ይሄ ገጠመኝ መቼቱ አይታወቅም፡፡ ገጠመኙ የሆነ የተፈፀመ ነው፣ የት እና መቼ እንደተፈፀመ ግን አይታወቅም፡፡ ታሪኩ ተራ የሚመስል ገጠመኝ ነው፣ በልቦናዬ የፈጠረው ጥልቀት ግን መለኪያ የለውም፡፡ ታሪኩ አጭር ነው፣ የታሪኩን ዳና ግን ሁለንታውን በጠቅላላ ባስስ እንኳን የምደርስበት አይመስለኝም፡፡ ቀን ላይ የተፈጠረ ገጠመኝ እንደሆነ ግን አውቃለሁ፣ ምክንያቱም የልጅቷን ብሩህ ፈገግታ አይቼዋለሁ፡፡
እንዲህ ነበር….
ሱሪዬን አውርጄ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ተቀምጫለሁ፡፡ የመፀዳዳት ተግባር እርካታ እንደሚሰጥ ሁላችንም እናውቃለን፤ እናም በዚህ እርካታ ታጅቤ፣ በሌላ ሀሳብ ውስጥ ሰምጬ የት እንደተቀመጥኩ እንኳን ረስቻለሁ፡፡ የት እንዳለሁ ብቻ ሳይሆን ምን እያደረግሁ እንደነበረም ረስቻለሁ፡፡ ጨርሼ ልታጠብ እጄ በልማዱ መሰረት ውሃ ፍለጋ ሲያማትር፣ ልቦናዬ ወደ ተጨባጭ ከባቢዬ ተመለሰ፡፡ ከተወሰድኩበት የሀሳብ አለም ስመለስ የት እንዳለሁ አወቅሁ፣ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ተቀምጬ ነው ያለሁት፡፡ ቀና ስል መፀዳጃ ቤቱ ክፍት ነው፡፡ በሩን ወርውሬ ለመዝጋት በተቀመጥኩበት ስንጠራራ መፀዳጃ ቤቱ በር የለውም፡፡ ደንግጬ ሰው ሳያየኝ ቶሎ ከጉልበቴ በታች ያለ የውስጥ ሱሪዬንና ሱሪዬን እየታጠቅሁ ልቆም ስል ሱሪ የለኝም፡፡ እየተጣደፍሁ ሀፍረቴን በውስጥ ሱሪዬ ልሸፍን እጄን ስሰድ የውስጥ ሱሪም የለኝም፡፡ ፊት ለፊቴ ሳይ ወደ መፀዳጃ ቤቱ ልትገባ ወረፋ ስትጠብቅ የነበረች ልጅ ቆማ እያየችኝ ነው፡፡ ደነገጥኩ፡፡ አፈርኩ፡፡ በደመነፍስ እጆቼን ጭኖቼ መሀል አደረኩ፡፡ ልጅቷ ቅንነት ከተሞላበት የሚያፅናና ፈገግታ ጋር “አይዞህ ፓንት የለኝም ብለህ አትፈር፣ እንትን የሌለው አለና” አለቺኝ፡፡ ከዚያ “ቆይ ፎጣ ላምጣልህ” ብላ ወደ ቤቷ ፈጠነች፡፡
መፀዳጃ ቤት የተገኘሁት ከቤቴ ወጥቼ ይሁን ከሌላ ቦታ ተነስቼ መጥቼ አላውቅም፡፡ ከመፀዳጃ ቤቱ ወጥቼ የት እንደምሄድ አላውቅም፡፡ ያለሁበትን እንጂ የመጣሁበትንም ሆነ የምሄድበትን አላውቅም፡፡ ልጅቷ ፎጣ ላምጣልህ ብላኝ እንደሄደች አልተመለሰችም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በህልሜ ፎጣውን አምጥታ ሰጥታኝ፣ አገልድሜ ሀፍረቴን ሸፍኜ ከመፀዳጃ ቤቱ ስወጣ አያለሁ፡፡ ገጠመኙ ግን በእውነት የሆነ እንጂ ህልም አልነበረም፡፡
ነገሩን ሳስበው ተከራይቼ የምኖርበት ግቢ ውስጥ የተፈፀመ ይመስለኛል፤ ለስራ ጉዳይ መስክ በወጣሁበት ሆቴል ውስጥ የሆነም ይመስለኛል፤ ደግሞ የሆነ ቤት በእንግድነት ሄጄ እዚያ የተፈጠረ ገጠመኝም ሆኖ ይታየኛል፡፡ ሌላም ሌላም ቦታና ሁኔታ ላይ የተፈጠረ ገጠመኝ እየሆነ ይታሰበኛል፡፡ ሁሉም ቦታ ላይ የሆነ ይመስላል፤ ግን የትም አይደለም፡፡ ምናልባት በሌላ ሁለንታ (Universe) እና በሌላ ፕላኔት ከሚኖረው እኔ ተላልፎ የመጣ የልቦና ቅጅ ይሆን ስል አሰብሁ፡፡ ሁለንታችን ከምናስበው በላይ ሰፊ ነው፡፡ ሌሎች የሰማይ አካላትን ትተን በከዋከብትና በፕላኔት ደረጃ ብናየው እንኳን በቴሌስኮፖቻችን አማካኝነት ማየት የምንችለው ሁለንታችን በመቶ ቢሊየን ትሪሊየን በሚቆጠሩ ከዋከብቶችና ፕላኔቶች የተሞላ ነው፡፡ ከእነዚህ ፕላኔቶች ውስጥ አንዷ የእኛዋ ምድር ናት፡፡ እናም የሰው ልጆች እስካሁን እስከምናውቀው ድረስ በሁለንታው ውስጥ ህይወት ያለባት ፕላኔት ምድር ናት፡፡ ግን በሁለንታችን ውስጥ ካለው በትሪሊየን የሚቆጠር ፕላኔት ውስጥ ህይወት የሚኖርባት ፕላኔት ምድር ብቻ ናት የሚለውን አምኖ ለመቀበል ይከብዳል፡፡ ደግሞ ይህ ብቻ አይደለም፣ በቴሌስኮፖቻችን ታግዘን ማየት ከምንችለው ሁለንታ ባሻገር ሌላ ራሱን የቻለ ሁለንታ ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚያም ባሻገር ሌላ፣ ከዚያም….፡፡ እናም ሌሎች የሰለጠኑ ፍጡራን (Aliens) በሌሎች የከዋክብት ስርአቶችና ፕላኔቶች ውስጥ ይኖራሉ የሚለው መላምት እንዳለ ሆኖ፣ ከሁለንታችን ስፋትና ቁጥር አንፃር የሁለንታችንን ባዶነት (ህይወት አልባነት) አምኖ ላለመቀበል ሰዎች ከሚያቀርቧቸው መላምቶች አንዱ በማናውቀው እያንዳንዱ ሁለንታና ፕላኔት ላይ የእኛ ቅጂ አለ የሚል ነው፡፡ እያንዳንዳችን ልክ እዚህች ምድር ላይ ዕለት ተዕለት የምናደርገውን ነገር እያደረገ እኛ የምንኖረውን ህይወት የሚኖር የራሳችን ቅጂ ሌላ ሁለንታና ፕላኔት ላይ አለን፡፡
ቅጂያችን በሌሎች ሁለንታዎችና ፕላኔቶች ላይ መኖሩ ብቻ አይደለም፣ የቅጂያችን ቁጥር ማለቂያ የለውም፡፡ በዚህ መላምት የተነሳ እኔም መቼቱን ላውቀው ያልቻልሁት ግን በትክክል የተፈፀመው ገጠመኜ፣ ከሌላ ሁለንታና ፕላኔት ከሚኖረው እኔ ለልቦናዬ የተላከልኝ ቅጂ ይሆን ስል አስባለሁ፡፡
ልጅቷን ግን እዚህች ምድር ላይ ባለቺኝ የቀን ተቀን ህይወቴ ውስጥ አገኛታለሁ፡፡ በስራ ቦታ፣ በመዝናኛ ስፍራ፣ በመጓጓዣ ውስጥ፣ በድግስ ቦታ፣ በቀብር ቦታ… አገኛታለሁ፡፡ አጋጣሚው ረድቶኝ ቀርቤ ያነጋገርኋት ቀን ምነው ወዳጄ ፎጣውን ሳታመጪልኝ ቀረሽ? ለማለት ይዳዳኛል፡፡ አንዲት ሴት አይደለችም፡፡ ልጅቷ የምትገለጥልኝ በተለያዩ ሴቶች ምስል ነው፡፡ እሷ መሆኗን የማውቀው በቅን ፈገግታዋና በገመና ሸፋኝ ሰብዕናዋ ነው፡፡
ተፈፀመ፡፡ የሆነ ጊዜ፣ የሆነ ቦታ፣ የሆነ ሁለንታ፡፡