የማዕከላቱ ሕልውና ለአደጋ መጋለጡ ተገልጿል
የግብርና ምርምር ማዕከላት እና የእንስሳት ብዜት ተቋማት በከተማ አስተዳደሮች የመሬት ይዞታቸውን እየተነጠቁ መሆኑ የተገለፁ ሲሆን የኖራ አቅርቦት ችግር መከሰቱም ተመልክቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሰኞ ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 4ኛ ዓመት፣ አንደኛ ልዩ ስብሰባ፣ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል። በዚህ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ለ2017/ 18 የምርት ዘመን የሚያገለግል ማዳበሪያ በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት እየተሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም በ156 ቢሊዮን ብር በጀት ለመስኖ፣ ለመኸርና ለበልግ ልማት የሚውል 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት “እየተሰራ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ “ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጂቡቲ ደርሷል” ብለዋል። አያይዘውም፣ በተያዘው የበጀት ዓመት የምርት ዘመን፣ ማዳበሪያ ገዝቶ ለማቅረብ 84 ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉንም አንስተዋል።
በአማራ ክልል ስለቀረበው የማዳበሪያ መጠን ሲናገሩ፤ ከ7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለክልሉ ተላልፏል ብለዋል። “ይህም ክልሉ ሰላም በነበረበት ወቅት አግኝቶት የማያውቀው መጠን ነው” ብለዋል፡፡
ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ወደ አገር ውስጥ እየገባ መሆኑን በመግለፅም፤ በድጎማ እንዲተላለፍ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
አሲዳማ አፈር እንዲያገግም ለማድረግ በሚሰሩ ስራዎች ላይ የኖራ አስፈላጊነት የጎላ መሆኑን ያወሱት ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ ለዚሁ ስራ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት። ሆኖም ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኖራ አቅርቦት ችግር “ገጥሞታል” ብለዋል፣ ሚኒስትሩ። የአቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ ግብርና ሚኒስቴር ከገንዘብ ሚኒስቴር በመተባበር እየሰራ መሆኑንም ዶክተር ግርማ ገልጸዋል።
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለሚኒስትሩ ባቀረበው ጥያቄ፣ የግብርና ምርምር እና የእንስሳት ብዜት ተቋማት በከተማ አስተዳደሮች የመሬት ይዞታቸውን እየተነጠቁ እንደሚገኙ አንስተዋል። በዚህም ማዕከላቱ እና ተቋማቱ ሕልውናቸው ለአደጋ መጋለጡ ተጠቁሟል።
የሆለታ፣ ጂማ፣ ቁልምሳ እና ቢሾፍቱ ማዕከላትን ለአብነት የጠቀሰው ኮሚቴው፣ 312 ሄክታር የምርምር ስራ የሚሰሩባቸውን መሬቶች በየከተማ አስተዳደሮቹ እንደተነጠቁ አብራርቷል። ይህንንም በየጊዜው ባደረገው ምልከታ እና ተቋማቱ በሰጡት መረጃ ማረጋገጡን ገልጿል።
በተጨማሪም፣ በአማራ ክልል የወረዒሉ የግብርና ምርምር ተቋምን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦ ግንባታው አለመጀመሩን፣ ብሎም የደብረ ማርቆስ የግብርና ማዕከል በቂ የመሰረተ ልማት ግንባታ እንዳልተደረገለት ቋሚ ኮሚቴው አመልክቷል። በየማዕከላቱ የሚደረገው የግንባታ ሂደት ለምን እንደዘገየ አያያዞ ጥያቄውን ለሚኒስትሩ አቅርቧል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በምላሻቸው፣ “አብዛኛዎቹ የግብርና ምርምር ተቋማት የይዞታ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው ለረዥም ዓመታት ቆይተዋል” ብለዋል። እነዚሁ ማዕከላት የሚገኙባቸው ከተሞች የማስተር ፕላን ለውጥ በማድረጋቸው፣ የመሬት አጠቃቀም ለውጥ መደረጉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ዶክተር ግርማ የምርምር ተቋማቱ ስራዎቻቸውን ማዘመን እና ማሳደግ እንደሚገባቸው ያመለከቱ ሲሆን፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የይዞታ ንጥቂያውን ”ለጊዜያዊ ችግር መወጣጫነት” በማሰብ የሚከናወኑ ድርጊቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ሚኒስትሩ ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት እነማን እንደሆኑ በግልጽ አላብራሩም።
የምርምር ተቋማት የሚጠቀሙበትን መሬት የፌደራል መንግስት የመስጠትና የመቀማት ሃላፊነት እንደሌለው ያመለከቱት ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ ለየማዕከላቱ መሬት መስጠት የክልሎች ሃላፊነት በመሆኑ፣ ፓርላማው “ያግዘን” ሲሉ ተማጽነዋል፡፡
የወረዒሉ እና ደብረ ማርቆስ የግብርና ማዕከላትን በተመለከት የግንባታ አፈጻጸማቸውን ማሻሻል ያልተቻለው ከመንግስት ተጨማሪ የካፒታል በጀት ባለመገኘቱ “ምክንያት ነው” ብለዋል፣ ሚኒስትሩ። የግብርና ዘርፉን ለማሻሻል ከተፈለገ በማዕከላቱ ላይ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው፣ የካፒታል በጀቱ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚሰጥ በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ መቆየቱን አስታውቀዋል። የካፒታል በጀቱ እንዲፈቀድ ምክር ቤቱ የግብርና ሚኒስቴርን እንዲያግዝ ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ጠይቀዋል።
Saturday, 01 February 2025 10:44
የግብርና ምርምር ማዕከላት የመሬት ይዞታቸውን እየተነጠቁ ነው ተባለ
Written by Administrator
Published in
ዜና