Saturday, 18 January 2025 22:09

“ሰማኒያውን ነህ… ዘጠናውን ነህ ወገቤን የያዝከኝ ገላጋይ መስለህ?!”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ሁለት ዕውቅ ሽማግሌዎች ወዳጃቸው ለሆነ አንድ ሽማግሌ፤ “ሴት ልጅህን ለልጄ ስጠኝ” እያሉ በተራ በተራ መልዕክተኛ ላኩበት። ያም ሽማግሌ መልክተኞቹን በተራ በተራ አስተናገዳቸው። ለመጀመሪያው መልዕክተኛ፡- “መልካም፤ ልጄን ለልጅህ እሰጥሃለሁ ግን ቤትህን አሰናዳ ብለህ ንገረው” ብሎ ይልክበታል።
ለሁለተኛው መልዕክተኛም፤ “ና ቅረብ ወዳጄ። ለጌታህ ስትለው፤ ደግ ነው ልጄን ለልጅህ ልድራት ዝግጁ ነኝ፤ ሆኖም አስቀድመህ ቤትህን አሰናዳ” አለው። መልዕክተኞቹም-እርስ በእርሳቸው የተባሉትን ሳይነጋገሩ ወደ ጌቶቻቸው ሄዱ።
አንደኛው መልዕክተኛ ወደ ጌታው ሄዶ፤ “ጌታዬ ጥያቄውን አቅርቤ ነበር። ነገር ግን የ3 ወር ጊዜ ሰጥቼሃለው፤ ቤትህን አሰናዳ በለው” አሉ።
በመጀመሪያ መልሱን የሰማው ሽማግሌ ለልጁ፤ “በል ወዳጄ ሦስት ወር ቅርብ ጊዜ ነው፤ በያለበት መሬት እየገዛህ እልፍኝና አዳራሽ ሥራ፡፡ ለሚስትህና ላንተ መቀመጫ ይደላሃል” አለው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ መልሱን የሰማው ሽማግሌ ግን፤ “ያጅሬን ብልሃት እኔ አውቃለሁ። በል ልጄ ተነስተህ ገንዘብ ይዘህ ሄደህ ወዳጅ አብዛ። እስካሁን የምታውቀው ሰው በቂ አይደለም። ቤትህን አሰናዳ ማለቱ ትርጉሙ ይሄ ነው።”
የተባለው ቀን ሲደርስ አባት ደግሶ ይጠባበቅ ኖሯል። ሁለቱ አባቶች በሰዓቱ ከች አሉ። ከተጋበዙ በኋላም አንደኛው፤ “መሬት ገዝቼ ለልጄ ሰጥቼዋለሁ።” ሲል ተናገረ።
የሠርጉ ባለቤትም፤ “የምድር ብዛት ከቁም-ነገር አይውልም። ባንድ ስተት ቀሪ ነው። እልፍኝና አዳራሹንም አውሎ ነፋስ ይጠርገዋል። የእሳት እራትና ምሳ ነው። ውሃ ሙላት ያጠፋዋል። ጠንቅ አያጣም” አለው።
ቀጥሎም ሁለተኛው አባት፤ “ገንዘብ ይዘህ ሂድ፤ ወዳጅ አብዛ” ብዬዋለሁ አለና አስረዳ። የሠርገኛው አባትም፤ “ሌላ ሀብት ሁሉ ጠፊ ረጋፊ ነው። ብዙ ወዳጅ ግን በየቦታው ቢፈራ ሀብት ነው። ጥቅምም ካንዱ ቢጠፋ ካንዱ ይገኛል፤ አንዲት ልጄን ለዚህ ልጅ መርቄ ሰጥቼዋለሁ” አለ።
* * *
ህዘብ የሚወደው መሪ ማግኘት ታላቅ ጸጋ ነው። ወዳጅ ለማፍራት የሚችል መሪ ማግኘት መታደል ነው። ለራሱ ማረፊያ እልፍኝ - ከአዳራሽ የሚሰራ መሪ ማግኘት ከቁምነገር የሚጻፍ አይደለም። ባንድ ስተት ቀሪ-ነው፤ አውሎ ንፋስ ይጠርገዋል። ህዝብ የክብሩ ምልክት የሚሆንለት መሪ ይፈልጋል። ተናግሮ የሚያጠግበው መሪ ይፈልጋል። እምነቱን የሚጥልበት፣ ለሾመው የሥልጣን ዘመን የሚበቃ ጥንካሬ ያለው ርዕሰ-ብሔር እንዲኖረው ይመኛል። በእርግጥም ህዝብ ሆደ-ሰፊ፣ እንደ ወጣት የማይቸኩል፣ በረዥምና በበሳል አካሄድ እንጂ በቆረጣ የማይመካ፣ ብልጥ ሳይሆን ብልህ የሆነ፣ የዕውቀት-የልምድና የዕድሜ ባለፀጋ የሆነ እንደራሴ ይፈልጋል።
የሀገር መሪ ሲመረጥ እንደ ቴአትር ገፀ-ባህሪ ለአንድ ወንበር (ሚና) ሁለት ሰው የሚሰለጥንበት (Double-cast እንደሚባለው) የመጠባበቂያ ሂደትም ሆነ መለዋወጫ የለውምና፣ አካላዊና አዕምሮአዊ ይዞታውና ብቃቱ በቅጡ መጤን ይኖርበታል።
የሕዝብ ስነ-ልቦናን የሚያሸንፍ መሪ የህዝብን ተስፋ ያለመልማል። መሪው ተስፋ የማይጣልበት ከሆነ፣ ተመሪውንም ይዞት ወደ ጨለምተኛ አቅጣጫ ያመራል። ዣን ፖል ሮችተር እንዳለው፤ “የእርጅና አሳዛኙ ነገር፤ ደስታችን ማለቁ ሳይሆን፤ ተስፋችን ጨርሶ መሟጠጡ ነው”። ተስፋ ያለው መሪ፤ የሆነ እንደሆነ ለነገ መቅረዝ ያበራል። ልምዱን፣ እውቀቱን፣ ደርዙን እንደ ሻማ እያቀጣጠለ የመጪውን ቀን ተስፋ የማያሳይ መሪ፣ አለቃ ወይም ሹም ከሆነ ግን ጭል-ጭል ትል የነበረችውን ነግ- ተነግ- ወዲያ ራዕይ ይጋርዳል። እርጅና ፀፀት የሚያመጣው ያልተዘጋጁበትን ቦታ እንደማታ-ሲሳይ፣ እንደማታ-እንጀራ ቆጥረው ሲቀመጡ ነው። “ምነው እዚህ እንደምደርስ ባወቅሁ፣ ራሴን በተሻለ ጠብቄ እቆይ ነበር” እንዲል ኡቢ ብሌክ፤ በስተርጅና የሚገኝ ሥልጣን ከትፍስህቱ ጭንቀቱ፣ ከተስፋው ፀፀቱ ይብሳል፡፡ እንደ ኖስትራ ዳሙስ The man who saw tomorrow ማለታችን ይቀርና The Man who’ll see Yesterday የሚል ዓይነት፤ ምስቅልቅል ውስጥ ሊከተንም ይችላል። (ራዕያችን ነገን አስቀድሞ ማየት መሆኑ ይቀርና፤ ትላንትን ነገ ለማየት መቋመጥ ይሆናል እንደማለት ነው።)
“የአንበሳ መንጋ መሪ በግ ከሚሆን ይልቅ፣ የበግ መንጋ መሪ አንበሳ ቢሆን ይሻላል” ሲል የፃፈልን ዳንኤል ዴፎ፤ የአገርን ምልክት፣ የአገርን መኩሪያ፣ የአገርን ወኪል፣ የኢገርን እንደራሴ ጉልህ ገጽታ አበክሮ ሲገልጽልን ነው። አንድም “ምነው ወጣቱ ባወቀ፣ ምነው ሽማግሌው መሥራት በቻለ” የሚለው የፈረንሳዮች አባባል፣ የዕውቀትንና የሥራን ኅብራዊ አስፈላጊነት ሲያሳየን ነው።
የነፃነትን፣ የፍትሕን፣ የመብት መከበርን ፍቱን አስፈላጊነት ከመቼውም በበለጠ እያየች፣ በላቀ ሁኔታም እየተገነዘበች፣ በመጣችው ሀገራችን ውስጥ ለዚህ እውን መሆን ብርቱ ጥረት የሚያደርጉ ብቁ ዜጎችን እንሻለን። ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤ The Young man knows the rules the old man knows the exceptions (ወጣቱ በህግ የሚፈቀደውን ያውቃል፤ ሽማግሌው በሕግ የሚከለከለውን ያውቃል) ብለን እንዳናልፍ የሀገር ክብር፣ የመንበሩ ልዕልናና የታሪክ አደራ እንቅልፍ ይነሱናል።
ለአንድ የኃላፊነት ቦታ የብቃት መመዘኛ የዚህ ወይም የዚያ ብሔር-ብሔረሰብ መሆኑ እንዳይደለ መቼም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ ሳንረዳው አይቀርም፡፡ በተግባር መከወኑ ላይ ባይሳካልንም፡፡
የአእምሮ መትባት፣ የአንጎል ብስለት፣ የእውቀት ደረጃና የሙያ ክህሎትና ሥነ-ምግባር እጅግ ወሳኝ የመሆኑን ያህል፤ የእነዚህ ሁሉ ማቀፊያ የሆነው አካላዊ ውሃ-ልክና ጤነኛነት፣ እንዲሁም የእድሜ ልከኛነት የዚያኑ ያህል ወሳኝ ነው። ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ ኃላፊነትና ሥልጣን አካላዊ ሸክም ሲሆን፤ ውሎ አድሮም አዕምሮአዊ ጭንቀት ወደመሆን እንዳይሄድ መስጋት ተገቢ ነው። “አይቶ ነው ገምቶ ነው…” እንዲሉ ዕድሜንም አቅምንም አገናዝቦ ኃላፊነትን መቀበል ደግ ነው። አለበለዚያ እድሜ እየገፋ ሲሄድ፤ ህዝብንም “ማንስ ቢወክልህ ምን ቸገረህ?” ብሎ እንደመናቅ ያለ ክፉ ደዌ የለም። ሌላ “ጥገኛ ዝቅጠት” መጋበዝም ይሆናል ዞሮ ዞሮ። ደግሞምም የሁሉም ኃላፊነት ነው- የአጪም፣ የታጪም፣ የ”እሰይ-አበጀህ የእኛ ሎጋ!” ባይ ታዳሚም። አለበለዚያ፤
“ሰማንያውን ነህ
ዘጠናውን ነህ
ወገቤን የያዝከኝ ገላጋይ መስለህ!”
ማለት ይመጣል። ኃላፊነቱም አጠያያቂ ይሆናል። ሁሉም ጥንቃቄ ያሻዋል።

 

Read 963 times