Monday, 27 January 2025 20:34

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንደገና እንዲዋቀር ወታደራዊ አመራሮች ወሰኑ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አንዳንድ ወታደራዊ አመራሮች ውሳኔውን አልተቀበሉትም

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንደገና እንዲዋቀር ውሳኔ ማሳለፋቸውን የክልሉ ወታደራዊ አመራሮች አስታውቀዋል። አመራሮቹ ጊዜያዊ አስተዳደሩን አምርረው በመተቸት፣ የአስተዳደሩን አመራሮች “የውጭ ሃይሎች መሳሪያ ሆነዋል“ ሲሉ ከስሰዋል።
ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ወታደራዊ አመራሮቹ በትግራይ ክልል ለሚገኙ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየሞከረ መሆኑን ገልጸዋል። “በትግራይ ሃይሎች ላይ የሚካሄደውን የስም ማጥፋት ዘመቻ መከላከል አልቻለም” ሲሉም ተችተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ውስጥ ይስተዋላል ላሉት አጠቃላይ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደሚያሻ የጠቀሱት እነዚሁ አመራሮች፤ “ማንኛውም ነገር ከትግራይ ሃይሎች አቅም በላይ አይደለም።” ሲሉ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡ “ይህንን ሰበብ በመጠቀም የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን አንቀበልም” ሲሉም አክለዋል፡፡
በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት በጊዜያዊ አስተዳደር ያለውን ከ50 በመቶ የዘለለ (50+1) ድርሻውን እንዲረከብ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት አመራሮቹ፤ “በትግራይ ክልል የሚገኙ ታጣቂዎች በትግራይ ሰላምና ጸጥታ ሴክሬታሪያት ስር መሆን አለባቸው። ከዚህ ውጪ በሆነ ወገን ላይ ግን እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ባለፈው ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም. በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በሚመራው ህወሓት ለተካሄደው 14ኛ ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔ ዕውቅና መስጠታቸውንም ወታደራዊ አመራሮቹ አስታውቀዋል፡፡ አክለውም፤ በጉባኤው ውሳኔ መሰረት፣ የጊዜያዊ አስተዳደር የአመራሮች ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
“በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ወሳኝ ስልጣን ያላቸው አመራሮችና አባላት ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ የሕዝብን ጥቅም ወደ ጎን በመተው ክህደት ፈጽመዋል። የውጭ ሃይል መሳሪያ ሆነዋል” ያሉት ወታደራዊ አመራሮቹ፤ “በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም” የሚል  ክስ አቅርበዋል። በዚህም ሳቢያ፣ “የተዳከመ ነው” ሲሉ የሰየሙት፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተነስቶ በምትኩ ሌላ አስተዳደር እንዲዋቀር መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይሁንና የወታደራዊ አመራሮቹ ጋዜጣዊ መግለጫ “አይወክለንም” ያሉ ሌሎች ወታደራዊ አመራሮች ደግሞ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ኮንነው መግለጫ ያወጡትን ወታደራዊ አመራሮች “አደገኛ አቋም ነው” በማለት ነቅፈውታል። ይህ መግለጫ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ፍጭት ከማባባስ ውጭ የሚበጀው ነገር እንደሌለ ያመለከቱት በሃሳብ “ተለይተናል” ያሉት ወታደራዊ አመራሮች፤ “ከዚህ ከፋፋይ የፖለቲካ ጨዋታ ራሳችንን በማራቅ፣ ከታሪክና ከትውልድ ተጠያቂነት ዕዳ እንድንላቀቅ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ፤ “ከተልዕኳቸው ውጭ ለአንድ ሕገ ወጥ ቡድን ወግነው ጊዜያዊ አስተዳደሩን የማፍረስ፣ ስርዓት አልባነት የማንገስና ሰራዊቱን የመበተን ግልጽ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን አሳውቀዋል” በማለት የወታደራዊ አዛዦቹን መግለጫ ወቅሷል። “ሕጋዊም ይሁን ሞራላዊ ቅቡልነት የሌለው” ሲል መግለጫውን ያጣጣለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ “የፕሪቶሪያ ስምምነትንም ለአደጋ የሚያጋልጥና ሃላፊነት የጎደለው ነው” ብሏል፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ አመሻሽ ላይ በይፋዊ የማሕበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው ማብራሪያ።
የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር የሚነቅፍ መግለጫ ያወጡት ወታደራዊ አመራሮች ከጥር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ስብሰባ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፤ በስብሰባው ላይ ሲሳተፉ የነበሩ አመራሮች ብዛት ወደ 200 ገደማ እንደሚጠጋ ለማወቅ ተችሏል። በአንጻሩ፣ ይህንን የወታደራዊ አመራሮች ጋዜጣዊ መግለጫ የነቀፉና ተጻራሪ መግለጫ ያወጡ ወታደራዊ አዛዦች ብዛት ከ12 በላይ እንደሚሆን ተነግሯል።

Read 1066 times