Thursday, 30 January 2025 00:00

ከአድማስ ትውስታ ፤ 1992

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

“እኔ ማን ነኝ?”

 

አንድ ጥንታዊ የቻይና ፈላስፋ ሁልጊዜም የሚያስደነግጠኝን እውነት ነግሮኛል፡፡ “ሰባ - ሰማንያ ዓመት እንኖር ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላዩ በእንቅልፍ የሚያልፍ ጊዜ ነው፡፡ ከቀሪው፣ አንድ - ሦስት ዓመቱ ጨርሶ በሌሎች ምህረት ስር ያለ፣ በሽንት የተጨማለቀ ህፃን ሆነን ያልፋል፡፡ አንድ - አስር ዓመቱ የሚበጅ - የሚከፋውን የማያውቅ ጥገኛ ሆነን ያልፋል፡፡ አንድ - ስምንት ዓመቱን አቅመ - ደካማ፣ እርዳታ ፈላጊ፣ ምስኪን ሆነን እናሳልፋዋለን፡፡ ቀሪው እንግዲህ ከህፃን ያልተሻለ የጃጀ ሽማግሌ የምንሆንበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ የተረፉት ጊዜያት በፍርሃት፣ በህመም፣ ጥቂቱ በጭንቀትና ውጥረት፣ በስካር፣ የማይረባ ተራ ነገር በማሰብ በከንቱ ያልፋል፡፡ እና መቼ ነው የኖርነው?!”
እርግጥ ነው፣ ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች ከፊሎቹ የህይወት ሀቅ ናቸው፡፡ ህይወትን ከነዚህ ውጪ ማሰብ አይቻልም፡፡ ግን መኖር መከራ እንዲሆንብን አንፈልግም፡፡ ህይወታችን አስደሳች፣ ኑሮአችን ምቾት ያልራቀው ቢሆን ነው ምርጫችን፡፡ ግን ህይወት፣ የጥረት ውጤት እንጂ ፀጋ አይደለም፡፡ አመርቂ ውጤት በሚያስገኝ መንገድ ለመጣር ደግሞ ማወቅ፡፡ ከመጅ - ወደ “ባቡር ወፍጮ” የወሰደን፣ በጣት ነክቶ የልብን ማድረስ ያስቻለን ሳይንስና ምርምር ነው፡፡ ለዚህ ነው እውቀት - ደህንነት /Security/ ነው የሚሉት፡፡
በደፋ - ቀና የሚጠፋው ጊዜ እየቀነሰ ለደስታና ለመዝናናት የሚውለው ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድ ይመስላል ጥረቱ፡፡ አልያም ብዙ ለመስራት - በዚያም ለመደሰት፡፡ ይሁንና ደስታ እውቀት (ትምህርት) ትፈልጋለች፡፡ ስለዚህ እንማራለን፡፡ መስራት እንችላለን፡፡ በመስራታችን እንደሰታለን፡፡ ይኸው ነው፡፡ ታዲያ እዚህ ላይ ደፋር ጥያቄ ላንሳ፡፡ “እውን ’ትምህርት’ ለደስታ አብቅቶናል?” የሚል፡፡ ደፋር ያልኩት፣ ለመመለስ ብርቱ ጥረትና ወኔ የሚጠይቁ ጉዳዮችን ስለሚያስታቅፈን ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ እውነተኛ ባለቤቶች ‘እዚህና አሁን’ ላይኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን እነሱን የሚፈጥረው ይኸው ተራ ሙከራ እንደሆነ እናያለን፡፡ በካሳ ተሰማ ስንኞች ድልድይነት ወደፊት እንሂድ፡፡
ኧረ-ባቲ- ባቲ…..
ግብዣዬን ስጨርስ የእንግድነቴን፣
ስጠግብ ግን ሂያጅ ነኝ ትቼ ስጋዬን ….አለ፡፡
ግን ወዴት?!!! “ፀጥ በሉ አደብ ግዙ፣…” ይሆን መልሱ፤ “እንጃ! ማን አውቆ” ነው፣ እውነቱን?
እነዚህ ናቸው፤ የሰው ልጅ ከባድ ፈተናዎች - ጥያቄዎች፡፡ ይኸን በሆነ መንገድ ሳይመልሱ መኖር አይቻልም፡፡ ደስታም ከነዚህ ጥያቄዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ ጥያቄዎቹን ለመመለስ እንማራለን /መደበኛ የሆነም - ያልሆነም ትምህርት/፡፡ እና “እውን ’ዕውቀት’ ወይም ትምህርት ለደስታ አብቅቶናል?” ስንል፣ የምንማረው ትምህርት ግቡ ያደረገ ምንን ነው? ማለታችን ነው፡፡ ያለፍንበት ትምህርት ይዘቱ፣ የማስተማር ዘዴው፣ ድርጅቱ፣ ያለው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ ምን መልክ አለው? እያልን ነው፡፡
ትምህርት ተብሎ ቀርቦ፣ ሰው ከመሆን የመነጨውን የተማሪውን እውነተኛ ፍላጎት ለመመለስ የማይችል መሆን የለበትም፡፡ ይህም ማለት፣ ተማሪውን የራበው ምንድነው? ጨጓራው ሊፈጨው የሚችለው ምንድነው? የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አለን ብሉም የተባለ አሜሪካዊ ምሁር፤ “የእያንዳንዱን ትውልድ ልዩ ባህርይና ፍላጎት በውል ማወቅ የሚቻለው ሰው የተባለው ፍጡር ሁሉ አትኩሮ የሚይዛቸውንና የያዛቸውን ጥያቄዎች፣ ያ - ትውልድ እንዴት እንደሚመለከታቸው በመመርመር ነው” ይላሉ፡፡
እኒሁ ምሁር እንደሚሉት፣ አንድ የተወሰነ ትውልድ ቋሚና ዘላቂ ለሆኑት የሰው ልጅ ፍላጎቶች ያለውን አመለካከት ለማወቅ፤ የትውልዱ ምርጫ ምን እንደ ሆነ እንዲሁም የሚያስደስተው፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚያናድደው ነገር ምን እንደሆነ ማጤን አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ “አስተምራለሁ ባይ” የተማሪውን /የቀጣዩን ትውልድ/ ፍላጎት ማወቅ ተገቢ እንደሆነ ይታየዋል፡፡ እንደዚያ ካደረገ፤ እውነትም አስተማሪነቱን፣ መሪነቱን /Guide/ በወጉ ይዟል ማለት ነው፡፡
“የሰው ልጅ ተፈጥሮ እንዲህ ነው” ብለን የያዝነው ሀሳብ ካለ የትምህርት ግቡ ያን ተፈጥሮውን በምላት እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ (ፍላጎት) እንዲህ ነው ለማለት ውስብስብ የአስተሳሰብ ሂደት አይታለፍም፡፡ እዛው ከተማሪው አይን ላይ ተቀምጠው ይታያሉ፡፡
ሰው የሚሻሻል ፍጡር ነው፡፡ ስለዚህ ከየትኛውም ደረጃ አንስቶ ብቃትና ምላት ከምንለው ደረጃ ማድረስ ይቻላል፡፡ ትምህርት ግቡ ይህ ነው፡፡ አንድን ሰው ለዚህ ማብቃት ለመምህሩ ደስታን ያጎናፅፈዋል፡፡ ከሌሎች ሞራላዊ ግዴታዎች ይልቅ፣ መምህር ለስራው የሚኖረው ትጋትና ሽልማት የሚመጣው ከዚህ እንደሆነ አለን ብሉም ይናገራሉ፡፡ ሰው ሊሆነው የሚገባውና እውነተኛ ተፈጥሮው ከታወቀ በኋላ በአካባቢው ያሉት አቀንጨራ ነገሮች “ሰውነቱን” እንዳያመክኑት፤ ተፈጥሮውን በሚያበላሽ ልማድና እምነት ታፍኖ እንዳይቀር ማገዝ ነው፣ የመምህሩ ስራ፡፡ መምህሩ የስራውን ሂደትና የተማሪውን ውጤት ለመመዘን የሚችለው ወደዚህ ግብ ለመቅረብና ለመድረስ መቻሉን እየተመለከተ ነው፡፡
ተማሪው “እኔ ማነኝ?” የሚለውን የሰው ዘር ጥያቄ ለመመለስ እንዲችል ጥረቱን የሚመራበት፣ ውጤቱን የሚፈትንበት መመዘኛዎች እንዲጨብጥ ማስቻል ነው - ትምህርት፡፡ እና የእኛ ትምህርት ለዚህ የሚያበቃን ነው?
ልማድ ሆኖ ይመስለኛል፤ “የተማሩ” የሚለው ቃል የሚውለው በዘመናዊው ትምህርት ውስጥ ላለፉት ብቻ ነው፡፡ የሀገራችን የተማሩ ሰዎች ሁለት አይነት የህሊና ጓዝ አላቸው፡፡ አንደኛው፣ አገር በቀል ሊባል የሚችል ነው፣ ከባህል፣ ከወግ፣ ከትውፊት የተገኘ ዕውቀት አላቸው፡፡ ሌላው ከዘመናዊው ትምህርት የተገኘ ሀሳብና አስተሳሰብ ነው፡፡
የዘመናዊው ትምህርት ውጤት የሆነው ትውልድ፣ ወደደም - ጠላ ከነባሩ “እውነት”፣ አስተሳሰብ፣ ወግ፣ ትውፊት ተራርቋል፡፡ የፀቡ ደረጃ ከአንዱ ወደ አንዱ ስንሄድ ሊለያይ ይችላል፡፡ በከፍተኛ የትምህር ተቋማት ውስጥ ያሉትን /ያለፉትን/ ሁሉ ስናስተውል፣ “በፍላጎታቸውም” ሆነ “በግባቸው” እያደር “ከውጭ ሰው” ጋ አንድ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ እርስ በእርሳቸውም እንደ መንትያ የተመሳሰሉ ናቸው፡፡ በአስተሳሰብ፣ በዓመል፣ በአለባበስ ያፈነገጠ ሰው መመልከት ከተዓምር እኩል ድንቅ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ የአኗኗር ዘይቤያቸው፣ ተስፋቸው፣ ምኞታቸው፣ አረማመዳቸውና፣ አሳሳላቸው /ለጉንፋን/ ምናልባትም፡፡ ህልምና ቅዠታቸው ሁሉ አንድ ይመስለኛል፡፡ እንደ መንትያ ይመሳሰላሉ፡፡
ተቀባይነት ያለው የእውነት መመርመሪያ ዋነኛ መሳሪያ ማስተንተን /Reason/ ነው፡፡ በየመስኩ የያዝነው ስራ መቃኛው ይህ ነው፡፡ ታዲያ የዘመናዊው ትምህርት ማዕከል / The home of Reason/ በዚህ አስተሳሰብ የታነፀ ሰው መፍራቱን የሚያጠራጥር ነገር ይገጥመኛል፡፡ ይህ ክፉ ውድቀት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን “ሆ! ብሎ የሚመጣን” ስሜት እየመረመሩ፣ በማስተንተን (Reason) ጎዳና እንዲሄድ ማድረግ ይሳናቸዋል፡፡ እንዲያውም ደንታቢስነት ሲከፋም ስህተቱን ማጠየምና መቀባባት የማይቀፈው ሰው የሚያፈሩ ናቸው፡፡
ወላጆች እንደ ቀድሞው በልጆቻቸው አስተሳሰብ ምርጫ፣ እሴት /Value/ ላይ “የህግም” ሆነ የሥነ - ምግባር ስልጣን የላቸውም፡፡ የልጆቻቸው - መምህሮች ለመሆን የሚያስችል በራስ የመተማመን ስሜት የላቸውም፡፡ ወልደው ያሳደጓቸው ልጆቻቸው የያዙት ስነ - ምግባር በምሁራዊ ክነት /Virtual/ ከእነሱ እንደሚሻል አምነዋል፡፡ ወይም ለማመን ተገደዋል፡፡ “በተራማጅነት” የሚያምኑ ልጆች “አፍርተዋል”፡፡ እንደ ብዙዎቹ፣ ተራማጅነት ከቀድሞው ዘመን ጋር የተያያዘውን፣ የወላጆቻቸውን ነገር ሁሉ ዝቅተኛና አስፀያፊ አድርጎ ማየት ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ውጤት ገና ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ እናም ወላጆች ለመጪው ዘመን መድኃኒት እሚሆን ነገር የላቸውም፡፡ መጪው - የልጆቻቸው የስልጣን ክልል ነው፡፡ ወላጆች የልጆቻቸውን አካባቢ /Environment/ ይዘትና መልክ መቆጣጠር የማይችሉና ለመቆጣጠርም ፍላጎት የሌላቸው ሆነዋል፡፡ እርግጥ በዚህ ዘመን ከሌሎች ተፅዕኖ የራቀ የግል አካባቢ /ቤታችንም - ቲቪና ሬዲዮ… አለ/ ይኖረናል ለማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን የሚገጥሙንን ሁኔታዎችና የምንሰማቸውን ሀሳቦች በመመዘን ለመምረጥ የሚስችል ሃሳብ ሊኖረን ይገባል፡፡ ችግሩም ይኽን ለማድረግ የሚያስችል የህሊና ሚዛን አለመያዛችን ነው፡፡ ትምህርት ለዚህ የሚያበቃ ጥሪት ካላስያዘን ትምህርት አይደለም፡፡ ግልፅ የኑሮ መመሪያና በተጠየቅ የተገዛ አመለካከት ከሌለን አልተማርንም፡፡ ደስታ የለንም፡፡
ትምህርት ከህይወት ተነጥሎ የሚያዝ የወግ ዕቃ መስሎ የሚታይበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ሀሳብን በነሲቡ መቀበል ትምህርት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሀሳብን ሸምቶ እንጂ አርሶ የሚያፈራ ሰው ለመሆን አልቻልንም፡፡ በእንዲህ ያለ “ምሁርነት” ላይ ልብ-ነጠቅ (Prejudice) አስተያየት የሚያሳፍር ሲሆን፣ ትምክህትና ግብዝነት ሲታከልበት ይበልጥ ያሳዝናል፡፡
በአፋችን የምናከብረውን ሃሳብ በድርጊታችን የምንጠየፈው፣ እንዲያውም ቅራኔው የማይታየንና ለመፍትሄ የማያነሳሳን መሆኑ ብዙ ጊዜ የሚታይ እውነት ነው፡፡ አንዳንዴ ሙከራ የሚያደርጉ ሰዎች ካሉ “በ5 ሳንቲም የሚሸመት መፍትሄ” የሚፈልጉ ይሆናል፡፡ ከምውት መፅሐፍ ስለ ህያዊት - የህይወት መልስ ማደንም ጎጂ ጎን አለው፡፡ እና ችግሩ በገጠመን ጊዜ የዴል ካርኒጌን መፅሐፍ ሳብ ማድረግ ለውጥ አያመጣም፡፡ የተደራጀ የህይወት አመለካከት - ፍልስፍና ለመያዝ መማር ያስፈልጋል፡፡ ይህም የአንድ ጀንበር ሥራ ሳይሆን በረጅም ያልተቋረጠ ጥረት የሚፈጠር ነው፡፡ በሚያውቁት ጥቂት ነገር የማያውቁትን ብዙ ነገር ለማወቅ መጣር ትዕግስት ይጠይቃል፡፡ ግን ይቻላል፡፡ “ለማወቅ እንደ መጣጣር የሚያስደስት ነገር የለም” ብሎ ይሆን አርስቶትል?
***
አስተማሪ - “አቡሽ መሬት ቅርጽዋ
እንዴት ያለ ነው?”
አቡሽ - “ድቡልቡል ነዋ ቲቸር”
አስተማሪ - “ድቡልቡል መሆንዋን
እንዴት አወቅክ?”
አቡሽ - “ምን አጨቃጨቀኝ፣ እሺ
አራት ማዕዘን ነች፡፡”

 

Read 434 times