የኢሮብ ሕዝብ በኤርትራ ጦር በደል እየደረሰበት መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፤ የፌደራል መንግስት ይህንን በደል ለማስቆም ምንም ያደረገው ነገር የለም ሲል ተችቷል።
“የትግራይ ሕዝብ አሳር ሊያበቃ ይገባል” በሚል ርዕስ የኢሕአፓ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ረቡዕ ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ አንዳንድ የትግራይ ክልል ወረዳዎች ከነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በኤርትራ ጦር መያዛቸውን አመልክቷል። በተለይም “ከፍተኛ በደል እያስተናገደ ነው” ሲል ፓርቲው የጠቀሰውን የኢሮብ ሕዝብ ለመታደግ የፌደራል መንግስት “ምንም ዓይነት መፍትሔ” ሲሰጥ አለመታየቱን ጠቅሷል።
አያይዞም፣ የኤርትራ ጦር የኢሮብ ወጣቶችን በገፍ እያፈሰ ወደ ሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም እየወሰዳቸው እንደሚገኝ የጠቆመው ኢሕአፓ፤ “የትምሕርት ስርዓቱን በመቀየር በኤርትራ የትምሕርት ስርዓት እያስተማረ ይገኛል” ሲል በመግለጫው አትቷል። “ከፍተኛ የአገር ሉዓላዊነት ወረራ” መሆኑን የጠቆመው ፓርቲው፤ የፌደራል መንግስቱ ድርጊቱን የማስቆም ሃላፊነት እንዳለበት አሳስቧል።
በሌላ በኩል፣ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች መካከል የተፈጠረው መከፋፈልና መወነጃጀል የትግራይ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋትን እንዳያገኝ ማድረጉን ፓርቲው አስታውቋል። “እነዚህ በሕዝብ ስም እየማሉ ሕዝብን ለመከራ በዳረጉ ሁለት ሃይሎች የመከኑ ፍላጎቶች የተነሳ የትግራይ ሕዝብ ሁሌም ከጎረቤቶቹ ጋር ጦርነት እየተማዘዘ ሰላም ርቆት ሊኖር አይገባም” ብሏል።
“ሕጋዊ እና ፍትሐዊ” ምርጫ ተካሂዶ የትግራይ ሕዝብ በእንደራሴዎቹ እስኪወከል ድረስ ሁሉንም ሕጋዊ ፓርቲዎች ያካተተ የመማክርት ምክር ቤት እንዲቋቋምም ኢህአፓ ጠይቋል። በህወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው ውዝግብ የተነሳ የተፈጠሩት ሁለት አንጃዎች “በንግግርና በመቻቻል” አስቸኳይ ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ማበጀት እንዳለባቸውም ፓርቲው አሳስቧል።
“በኢትዮጵያ ያሉ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትግራይ ሕዝብን የረሱት በሚመስል ሁናቴ አንድም ቀን ስለሕዝቡ ሲጨነቁ አይታይም” በማለት የነቀፋው ኢሕአፓ፤ አገራዊ ፓርቲዎች “ስለትግራይ ሕዝብነ ሲሉ ፖለቲካዊ መፍትሔ ማበጀት” ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።