የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስፖርት ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዮኒቨርስቲ አዘጋጅነት ዛሬ ይጀመራል። የስፖርት ፌስቲቫሉ በተለያዩ ምክንያቶች ለዘጠኝ ዓመታት ተቋርጦ የቆየ ነበር። በአዲስ መልክ እንዲጀመር የኢትዯጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ማህበርና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ልዮ ትኩረት በመስጠት ተንቀሳቅሰዋል።
የስፖርት ፌስቲቫሉ እስከ ጥር 27 በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዮኒቨርስቲና በአካባቢው በሚገኙ የስፖርት ሜዳዎች የሚካሄድ ሲሆን 49 የኢትዯጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል። በአምስት የስፖርት አይነቶች እግር ኳስ ፤ አትሌቲክስ ፤ ዎርልድ ቴኳንዶ ፤ ቼዝና የባህል ስፖርት ውድድሮች እንደሚካሄዱም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደረጀ እንግዳ እንደተናገሩት ስፖርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲስፋፋ መስራት ያስፈልጋል። “ስፖርት ለአንድነትና ለጋራ እድገት” በሚል መርህ ፌስቲቫሉ እንደሚካሄድ ጠቅሰው ዮኒቨርስቲያቸው ለፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች የምግብና የማደርያ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን የስፖርት ውድድሮችን በግቢው እና በአቃቂ ቃሊቲ ሌሎች ሜዳዎች ላይ እናስተናግዳለን ብለዋል።
በፌስቲቫሉ ላይ በአህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ውድድሮች ኢትዮጵያን መወከል የሚችሉ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ማፍራት እንደሚቻል የገለፁት ደግሞ የኢትዯጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አባይ በላይሁን ናቸው። በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ መነሳሳትን እንደሚፈጥርና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ልማት ለማጠናከር እንደሚያግዝም አብራርተዋል። በፌስቲቫሉ ላይ ከሚገኙት 49 ዮኒቨርስቲዎች 46 በእግር ኳስ ቡድኖቻቸው መሳተፋቸውን የጠቆሙት አቶ አባይ በእግር ኳስ ላይ የሚሰሩ ክለቦች፤ የክለብ ባለቤቶችና መልማዮች ፌስቲቫሉን በመታደል እድሎችን እንዲፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በየክልሎቹና በከተማ መስተዳድሮች ያሉ ዮኒቨርስቲዎች በክላስተር አደራጅቶ የውስጥ ውድድሮች በማካሄድ በአሸናፊዎች አሸናፊ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስፖርት ፌስቲቫልን ለማከናወን መታቀዱን የኢትዯጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አባይ በላይሁን አስታውቀዋል።
Monday, 27 January 2025 20:45
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስፖርት ፌስቲቫል ይካሄዳል ስፖርት ለአንድነትና ለጋራ እድገት በሚል መርህ ነው
Written by Administrator
Published in
ስፖርት አድማስ