Saturday, 01 February 2025 10:40

ከ340 ሚ. ብር በላይ በጀት የወጣበት የእናቶችና የህፃናት የጤና ማዕከል ስራ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

በክፍለ ከተማው ብቸኛው የህክምና ማዕከል ነው ተብሏል


ከ340 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የወጣበትና ለእናቶችና ሕፃናት ሕክምና አመቺ እንዲሆን ተደርጎ በተሰራ የራሱ ባለ አምስት ወለል ሕንፃ ላይ የተደራጀው “ ማርህይወት  የእናቶችና የህፃናት ልዩ የህክምና ማዕከል ስራ ጀመረ። ባለፈው ሳምንት በይፋ የተመረቀው ይሄው የህክምና ማዕከል በልደታ ክፍለ ከተማ  በተለምዶ ሶስት ቁጥር ማዞሪያ በሚባለው ቦታ የሚገኝ ሲሆን፤ ለክፍለ ከተማው ብቸኛው የግል የእናቶችና ሕፃናት የሕክምና ማዕከል መሆኑ ተገልጿል።
ስራ ከጀመረበት ከጥቅምት ወር አንስቶ እስከተመረቀበት ዕለት ድረስ ለ700 ያህል ታካሚዎች አገልግሎት መስጠቱን የገለፁት ባለቤቶቹ፤  አሁንም በተመጣጣኝ የአገልግሎት ክፍያ፣ልምድ ባካበቱ ሐኪሞች፣ምቹ በሆነ ስፍራና የዘመኑ ቴክኖሎጂ ባፈራቸው  የህክምና መሳሪያዎች እየታገዘ እናቶችና ሕፃናትን ያገለግላል ብለዋል።
 በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ሪቫን በመቁረጥ የምረቃ ስነስርዓቱን ያከናወኑት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሐላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ ባደረጉት ንግግር  የህክምና ጉዳይ በተለይ የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ጉዳይ ለመንግሰት ብቻ የሚተው አለመሆኑን ገልፀው እንዲህ አይነት የግል ተቋማትም ዘርፉን በማገዝ በኩል ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት 10 ልምድ ያካበቱ ስፔሻሊስትና ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪሞችን  ጨምሮ ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ሐኪሞችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች በአጠቃላይ ለ90 ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል። ማዕከሉ በውስጡ እጅግ ዘመናዊ የቀዶ ህክምና ክፍሎች፣ እናቶችና ህፃናት ተኝተው የሚታከሙበት መደበኛና ቪአይ ፒ ክፍሎች፣ ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ ማሽን፣ የጨቅላ ሕፃናት ፅኑ ህሙማን (ICU) ን ጨምሮ እጅግ ዘመናዊ የአልትራ ሳውንድ፣ የራጅ እና የተሟላ ላብራቶሪን አደራጅቷል ተብሏል።
የመብራትና የውሃ መቆራረጥ በሕክምና ሒደቱ ላይ የሚፈጥረውን ጫና ግምት ውስጥ በማስገባት የራሱን የውሃ ጉድጓድ በመቆፈርና የሶላር ኢነርጅን በመጠቀም 24 ሰዓት ያለውሃና መብራት መቆራረጥ ስራውን ማከናወን የሚያስችለውን አቅም ስለመፍጠሩም ነው የማዕከሉ አመራሮች የተናገሩት። ማእከሉ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣትም በርካታ ተግባራትን  እያከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል  1 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ በማዕከሉ አካባቢ የሚገኘው ጥርጊያ መንገድ እንዲሰራ ማድረጉም ተጠቅሷል። በተጨማሪም በየዓመቱ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የህክምና አገልግሎት በአካባቢው ለሚገኙ አቅም ለሌላቸው እናቶችና ሕፃናት በነፃ ለመስጠት ብሎም በየሶስት ወሩ ሰራተኞቹን አመራሮቹንና በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የደም ልገሳ በማድረግ ማህበራዊ ሐላፊነቱን ለመወጣት ማቀዱን አስታውቋል። እስካሁንም ሶስት እናቶች ሙሉ ነፃ የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ማዕከሉ አስታውቋል።

Read 614 times