Saturday, 01 February 2025 10:46

መንግስት በሲቪል ድርጅቶች ላይ የሚወስደው እርምጃ መባባሱ ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ መንግስት በሲቪል ድርጅቶች ላይ የሚወስደው እርምጃ እየተባባሰ መምጣቱን ሂውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ። ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሲቪል ድርጅቶች ላይ በጣለው ዕግድ ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ የማድረግ ፍላጎት አለማሳየቱን አስታውቋል።
ሂውማን ራይትስ ዎች ባለፈው ረቡዕ ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው በዚህ መግለጫ፣ ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በሁለት የሲቪል ድርጅቶች ላይ የወሰደውን የዕግድ እርምጃ አውግዟል። መንግስት በሲቪል ድርጅቶቹ ላይ የወሰደው ዕርምጃ ከሲቪል ድርጅቶች ዓዋጁ ጋር እንደማይጣጣም ገልጿል።
ድርጅቱ ይህ ዕርምጃ መንግስት የዘፈቀድ እስሮችን ጨምሮ ትችትን ለማፈን ሲያደርጋቸው የቆዩ ጥረቶች “አንድ አካል ነው” ብሏል። የሂውማን ራይትስ ዎች መግለጫ ሲቀጥል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ መንግስት የመብት ተሟጋቾችን ዒላማ አድርጎ ጥቃት መሰንዘሩን በጥብቅ እንዲቃወሙት ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ አጋሮች፣ በተለይም አሜሪካና ፈረንሳይ ሲቪል ድርጅቶች በአገሪቱ ላላቸው ሚና ድጋፋቸውን እንዲገልጡ፣ ብሎም ዕገዳዎቹን እንዲያወግዙም  ጥሪ አስተላልፏል፣ ድርጅቱ።
ተቆጣጣሪው የመንግስት አካል ለዕገዳው “ማሕበራቱ ነጻነት የጎደላቸው እና ከተፈቀደላቸው ስልጣን ባሻገር እየሰሩ ነው” የሚል ክስ ማቅረቡን ሂውማን ራይትስ ዎች በመግለጫው አመልክቷል። እንዲሁም ሂውማን ራይትስ ዎች መንግስት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤን ጨምሮ በመብት ተሟጋች ሲቪል ድርጅቶች ላይ በቅርቡ የጣለውን ዕገዳ እንዲያነሳና  ድርጅቶቹን ዒላማ ከማድረግ እንዲቆጠብ ጠይቋል።  
በሂውማን ራይትስ ዎች  የአፍሪካ ዳይሬክተር ማውሲ ሴጉን፤ “የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል” ብለዋል። ዳይሬክተሯ አያይዘውም፣ “መንግስት ወሳኝ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን በመመርመርና በመሰነድ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን በማገድ በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ምርመራ የማድረግ ፍላጎት አላሳየም” ሲሉ ገልጸዋል።
መንግስት በእነዚሁ ማሕበራት ላይ ከወሰደው እርምጃ አስቀድሞ  የመብቶች እና የዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ በሰብዓዊ መብቶች ጠበቆች ማሕበር እና የሰብዓዊ መብቶች ማሕበር ላይ ተመሳሳይ ዕገዳ መጣሉ የሚታወስ ነው። በኋላ ላይ ግን በሰብዓዊ መብቶች ማሕበር ላይ የተጣለው ዕገዳ ተነስቷል።
የሲቪክ ድርጅቶችን የሚቆጣጠረው የመንግስት አካል ባለፈው ታሕሳስ ወር አንጋፋው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል  ከስራ ማገዱ ይታወሳል።

Read 799 times