Tuesday, 28 January 2025 20:13

የአምባሰሏ አምባሰል - አርቲስት ማሪቱ ለገሰ

Written by  በባንቺዐየሁ አሰፋ
Rate this item
(1 Vote)

 

ይህ ፅሑፍ የባለሙያዎች ሀሳብ የገባበት ቢሆንም፣ ሙሉ ሀሳቡ የባለሙያ ሳይሆን የግል ስሜት ነው።
አምባሰልን ስለምታኽለዋ አምባሰል።
የለም አትነካኩት አምባሰል ያለሷ ሲነካ ያመዋል የሚል ይመስለኛል አምባሰል ራሱ፡፡ በእርሷዉ ተጀምሮ በእርሷዉ ቢቀር መልካም ነው ይላሉ፤ የሙዚቃ ባለሙያዎችም፡፡  አዎ እርሷ በአምባሰል ላይ በገዛ ስልጣኗ ተሹማ ነግሳበታለች፡፡ የእርሷ ጉሮሮ በቅኝት የተሸበበ አይደለም፡፡ እንደ ሀገሯ መንገድ ልክ እንደ ሀረጎ ታጥፎ የሚዘረጋ፣ ነፍስን ሰቅዞ የሚያቅበጠብጥ ድምጽን ታድላዋለች፡፡  የአምባሰሏ ንግስት አርቲስት ማሪቱ ለገሰ። ትለዋለችም አምባሰልን፦
ከደም ተቀላቅሎ ካንጀት የሚያማስል
ያ የመንፈሴ ጥንስስ የኑሮዬ አክሊል
የልቤ ቅኝቱ ተገኝቷል ከአምባሰል
ማርዬ የጥበብ ሥረ መሰረት፣ የኢትዮጵያ ተምሳሌትና መገለጫ በሆነችው ወሎ  ተወልዳ በወሎኛ የምታዜም፣ በኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የምትወስድ አንጋፋ የሙዚቃ ሰው ነች፡፡ ሙዚቃ በሰው ልጆች ዘንዳ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ሲሆን፤ እርሷ ደግሞ ለሙዚቃ ተሰጥታዋለች፡፡ አምባሰል ቅኝት መናገሻዋ ቢሆንም ቀሪ ሦስቱ የኢትዮጵያ (የወሎ) ቅኝቶች ትዝታ፣ አንቺ ሆዬና ባቲንም ስታዜም አጃኢብ ታሰኛለች። ዳሩ ቅኝትን እየጠጡ ጠንስሰዋት ቅኝት ሆና ብታድግ ያአጅባል ወይ ጃል?
እኔም
አንችሆዬ ባቲ አምባሰል አምባሳል
አነሳሳሻለሁ ትዝታሽ ነው መሰል
እያልኩ እወርዳለሁ። ለምን? ናፋቂ አካሄዱ በተመልካች ዘንዳ በክፉ ትዝብት ውስጥ አይጥለውምና ነው።
ሲራራ ነጋዴ ተሆነ አባትህ
ማተብ ስደድልኝ ድምብል ጨምረህ
የሲራራ ነጋዴ ምርቱን  ሸጦ ለመመለስ የሚወጣውን አቀበት ቁልቁለት ማሪቱ፣ በአምባሰል ቅኝት ላይ አቀበቱን ሽቅብ እየወጣች ቁልቁል ተዳፋቱን እያረገደች ድካሙን አሳይታናለች፡፡ ለዚህም ይመስላል አምባሰል ያለ እርሷ ሲነካ የሚያመው።
ማሪቱ ለገሰ ወደ ሙዚቃ ባትመጣ አንጋፋው የወሎ ቕኝት አምባሰል ባልገነነ ነበር፡፡ ማርዬ ወሎ ምድር  ያሉ ቦታዎችን እየጠራች አንድ በአንድ እንዲታወቁ ባይሆን ነበር፡፡ ከንጉሱ የክተት አዋጅ በላይ ወረኢሉ በማሪቱ ገናለች፡፡ ከውጫሌው ስምምነት የገዘፈ በማሪቱ ውጫሌ ህይወት አግኝታለች፡፡ ሀውሳስ ያለ ማሪቱ ማን አላት።
ሀውሳ ዝናብ አይጥል ያበቅላል በመስኖ
ታየኝ አካላትህ ጃምዮ እሸት መስሎ
ያለች እንደሆነ ሀውሳ ማርና ወተት በመስኖ አጠጥታ ያበቀለችው ተክለ ሰውነት፣ እንደ ጃምዮ እሸት ከንበል ደፋ ሲል ዓይኗን ከመንገዷ አንስታ እሱ ላይ ብትጥል፣ ስንቷ ጉብል እንቅፋት መቷት በአውራ ጣቷ ትዝታን ይዛ ቀርታ ይሆን? ቦረናስ ብንጓዝ ያ የጎበዝ አለቃ አሊ በለው ስሙ ባይራኳ ጀብዱ ከመንደር ወጥቶ በአደባባይ በማን ጣይ ሞቀው። የቦረና ሽመል የጎበዞች ክናድ የደፋሮች ቀየ ነው። ቦረና ጤፍ አስረግጦ እንደጨረሰ ሞፈሩን ነቅሎ ቁመህ ጠብቀኝ ያደርገዋል። ማን ጠያቂ አለበት። ማርየም ብትሆን
ሸጌ የዱላው ‘ለት የፈራህ እንደሆን
ሸጌ የጠቡ ‘ለት የፈራህ እንደሆን
እንኳን ከንፈር ወዳጅ ጎረቤትም አንሆን
ትለው የለም እንዴ ኧ?
ይኸንን የሚያውቅ የቦረና ጎበዝ
ሸጌ ሽመልህን (ሽመል ረዥም ቀጥ ያለ በትር)
ማን አልከው ስሙን
ብሎ አይደል ወይ ለዱላው ሳይቀር የሚዘፍንለት።
ማሪቱ ለገሰ ስም ከአነባት የተዋደዱላት፣ ውዴታውም በግብር የተገለጠላት ገምሻራ ኪነተኛ ነች።
ገምሻራየዋዬ ከወንዝ ወዳ ማዶ ርቃ ቆይታ ለዛየራ በመጣች ጊዜ፣ የመጀመሪያ የአልበም ሥራዋን  ከሰራላት የወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን መሥራች አባል አርቲስት ዳምጤ መኮነን (ባቢ) ጋር ባደረግነው ቆይታ፤ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ማርዬ ባትኖር ኖሮ፣ የባህል ሙዚቃችን የሚጎድለው ታላቅ ነገር ነው ብሎኝ ነበር።
ማሪቱ አንችሆዬ ለእኔ አንችሆዬው ለእርሱ እያለች ከሙዚቃ የደራ ወግና ጨዋታ ስለምትይዝ፣ በአንችሆዬ ቅኝት አንጀት በሚሰረስር ዜማ እንዳሻት ተቦላክታበታለች፡፡
በትዝታ ባህር ተሆድህ ሰጥሜ
ስጋዬን ጨርሼ ቀርቻለሁ ባጥሜ››
በትዝታ ፈረስ ቼ በለው እያለች፣ እንኳን የናፈቀን ሆደ ቡቡ ቀርቶ ቀልበደረቁንም በናፍቆት ወዝ ሽው አርጋ አለዝባ  ሽምጥ አስጋለባዋለች፡፡ ያኔ ቀልቡ በድርቅና ሲንጓጓ ሲመናተል የነበረ ሁሉ ለአንድ አፍታ እህህ የሚልበት ጥሞና ይታደለዋል። እንደ ማሪቱ ያለ ድምጽ በቅኝቶች ወርድና ቁመና ተለክቶ የተሰጠው ሙዚቀኛ፣ አልፎ ሂያጅ ውሃ ቀጅ ሁላ ሳይሆን በዘመን ሂደት ውስጥ ለአንዴ ጣል የሚደረግ የህይወት ስጦታ ነው ይላል፤ ገጣሚና የህግ ባለሙያ መንግስቱ ዘገዬ።
ይህ ማለት የእርሷን ቅኝት ተቀኙ ብሎ ሌሎችን ማዘዝ ሱሪ በአንገት ይሆናል ነው ነገሩ። የሙዚቃ ቅኝት በዘፋኞች ጉሮሮ ውስጥ ገብቶ እንደጓል ሲፈራርስ ይስተዋላል፡፡  በማርዬ ግን ውልፍት የለም፤ እንደልቧ ትገማሸርበታለች፡፡  ዳምጤ መኮነን (ባቢ)ም ዛሬም እንደጥንቱ  ድምጸ ደንግል መሆኗ የተፈጥሮ ፀጋ እንደሆነ ያነሳል።
አድሮ መሸት አድሮ መብሰል፣ አድሮ እንደወይን ጠጅ መጣፈጥ፣ እንደግ አዝመራ መጎምራት ለድምፅም የተሰጠ መሆኑ ነው።
‹‹ኣረ ባቲ ባቲ ባቲ ገንደላዩ
ሀድራህ የሚመጣው ደራርበው ቲተኙ
እኔ ምንቸገረኝ ያልሰማ ቢያየው
ያንተ መቆያህ ነው ባቴ ላይ ያለው››  እያለች ሙሀባ እንደ ጋቢ ታጥፎ ሲለበስ ሰሙ ባልተገለጠ  እና ወርቁ በተለበጠ ቅኔ የወዳጇን ቀልብ የሳበውን የባቲን ( የባቷን ) ውበት ትነግረናለች፤ የማርዬ ገፀ ሰብ፡፡ ሀድራ ያለ ሙቀት ከወየት አባቱ አያስብል ታዲያ። ከወዳጅ ወዳ በባት ላይ እርስት ማንም የለውም እቴ።
ባለቅኔም አይደለች ትቀጥልና፤
የኔ ባቴን መስጠት ካስገረማትማ
ያቺ መዘዘኛ ትጠብቅ ቁማ
ትለዋለች።
ይህች እስቲ ጠይቃቸው ሸህ እንድሪስን
በኒካ ላይ ኒካ ይቻል እንደሆን
ብላ እንደጠየቀችው የሀገሬው ዘፋኝ ናት። በወዳጅ ላይ እንደተተከለ ዓይን መዘዘኛ የለም። ይመጣል እያለች ቆማ ትቅር እንጂ ማን ይሰማታል ነው ነገሩ።
ማሪቱ ቅኝት ብቻ አይደለችም፡፡ የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ብቻም አይደለችም፡፡ እርሷ ቋንቋም ናት፡፡ የወሎ ብቻ የሆኑት ወሎኛ ቃላቶች በሙሉ ክብር በማሪቱ ሙዚቃዎች ውስጥ ያለአንዳች መቀየጥ እንደወረዱ ጣፋጭ በሆነ ለዛ ተዚመው ለዘለዓለም ተቀምጠዋል፡፡  
እቴ ምንሽነው?
ወገቤን ነው የጅሩን ጎዳና የመሰለው
እቴ ምንሽን ነው ?
አንገቴን ነው ጠጅ የተሞላበት የመሰለው
እቴ ምንሽን ነው?
ያው ጉንጬን ነው የትርማን ትርንጎ የመሰለው
እቴ ምንሽን ነው?
ያው ዓይኔን ነው የብርን ጉልላት የመሰለው
የወገቧ ነገር ሲነሳ ሰው በሚያውቀው በዛ በቀጭኑ በጅሩ ጎዳና እየመሰለች ስትነግረው አውቋት ይጨርሳል። ያንገቷ መቃነት የማር ጠጅ በተሞላ ብርሌ ሲመሰል፣ የጠጅ ነገር የሚያውቅ ያውቀዋል። ብቻ ጠይቋት በሚገባችሁ ታስረዳችኋለች። መመሰል ቀላል ነው።
ምንም እንኳን የአምባሰል ንግስ ትባል እንጂ የእርሷ ንግስና በሁሉም የሙዚቃ ቅኝት ነዉ፡፡ ትዝታንስ ከርሷ ወዲያ ሲል የትዝታው ንጉስ ማህሙድ አህመድ ሳይቀር መስክሮላታል፡፡  የባቲ ንግስት ናትም የሚሉ አሉ፡፡ አንችሆየስ ያለእርሷም ትባላለች፤ ማሪቱ ለገሰ።
እኛ አዛውንቶቹ ያለፍነውን ነገር
ልጆቻችን ቢያዩት ምንኛ ደግ ነበር
ትላለች እሷም። ጊዜ እንደ ክፉ በቅሎ ወደ ኋላ የሚረግጣቸው ብዙ ህይወቶች አሉ። እርግጫው አጨራምቶ ስለሚጥላቸው ወደ ኋላ ሄዶ ለሚፈልጋቸውም ቢሆን እንደነበር አይገኙም። ማርዬ ይኸን ያለችው ለአራዳ ልጆች ነበር። አራዳና ህይወት። ህይወት ጊዜ ገጠመኝና አብሮነት ከቁስ በላይ በነበረ ጊዜ።
ይገማሸራል በልቤ የሀገር የወገን ናፍቆቱ፤ እንደ ግንደ ቆርቁር ሲሰረስራት ትዝታ የፊጥኝ ነፍሷን ሲያስራት ስለ ሀገሯና ስለ ወንዟ እህህም ትላለች፡፡ እኛም ስንናፍቅ እህህ አለን።
ብቻ፦
የአምባሰል ማር ቆራጭ ይወጣል በገመድ
አደራ ቢሰጡት ይበላል ወይ ዘመድ
እንዳለችው ውለታ ላለመርሳት እንጂ አውግቶ ለመጨረስ ለመፈከርም አይደለም። ለመጀመር’ኳ የሚበቃ አይደለም። ሆኖም ከነፍሴ ግድግዳ የተሰቀለችውን ጌጥ ዞር ብዬ እንዲህ ተመለከትኳት።

Read 154 times