Monday, 27 January 2025 20:39

በኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የቁርአንና አዛን ውድድር ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

- ከ60 አገራት የተውጣጡ 100 እንግዶች ይሳተፋሉ

ዓለማቀፍ የቁርአንና አዛን ውድድር በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ሊካሄድ መሆኑ ተገለፀ። የፊታችን ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስቴዲየም በሚካሄደው ታላቅ ዓለም አቀፍ የቁርአን ውድድር ላይ ከ60 አገራት የሚመጡ 100 የሚደርሱ ተወዳዳሪዎች፣ የልኡካን ቡድን ተሳታፊዎች እንዲሁም ኢንቨስተሮችና ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

በዛሬው ዕለት ምሽት በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፉ የውጭ አገር እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ መግባት እንደጀመሩ አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

የውድድር መድረኩ ቱሪስቶችን ወደ አገራችን ለመሳብ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የተገለፀ ሲሆን፤ የአገር ገጽታ ግንባታ አበርክቶውም የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በዘይድ እብን ሳቢት የቁርዓን ማህበር አዘጋጅነትና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት የበላይ ጠባቂነት የሚካሄደውን ይህን የቁርዓን ውድድር አስመልክቶ፣ ባለፈው አርብ ጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል።

ውድድሩ በሁለት መርሃ ግብር የተከፋፈለ መሆኑን ያብራሩት አዘጋጆቹ፣ የመጀመሪያው የማጣሪያ ውድድር በዛሬው ዕለት ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል የተካሄደ ሲሆን፤ ሁለተኛውና የፍፃሜው ውድድር ደግሞ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም በዕለተ እሁድ በደመቀ ሁኔታ ይካሄዳል ተብሏል።

ዓለማቀፍ የቁርአንና አዛን ውድድሩ ለመስተንግዶ ከፍተኛ ባጀት እንደሚጠይቅ የተናገሩት አዘጋጆቹ፤ የዚህ ውድድር ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑ አብዛኛው የፋይንስ ምንጭም ባለቤቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ብለዋል።

ለዚህም አጋዥ ይሆን ዘንድ አማራጭ የመግቢያ ትኬቶች መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል። የቪአይፒ ትኬት 5ሺ ብር፣ የመደበኛ ትኬት 800 ብርና የተማሪዎች መግቢያ ትኬት ደግሞ በ400 ብር መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ታላላቅ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት እንደሚስብ በተነገረለት በዚህ የቁርአንና የአዛን ውድድር፤ ከተለያዩ የዓለም አገራት 100 የሚደርሱ እንግዶች ይመጣሉ ተብሏል። ከአገራቱም መካከል አሜሪካ፣ ህንድ፣ ቱርክ፣ ሩሲያ፣ ኖርዌይ፣ ኳታር፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ አልጀሪያ፣ ፍልስጤም፣ ጅቡቲና ሌሎች አገራት እንደሚገኙበትም ተነግሯል።

የቁርአን ውድድሩ አዘጋጆች እንደሚያስረዱት፤ ይኼ ታላቅ ዓለማቀፍ ውድድር ከሃይማኖቱ ባሻገር ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው ነው። በአንድ በኩል ብዝሃነታችንን እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብታችንን ለዓለም የምናሳይበት መልካም አጋጣሚ ነው የሚሉት አዘጋጆቹ፤ ቱሪስቶችን ወደ አገሪቱ ለመሳብም ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለው ያምናሉ፡፡ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር ያለንን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርም ፋይዳው የጎላ መሆን ያስረዳሉ።

ለውድድሩ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ተሳታፊዎችና እንግዶች ለሳምንት ያህል በመዲናዋ እንደሚቆዩ የገለፁት አዘጋጆቹ፤ ነዋሪው እንግዶቹን ሁሌም በሚታወቅበት ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ እንዲቀበል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የቁርዓንና የአዛን ውድድር ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተካሄደው የዛሬ 3 ዓመት በ2014 ዓ.ም ሲሆን፤ ይሄኛው ዓለማቀፍ ውድድር ሲካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የቁርአን ንባብ ውድድር ባህላዊ፣ መንፈሳዊና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የእስልምና ሃይማኖት ታሪክ ተመራማሪና ደራሲ የሆኑት ተሾመ ከድር ብርሃኑ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ውድድሮች፤ ተሳታፊዎችና ታዳሚዎች ስለ ቁርአንና ኢስላማዊ አስተምህሮ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉም ያበረታታል ይላሉ፡፡

በተጨማሪም፤ አስተናጋጅ ሀገራት ተሳታፊዎችን፣ ቤተሰቦችንና ተመልካቾችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን ይስባሉ። ይህም ለአካባቢው ኢኮኖሚና ቱሪዝም ዘርፍ ገቢ እንደሚያስገኝ ይገልጻሉ፡፡

መድረኩ የአስተናጋጅ ሀገር ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ያሳያል፣ ወደፊትም ብዙ አለም አቀፍ ጎብኚዎችን ይስባል፤ ሲሉ መሰል የቁርአን ውድድሮች ያላቸውን ፋይዳ አስረድተዋል፡፡

Read 778 times