“አማኑኤል!... አማኑኤል!”
የውይይቷ ታክሲ በር ሲከፈት፤ አምስት ሰዎች ተገፈታትረው ገብተው ቦታ ያዙ፡፡ ከገቡ በኋላ ረዳቱን “የት ነው የሚሄደው?” ብለው ጠየቁት፡፡ ረዳቱ ግራ የተጋባ መሰለ፡፡
“የትም አይሄድ” ብሎ መለሰ፡፡ “ምን…ታክሲ መስሏችሁ ነው?”
“እህሳ?” አሉት፡፡
“አይደለም! ሻይ ቤት ነው… ምን ልታዘዝ?” አላቸው፡፡ እውነትም ሽርጥ መሳይ ጨርቅ በአንገቱ አጥልቆ ወገቡ ላይ አሰረ፡፡ የቆርኪ መክፈቻ ከሽርጡ ኪስ ውስጥ አወጣ፡፡
“ምን ልታዘዝ?” አለ፣ ደግሞ፡፡
ሰዎቹ ተገፋፍተው እንደገቡት፤ ተገፋፍተው ተሽቀዳድመው አዘዙ፡፡ ሦስቱ ወንዶች ቡና፣ ሴቷ ወተት፣ ከሴትየዋ ጋር ያሉችው ትንሽ ልጅ ሚሪንዳ፡፡ ረዳቱ አስተናጋጅ፣ “ሂሳብ በቅድሚያ” ብሎ አጎንብሶ እመሃላቸው ገባ፡፡
“ሦስት ቡና” አለና የወንዶቹን ጭንቅላት “አንድ ሁለት ሦስት” ብሎ በእጁ መታ-መታ እያደረገ ቆጠረ፡፡ ከሦስቱ መሀል አንዱ (በሩ ጥግ ላይ የተቀመጠው) መላጣ ነው፡፡ ራሰ-በራ፡፡ ቦርጫም፡፡ ረዳቱ በእጁ መላጣውን ነክቶ ስለቆጠረው መሀረብ አውጥቶ ጭንቅላቱን ጠረገ፡፡ ከዚያ ንፍጡን አፍንጫውን እንደጡሩንባ እጩኾ ተናፈጠ፡፡ ረዳቱ ከታክሲዋ ላይ ከመውረዱ በፊት “እርስዎም ቡና ነው ያሉኝ አይደል?” ብሎ የሰውየውን መላጣ በእጁ ይዞ ጠየቀ፡፡
ሰውዬው እንደገና መሀረቡን አውጥቶ መላጣውን ወለወለ፡፡ ወዲያው አስተናጋጁ ከሄደ በኋላ ሁሉም በራሱ ሀሳብ ተውጦ ትንሽ ቆየ፡፡ ከመላጣው ሰውዬ ጎን የተቀመጡት ሁለቱ አንድ ላይ ናቸው፡፡ አንደኛው በጣም ረጅም ገልጃጃ ነው፡፡ ጭንቅላቱ የታክሲዋን ጣራ ይነካል፡፡ ሰውነቱ ላይ መአት ረጃጅም ነገሮች አሉት፡፡ ረጃጅም እጆች፣ ቅልጥሞች፣ ጆሮዎች…. ፀጉሩም ረጅም ነው፡፡ ጓደኛው ደግሞ ምጥን ምጥጥ ያለ ነው፡፡ ኑሮ ጥቅጥ አድርጎ ያሸገው ነው፡፡ መልኩም ኑሮን ነው የሚመስለው፡፡
ብዙ ቁጭ ብለው ጠበቁ - አስተናጋጁ እስኪመጣ፡፡ ህጻኗ ከግልፅነት በመነጨ አንደበት በታችኛው ከንፈሯ ወደ አፍንጫዋ አየር እየነፋች “እፍ! ጫማችሁ ይገማል” አለች፡፡
ቦርጫሙ ሰውዬ አሁንም መሀረቡን አውጥቶ መላጣውን ጠረገ - ስላላበው፡፡
“የማ የኔ?” አለ ገልጃጃው ሰውዬ፤ እጁን ወደራሱ ደረት እየጠቆመ፡፡ ከህፃኗ ጋር ያለችው ሴትዮ ከቦርሳዋ ውስጥ የሆነ ነገር እየበረበረች ቆይታ አስር ሳንቲም አወጣች፡፡ በመስኮት ውጭ ውጭ እያየች፤
“እስቲ እቺን ሳንቲም ለየኔ ብጤው ስጥልኝ” አለች፤ “ዛሬ አቡዌ ናቸው”
በሩ ጥግ የተቀመጠው መላጣው ሰውዬ ስለሆነ ሳንቲሙን ተቀብሎ ከበሩ ውጭ የኔ-ብጤ ይፈልግ ጀመር፡፡ የኔብጤ ግን ባካባቢው አልነበረም፡፡
እታክሲው ጋቢና ተቀምጦ ወደ ኋላ በሚያሳይ መስታወት ነገሩን የሚከታተለው ሹፌር፣ እግሩ ስር ካስቀመጠው ፌስታል ውስጥ ብጥስጥስ ያለ ጨርቅ አውጥቶ ትከሻው ላይ ደርቦና ከዘራውን ይዞ፣ “ስለ አቡዌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ” እያለ፣ በተሳፋሪዎቹ በር በኩል መጥቶ ሳንቲሙን ተቀብሎ ተመልሶ ጋቢና ገብቶ ተቀመጠ፡፡
ጭርቁስ ቡቱቶውንና ባርኔጣውን ወደ ቦታው መለሰ፡፡
አስተናጋጁ ወያላ ስለዘገየ፣ ምጥጥ ያለው ሰውዬ ለገልጃጃው ጓደኛው ወደ ጆሮው ተጠግቶ፤ “ለምን ልጁ እስኪመጣ ወደዛ ሄደህ በውሃ እግርህን አትታጠብም?” አለው፡፡
ቀውላላው ሰውዬ ጮክ ብሎ፤ “የሚሸተው እኮ ያንተ ጫማ ነው፤ የኔ አይሸትም ንፁህ ነው!” አለው ቆጣ ብሎ፡፡
አሁንም ያኛው ወደ ጆሮው ተጠግቶ፤ “ግዴለም አንተ የምልህን አድርግ…ጊዜ’ኮ አይፈጅብህም፡፡ በዛ ላይ ያንተ እግር ታጠበ ማለት የኔ እግር ታጠበ ማለት አይደል? ጓደኝነቱ ለመቼ ነው?”
ቀውላላው እያጉተመተመ የወፍራሙን ሰውዬ መላጣ በመዳፉ ተመርኩዞ፣ ከታክሲዋ ላይ ወረደ፡፡ ባለ መላጣውንና አይኖቹን በምሬት አበሰ፡፡
ቀውላላው በጆግ ውሃ አግኝቶ በታክሲው በር ፊት ለፊት ድንጋይ ላይ ቁጭ አለ፡፡ ከኪሱ ሳሙና አወጣ፡፡ ጫማውን ፈታና አወለቀ፡፡ ታክሲዋ ውስጥ ካሉት ሰዎች አንዱም ስራዬ ብሎ አላየውም፡፡ መታጠብ ጀመረ፡፡
ካልሲው እግሩ ላይ እንዳለ እግሩንም ካልሲውንም አንድ ላይ ሳሙና እየቀባ ውሀ እያፈሰሰ አጠበ፡፡ አጥቦ ሲጨርስ እግሩንም ካልሲውንም አንድ ላይ ጨመቀ፡፡ ጫማውን አደረገ፡፡ ሳሙናውን ወደ ኪሱ መለሰ፡፡
“እፍ! ጫማችሁ ይገማል” አለች ህፃኗ፤ ለሦስተኛ ጊዜ፡፡ ማንም አላዳመጣትም፡፡
ገልጃጃው ተመልሶ ሲመጣ መላጣውን እንዳይነካው ቦርጫሙ ሰውዬ ከተቀመጠበት ጥግ ተነስቶ ወደ ውስጥ ቦታ ቀየረ፡፡ እንደተቀመጠ፣ ሾፌሩ ትንሿን መስታወት አንሸራቶ እጁን አሾልኮ መላጣው ላይ ነካ ነካ አድርጎ ጠርቶት፤ “ይቅርታ ጋሼ ስንት ሰአት ነው?” አለው፡፡
ባለ ቦርጩ መላጣውን በኮቱ ሸፍኖ “በራሴ መላጣ! ልኑርበት…” እያለ በሩጫ ከታክሲዋ ወርዶ ጠፋ፡፡
“ውይ ሰውየው ቡናቸውን ሳይጠጡ ሄዱ” አለች ሴትየዋ፡፡ አስተናጋጁ ወያኔ አሁንም አልመጣም፡፡ ሹፌሩን ጨምሮ ሁሉም ትእግስት አጡ፡፡ መላጣው ሰውዬ ወርዶ ከሄደ በኋላ የተሳፋሪዎቹ ቁጥር በመጉደል ፈንታ አሁንም አምስት ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ብለው እርስ በራስ በደንብ ሲተያዩ፣ አስተናጋጁን ወያላ እመሀላቸው ቁጭ ብሎ አገኙት፡፡ ከነሱው ጋር አብሮ ስለአስተናጋጁ መዘግየት እየተነጫነጨ ሲያማርር፡፡
“አንተ! እስካሁን እዚህ ነህ?... ስራ አለብን እኮ…” እያሉ ሲንጫጩበት ኮስተር ብሎ አስር አስር ሳንቲም መልሶላቸው “እንዲያውም ልዞር ነው አልቀጥልም! ውረዱ!” ብሎ አስወረዳቸው፡፡
ሾፌሩ እንደገና የተበጣጠሰች ዲሪቶውን ለብሶ ሰዎቹ ሊወርዱ ሲሉ በር ላይ ጠብቆ “ስለ አካል ገበያ ምሳዬን ጣሉልኝ” እያለ ዱላውን ተደግፎ አንጀት በሚበላ ድምጽ እያንጎራጎረ ጠበቃቸው፡፡ ከተቀበሉት ሳንቲም ላይ እንደ ርህራሄያቸው አምስትም አስርም፣ ሳንቲም እያነፈሰ ከሚያቃጭልበት እጁ ላይ አደረጉለት፡፡ ተመልሶ ወደ ጋቢና ገብቶ መሪውን ጨበጠ፡፡ ሞተር አስነስቶ መኪናውን አዙሮ በተመላሽ አቅጣጫ አቆማት፡፡ ወያላው መጥራት ጀመረ፤ “አማኑኤል! አማኑኤል!”
ቅድም የወረዱት ተሳፋሪዎች እንደገና ግብግብ ፈጥረው ተጋፍተው ገብተው ቦታ ያዙ፡፡ ባለ ቦርጩ መላጣ ሰውዬ ተመልሶ መጥቷል፡፡ መላጣውን በመሀረቡ እየጠረገ ነው፡፡
ወያላው እንደገና የአስተናጋጅ ሽርጡን አጥልቆ፣ ቆርኪ መክፈቻ በጣቱ ላይ እያሽከረከረ፤
“ምን ልታዘዝ?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡
(አዲስ አድማስ፤ ህዳር 9 ቀን 1999 ዓ.ም)