Saturday, 01 February 2025 10:43

ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ከፈተ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ  ለደንበኞቹ የሚሰጠውን ዘርፈ ብዙ የባንክ አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ እንዲሁም ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚረዳውን በአይነቱ  ልዩ  የሆነ የዲጅታል ባንኪንግ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉን  የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ  ዶ/ር ተስፋዬ ቦሩ ገልፀዋል፡፡ ይህ የዲጂታል  ባንኪንግ አገልግሎት መስጫ ማዕከል የ24 ሰዓት የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ እንደገለፁት ይህ የዲጂታል ባንኪንግ ማዕከል የባንክ ስራን የሚያቀላጥፉ  ቴክኖሎጂዎችን ስራ ላይ በማዋል እንዲሁም ብቃት ያለው የሰው ኃብትን በመፍጠር  ባንኩ ከምንጊዜውም በላይ ተወዳዳሪ እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር፣ የባለአክሲዮኖችን ጥቅም ከፍ በማድረግ የሀገርን ኢኮኖሚ የመደገፍ ስራውን በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል የራሱን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል ፡፡
የባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ ማዕከል  ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የባንክ ሂሳብ መክፈት፣ ገንዘብ ገቢና  ወጪ ማድረግ፣ ቀሪ ሂሳብና የሂሳብ መግለጫ ማሳየት፣ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን መመንዘር፣ የተለያዩ ክፍያዎችን መፈፀም፣ ያለ ኤቲኤም ካርድ አገልግሎት ማግኘት፣ ቼክ መመንዘርና ገቢ ማድረግን  ጨምሮ ደንበኞች የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት መጠቀም በሚፈልጉበት ወቅት በማዕከሉ በመገኘት ለዚሁ አገልግሎት በተዘጋጁ ታብሌቶች መጠቀም ይችላሉ፡፡
 በዚህ ብቻ ሳይወሰን ማዕከሉ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ክፍል ያለው ሲሆን ተቀዳሚ (corporate) ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው የቪዲዮ ባንኪንግ አገልግሎት ማገኝት የሚያስችላቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም በአዲስ አስተሳሰብ፣  አቀራረብና ብራንድ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ  እጅግ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው  በዘንድሮው አመትም ከታክስ በፊት  757.6 ሚሊዮን ብር በማትረፍ በከፍተኛ የእድገት ግስጋሴ ላይ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
ባንኩ ይህን ውጤት ማሳካት የቻለው ባሳለፈው አመት በቅርንጫፍ ማስፋፋት፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃብት ልማትና በወጪ አስተዳደር ሥርዓት ላይ በሰራው ዘርፈ ብዙ  ውጤታማ ሥራዎች መሆኑ ተገልጧል፡፡ ባንኩ በመላው ሃገሪቱ ተደራሽነቱን ለማስፋት በሰራው ስራ የቅርንጫፍ ብዛቱን  238  ያደረሰ ሲሆን በአሁን ሰአትም  ከ 1.7 ሚሊየን በላይ ደንበኞች እንዳሉት አሳውቋል፡፡
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ፤ ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን የባንክ ካፒታል ዕድገት ዝቅተኛ ጣሪያ በቀረው ጊዜ ውስጥ እንደሚያሳካ የገለፁት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ተስፋዬ ቦሩ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተረባርበው በጋራና በላቀ ቁርጠኝነት ለጋራ ሥኬት መስራት እንደሚገባ  አሳስበዋል፡፡
ባንኩ የገበያውን ተለዋዋጭነት በመረዳትና በዛው መሰረት የሚንቀሳቀስ የስራ አመራር በመገንባት እንዲሁም  ሀብት ለማሰባሰብ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ  የተቀማጭ ሂሳቡን   ከ 20.6 ቢሊዮን ብር በላይ  ያደረሰ ሲሆን፤  የባንኩ ጠቅላላ ሃብት ደግሞ  ከ 26.6 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱ ታውቋል ፡፡
በዚህ ብቻ ሳይወሰን ባንካችን  የያዘውን የዕድገትና የሥኬት ጉዞ በማስቀጠል ባለፈው አመት በግል ባንኮች ዘርፍ ባስመዘገበው የላቀ አፈፃፀም የአቢሲንያ አዋርድ የ2016 ዓ.ም የወርቅ ደረጃ የኢንደስትሪ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ባንኩ ‹‹ለጋራ ስኬታችን›› የሚለውን መሪ ቃል በተግባር መሬት ላይ በማውረድና ማህበራ ኃላፊነቱን በመወጣት በአካባቢ ጥበቃ ፤ በማህበራዊ ደህንነት፤ በሰብዓዊ እርዳታና በልማት ስራዎች አሻራውን ያሳረፈ ስኬታማ ባንክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሜክሲኮ አካባቢ  ለዋና መ/ቤት ግንባታ በተረከበው  5,550 ካ.ሜ ቦታ ላይ የወደፊት የዋና መ/ቤት ህንፃ ለመገንባት በሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ እየሰራ  እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 573 times