Monday, 27 January 2025 20:44

በልታ በልታ ጨው የለውም፣ ሄዳ ሄዳ መንገድ የለውም [በሊዓ በሊዓ ጨው የብሉን፣ ከይዳ ከይዳ መገዲ የብሉን] የትግሪኛ ተረት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

እጅግ አድርገው ቀልድ ወዳጅ የነበሩ አንድ ሀብታም ጌታ ነበሩ፡፡ እንደ ጌታው ቀልድ ወዳጅ የሆነ አንድ አጋፋሪም ነበራቸው፡፡ አንድ ቀን ጌታው አንዲት ያልተገራች በቅሎ ይገዛሉ፡፡ በቅሎይቱ ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ናት፡፡ ስለዚህም ጌትዬው አጋፋሪውን ይጠሩና “እቺን በቅሎ ጫንና መንገድ አሳያት” ብለው አዘዙት፡፡ አጋፋሪውም ትዕዛዙን ተቀብሎ፣ በቅሎዋን ጭኖ፣ ተቀምጦባት መጭ አለ፡፡ አንድ መንታ መንገድ ላይ ሲደርስ፣ ዱብ አለና በቅሎዋን፤
“በቅሎ ሆይ፤ ያውልሽ እንግዲህ፡፡ የሸዋ መንገድ ይህ ነው፡፡ የጎጃም መንገድ ይህ ነው፡፡ የጎንደርም መንገድ ይህ ነው፡፡ የትግሬም መንገድ ይህ ነው፡፡ ጌታሽ መንገድ አሳያት ብለውኛልና የወደድሺውን መንገድ ይዘሽ ሂጂ” ብሎ እንደተጫነች ለቀቃትና እሱ ወደ ቅልውጡ ሄዶ አምሽቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፡፡ ጌታውም፡- “ለበቅሎዋ መንገድ አሳየሃት? ሲሉ ጠየቁት፡፡
“አዎን ጌታዬ የአራቱንም አገር መንገድ አሳይቼአት ሳበቃ የወደድሺውን ያዥና ሂጅ ብዬ ለቀቅኋት፡፡” ብሎ መለሰ፡፡ ጌትየው በጣም ተናደዱ፡፡ በነጋታው “ተነሱ ፍለጋ እንሂድ” ብለው አሽከሮቻቸውን ሁሉ አስከትለው ፍለጋ ተሰማሩ፡፡ በቅሎዋ ድራሿ ጠፋ፡፡ በመጨረሻ ያ የጣላት አጋፋሪ ራሱ መልሶ አገኛት፡፡ ዳሩ ግን ገሚስ ጎንዋን ጅብ ተጋብዟት ነው ያገኛት፡፡ በመካያው አጋፋሪው በሌላ አቅጣጫ ወደሄዱት ወደ ጌታው ዘንድ አመራ፡፡
ጌትየው፡- “እህስ ምንም ፍንጭ የለም?” አሉና ጠየቁት ገና ሲያዩት፡፡
“እንዴት ፍንጭ አይኖርም፤ አለ እንጂ ጌታዬ! ግማሿን በቅሎ አግኝቻታለሁ፡፡ ግማሿን ለጅብ አካፍላዋለች” ሲል መለሰላቸው፡፡
* * *
በማንኛውም ወቅት የጅብ ሲሳይ እንዳንሆን መንገድ የሚያሳይ እንጂ መንገድ ላይ የሚጥለን መሪ፣ ኃላፊ፣ ሹም አይጣልብን ማለት ደግ ፀሎት ነው፡፡ አቅጣጫ ሳይለዩ አለ በተባለው በተለመደው መንገድ ሁሉ ጊዜ - አለጊዜ መሄድ ትርፉ እንደ በቅሎዋ መበላት ነው፡፡ አዲስ መንገድ ማየትና መልመድ የሚቻለው በመጀመሪያ ያ መንገድ ሁነኛው መንገድ፣ ጅብ የማያስበላው መንገድ፣ መሆኑን ልብ እንድንል የሚያደርግ በአገር ጉዳይ የማይቀልድ፣ የማያስበላን አጋፋሪ ሲገኝ ነው፡፡
ወደ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያደርሰን መንገድ የቱ ነው? ከሙስና የፀዳ ሹምና ሿሚ የምናገኝበት መንገድ የቱ ነው? ፍትህ ወደሰፈነበት፣ ወገናዊነት ወዳልተንሰራፋበት፣ ሰው በሰውነቱ ወደሚከበርበት፣ በጠባብ አመለካከት ወደማንታወርበት፣ “ከእኔ በስተቀር ለሌላ ጌታ አትደር” የሚል ክፉና ቀናኢ ጌታ ወደማይኖርበት፣ ሰፊ የፖለቲካ ሥርዓት የሚወስደን አውራ ጎዳና የትኛው ነው? የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ወደሚቋደሱበት የስልጣን ገበታ የሚወስደው፤ “ጎንህ እንዲያርፍ፣ የጓደኛህ ጎን ይረፍ” ለማለት የሚችሉ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ወገኖች ለሀገር ሲሉ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በአንድ መድረክ ወደሚነጋገሩበት የፖለቲካ ጀማ የሚያመራው፣ “አፈ-ቅቤ ልበ-ጩቤ” ወደማይበዛበት ብሄራዊ ሸንጎ የሚያቀናው ሁነኛ ጥርጊያ መንገድ የቱ ነው? አዲስ ብለን የመረጥነው አቅጣጫ፣ አዲስ ብለን የሾምነው ሹም፣ አዲስ ብለን የጠመቅነው አስተሳሰብ፣ “አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን” ወደማይሆንበት “የአካሄድ”ና “የሥርዓተ-ሲመት” እንዲሁም “የአቋቋም” ፖሊሲዎቻችን መልሰው እግ -ተወርች ወደማያስሩበት ወግ (Order) የምንደርሰውስ በምን መላ ነው? ነገ የሚታለመው ሥርዓት ሁሉ በአንድ ተውኔት ውስጥ በምፀት እንደተጠቀሰው፤ “ዐይናማው ብለነው እውር ሆኖ ቢወለድስ?”፣ “ክንዴ ብለነው ክንደ-ቆራጣ ቢሆንስ?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
“የአዛውንቶች ልብ ባህር ነው፣ ግን አይዋኝበትም” እንዲል መፅሐፈ-ትግሬ፣ የአዋቂዎቻችንን፣ የብልህ አረጋውያንን እውቀት ለመጠቀም የሚያስችለን መንገድ የትኛው ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ “አስተዋይ ሰው ወይ ገለል ሲል፣ ወይ አገር ለቅቆ ሲሄድ ይታወሳል” ይባላልና በየሰበብ አስባቡ ከአገር ወጥተው በውጭ አገር የሚገኙ አስተዋይ ኢትዮጵያውያንን አእምሮስ የምንጠቀምበት ምን ዓይነት መንገድ አለ? ብሎ መጠየቅ ያሻናል፡፡ ለሀገርና ለህዝብ ሲባል የሚጠየቅ ጥያቄ ይህ ወሰንህ፣ ይህ ዲካህ የሚባል አይደለም፡፡ የተመኘነው እስኪገኝ፣ የጎደለው እስኪሞላ መጠየቅ አለበት፡፡ የሚመለከተው ክፍልም ደከመኝ፣ ታከተኝ ሳይል መልስ መስጠት አለበት፡፡ ትክክለኛ መንገዶችን መጠ|ቆም፣ ማሳየት፣ እንዴትስ እንደሚኬድበት መነጋገር የግድ ነው፡፡
መቼም “አገርና አውድማ መክደኛ አለው” ይሏልና ለየጉዳዩ ሁሉ ቁልፍ ማበጀት፣ መፍትሄና መንገድ ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከእንግዲህ የየሥርዓቱ የቤተ-ሙከራ መፈተኛ - እንስሳ (Guinea-pig) መሆንን የምትሸከምበት ጥኑ ትከሻ የላትም፡፡ የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭቷ፣ ማህበራዊ ቀውሷ፣ የኑሮ ውድነቷ፣ የሹመኞች ሙስና፣ የዜጎች ተስፋ ማጣት ---. ሁሉም የችግር ጠርዞች መፈናፈኛ እያሳጧት ወደ ሌላ የፖለቲካና የሥነ-አዕምሮ አለመረጋጋት ወጀብ ውስጥ እንዳይከታት ብርቱ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡ የምንሰራው ሁሉ ባይሳካም እንደገና እንሞክረዋለን ወደሚልና ሌላ የሙከራ -ቅጽ ወደመሙላት የሚያስኬድ የሚያወለዳ ሁኔታ ከቶ የለም፡፡
“በልታ በልታ ጨው የለውም፣ ሄዳ ሄዳ መንገድ የለውም አለች” እንደሚባለው፤ ጉዟችን ለዕድገት ወደሚከፈት በር እንጂ ወደተገደገደ - አጥር (Dead-end) ከሆነ ለሀገር ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ከዚያ ይሰውረን፡፡

Read 688 times