Monday, 27 January 2025 20:48

የመዲናዋ የገበያ ማዕከላት ፋይዳ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት በማለም፣ በተለያዩ አካባቢዎች የገበያ ማዕከላትን አስገንብቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ ይታወቃል፡፡ በከተማዋ አምስቱም መግቢያ በሮች ላይ የተገነቡት እነዚህ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት፤ ለማሕበረሰቡ የግብርና ምርቶችንና አትክልትና ፍራፍሬዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
በእነዚህ ማዕከላት ነጋዴዎች ምርቶችን ከህገ ወጥ ደላሎች ውጭ፣ ከገበሬዎች በቀጥታ የሚረከቡ ሲሆን፤ ጥራት ያላቸው የግብርና ምርቶችን ከመደበኛ ገበያዎች ከ15 – 20 በመቶ ባነሰ ዋጋ በማቅረብ ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በሁሉም የመንግሥት የገበያ ማዕከላት የሚሸጡ ምርቶችን የዋጋ ተመን የሚያወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ሲሆን፤ የአንድ ሳምንት የዋጋ ተመን ለማውጣት ቢሮው በየሳምንቱ ጥናት በማድረግ፣ ነጋዴዎች የሚሸጡበትን ዋጋ ይተምናል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በመዲናዋ ከገነባቸውና ለአገልግሎት ክፍት ካደረጋቸው የገበያ ማዕከላት መካከል የለሚ ኩራ ሁለገብ የግብርና ምርቶች መገበያያ ማዕከል ተጠቃሽ ነዉ፡፡ በዚህ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ተገኝተን የግብርና ምርቶችን ሲገበያዩ ያገኘናቸው ሸማቾች፣ ማዕከሉ ለነዋሪዎች እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አስመልክተው አስተያየታቸውን አጋርተውናል፡፡
ወ/ሮ ፋጡማ መሀመድን በማዕከሉ ግብይት ሲፈጽሙ ነው ያገኘናቸው፡፡ በማእከሉ የተለያዩ የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በመቅረባቸው ኑሮ በማረጋጋት ረገድ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይም የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እንዲሁም ዱቄት ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡ ማእከሉ የግብርና ምርቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑንና የዋጋው ሁኔታ ከውጭ ከሚሸጠው ጋር ሲነጻጻር ማእከሉ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጭምር ገልጸዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ወልዴ በማእከሉ ሲገበያዩ ያገኘናቸው ሌላኛው ተጠቃሚ ናቸው። ጥቅል ጎመን፣ ካሮት፣ ቲማቲም፣ አቮካዶ፣ ሽንኩርት፣ ድንችና ሌሎች አትክልቶች በማዕከሉ መቅረቡን ጠቁመው፤ ዋጋውም ተመጣጣኝ መሆኑን ተናግረዋል። ሆኖም ወደ ማእከሉ የሚገቡ ምርቶች በብዛት እንዲቀርቡና የምርት ጥራትም ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡ በአካባቢያቸው ማእከሉ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠቱ፣ የግብርና ምርት በአነስተኛ ዋጋ በማቅረብ የነዋሪዎችን ኑሮ በማረጋጋት፣ በግብይት ይጠፋ የነበረውን ጊዜ በመቆጠብ፤ ካላስፈላጊ ወጪ ማዕከሉ እንደታደጋቸው ተናግረዋል፡፡
በማእከሉ ምርት እያቀረቡ ከሚገኙት የግብርና ምርት አቅራቢዎች መካከል አቶ አለማየሁ አሮጎ ይገኝበታል፡፡ በቀጥታ ምርት በማቅረብ ሽያጭ ሲያከናውን ያገኘነው ሲሆን፤ በዋናነት ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲም እንዲሁም እንደ ማንጎ፣ ፓፓዬና ሃብሃብ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን በማምጣት ከመደበኛው ገበያ ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ፣ ለሸማቹ ማሕበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ገበያ እያረጋጉ መሆኑን ገልጿል። የምርት አቅርቦት በተወሰነ መጠን ከእርሻው እንደሚያገኝ የገለጸው አቶ አለማየሁ፤ የተቀሩትን ከሌሎች አምራቾች በመውሰድ ለሸማቾቹ እንደሚያቀርብ ይናገራል፡፡
የገበያ ማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አበራ፣ በዚህ ማዕከል በዋናነት አትክልትና ፍራፍሬ፣ የሰብል ምርትና ጥራጥሬ፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦና ውጤቶች በቅናሽና በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ሌላው የቃኘነው የአቃቂ ቃሊቲ የገበያ ማዕከልን ነው፡፡ የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙዔል ጫኔ፤ የገበያ ማዕከሉ እንቅስቃሴ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱን ይገልፃሉ፤ በማእከሉ የግብርና ምርቶች ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ተደርጎባቸው ስለሚሸጡ፣ ሸማቾች ከመደበኛ ገበያዎች ይልቅ ማዕከሉን እንደሚመርጡና ራቅ ካሉ አካባቢዎች ጭምር እየመጡ እንደሚሸምቱ ገልጸዋል።
የአካባቢው ነዋሪ በማዕከሉ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኑን የሚናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ለሸማቾች ትልቅ ጥቅም በመፍጠሩ የሚፈልጉትን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ መርጠው በአቅራቢያቸው መሸመት ችለዋል ብለዋል፡፡
ሜሮን ሰራዊት በአቃቂ ቃሊቲ የገበያ ማዕከል የእህል ምርቶችን የሚያቀርብ ድርጅት በሥራ አስኪያጅነት ትመራለች፡፡ ገበያው ጥሩ ነው የምትለው ሜሮን፤ ሆኖም ሰው በሚፈለገው ደረጃ አያውቀውም፣ የማስተዋወቅ ሥራ ቢሰራልን የበለጠ ገበያ ይመጣል ብዬ አስባለሁ ትላለች፡፡ የቦታው አለመታወቅ ነው እንጂ ቢታወቅ፣ ሸማቹ ህብረተሰብ በደንብ ተጠቃሚ ይሆናል ብላ እንደምታምን ትናገራለች፡፡
የሚያቀርቡት ምርቶች ዋጋ ከመደበኛው ገበያ ዋጋ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለውም ትገልጻለች፡፡ “እኛ አምራች ገበሬ ነን፤ በቀጥታ ነው ምርት የምናስገባው” የምትለው ሜሮን፤ “ውጪ ላይ ማኛ ጤፍ የሚሸጠው 140 እና 145 ብር ነው፤ እኛ ጋ ግን 118 እና 120 ብር ነው የሚሸጠው” በማለት ለአብነት ጠቅሳለች፡፡
በመለጠቅ የቃኘነው የኮልፌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 የገበያ ማዕከልን ሲሆን፤ ማዕከሉ የተለያዩ የገበያ እንቅስቃሴዎች እንደሚታይበት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወ/ት ትዕግስት አይችሉህም ጠቁመዋል፡፡ በገበያ ማዕከሉ የተሻለ የገበያ እንቅስቃሴ የሚታይባቸው የእህል ምርት ሽያጭ መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ሥራ አስኪያጇ፤ ምርት በቀጥታ ከገበሬዎች እንደሚያስመጡም ይናገራሉ፡፡
በአትክልትና ፍራፍሬ አቅራቢዎች በኩል የሽንኩርት ምርት በቀጥታ ተረክበው የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ወደ ማዕከሉ መግባታቸውንና ቲማቲምና ሙዝ በተወሰነ መልኩ እየገቡ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ከአርባ ምንጭ ሙዝና ፍራፍሬ እያስመጣ ለኮልፌ የገበያ ማዕከል የሚያቀርበው አቶ ግርማ ማላ፤ የገበያው እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑንና ዓለም ባንክ አካባቢ ከሚገኘው መጋዘኑ ሙዝ እያመጣ በመሸጥ ገበያውን እያለማመደ መሆኑን ይገልጻል፡፡ “እስካሁን ባለውም ጥሩ ተስፋ አለው ብዬ እገምታለሁ።” ይላል፡፡
ግርማ አክሎም ሲናገር፤ ”የገበያ ማዕከሉ የሚገኝበት ቦታ ማሕበረሰቡ እየለመደው አይደለም። በመንገድ ችግር ምክንያት ሊሆን ይችላል። እኛ ግን እያስለመድነው እንገኛለን። ወደፊት ያለውን ውስን ችግር በመፍታት የተሻለ ሁኔታ እንደሚፈጠር ተስፋ አለን” ብሏል፡፡
ዮሐንስ ቱፋ ደግሞ በኮልፌ የገበያ ማዕል የበቆሎ ዱቄት፣ ቂንጬ ፣ጤፍና ሩዝ አቅራቢ ነው፡፡ የፋብሪካው ወኪል በመሆንም ምርት እያከፋፈለ እንደሚገኝ ነው የገለጸው። በኮልፌ የገበያ ማዕከል ሥራ የጀመርነው በቅርቡ ነው የሚለው ዮሐንስ፤ ከዚህ ቀደም እህል በረንዳ ይሰሩ እንደነበርና አሁን በማዕከሉ ምርቶቻቸውን እያከፋፈሉ በመሆኑ የገበያ እንቅስቃሴው የተሻለ ነው ብሎ ያምናል፡፡ “ጤፍን ጨምሮ ሁሉም አይነት የእህል ምርት ስለሚገኝ፣ ከዚህ ቀደም ወደ መሳለሚያ በመሄድ ለሚገዛ ሸማች፣ አሁን በአቅራቢያው ለመግዛት የሚያስችል ሁኔታ ተመቻችቶለታል፤ ስለዚህም እዚህ መጥቶ እንዲሸምት እያስተዋወቅን ነው” ይላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅ፣ “በመዲናዋ የገበያ ማዕከላት የተከፈቱበት መሰረታዊ ዓላማ፣ የነዋሪውን የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል እንዲሁም ሸማቹንና አምራቹን በማገናኘት ከደላላ ሰንሰለት ውጪ አርሶአደሩ ምርቱን ወደ ሱቅ በማምጣት፣ ሸማቹ በቀጥታ ሄዶ እንዲገዛ ነው።” ይላሉ፡፡

 


አንዳንድ የገበያ ማዕከላት ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ባይገቡም፣ ስራ የጀመሩት ማዕከላት ግን ገበያውን ማረጋጋት ችለዋል የሚሉት ሃላፊዋ፤ አብዛኛዎቹ ሱቆች የተሰጡት ለአምራቾች መሆኑንና የተወሰነው ለቸርቻሪዎች መሰጠቱን ይናገራሉ፡፡
አሁን ላይ እየሰሩ ያሉት ኮልፌ፣ አቃቂ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ለሚ ኩራ የገበያ ማዕከላት እንደሆኑ የጠቆሙት ወ/ሮ ሃቢባ፤ ሁሉም የማስፋፊያ ስራ እየተሰራላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ የንግድ ሥርዓት በአብዛኛው የተጠላለፈው በደላላ ነው የሚሉት የቢሮ ሃላፊዋ፤ ከሌሎች ገበያዎች ጋር ስናነጻጽረው፣ የገበያ ማዕከላቱ ውስጥ ያለው የደላላ ሰንሰለት በጣም የቀነሰ ነው፤ ይላሉ፡፡ “ሥራ የሚያቀላጥፉ ህጋዊ ደላላዎች በተወሰነ ቁጥር አሉ፡፡ የገበያ ስርዓቱን የሚያስተጓጉል የደላሎች አካሄድ ግን በገበያ ማዕከላቱ ውስጥ የለም።” ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
አምራቾች በገበያ ማዕከላቱ ውስጥ ስራ ለመጀመር ከፈለጉ፣ ሦስት መስፈርቶችን ማሟላት ይገባቸዋል፤ ይላሉ የቢሮ ሃላፊዋ፡፡ አንደኛ፤ ከ15 እስከ 20 በመቶ በሚያቀርቧቸው ምርቶች ላይ ቅናሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም የሚከፍሉት ኪራይ አነስተኛ ነው። ወጪያቸውም የአስተዳደር ክፍያ ብቻ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፣ የምርት አቅርቦት መኖር አለበት። የአምራቹ የራሱ የእርሻ ማሳ መኖር አለበት፤ ወይም ኢንቨስተር ሆኖ በእርሻ ስራ ላይ መሰማራቱን እናረጋግጣለን። ትልቁ መስፈርት ደግሞ ዓመቱን በሙሉ ምርት ማቅረብ መቻሉ ነው። አምራቹ ይህንን ሲያሟላ ነው ወደ ውል መፈራረምና ኪራይ የሚገባው። ይህንን መስፈርት ያሟሉ አርሶአደሮች ወደ ማዕከሉ ከገቡ በኋላ ለቸርቻሪዎቹ ምርት ያከፋፍላሉ ብለዋል፤ ወ/ሮ ሃቢባ፡፡
የመሰረተ ልማት መሟላትን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያም፤ “የመሰረተ ልማት ማሟላት ስራዎች ከሞላ ጎደል እየተጠናቀቁ ቢሆንም፣ የመንገድ ስራ ይቀረናል፡፡ የመንገዶች ባለስልጣን እንደነገሩን ከሆነ፣ በዚህ ወር ውስጥ ሰርተው ይጨርሳሉ። አንዳንድ ነጋዴዎች ከማዕከሉ የሚወጡት በመንገድ ምክንያት ነው።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“የኮልፌ የገበያ ማዕከል ብቻ ሳይሆን፣ የለሚ ኩራ ማዕከል ጭምር መብራት የገባለት በቅርብ ጊዜ ነው። በተመሳሳይ መልኩ፣ የኮልፌ ማዕከል የመንገድና የመብራት ችግር አለበት። አቃቂም ላይ የመንገድ ችግር አለ። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመመካከር ወደ ስራ ተገብቷል።” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የምርት አቅርቦትን በተመለከተም የንግድ ቢሮ ሃላፊዋ እንዲህ ይላሉ፤ “ከሁሉም የገበያ ማዕከል በየቀኑ ዕለታዊ መረጃ እንወስዳለን። በየገበያ ማዕከላቱ ያሉ ምርቶችንና የሸማቹን ፍላጎት እንጠይቃለን። አንደኛው ገበያ ላይ የተትረፈረፈ ምርት ካለ፣ ነጋዴዎቹን የምርት እጥረት ወዳለበት እንዲወስዱ እናደርጋለን፡፡ እስካሁን ግን ያን ያህል የምርት እጥረት ችግር አልገጠመንም። አዲስ አበባ ላይ ተፈልጎ የታጣ ምርት የለም።”
በገበያ ማዕከላቱና በመደበኛው ገበያ ላይ ያለው የዋጋ ልዩነት የሚገናኝ አይደለም የሚሉት የቢሮ ሃላፊዋ፤ በጤፍ ዋጋ ላይ በትንሹ የ2500 ብር የዋጋ ልዩነት መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡ “ሆኖም ሌሎች ገበያዎች ላይ ያለው የሸማች እንቅስቃሴ በገበያ ማዕከላቱ ላይ አይታይም፡፡ በእኛ በኩል ማሕበረሰቡ አላወቀም ብለን ነው የምናስበው።” ይላሉ፡፡
ማዕከላቱን የማስተዋወቁ ስራ ላይ የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ በግምገማችን ለይተናቸዋል፤ ባይ ናቸው፡፡ ለዚህም በቀጣዮቹ ስድስት ወራት የገበያ ማዕከላቱ ከሌሎች የገበያ ስፍራዎች ያላቸውን የዋጋ ልዩነት ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ የማስተዋወቅ ሥራዎች ለመሥራት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ እየሰሩ ያሉትን ሥራ አስመልክተው ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅ ሲናገሩ፤ ከአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር፣ በየገበያ ማዕከላቱ የሚገኙ ካሜራዎችን የማስተሳሰር ሥራ እንሰራለን፤ ይላሉ። “ካሜራዎችን ካስተሳሰርን በኋላ፣ የየገበያ ማዕከላቱን ዕለታዊ ዋጋ የምናወጣው እኛ ነን። በማዕከላቱ ውስጥ ስክሪን ስላለ፣ ዋጋው በዚያ በኩል እንዲታይ ይደረጋል። በተጨማሪም፣ በየገበያ ማዕከላቱ ያለውን ዕለታዊ ዋጋ የሚያሳውቅ መተግበሪያ እያዘጋጀን ነው። ማንኛውም ሸማች ባለበት ቦታ ሆኖ የየማዕከላቱን ዋጋ በቴክኖሎጂ አማካይነት እንዲያውቅ ነው እየሰራን ያለነው።” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
እነዚህ ሁሉ በሂደት እየተሟሉ ሲመጡ የገበያ ማዕከላቱ በእርግጠኝነት የታለመላቸውን ግብ ሙሉ በሙሉ እንደሚያሳኩ አያጠራጥርም፡፡ አሁንም ግን የኑሮ ውድነትን ጫና እያቃለሉና ገበያውን እያረጋጉ ስለመሆናቸው ምስክሮቹ ራሳቸው ሸማቾቹ ናቸው፡፡

Read 288 times