግድብ ጋር አያይዘው ህዝባቸውን እያሞኙበት ነው። ተፈጥሮአዊው ችግር የተከሰተው አፋር ላይ  ሲሆን፣ ግድቡ ያለው ቤንሻንጉል ውስጥ ነው። በሁለቱ መካከል 700 ኪሎ ሜትር ርቀት አለ። በዚህ ርቀት ላይ  ሆኖ የህዳሴው ግድብ  እንዴት ለርእደቱ ምክንያት ይሆናል? ስል የግብጽ “ምሁራንን” መጠየቁን እወዳለሁ። ይህም ጉዳይ ለጥራዝ በቅቶ 223ኛ መጽሐፍ ይሆን ይሆን ?!
አሜሪካውያን “ወረቀትን መቅረጥ፣ እውቀትን መቅረጥ ነው” የሚሉት ብሂል አላቸው። ድንቅ አባባል ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው አገሮች ይህ ገብቷቸው የዘለቁበት ይመስለኛል። ከምእራብ የህትመት ታሪክ ቢያንስ ከ200 እስከ 300 አመታት የዘገየችው አገራችን አሁንም ምስጢሩ አልገለጥልሽ ብሏታል፡፡  
 ኢትዮጵያ የመጻሕፍት አገር ናት፤ ለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ህያው ምስክር ነች። ሩቅ ሳንሄድ የቅዱሳን መጻሕፍት አደጓጎስን ልብ እንበል፤ መጻሕፍቱ ዘላለማዊ እንዲሆኑ የምታዘጋጅላቸውን የቆዳ ማህደሮች በአይነ ህሊናችን እንቃኝ። ይህ መጻሕፍትን አክብሮ የመደጎስ ባህል በትንሹ ከሁለት ሺህ አመታት በላይ አስቆጥሯል። መጻሕፍትን  በጥንቱ ባህል ብራናን ፍቆ ፣ ቀለም ቀምሞ መጠበብ አሁንም ሊቃውንተ አበው እንደቀጠሉ ነው። በዘመናዊ ማተሚያ ቤትም ቅዱሳን  መጻሕፍቱን ያሳትማሉ ፤ ይሁን እንጂ መጸሐፈ ሃይማኖት የምናስደጉሰውን ያህል ለምን መጸሐፈ ጥበብ፣ መጸሐፈ ሳይንስ አልተዋጣልንም? አገራችን የተማረ ከሚባለው ትወልድ 1% በታች ነው የሚያነበው፤ አገራችን ትውልዱ እንዲያነብ የምታተጋበት ዘመን ከተሻረ ግማሽ ምእተ አመት ተቆጠረ። አገራችን በአሁኑ ጊዜ ወረቀት ትቀርጣለች፥ ቀለም ትቀርጣለች፥ ኬሚካል ትቀርጣለች፡፡
‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንዲሉ አሁን ደግሞ መጻሕፍት ላይ 15% ተጨማሪ እሴት ታክስ ተደነገገበት። ቀደም ብሎ ደራሲያኑ ብዙ አሳተሙ የሚባለው 5000 ኮፒ ሲሆን ፣ ዝቅተኛው 3000 ነበር ፤ አሁን ለህትመት የደፈረ ምርጫው ከላይ ከቀረበው ሁለተኛው ሆኗል። ከዚህ ህግ መውጣት በኋላ አብዛኛው ደራሲ ቆም ብሎ ማሰቡን መርጧል። ላጠና የሞከርኳቸው ማተሚያ ቤቶች ሥራቸው በ50% ቀንሷል።  ፀሐፍት በቀጣይ ይህንን ሸክም የሆነባቸውን ህግ አክብረው ይጠበቡ ይሆን፤ አልያስ ጫናው  ከጨዋታው  ያስወጣቸው ይሆን? ልንመክርበት ይገባል። ጉዳዩን በዚህ ብቻ የማልፈው ሳይሆን፣ ከላይ ያነሳኋቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ይዤ  ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡

Read 247 times