Wednesday, 29 January 2025 00:00

ጭልጭል የምትለውን ብርሃን “እፍፍ!” ብሎ ማጥፋት

Written by  ዘነበ ወላ
Rate this item
(2 votes)

“ከአመጿ ጀርባ” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ኤደን ሐብታሙ፣ በአንድ ወቅት ለእረፍት ግሪክ ሄዳ መመለሷን ሰምቼ አጀብ ማለቴን አስታውሳለሁ። ከልብ አድንቄአለሁ፤ ተገርሜአለሁም። (ልብ አድርጉልኝ፤ በመጻሕፍት ሽያጭ ባህር ማዶ ሄዳ ተዝናናች አላልኩም) ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሞልቶለት፣ የመጻሕፍት ሽያጩ አበልጽጎት ለእረፍት ባህር ማዶ የተሻገረ አልገጠመኝም፤ ታላላቆቼም ከውነውት አላነበብኩም፤ ሲነገርም አልሰማሁም። ስለዚህ የኤደን ገጠመኝ ለእኔ የማይረሳም የሚያስደስትም ነው።
አንዴ በሆነ ጉዳይ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴ ተገኘሁ። አብሮኝ ነብሱን ይማረውና አንጋፋው አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ነበር። በአጋጣሚ ድምጻዊት ትግስት በቀለ መጥታ ጌችን ሰላም ትለዋለች።
“የት ጠፋሽ ?” ሲል ይጠይቃታል፤ ጉንጯን እየሳመ።
“ጋሼ ጌቾ እኔ እኮ አሁን የምኖረው ሮም ነው” አለች ዜማ በታከለበት ድምጽ። መንፈሳዊ ቅናቴን ቀሰቀሰችው፡፡ መቼ ይሆን ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሞልቶለት “እኔ እምኖረው ፍራንክፈርት ነው፣ ኒውዮርክ ነው ወዘተ” ... ሲል የምሰማው ? አልኩ በልቤ።
አውቃለሁ፤ ኢትዮጵያውያን ደራሲያን በአውሮፓም ሆነ በሰሜን አሜሪካ በስደተኝነትም በሥራ ምክንያትም ኖረዋል። እንዳልኩት ይህ ኑሮ በሌላ ምክንያት የተፈጠረ እንጂ የድርሰት ገቢያቸው እንደማይፈጥረው እገምታለሁ፡፡ ለምን ቢሉ፣ ራሱን መግለጽ የሚችል ፊደል ቢኖራቸውም አንባቢ ሊፈጥር ባለመቻሉ፤ ፊደሉም ባህር እንዲሻገር ባለመሆኑ፣ አሁንም ያለው ድህነትና ማጣት ውስጥ ነው።
ነብሱን ይማረውና ነገረ ፈጁ አቶ ዮሴፍ ገብረ እግዚአብሔር በጣም ጥሩ መጽሐፍ አንባቢ ነበር። ከታላላቆቹ ወንድሞቹ በፍጹም ማነስን አይፈቅድም፤ ወንድሞቹ ጋሼ ስብሐትም ሆነ ጋሼ ተወልደ ብርሃን ራሳቸውን ሆነው የወጡ ባለሙያዎች ናቸው። ዮሴፍም አንቱ የተባለ የህግ ባለሙያ ነው። አንዴ ሌሎች ጓደኞቻችን በተገኘንበት ዮሴፍና ስብሐት ሲወያዩ፤ “አንተ እኮ ነህ ደራሲ እንዳልሆን የከለከልከኝ” ይላል ዮሴፍ። ጋሼ ስብሐትም ካፉ ላይ ቀበል አድርጎ፤ “ከአንድ ቤተሰብ ሁለት ችስታ እንዳይፈጠር ብዬ ነው። ደራሲ ብትሆን ኖሮ ይህን ጊዜ ችስታ ትሆን ነበር !” ሲል መለሰለት፡፡
ጋሼ ማሞ ውድነህን “ለቁልቢ ገብርኤል ንግሱ ላይ አንደኛው መጽሐፍህን ይዘህ ብትሄድ ደህና አድርገህ ቸብችበኸው ትመለስ ነበር !” ሲል ወዳጅ መከራቸው። እርሳቸውም ምክሩን ተቀብለው የንግሱ እለት ለመገኘት ወደዚያው ዘለቁ። ምእመኑ ስርአተ ጸሎቱን አድርሶ ሲመለስ መንገድ ዳር አፋፍ ላይ ቆመው “የገባር ልጅ የተባለ መጽሐፍ ድንቅ ቁም ነገር ያለው፣ ዋጋው አንድ አንድ ብር” እያሉ ለፈፉ። እድለኛ ናቸው፤ ከዚያ ሁሉ ምእመን አንድ ሰው ብቻ አንድ መጽሐፍ ገዝቷቸው ፤ አንድ ብር ከፈላቸው። በበነጋው ተሸክመው ቁልቢ ያደረሱትን መጽሐፍ፣ ተሸክመው አዲስ አበባ ተመልሰዋል።
መጽሐፉን መጻፍ ብቻ ሳይሆን፤ ማሳተሚያው ራሱን የቻለ እራስ ምታት ነው፡፡ አንጋፋው ታሪክ ጸሐፊ ተክለጻድቅ መኩሪያ ለአንድ ሥራቸው ማሳተሚያ ጃንሆይ ገንዘብ እንዲረጥቧቸው ድሬዳዋ ዘለቁ ። ጃንሆይ ሁዳዴን የሚያሳልፉት ድሬዳዋ ነበር፡፡ ለዚህ ነው ተክለጻድቅ መኩሪያ ወደ ድሬ የሄዱት። ይሁን እንጂ ከጃንሆይ ጋር ተደባብረው ኖሯል፡፡ ቢሆንም ተክለጻድቅ የሚጨከኑባቸው አልመሰላቸውም ነበር። ይሁንና ጃንሆይ ፊት ነስተዋቸው ሲመለሱ፣ አብሮአቸው የዘለቁት ፕሮፌሰር ቀንቷቸው 5000 ብር ተፈቅዶላቸው መመለሳቸውን ያነበብኩት፣”የህይወት ታሪኬ” ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ ነው።
Black lion በሚል ርእስ ሞልቬር የ32 ኢትዮጵያዊያን ደራሲያን ህይወትና ሥራ ላይ የሚያጠነጥን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ አሳትሟል። ይህ መጽሐፍ በቅርቡ የአፍሪካ ሥነጽሁፍ ላይ ለጥራዝ በበቃ ኢንሳይክሎፒዲያ ውስጥ የኢትዮጵያን ገጽታ ለማሳየት ማለፊያ መስታወት ሆኗል። ደራሲው እንደሚያወጋን፤ ከላይ የጠቀስኳቸው 32 ደራሲያን በሙሉ የሚኖሩት አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ሁሉም የመንግሥት ሰራተኞች መሆናቸውን ደራሲው ይገልጻል። አንድም የሙሉ ጊዜ ደራሲ እንዳልገጠመው ያትትና፣ እንዳይምል አቤ ጉበኛ በዘመኑ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ለመሆን የጣረ፣ በድርሰት ሥራው በርካታ መከራን የተቀበለ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ሁሉም ደራሲያን ማለት ይቻላል ለመኖርና ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር የመንግሥት ሠራተኛ መሆን ነበረባቸው፡፡ በድርሰቶቻቸው ገቢ ብቻ ለመኖር የቻሉ ደራሲያን አልተገኙም፡፡
”አደፍርስ” የተሰኘው የዳኛቸው ወርቁ መጽሐፍን በተመለከተ በቅርቡ ጋሼ ሣህለ ሥላሴ እንዲህ ሲል አጫወተኝ፡- “የመጀመሪያው ህትመት ዋጋው 5 ብር ነበር። ዳኛቸው ሲያወጋኝ አንባቢያን ገዝተው አላነበቡትም፤ ስለዚህ 10 ብር አደረግሁት። አሁንም ሳያቸው አልሸመቱትም፤ ስለዚህ 15 ብር አድርጌዋለሁ” ብሎኝ እኔ ባለ አስራ አምስት ብሩን ከእርሱ ላይ ገዝቼ ነው ያነበብኩት፡፡”
ይህ ድርሰት በአሁኑ ጊዜ ዘመን አይሽሬ ፈጠራ ሆኖ በአገራችን ተጠቃሽ መጽሐፍ ነው። ሥራው እዚህ ዘንድ እንደሚደርስ ዳኛቸው ቢገምትም፤ ተደራሲያኑ የመጽሐፉን ትልቅነት ባለመረዳት በዚያን ዘመን እንደዋዛ ተላልፈዋል፡፡
መጻሕፍትን በተመለከተ አንድ ልብ የሚነካ ገጠመኝ አለኝ፡፡ ይህ ገጠመኜ ምን አልባትም የድፍን ኢትዮጵያን ህዝብ የምትወክል ሃሳብ ነች። ከአንድ ከሃያ ዓመት በፊት ነው፡፡ ጋሞ ተራራማው ምድር ላይ ሙዳ በምትባል ገበሬዎች መንደር፣ አጎቴ ሁዱጋ ወዜ ወጋ ጎጆ ውስጥ አንዱ መደብ ላይ በጀርባዬ ተኝቼ መጽሐፍ አነባለሁ። በወቅቱ 100 አመት ይሞላት የነበረች አክስቴ ፈንጠር ብላ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጣለች። እኔ እያነበብኩ ከመጽሐፉ ጋር ስሳሳቅ አክስቴ ወዘንቴ ወጋ ልብ ብላ አስተውላኝ፤ “ይህ የያዝከው ምንድነው ?” ስትል ጠየቀችኝ። መጽሐፍ ስታይ በህይወቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። የያዝኩት አልኩና በትህትና ዝግ ብዬ አስረዳኋት። በመገረም ስሜት ሆና አደመጠችኝ። ልክ እንደ አክስቴ መጽሐፍ ምን እንደሆነ የማያውቁ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ልብ በሉልኝ። መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ስል የቅንጦት ጉዳይ አይደለም የአስፈላጊነት፣ የአይን ገላጭነት ጉዳይ ነው። እሩቅ መመልከቻ መነጽር ነው። ምንም ሳያዩ እንደዋዛ ያለፉ በሚሊዮን የሚሰሉ ወገኖቻችንን እንደነበሩ እገምታለሁ። ...
ባለፉት ሦስት አስርት አመታት ሥራዬ ብለው ድርሰቱ ዓለም የከተሙ የሙሉ ጊዜ ደራሲያን መኖራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አንዳቸውም ራሳቸውን “የሙሉ ጊዜ ደራሲ ነኝ” ሲሉ አልሰማሁም። ህይወታቸውን ሳስተውል ግን ሁሉም ጊዜያቸውን ለድርሰት ስራ የሰጡ መሆኑን አምናለሁ። ትውስ ብለውኝ ከምጠቅሳቸው መካከል አለማየሁ ገላጋይ ፣ እንዳለጌታ ከበደ ፣ ታገል ሰይፉ ፣ በዕውቀቱ ሥዩም ፣ ኤፍሬም ሥዩም ፣ ደረጀ በላይነህ፣ ዳንኤል ወርቁ ፣ በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር-- እኔንም አክሉኝ። መጻሕፍትን ማንበብ፣ ማጥናትና መመርመር፤ አንድ እልባት ላይ ሲደርስ ለጥራዝ ማብቃት የተለመደ ተግባራችን ሆኗል፤ ይሁን እንጂ ይህ ባህል እንዳይቀጭጭ መንግሥት ከማበረታታት ይልቅ የሚያደናቅፍ ተግባር እየከወነ ነው። በ1990ዎቹ መጻሕፍት ከህትመታቸው ታክስ እንዲከፍሉ መንግሥት መደንገጉን ተከትሎ ብዙ ጩኸት ተሰማ፡፡ በወቅቱ የነበሩት ሹመኞች ጩኸቱን ሰምተው ይሁን በሌላ ምክንያት ወዲያው ውሳኔያቸውን አጠፉ፡፡ መጻሕፍት ከታክስ ነጻ ሆኑ፡፡ አሁን በአገራችን ወረቀት ይቀረጣል፡፡ ኬሚካል ይቀረጣል፡፡ ለመጻሕፍት ቫት ይቆረጣል፡፡ ነገሩ “ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ” እንዲሉት ቢሆንም፣ ጥረቱን ግን ሙሉ ለሙሉ አላደናቀፈውም።
ከግማሽ ምእተ አመት በፊት ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ “ዓለም የሠራተኞች ናት!” በሚል ስራቸው፤ “ማንኛውም ሰው የሚመገብበትን ማእድ ቤት በወጉ እንደሚያሰናዳ ሁሉ፣ የሚያስብበት ቤተ መጻሕፍት በቤቱ ውስጥ ሊኖረው ይገባል” ብለውን ነበር። ስንቶቹ ሰምተዋቸው ይሆን? ላለፉት ሃምሳ ዓመታት አገራችን አልተረጋጋችም፤ ሁሌም በመንከውከው ላይ ነን። ስለሆነም በቅርብ ጊዜ ታሪካችን እገሌ”የማሰቢያ ክፍል” አለው ለማለት አልደፍርም። ከአበው ትውልድ አቶ ሀዲስ አለማየሁ፣ ዶ/ር ተወልደ ብርሃን፣ አቶ ከበደ ቤኛ (ተመስገን ወርቁ እንዳጫወተኝ) ጸጋዬ ገብረ መድህን፣ አስፋው ዳምጤ፣ ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማሪያም፣ ራሳቸው ተቀዳሚ ኃይለ ሥላሴ-- በኖሩበት ሁሉ ማብሰልሰያ ክፍላቸው በምርጥ መጻሕፍት የተሞሉ ነበሩ።... ሌላ ትውስ የሚለኝ የለም፡፡
የመጻሕፍት መቀረጥና የወረቀት ዋጋ መወደድ የመጻሕፍት ዋጋን ያንረዋል። በዚህም አብዛኛው የህብረተሰባችን ክፍል ከንባብ ይገለላል፤ ንባብ የጥቂቶች የታደሉት ተግባር ብቻ ይሆናል። ይህ ደግሞ እንደ አገር ክፉኛ ይጎዳናል፡፡
ከ32 ዓመታት በፊት “ህይወት በባህር ውስጥ” የሚል መጽሐፌ ለህትመት በቅታ ነበር። እንደ ጀማሪ ደራሲ የማከፋፈሉንም ሆነ የመቸርቸሩን ሥራ የምሰራው ራሴ ነበርኩ፡፡ ድምጻዊት ብፅአት ሥዩም የሰፈሬ ቂርቆስ ልጅ ነች። በወቅቱ ምሽት ቤት ስለነበራት አንድ ሃያ ኮፒ ወስዳ እንድትሸጥልኝ ለመንኳት፡፡ እርሷም፤ “ዘነበ አትሳሳት፤ በዚህ ሥፍራ ቺፕስ ጠብሼ ባቀርብላቸው ስምንት ብር ገዝተው ይበላሉ፤ መጻሕፍትን ሳቀርብላቸው ግን ተወደደ ይላሉ!” ያለቺኝን ምንጊዜም ቢሆን አልረሳውም፡፡ መቼ ይሆን ለጭንቅላት ምግብ ትኩረት የምንሰጠው?
በሰላሙ ወቅት መቀሌ በመጻሕፍት ሸመታ አንደኛ ነበረች፤ በእነ መለስ ዜናዊ ዘመን መቀሌ ላይ በተካሄደ አንድ የመጻሕፍት አውድ ርእይ ላይ መጻሕፍት ነጋዴዎቹ መቀሌ ይዘው የገቡትን መጻሕፍት ሁሉ ቸብችበው በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን አውቃለሁ። አሁን መቀሌ ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት ከዚህ ድብርት እንደትወጣ ጦርነቱ እንደተጠናቀቀ አንድ የመጻሕፍት አውደ ርእይ እንዲዘጋጅ ያገባቸዋል ብዬ ያሰብኳቸውን ሁሉ አማክሬያለሁ። እስካሁን የተጨበጠ ውጤት ባላገኝም ጥረቴን አላቋርጥም፡፡ ትግራይ ውስጥ ከሚገኝ አማኑኤል ከተባለ ወዳጄ ጋር ተደዋውለን፣ እኔ እዚህ የማደርገው እንቅስቃሴ ከሰመረልኝ፣ እዚያ ያለውን እርሱ እንደሚጨርሰው ተነጋግረናል። ጥረቱ ቀጥሎ መልክ ቢይዝ ድብርቱን ገለል አድርገን፣ ያንን ወርቃማ ጊዜ በመቀሌ እንመልሰው ይሆን ስል አውጠነጥናለሁ፡፡
ከማተሚያ ቤቶች ጋር ከሦስት አስርት አመታት በላይ የዘለቀ ግንኙነት አለኝ። ከራሴም ሥራ በተጨማሪ ለጓደኞቼም ቢሆን በስልክ ‘ፕሮፎርማ’ እጠይቃለሁ። ይህ ማለት የአንድ አዲስ መጽሐፍ ህትመት አስፈላጊውን መረጃ ከሰጠኋቸው በኋላ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስከፍሉኝ መረጃ የምንለዋወጥበት ፎርም ነው። ሰሞኑን አንዱ መጽሐፌ”መልህቅ” የተጨማሪ እሴት ታክስ ታክሎበት ማተሚያ ቤት ገብቶ ስለነበር በአካል አንድ ሁለት ማተሚያ ቤቶችን ጎበኘሁ። ሥራቸው 50 በመቶ ቀንሶ ከመጻሕፍት ህትመት ይልቅ የብስኩትና የስጦታ እቃዎች መጠቅለያ ካርቶን ሲታተም አይቻለሁ።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አባል ባልሆንም በህብረት ሊያሰራን በሚችል ጉዳዮች ላይ እሳተፋለሁ። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት ውስጥ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተሳትፌያለሁ። ይህንኑ ችግር አስመልክቶም “ከፀሐይ በታች” በተባለው ዩቲዩቤ ላይ ሁለት ፕሮግራሞችን ሰርቻለሁ። የደራሲያን ማህበሩም የሚያደርገውን ጥረት እከታተላለሁ። የገረመኝ በተወካዮች ምክር ቤት ድምፅ ሰጥተናቸው የገቡት ደራሲያን ወዳጆቻችንን የበላው ጅብ አለመጮሁ ነው።
በርካታ ችግራችን ሥር የሰደደ ነው። ይህ አላዋቂነታች ግማሽ ምእተ አመት አስቆጥሯል። “ሪፎርም “ የሚሻትን አገር በጎረምሳ ወኔ “ስር ነቀል አብዮት!” ብለን አሁን በምንገኝበት አረንቋ ውስጥ አገራችንን ከተትናት፡፡ ሁሌም “ከድጡ ወደ ማጡ” እየሄድን ነው። ይህንን ችግር መቅረፊያው ማወቅ ነው። የማሳወቂያ ትልቁ መሳሪያ ደግሞ መጽሐፍ ነው። መጻሕፍትን ልክ እንደ መኳኳያ፣ አስካሪ መጠጥ ወዘተ ቁሶች ቀረጥ ውስጥ መዶል ድንቁርናውን ማባባስ አይሆንም? ጭልጭል የምትለውን ብርሃን “እፍፍ !” ብሎ ማጥፋት አይሆንም ?
አሁን በኮሪደር ልማት በተፈጠረው እንቅስቃሴ ከሃምሳ በላይ መጻሕፍት ነጋዴዎች መደብራቸው ፈርሶባቸው ከጨዋታ ወጥተዋል። እነዚህ መጻሕፍት ነጋዴዎች ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ ሜክሲኮ አደባባይና የድሮው ናዝሬት መኪና ተራ አካባቢ ይሰሩ የነበሩ ናቸው። በእኔ ግምት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት በመጋዘኖቻቸው፣ በየጓዳውና በየኩሽናው ውስጥ ተከማችተዋል፡፡ መጻሕፍትና ኬክ አንድ ናቸው፤ መጻሕፍት በወቅቱ መነበብ አለባቸው። ኬክም በትኩሱ ካልተበላ ይበላሻል። ይህ ልማት ምንም አማራጭ መፍትሄ ስላልሰጣቸው መጻሕፍቱ የመበላሸት አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡
በነገራችን ላይ መጻሕፍት ነጋዴ ሃሳብ ነው የሚያከፋፍለው። ሥጋ ነጋዴ ደግሞ ጮማ ከእነ ማጣፈጫው እነሆ ይለናል። አንድ የታወቀ ቁርጥ ቤት በቀን 2 ሚሊዮን ብር የተጣራ ሽያጭ እንደሚኖረው ይገመታል፡፡ በቀን ስምንት ሰንጋ ሊያጣራ ይችላል። ይህን ሽያጭ ወደ መጻሕፍት ብናመጣው በመላ አገሪቱ የሚገኙ መጻሕፍት ነጋዴዎች ዓመቱን ሙሉ ለፍተው አያገኙትም። በመጻሕፍት ንግድ አትደኸይም፤ የሚበላም ሆነ የሚጠጣ አታጣም፤ በምንም ተአምር ግን አትበለጽግም፡፡
አንድ ደራሲ አዲስ ስራ ይዞ ወደ ተደራሲያን ለመድረስ ሲያስብ፣ አራት ከተሞቻችን ላይ ኮሽ እንዳይል መጸለይ አለበት፤ ባህርዳር፣ አዲስ አበባ፣ መቀሌና አዋሳ ከተሞች ከፍተኛ መጻሕፍት አንባቢያን የሚገኙባቸው ናቸው፡፡ አንድ አይነት እክል በእነዚህ ከተሞች ላይ ቢከሰት የመጻሕፍት ገበያው ድርግም ብሎ ይዘጋል። ምንም አትጠራጠሩ፤ አዲስ መጽሐፍ ይዞ ወደ ገበያ የገባው ደራሲ፤ በፍጥነት የመጻሕፍቱን ደህንነት መጠበቅ የሚችልበትን ብልሃት መዘየድ አለበት። መጻሕፍቱ ቤቱ ወይም መጋዘን ውስጥ ስለሚከመሩ የንብረቱን ደህንነት ለመጠበቅ “በቀላሉ አይጥን መከላከል” የሚል መጽሐፍ ካጋጠመው ቶሎ አንብቦ የልፋቱን ፍሬ መጠበቅ አለበት።
ለምሳሌ የእኔን ሥራ “የምድራችን ጀግና”ን ላንሳ፡፡ ይህ መጽሐፍ ከህይወቴ 20 ዓመታትን ያህል ወስዶብኛል፡፡ በጽናት ሰርቼ ሳጠናቅቅ ብዙ መልካም ነገሮችን እንደምጠብቅ ልብ በሉልኝ። “ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” እንዲሉ፣ “አንቱ!” መባሉ ቀርቶብኝ ለህትመት ያወጣሁት 1,000, 000 ብር እሳት ላይ እንደወደቀ ቅቤ ቀልጦ ቀርቷል። ምክንያቱም የእርስ በርስ ጦርነት ትግራይ ላይ በመከሰቱ ሥራዬ ችግር ላይ ወደቀ። “አባ ከና?!” የሚለኝ አጣሁ። ይሁን እንጂ በዚያም ወቅት በመታተሜ ደስተኛ ነኝ ፤ ምክንያቱም አንዱ ግቤ ሞትን መቅደም ነበረና መጽሐፉ ዶ/ር ተወልደ ብርሃን በህይወት እያለ ታትሞ አይቶት ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተሰናበተው። “እየሳቁ ማልቀስ” ልንለው እንችላለን ። ስለዚህ በመጻሕፍት ሥራ ላይ የሚሰማራ ሰው፣ ሆደ ሰፊ ሆኖ ነው ወደ መስኩ መግባት ያለበት።
በቅርቡ “የግዞት ሠንሠለት” በሚል ርዕስ ለህትመት የበቃው የስሜነህ ባይፈርስ መጽሐፍ ጥሩ መረጃ ሰጪ ነው። የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን ፣ ሥነ ልቦናችንን ወዘተ በቅጡ አመላካች ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አንዷ ገጽ ላይ አቶ በረከት ስምኦን፤ “ ታክቶኛል ማረፍ እፈልጋለሁ !” ሲል ለአቶ መለስ ያዋያየዋል፤ “እያረፍክም አንብብ፤ ይህቺን አገር እስካሁን የመራናት በድንቁርና ነው !” ያሏቸውን ሃሳብ ምንጊዜም አስበዋለሁ።
Schindler List በሚል ርእስ የተሰራ አንድ ፊልም በቅርቡ አይቻለሁ። ታሪኩ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ባሉ ተጨፍጫፊዎች ላይ የሚያጠነጥን ነው። የካምፑ ሀላፊ አንድ ከፍ ያለ ስፍራ ላይ ሆኖ ኢላማ የገባለትን ተኩሶ ይገድላል። አንድም እኔን ባይ የሌለው ወገን ድፍት ይላል። ይህ ማን አለብኝ ባይ ጫጫታ ይሰማና ወረድ ብሎ ያያል። አንድ ጀርመናዊ ወታደርና አንዲት ይሁዲ ይጨቃጨቃሉ። ተጠግቷቸው፤ “ምን ሆናችሁ ?” ሲል ይጠይቃል፡፡
ይሁዲዊቷ ሴት፤ “እኔ ሲቪል ኢንጂነር ነኝ፤ ይህ ሰው እዚህ ጋ ቤት ሊሰራ አስቦ ቁፈራ እያካሄደ ነው። እኔ ደግሞ የሚሰራው ሥራ ሙያዬ ስለሆነ ሙያዊ ምክር ስሰጠው አልሰማም አለኝ !” ብላ አቤቱታዋን ታሰማለች። ልብ ብሎ ሲያደምጥ የነበረው ገዳይ ሰውዬ ወደ ጀርመኑ ወታደር ዞረና፤ “ውሰድና ግደላት!” አለው። ያም የታዘዘውን ፈጽሞ እንደመጣ “ቤቱን እርሷ እንዳለችህ ስራው !” ብሎት ወደ ግድያው ፊቱን አዞረ።
እኔ በትውልድ ተስፋ ቆርጬ አላውቅም። ጥቂት ቢሆኑም አስተዋይ የአዲሱ ትውልድ አባሎችን ሳይ እጽናናለሁ። ይሁን እንጂ አላዋቂነት ገዝፎ “እሷ እንዳለችህ ሥራው!” ዘንድ እንዳንደርስ እፈራለሁ።
ሰሞኑን “ልጅነት” የተሰኘው መጽሐፌን ቀደም ብሎ ያሳተመው አቶ መኮንን ፈንታው (ጦቢያ መጻሕፍት መደብር) ማለቁን ነገረኝና፤ “ተጨማሪ እሴት ታክስ ስለሚታከልበት ዋጋውን 500 አድርገህ ይታተም!” ብሎኝ ተስማምቻለሁ፡፡ “ዘጠኝ ሞት መጣ ቢሉት አንዱን ግባ በለው” ይሉት ቁርጥ ይህ ይሆን?! በነገራችን ላይ ከ17 ዓመታት በፊት “ልጅነት” ለመጀመሪያ ጊዜ ገበያ ላይ ሲውል ዋጋው 28 ብር ነበር!

Read 530 times