Wednesday, 29 January 2025 00:00

እምቢ!

Written by  ደራሲ፡- ቮልፍጋን ብሮሸርት አዛማጅ ትርጉም፡- ዮናስ ታረቀኝ
Rate this item
(0 votes)

የነብይ ገፅ

በተለያየ ሙያ ላይ ያለህ አንተ ሰው፤ ከሙያህ፣ ከህሊናህ ውጪ ለጥቅም፣ ለፖለቲካ ተገዝተህ እንድትኖር ሲጠይቁህ፣ ያለህ መልስ አንድ ብቻ ይሁን፡፡ እምቢ!

በተለያየ ሙያ ላይ ያለሽ አንቺ ሴት፤ ከሙያሽ፣ ክህሊናሽ ውጪ ለጥቅም፣ ለፖለቲካ ተገዝተሽ እንድትኖሪ ሲጠይቁሽ፣ ሴትነትሽን መጠቀሚያ ሊያደርጉት ሲያስቡ፣ ያለሽ መልስ አንድ ብቻ ይሁን፡፡ እምቢ!
እናንት መምህራን፤ በተማሪዎቻቸሁ ጭንቅላት የተዛባ ትርክት፣ ከሚያቀራርበው ይልቅ የሚያለያየውን አስተምሩ ስትባሉ፣ መልሳችሁ መሆን ያለበት፣ እምቢ!
እናንት ተማሪዎች፤ በአንድ ዴስክ፣ በአንድ ክፍል ከምትማሩ ጓደኞቻችሁ ጋር እንድትቃቃሩ የሚያደርግ ምንም ነገር ተቀበሉ ስትባሉ፣ እንዲህ በሏቸው፣ እምቢ!
አንት የኪነት ሰው፤ ካሁን በኋላ የፍቅር ስብከት ሳይሆን የጥላቻ መዝሙር ንዛ፣ ቢሉህ መመለስ ያለብህ እንዲህ በማለት ነው፡፡ እምቢ!
አንት የኃይማኖት አባት፤ መግደልን ባርክ፣ ቅዱስ ጦርነትን ስበክ ስትባል፣ ማለት ያለብህ አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እምቢ!
አንት የመርከብ ካፒቴን፤ በስንዴ ፈንታ መድፍና ታንክ ጫን፣ አጓጉዝ ሲሉህ፣ የምትመልሰው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እምቢ!
አንት አብራሪ፤ ቦምብና የመርዝ ጋዝ አዝንብ ተብለህ ስትታዘዝ፣ የምትለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እምቢ!
አንት ሾፌር፤ ነገ ተነስተው ጥይትና ወታደሮችን አጓጉዝ ቢሉህ፣ እንዲህ ብለህ አንድ መልስ ስጣቸው፡፡ እምቢ!
አንት ልብስ ሰፊ፤ ቀሚስና ሱሪ መስፋትህን አቁመህ የወታደር ዩኒፎርም ስፋ ስትባል፣ መልስህ የሚሆነው አንድ ነው፡፡ እምቢ!
አንት ባለሃብት፤ ገንዘብህን ለሰብዓዊ እርዳታ ሳይሆን፣ ለጦርነት ለግስ ሲሉህ፣ መልስህ አንድ እና አንድ ብቻ ይሁን፤ እምቢ!
አንት ዳኛ፤ ፍርድ አዛባ፣ ደሃ በድል፣ የሀሰት ፍርድ ስጥ ቢሉህ፣ አንድ መልስ ብቻ መልስላቸው፡፡ እምቢ!
አንት ጋዜጠኛ፤ የሃሰት ዘገባን ንዛ፣ ትክክለኛውን ትተህ የተዛባውን አንብብ ስትባል፣ የሚኖርህ መልስ አንድ ብቻ መሆን አለበት፡፡ እምቢ!
አንት ፖሊስ፣ አንት ወታደር፣ አንድ ባለስልጣን ለኔ ጥቅም ስትል ቃታህን በህዝብ ላይ ሳብ፣ ቢልህ መልስህ እንዲህ ያለ ይሁን፣ እምቢ!
እናንት ፓርቲዎች፤ በሰውነት ሳይሆን በሰፈር፣ በጎጥ፣ በቡድን ተደራጁ ሲሏችሁ፣ እንዲህ መልሱ፣ እምቢ!
በሁሉም አቅጣጫ በከተማም በገጠርም ያላችሁ ሰዎች፤ ወንድሞቻችሁ ላይ ለመዝመት ወደ ጦር ካምፕ ክተቱ የሚል ትዕዛዝ ቢደርሳችሁ፣ መልሳችሁ መሆን ያለበት አንድ ብቻ ነው፡፡ እምቢ!
በምስራቅም በምዕራብም፣ በደቡብም በሰሜንም ያለሽ እናት፤ ነገ ለአዲስ ጦርነት የሚውሉ ልጆችን እንድትወልጂ ቢጠይቁሽ፣ መልስሽ አንድ ብቻ ይሁን፡፡ እምቢ!
ምክንያቱም እናቶች፣ ሌሎቻችሁም ጭምር፣ እምቢ ካላላችሁ!
መርከቦች በወደቦቻቸው ላይ ተገትረው ይዝጋሉ፡፡ ባቡሮች ሽቦዎቻቸውና ፉርጎዎቻቸው እንደ አጥንት ገጦ ይወጣል፡፡ ጣራዎቻቸውም ይበሰብሳሉ፡፡ ቤቶቻችሁ ኦና ሆነው በሸረሪቶች ይሞላሉ፡፡ በሌማታችሁ ያለው እንጀራ አረንጓዴ እስኪሆን ድረስ ይሻግታል፡፡ አዝመራው ባለበት ይመክናል፡፡ ከብቶቻችሁ አራት እግሮቻቸውን ወደ ሰማይ አንጨፍረው ያሸልባሉ፡፡ መሬቶቻችሁ በዳዋ ይዋጣሉ፡፡ ባህርና ወንዞቻችሁ በሬሳ ይሞላሉ፡፡ አሳዎች ይጠረቃሉ፡፡ ውሃዎች ይቀረናሉ፡፡
የልጆቻችሁ ስጋ በየሜዳው አንጀታቸው ተዘርግፎ፣ አናታቸው ተበሳስቶ ለጥምብ አንሳዎች እንኳን ጠምብተው፣ ጅቦች ይፀየፏቸዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን፣ በመስጊድ ፍርስራሾች እምነታችሁ ይቀበራል፡፡ ደም ብታነቡ፣ በሲቃ ብትንሰቀሰቁ፣ ለምን ብትሉ ሰሚ አይኖራችሁም፡፡ ጩኸታችሁ የመጨረሻው የእንሰሳ፣ የሰው እንሰሳ፣ ጩኸት ሆኖ ይቀራል፡፡
አትጠራጠሩ ይህ ሁሉ ይሆናል፡፡ ነገ፣ ምናልባት ዛሬ፣ ዛሬ ምሽት ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ እምቢ! ካላላችሁ፡፡

Read 255 times