Tuesday, 28 January 2025 19:23

የከፍታ ጉዳይ፤ ከማማ በሰማይ እስከ ተድባብ

Written by  ዮርዳኖስ አልማዝ
Rate this item
(3 votes)

(ክፍል ሁለት)

5. የልጅ ነገር
ከዚህ ቀደም በተለያዩ መጻሕፍት ውስጥ ስለልጅ ጥቅም አይቻለሁ። በትምህርት ቤት ልጅ ኢንሹራንስ መሆኑን ተምረናል። የእኛም ሀገር ወላጆች “ጧሪ ቀባሪዬ!” ይላሉ። በተለይ ለአረጋውያን ምንም ዓይነት መድኅን (ኢንሹራንስ) በሌለበት እንደኛ ዓይነት ሀገር ውስጥ ብዙ ወላጆችን ልጅ የሚወልዱት በስተርጅና ምርኩዝ እንዲሆኗቸው ነው። ይህ ግን አንዳንድ ጊዜ ይለጠጥና ለዛውን ያጣል። አንዳንድ ወላጆች ልጅ ወልደው፣ አሳድገው ጉልበት ለመበዝበዝ፣ ድረው ለማትረፍ፣ ወይም ስደት ልከው ገንዘብ ለማግኘት ሲሯሯጡ ይታያል፤ አርብቶ አደር እንዲል በዕውቀቱ ሥዩም። በሌላ በኩል Abraham Verghese የሚባል ጸሐፊ Cutting for Stone በሚል መጽሐፉ፤ “ልጅ ሞትን መሸወጃ ብቸኛ መንገድ ነው” ይላል፤ ዘርን ማስቀጠያ ዓይነት መሆኑ ነው። የትና መቼ እንዳነበብኩት እንጃ በጣም ያስደነገጠኝ አንድ የወላጆች ዓላማ አለ፤ በሕይወት ዘመናቸው ለማሳካት ያልቻሉትን ጉዳይ ማስፈጸሚያ እንዲሆን ልጅ የሚወልዱ ወላጆች መኖራቸውን ይናገራል! ስድብን (መኻን ናቸው መባልን) ለማራቂያ፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ለመስማማት ወይም ከወደረኞቻቸው ጋር ለመበሻሸቂያ ሲሉ ብቻ ልጅ የሚወልዱም አሉ። አንዳንዱ ደግሞ ወልዶም ልጆቹን መከራ፣ ጸብና ስድብ ማጠራቀሚያ ያደርጋቸዋል፤ ሰባት ስድብ ወለደች እንዲል ዓለማየሁ ገላጋይ።
በዚህ መጽሐፍ ልጅ ለተለየ ዓላማ ነው የሚውለው፤ ለበቀል። አክስቱ እልፍነሽ ጌታን የምታሳድገው የወንድሟን ደም እንዲመልስላት ነው። ስሙንም ደም-መላሽ ትለዋለች። “አሳድገሽ የምትቀጥፊኝ እኔ የጓሮ ጎመንሽ አይደለሁም” በሚል የሚያምጸው በኋላ ነው። ስሙንም “ጌታ” ያለው በዚሁ ምክንያት ነው፤ በልቤ ፍላጎትና በዕጣ-ፈንታዬ ላይ የምወስን እኔ ነኝ የራሴ ጌታ! ጌታ ይህን ይበል እንጂ፣ ከላይ እንደተመለከተው፣ ከአጎቷ ምርጫ በተቃራኒ በልቧ ፍላጎት ላይ የምትወስነው ግን “ሚስቱ” ዱሬቲ ናት። አንዱ ሐሳብ ያመጣል፣ ሌላው ይተገብራል!
ከልጆች ስያሜ ጋር በተያያዘ “ደመላሽ” ዓይነት ስሞች የሚያስተላልፉትን መልእክት ወደ ጎን አድርገን፣ ወላጆች (አባቶች) ለልጆቻቸው የሚያወጡትን ሥያሜ ስናጤን፣ ጥቂት የማይባሉ ወላጆች ለራሳቸው ሹመትና ማዕረግ የሚሰጡ እንጂ ለልጅ ስም የሚያወጡ አይመስሉም። ዶክተር ገዳሙ የሚባል አብሮኝ የተማረ ልጅ ነበር። ገዳሙ የአባቱ ሥም ነው! ሌሎች ስሞችንም ማጤን ነው።
በጣም የወደድኩትና ቢሆን ብዬ ያሰብኩት በአሰፋ ገብረማርያም እንደወጣች ቀረች መጽሐፍ ላይ ስለልጅ የሚናገረውን ነው። የባልና ሚስት ፍቅር ከእነሱ ተርፎ ሲገነፍል፣ የአምባቸውን ውበት በሕይወት ዘመናቸው ጠብቀው ለማቆየት ዕድሜ አልበቃ ሲላቸው ነው ልጅ መውለድ የሚፈልጉት። ያንን ሞልቶ የፈሰሰ ፍቅር ለማኖሪያ፣ ያንን የውበት መንበር ለማቆያ!

6. ፕሮፓጋንዳ፤ ሜንቶርሺፕ እና የመንጋነት አስተሳሰብ
የመጽሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ፣ የመጀመሪያ አንቀጽ እንዲህ ይላል፤ “አንዳንድ ጊዜ ለገድል የሚጠሩት ግለሰቦች ይሆናሉ፣ ሌላ ጊዜ ሕዝብ። ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነው የኋለኛው ነው።” ሕዝብ ለገድል ተጠርቶ ወዳልታወቀው ሲሄድ ለምን እንደተጠራ በመንገዱ ይረዳል፤ በዋናነት በተማሪውና በመምህሩ በኩል። መምህሩ ስለ ቅኝ ግዛት የሚያደርጉት ንግግር (lecture) ከተለመደው ዓይነት ፕሮፓጋንዳ ሥራ ይልቅ የሜንቶርሺፕ ሙያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። የመምህሩ ዓይነተኛ ተግባር ተማሪያቸውን ማትጋትና ማብቃት እንዲሁም ዘማቾቹን ማስተማርና ማንቃት ነው። እዚሁ መጽሐፍ ላይ “የሚያተጉን ሰዎች በመኖራቸው ዕድለኞች ነን!” ይላል።
ከመምህሩ ንግግር በተጨማሪ ዘመቻውን በድል ለመወጣት በርካታ ሥሜት ቀስቃሽ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ተሠርቷል። ዘፈኖች፤ ልዩ ልዩ ፉከራዎች፣ ሽለላዎችና ውዝዋዜዎች፤ ሌሎችንም ወኔ ቀስቃሽና ቆስቋሽ ክስተቶችን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ተዳምረው ዘማቹን ይበልጥ ያተጉታል። ይህ ዓይነቱ ፕሮፓጋንዳ ጤነኛ እና ከፍ ያለ ዓላማ ያለው ነው። ከዚህ በተቃራኒ ፖለቲከኞች፣ የገበያ ሰዎችና ተንኮለኞች የሰውን ልጅ በፕሮፓጋንዳ ለክፉ ዓላማ ሊያተጉትና ሊጠመዝዙት ይችላሉ። ለሥራ ጉዳይ በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ክፍሎች በተዘዋወርኩ ጊዜ ፖለቲከኞች የዋሆቹን ደቡብ አፍሪካውያን በቀላሉ ጠምዝዘው የመንጋ አስተሳሰብ ውስጥ በመክተት እርስበርስ ሲያጋጯቸው፣ በመጤዎችም ላይ ሲያስነሧቸው አይቻለሁ። የገበያ ሰዎችም በቀላሉ ጠምዝዘው ምርቶቻቸውን በገፍ ሲሸጡ ተገንዝቤያለሁ። ይህ ተግባራቸው የሰው ልጅ እንዴት ወገንተኛ ወይም ቡድናዊ እንደሚሆን እና የገበያም ይሁን የፖለቲካ ወይም ሌላ ዓይነት ፕሮፓጋንዳ እንደ marionette ሊወዘውዘው እንደሚችል ያሳያል።
“እፋረደዋለሁ አልለቀው በዋዛ
ከምድር ላይ ሲያጠፋ የሰውን ልጅ ለዛ” የሚል ሥነ-ቃል አለ።
በዚህ መጽሐፍ በፕሮፓጋንዳ፣ በባሕል ወይ በሌላ ምክንያት የሰው ልጅ ለዛውን ሲያጣና በቀልን እንደ ወግ ቆጥሮ ሲንቀሳቀስ ይታያል። በመጽሐፉ ገጽ 77 ላይ እንዲህ ያለው የመንጋ አስተሳሰብ የሚገለጽ ይመስለኛል፤ “ጌታ ከሁሉ በላይ ወጣቶቹ በአንድ ቋንቋ የሚናገሩ፣ በአንድ ጭንቅላት የሚያስቡ፣ በአንድ አንደበት የሚናገሩ፣ በአንድ የልብ ትርታ የሚንቀሳቀሱ መሰሉት።” ይህ ዓይነቱ የመንጋነት ሥሜት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ እየተስተዋለ ያለ ጉዳይ ይመስለኛል። ከዚህ አንጻር ሕዝባችን ፖለቲከኞች እና የገበያ ሰዎች እንዳረጉት ነው ወይ የሚወዘወዘው፤ እንደጠመዘዙት ነው ወይ የሚጠመዘዘው? የሚል ጥያቄን ያጭራል። በውጪ ጠላት ላይ በወገንም ላይ ሲያነሣሱት መቀበል ነው ወይ?! የውጪውን ከውስጡ፣ ጠቃሚውን ከጎጂው፣ ትክክለኛውን ዓላማ ከእኩዩ መለያው ምንድነው? መዳኛው የት ነው? የሚለው አሳሳቢ ጉዳይ ይመስለኛል።

7. የዓድዋ ድል፡ ተቋማት እና አብሮነት
Why Nations Fail የሚል መጽሐፍ ኢትዮጵያ ውስጥ በፊውዳል አገዛዝ ጊዜ የተፈጠሩ extractive እና exclusive ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት መኖራቸውን ያብራራል። ኢትዮጵያ ቅኝ ባትገዛም እነዚህ ተቋማት ለድኽነት መንሰራፋት ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ይተነትናል። ኢትዮጵያ ቅኝ አለመገዛቷ የባሕል ወረራን መከላከሉና የሥነ-ልቡና የበታችነት አለመፍጠሩ አንዱ ጥቅም ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወኔ መኖሩ ለዓድዋ ድል አንድ ምክንያት ቢሆንም፣ በራሱ በቂ አይመስልም። በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችና ግንኙነቶች እንዲሁም ባሕላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ወታደራዊ ተቋማት ዘማቹን አንድ ላይ አስረው ለድል አብቅተውታል ማለት ይቻላል።
ከተቋማት ጋር በተያያዘ፣ ደራሲዋ ዘመነ መሳፍንት የሚጀምረው የተቋማት መፍረስ ወይም መዳከምን ተከትሎ እንደሆነ በሌላኛው መጽሐፏ (ምንትዋብ) ትጠቁማለች። ለዚህ አንዱ ምክንያት ዘውዱን ለመጠበቅ ወይም ሥልጣንን ለማደላደል በሚል merit-based የሆነ አሠራርን ወደ ጎን አድርጎ የራስን ወገን በዙሪያ መሰብሰብ ነው። ይህ ደግሞ በእቴጌ ምንትዋብ ጭምር የደረሰባት ይመስላል። ከሠዓሊው ጥላዬ ጋር የምታደርገው ውይይት ይህን ያሳያል። ጥላዬ ይህን ይላታል፤ “ነገረ ማርያም ያስጣፉትን አንብቤያለሁ። ደግ ሠሩ። ወደዠመርነው ልመለስና መቸም ዝምድና ለመቸ ነው? ልንገርዎ እንጂ። መኳንንቱ እኮ በእርስዎ ተቀይመዋል። በአስተዋይነትዎ፣ በዘዴኝነትዎ፣ በጽናትዎና በብሩህ አእምሮዎ ቢያመሰግንዎትም ቤተዘመዶችዎን ቤተ-መንግሥት ባገቡ ቁጥር፣ ቀድሞ በጦር ሜዳ ዠግንነት፣ በዕውቀትና ባስተዋይነት ሚሾሙ መኳንንት ነገሩ የዝምድና መሆኑ ኻስቆጣቸው
ሰነባብቷል። አሁን ዘመዶቻቸው ሲሞቱና ሲያረጁ፣ አገር ያስተሳስር የነበረው… ምሶሶው… ዘውዱ… የንጉሡ ሥርዓቱ… ተዳከመ። እርስዎ ብቻ ሳይሆኑ ዐጤ አድያም ሰገድ ኢዮአስም ወደናታቸው ዘመዶች በማድላታቸው፣ የናታቸውን ዘመዶች በመሾማቸው መኳንንቱ ድጋፋቸውን ነፈጓቸው። ዛዲያ ዛሬ ሥርዓቱ ሁሉ ቀርቶ ንጉሥ የሚያነግሥና ሚያወርድ አንድ ሰው ብቻ ሁኗል። ዛሬ ሚሾሙ ሚሽሩት ንጉሡ ሳይሆኑ… የፍርድ ሥርዓቱ… ፍትሐ ነገሥቱ ቀርቶ… ሚፈርድ፣ ሚያስርና ሚገል፣ ያሻውንም አገር አንሥቶ ለፈለገው ሚሰጥ፣ አድራጊ ፈጣሪው አንድ ሰው ነው። ዘውዱን ሚጠብቁና ሚያቆሙ፣ የወጉና የሥርዓቱ ማገር የነበሩት ዓቃቤ ሰዓቱ፣ አቡኑና የመሳሰሉት… እንዲሁም የመኳንንት፣ የምክክር ሸንጎ ሲቀር፣ ቤተ-ክርስቲያን ተመልሳ ስትከፋፈል፣ በዝኽ የተነሣ ሥርዓቱ ሁሉ ፈራረሰ ይላሉ። እንዲያም ቢሆን ታላቁ ኢያሱ ከሞቱ በኋላ፣ አገራችን ለኻያ ለሚበልጡ ዓመታት ጨለማ ውስጥ ገብታ ነበር። እርስዎና ዐጤ ብርሃን ሰገድ ኢያሱ ኸጨለማ አውጥታችሁ ብርሃን ፈንጥቃችሁልን፣ ትምህርት አሳድጋችሁ የተድላ የደስታ ዘመን ሁኖልን ነበር። እርስዎ በመንበርዎ በቆዩልን ኑሮ።”
ወድ ዓድዋና የአብሮነት ነጥብ ስንመለስ የዓድዋ ዘመቻ በወኔ፣ በተቋማዊ አሠራርና በሕዝብ ተሳትፎ የውጪውን ጠላት ድል ካማድረግ ባሻገር ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ማኅበረሰቦችን እርስበርስ ያስተዋወቀ፣ ያቀራረበና በደም ያቆራኘ መሆኑ በመጽሐፉ ተመልክቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠረብኝ ጥያቄ ዘመቻው የውስጡን በደልና ንቀት ከመቅረፍ ወይም ከመፈወስ አንጻር ምን ያህል ሚና ነበረው? የሚል ነው። በመጽሐፉ የቅኝ ገዢዎች መገለጫ ተደርገው የተገለጹት እብሪት፣ ትምክህት፣ ንቀትና፣ ትዕቢት በሀገር ውስጥም በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ይስተዋላሉ። ዘመቻው መተዋወቅና መረዳዳቱን እንዳመጣ ግልጽ ነው። መከባበርና መኳኳኑንስ? ወይስ ተጽዕኖው ዘመን ተሻጋሪ አይደለም?
ሌሎችም ጥቂት ጉዳዮች ነበሩኝ። እንዳይበዛ ብዬ ተውኳቸው።

ማጠቃለያ
ሕይወት፤ ከማማ በሰማይ (ተምኔታዊ ሶሻሊዝም) እስከ ተድባብ ድረስ የከፍታ ነገር የሚመስጣት ትመስላለች። Mine to Win ወይም ኀሠሣ በሚለው መጽሐፍ ዐወቀ አንዴ ከተፈጠረ በኋላ የሕይወት ከፍታ ላይ ለመድረስ የራሱ ጥረትና ኃላፊነት መሆኑን በአጎቱ በኩል በቅኔ መስላ ታቀርባለች። ዐወቀ የቅኔ ሊቅ የሆነውን አጎቱን፤ “በርትቼ ተምሬ አንድ ቀን የቅኔ መምህር ነው እምኾን። …ልክ እንዳንተ” ስል አረጋገጥኹለት ይላል። በዚያች ቅጽበት፥ እዚያች ቦታ ላይ የቅኔ መምህር የመሆን ሐሳብ በዐወቀ ልብ ውስጥ ያብባል።
“ቅኔ ግን ከባድ ትምህርት ነው ሲባል ሰምቻለኹ” ስል ጨምሬ ተናገርኹ። ይላል ዐወቀ
አጎቱ፤ “ቅኔ፥ በሕይወት እንደሚገጥምኽ እንደማንኛውም ነገር፥ የትጋትና የኀሠሣ ሽልማት ነች”
ዐወቀ፤ “ተተጋኹ እምሸለማት?”
አጎቱ፤ “አዎን የልፋትህ አዝመራ፥ ፍሬ ፃማ፥ ሽልማትኽ ናት። ገና ስትፀነስ በሕይወት ዘመንኽ ትልቅ ቦታ የመድረስ ምርጫ ተመነሻውም የተሰጠኽ መኾኑን ተገንዘብ። ፈጣሪ ሕይወትን ሰጥቶኻል፥ ሕይወትኽን ደርዝ እምታስይዘው ግን አንተ ነህ። ቢያንስ መሞከር አለብኽ። ወኔ ማለት መለወጥ እምትችለውን ነገር መለወጥ መቻል ነው።
በምንትዋብ መጽሐፍ ደግሞ በሰዓሊው ጥላዬ በኩል የቤተክርስቲያን ሥዕሎች ሲሣሉ የሚታለፍባቸውን ሒደቶችና ሥዕል ለመሣል ሠዓሊው የሚያደርገውን ጽናት ትተርካለች። ጾምና ጸሎቱ፣ ንጽሕናውና ትጋቱ ነው ከፍታ ላይ አስቀምጦት ልዑል የሆነ ሥዕል ለመሣል የሚያበቃው። እንደቅኔው ሁሉ።
በዚህኛው (ተድባብ) መጽሐፍ ደግሞ የዓድዋ ድል የድሎች ክምችት፣ የጋራ ከፍታ፣ የወል ማማ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው በየዘርፋቸውና በየሙያቸው ከፍታ ላይ የሚደርሱበትን ሒደት ታሳያለች። የዓድዋ ድል የጀግኖች ጉዞ መሆኑን ትተርካለች። ይመር በመሲንቆ፣ ነሞ በፈረስ ግልቢያና በጦር ውርወራ፣ ጌታ በጠመንጃ ተኩስ፣ ሌሎችም በየሙያቸውና በየዘርፋቸው። ይህ ይመስለኛል ዓድዋን የወል ከፍታ፣ የድል ክምችት - ተድባብ የሚያደርገው።

Read 170 times