በቀጣይ ዓመት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በዝግጅት ላይ ነው
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመትና የማስተማሪያ አጠቃላይ ሆስፒታሉን የመቶኛ ዓመት ምስረታ በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች ማክበር ጀምሯል። ባለፈው ረቡዕ ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በተገኙበት በይፋ የተከፈተው ክብረ በዓል፤ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል።
በ1942 ዓ.ም ኢትዮጵያ የጤና ሰራተኞች እንደሚያስፈልጋትና የጤና አጠባበቅ ትምህርት የሚቀስሙበት ማሰልጠኛ ተቋም እንዲከፈት የዓለም የጤና ድርጅት ማሳሰቡን ተከትሎ ነው የጎንደር ጤና ማሰልጠኛ ጣቢያ የተቋቋመው፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን የጤና ባለሙያዎች ስላልነበሩ ወጣቶች እየተመረጡ ውጪ ሐገር እንዲሰለጥኑና የጤና አጠባበቅ ሰራተኞች በሃገር ውስጥ የሚሰለጥኑበት ተቋም እንዲመሰረት የተወሰነ ሲሆን፤ መስከረም 24 ቀን በ1947 ዓ.ም የጎንደር ጤና አጠባበቅ ኮሌጅ ከሐሳብ ወደተግባር መቀየሩን የዩኒቨርሲቲው ታሪክ ይጠቁማል፡፡
ምስረታው እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የዓለም የጤና ድርጅትና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት የተባበሩ ሲሆን፤ በወቅቱ “የጎንደር ጤና ማሰልጠኛ ጣቢያ” በሚል ስያሜ መቋቋሙ ተገልጿል። በዚሁ የምስረታው ዓመት በአገር ግዛት ሚኒስቴር ስር አንድ ዘርፍ ይዞ የነበረው የህዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመባል ከፍ ባለ ደረጃ እንዲመራ በነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 91 መታወጁን የሚያትተው የዩኒቨርሲቲው ታሪክ፤ በ1948 ዓ.ም ደግሞ በሐገሪቱ የሚካሄደው ማንኛውም የጤና ትምህርት በሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር እንዲተዳደር በመታዘዙ፣ ይህ የማሰልጠኛ ተቋምም በሚኒስቴሩ አመራር ስር እንዲውል መደረጉ ተመልክቷል። ማሰልጠን ከመጀመሩ በፊትም፣ የጤና ማሰልጠኛ ጣቢያ የሚል ስያሜውን በ1947 ዓ.ም ስራውን ሲጀምር፣ የጎንደር ህዝብ ጤና ጥበቃ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ወደሚል ቀየረ። ከዚህ በኋላ ብዙ ሂደቶችን ያለፈው ኮሌጁ፤ ከጤና ዘርፍ ውጪ በርካታ የትምህርት ዘርፎችን አካትቶ፣ በ1996 ዓ.ም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ወደሚል ስያሜ መሸጋገሩን ፕሬዚዳንቱ አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) አብራርተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት እያከበረ ባለበት በዚህ ወቅት 11 ኮሌጆች ፣ 87 ቅድመ ምረቃ እና 280 ድህረ ምረቃ፣12 የምርምር ማዕከላት፣ ከተለያዩ ወረዳዎች እስከ መዲናዋ አዲስ አበባ ድረስ 22 የምርምርና የስልጠና እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት መስጫ ግቢዎች ያሉት አንጋፋና ግዙፍ የትምህርት ልህቀት ማዕከል መሆኑ ተነግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ የሚገኝ አንጋፋ የልህቀት ማዕከል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያዎቹን ተማሪዎች በ1958 ዓ.ም ያስመረቀ ሲሆን፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ 2016 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ዘርፎች ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለሃገሪቱ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማበርከትም ሚናው የጎላ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለሃገራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ 10 ሰዎች የክብር ዶክትሬት የሰጠ ሲሆን፤ በቀጣይ ዓመት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ ለመሆን በዝግጅት ላይ እንደሚገኝና በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ ከ150 በላይ አጋር ተቋማት እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል።
ከጣሊያን ወረራ ጊዜ ጀምሮ ታሪክ ያለው የዩኒቨርስቲው አጠቃላይ የማስተማሪያ ሆስፒታል፤ ለጎንደርና ለአካባቢው ህዝብ ጤና ታሪክ የማይዘነጋው ውለታ መዋሉ የተገለፀ ሲሆን፤ 100ኛ ዓመቱን መድፈኑ ታሪኩን ያጎላዋል ተብሏል። በጎንደር ከተማ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብቸኛው ሆስፒታል በመሆን በማከም፣ በምርምር፣ በግንዛቤ ማስጨበጥና በማስተማሪያነት ያገለገለው ይሄው ሆስፒታል፤ አሁንም ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢ ዎች ለሚመጡ ከቤኒሻንጉልና ከሱዳን ጭምር ለሚመጡ በአጠቃላይ ለ13 ሚሊዮን ህዝብ ሪፈራል ሆኖ እያገለገለም ነው ተብሏል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ልህቀትና በጤና አገልግሎት የደረሰበትን የ70 እና የመቶ ዓመት ስኬት፤ ከጥር 14 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ እንደሚቆይ የተገለጸ ሲሆን፤ ከመርሃ ግብሮቹም መካከል ሩጫን ጨምሮ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ ነፃ የጤና ምርመራ፣ ደም ልገሳና ሌሎች የማህበረሰብ አገልግሎቶች ይገኙበታል፡፡ የጎንደር ቃልኪዳን ቤተሰብ ቀን፣ የህክምና ተማሪዎች ምረቃ በዓል፣ የታዋቂ ሰዎች ስኬትና ተሞክሮ ማካፈያ መድረክ፣ የፕሮጀክት ስራዎች ምርቃት፤ የአውደ ርዕይ መርሃ ግብር፣ የጥናትና ምርምር ጉባኤና ሌሎችም የመርሃ ግብሩ አካል እንደሚሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የበዓል አከባበሩ ከዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመት አከባበር ልምድና ከውጪ አገር ተሞክሮ ተቀምሮ ትላንትን፣ ዛሬንና ነገን የሚያስተሳሰር ታሪካዊ አከባበር እንዲሆን ታስቦ ከፍተኛ ዝግጅት እንደተደረገበት ፕሬዚዳንቱ አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) አብራርተዋል።