Saturday, 01 February 2025 10:49

ኢትዮጵያዊ “ሥነ-ጽሑፍ” በጨረፍታ

Written by  ሽብሩ ተድላ (ኤመረተስ ፕሮፌሰር)
Rate this item
(1 Vote)

የዚህችን ጽሑፍ ይዘት ብሎም ቅኝት የገራልኝ እና መረጃ ያበረከተልኝ ወዳጄ (የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ቅርብ ጓደኛዬ) ኃይሉ ሃብቱ በቅርብ ጊዜ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በዛምራ ፕሬስ በኩል በ2024 እ.ኤ.አ ያሳተመው “AKSUM: A glimpse into an African civilization” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ብዙ እና ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ያካተተ፤ ያልተቋጩ ነባር ግንዛቤዎችን እንደገና የፈተሸ፤ ብሎም እርግጠኝነታቸውን የሞገተ፣ ለዚሁም በቂ መረጃዎችን ያቀረበ ጽሑፍ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ ወደየተለያዩ የአገር ቤት ቋንቋዎች ቢያንስ ወደ አማርኛ እንደሚተረጐም ተስፋ አለኝ፡፡
በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በአፄ ምኒልክ ሜዳልየ ተሸለመ፡፡ የግዕዝ ቋንቋ አዋቂ፣ ብሎም በግዕዝ የተጻፉ መጻሕፍትን ወደ እንግሊዝኛ የተረጐመ፤ ‘ዋሊስበጅ’ (Wallis Budge, Sir) የሚባል ግለሰብበ፣ በ1920ዎቹ ባሳተመው መጽሐፍ፣ ስለ ኢትዮጵያውያን “ሥነ-ጽሑፍ” ፈጠራ ጭፍን አስተያየት  አስፍሯል፡፡ አስተያየቱም ጠለል ብሎ ሲታይ፤ ኢትዮጵያ ዝነኛነ ገሥታትን እንዲሁም ጦረኞችን ብታፈራም፤ የሥነ-ጽሑፍ ፈጠራ ሊቃውንት እንዳላፈራች፤ አልያም የፈጠራ ሥነ-ጽሑፍ እንደሌላት እና ጽሑፎቿም ሁሉ ሃይማኖት ነክ ሆነው ከውጭ ቋንቋ ወደግዕዝ የተተረጐሙ እንደሆኑያስረዳል፡፡ ይህን ሲያደርግም ከላይ እንደተጠቀሰው የግዕዝ ቋንቋ አዋቂ ሆኖ ሳለ ነው፡፡
የዚህን ግለሰብ ድምዳሜ የሚያኮላሽ መረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ የጥንት መጻሕፍት ሁሉም በሃይማኖት ዙሪያ ያጠነጠኑ አልነበሩም፡፡ እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፉ የነገሥታት ዜና መዋእሎች በደጃዝማች ኃይሉ እሸቴ በአንድ ጥራዝ እንደተሰባሰቡ ተመዝግቧል፡፡ እንዲሁም በፍልስፍና ሁለት የሚደነቁ መጻሕፍት በአክሱማዊው ዘርዓያዕቆብ እና በእንፍራንዛዊው ወልደ ሕይወት የተደረሱ አሉ፡፡ እንደሌሎች አገሮች ሁሉ ትምህርት ነክ የሆኑ ጽሑፎችም አሉ፤ ለምሳሌ ‘ነገረ እፅዋት’ (ስለእፅዋት)፣ ‘ነገረ እብን’ (ስለድንጋይ/ ጂኦሎጂ)፣ ‘ነገረፈለክ’ (ስለ ከዋክብት) አሉ፡፡ ሌሎችም ረቂቅ የሆኑ ሰነዶችም አሉ፤ ለምሳሌ ኃይሉ ሃብቱ በብሪታንያ መጻሕፍት ቤት ባገኘው የግዕዝ ማኑስክሪፕት (የብራና ጽሑፍ) ላይ ስለ ኤነርጂ እና ቁስ ግንኙነት (atomic energy)፣ በቁስ (matter) የታመቀው ኤነርጂ ነፃ ሲወጣ የቱን ያህል ኤነርጂ አመንጭ ሊሆን እንደሚችል ተተንትኗል። ይህም የኒኩልየር ኤነርጂን ገላጭ ሲሆን፤ጉዳዩ የድህረ-አንስታይን ዘመን ግንዛቤ ነው፡፡
ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ አንዱ ዋነኛው መሠረት የሥነ-ቃል አካል የሆነው ቅኔ ነው፡፡ ሥነ-ቃል በጽሑፍ በሚሰፍርበት በዚያችው ቅጽበት፤ ወዲያውኑ ሥነ-ቃል መሆኑ ይቀር እና ሥነ-ጽሑፍ ይሆናል። ሥነ-ቃል ይዘቱን ቀይሮ ወደ ሥነ-ጽሑፍ መሸጋገሩ ከጥንት የነበረ እንጂ፤በኢትዮጵያ የተጀመረ አይደለም። የሥነ-ቃል ዘውግ ተቀይሮ፤ ሥነ-ጽሑፍ የሆነው፤ በብዙ የዓለም አካባቢዎች ሲሆን፤ ወፍ በረር ገለጣውን ከአፍሪካ ልጀምር፡፡
በምዕራብ አፍሪካ ሥነ-ቃል በጣም የታወቀ ነው፤ በአብዛኛው የሚገለጠውም በአፈ ታሪክ፣ በተረት ነው፡፡ ይህም ድርጊት ከትውልድ ወደ ትውልድ ታሪክን እና ባህልን የሚያሸጋግረው ዋናው ሥርዓት ነበር፤ ነውም፡፡ “The epic of Sundiata” በመባል የሚታወቀው፤ በመላሳህል፣ በኮራ የሙዚቃ መሳርያ ታጅቦ፤ የማሊ ሰፊ ንጉሰ ነገስታዊ ግዛት አመሰራረትን በግሪዮዎች [ተራክያን አዝማሪዎች] የሚተረከው ረጅም ግጥማዊ ድርሰት እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ሕያው ሥነ-ቃል ነበረ። ባሁኑ ዘመን፣ ሥነ-ጽሑፍ ሆኗል። ታዋቂው ደራሲ ችንዋ አቸቤም በብዙ ድርሰቶቹ አፈ ታሪክን ነካክቷል፤ አካቷልም፡፡ በዚህም መንስዔ፤ አፈታሪክ እንደገና በአካባቢው እንዲነቃቃ አስተዋጾ አበርክቷል፡፡ በደቡብ አሜሪካም ሥነ-ቃል ከፍተኛ ቦታ ነበረው፡፡ የአካባቢው ማህበረሰቦች ባህልንና ታሪክን ለመገንዘብ የሚበቁት፤ ወደ ተከታይ ትውልድም የሚያስተላልፉት በሥነ-ቃል ነበር፡፡ ሥነ-ቃልም በተረት፣ በዘፈን፣ በእንቆቅልሽ፣ ቀልድ፣ ተረብ ወ.ዘ.ተ. ይገለጥ ነበር፡፡
በቻይና በመጀመሪያ ረድፍ የሚገኝ ሥነ-ጽሑፍ ከሥነ-ቃል ነው የተቀየሰ፤ የተገነባም፡፡ ሥነ-ቃልም በእርኩስ መንፈስ በማስወጣት፤ በትንቢት (የወደፊቱን የግለሰቦች የወደፊት እጣ በመተንበይ (ጥንቆላ) እድል ወይም ዕጣ በመናገር)፤ በሙዚቃ ወ.ዘ.ተ. ነበር የሚገለጥ፡፡ የቃል ማነብነቡንም የሚተገብሩ ብዙ ዝነኞች የሆኑ ሊቃውንት ነበሩ፡፡ አብዛኻኙ የዚህ ተግባር ሊቆች ማየት የተሳናቸው እንደነበሩ ይወሳል፡፡ በሕንድ በተለይ በቡድሃ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ዝነኛና ተቀባይነት ተጎናጽፈው የዘለቁት፤ የሥነ-ቃል አካል የሆኑት ‘የራማያ’ እና ‘የማህብሃረታ’ ናቸው፡፡ እነሱም በቃል የሚነበነቡ በጣም ረጃጅም ተራኪ ስንኞችን ያካተቱ ናቸው፡፡ በግጥሞች የተካተቱም ረጃጅም የጦረኞች ታሪክ፣ ስለ ጣኦቶች እንዲሁም ስለ ሰይጣን (እርኩስ መንፈስ) የሚተርኩ ናቸው፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ተቀባይነትን ያተረፉ ሥነ-ቃላት፤ ስለ ሥነ ምግባርና  ስለፍጹም ሕይወት (እንከን አልባሕ ይወት) ያካተቱ ስንኞች   ናቸው፡፡
በምዕራብውያን ሥነ-ጽሑፍ ዝነኛ የሆኑት ሥነ-ጽሑፎች፤ የመጀመሪያዎቹ፣ በሆመር የተጻፉ ናቸው የተባሉት “ኢሊያድ” እና“ ኦደሲስ” ናቸው፡፡ የ”ኦደሲስ” ትረካ የጀግና ትረካ ሆኖ፤ ዋና ተዋናይ ‘ዩሊሰስ’ (Odysseus, or Ulysses) አደጋ የተሞላበት የአሥር ዓመት ጉዞን ያካተተ ጽሑፍ (ረጅም ግጥም) ነው፡፡ የ”ኢሊያድ” ሆነ የ”ኦደሲስ” መሰረታቸው ሥነ-ቃል ነው፡፡ ተረቶቹ ለዘመናት በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ ኖረው፤በመጨረሻም በሆመር ዘመን እንደተጻፉ ይወሳል፡፡ ሆመር ማየት የተሳነው የሥነ-ጽሑፍ ሊቅ እንደሆነ ተመዝግቧል። ማየት የተሳነው ግለሰብ ስለነበረ፤ ጽሑፉን ያዘጋጀለት ሌላ ግለሰብ እንደነበረ ቢገመትም፤ የሆመርን ደራሲነት    አያኮላሸውም፡፡
እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ የኢትዮጵያም ሥነ-ጽሑፍ መሰረቱ ሥነ-ቃል ነው፤ ዋናውም ቅኔ ነበር፡፡ የሚገርመው ደግሞ እንደ ቻይናውያን ማየት የተሳናቸው፤ ትርክት አቀባባዮች ሁሉ በኢትዮጵያም ብዙ የቅኔ ሊቃውንት ማየት የተሳናቸው ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ሞጣ ጊዮርጊስ የቅኔ መምህራን የነበሩት አራት ዐይና ጎሹ፣ አለቃ አልድራስ፣ ትንሹ ጌጤ፣ እንዲሁም በሌሎች ገዳማት የነበሩ የቅኔ ሊቃውንት እነ እማሆይ ገላነሽ (ዘጎንጅ)፣ አለቃ ተጠምቀ (በዲማ)፣ ጎንደር የቅኔ መምህር የነበሩት፤ የእማሆይ ገላነሽ ልጅ አለቃ ኃይለማርያም፣ በቅርብ ዘመን የተክለ ሃይማኖት (መርካቶ) አለቃ የነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩም ማየት የተሳናቸው ነበሩ፡፡
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስ፣ ይህ ሁሉ እያለ ነው ‘ዋሊስበጅ’ “ኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ሊቃውንት ደሃ ናት” ብሎ የተዛባ መረጃ የዘራ፡፡ በቃል የተደረሱ በሺዎች የሚቆጠሩ የግዕዝ ቅኔዎችም፤ ከዘመናት በኋላ በጽሑፍ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል፡፡ የቅኔ መድብሎችም በመጀመሪያ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ከዚያም በሁለት ጥራዝ፣ ሁለት ሺ ስምንት መቶ ሃያ ዘጠኝ በተለያዩ ዘመናት ሊቃውንት በተቆጠሩ/ የተደረሱትን ቅኔዎች፣ “ዝክረ ሊቃውንት” በሚል ርእስ በመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ተዘጋጅተዋል፡፡ እንዲሁም በመድበል መልክ የተዘጋጁ የአማርኛ ቅኔዎችም አሉ። እነዚህም የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “የልቅሶ ዜማ ግጥም” እና የአቶ ዓለማየሁ ሞገስ “የኢትዮጵያ ቅኔ” ናቸው፡፡ በተለያዩ ዘመናት የተደረሱ የኢትዮጵያ መጻሕፍትም በ’ቢብሊዮግራፊ’ መልክ ተሰናድተዋል። ለምሳሌ፣ በአምሳሉ ተፈራ “ነቅዐ መጻሕፍት” (የመጽሐፍት ምንጭ) በሚል ርእስ፣ ከስድስት መቶ በላይ የግዕዝ ጽሑፎችን ያቀፈ ‘ቢብሊዮግራፊ’ ተዘጋጅቷል፡፡ ተመሳሳይ ጥረቶችም በዘመናችን እየተስተናገዱ ናቸው፡፡    
ያም ሆኖ በውጭ አገር በታወቁ ቤተ-መጻሕፍት፣ ለምሳሌ በብሪታንያ ቤተ-መጻሕፍት በአንድ ቦታ የሚገኙትን መሰል መረጃዎችን በኢትዮጵያ ለማግኘት፤ እንደ ጣና ቂርቆስ (በጣና ደሴት)፣ ደብረ ዳሞ እና ጉንዳ ጉንዲ (በትግራይ)፣ ደብረ ድማህ (ዲማ) (ጎጃም)፣ ደብረ ሊባኖስ (ሸዋ) ወዘተ. ያሉትን ብዙ ገዳማትን መጎብኘት ያሻል፡፡ ልፋቱ ቀላል አይደለም፡፡
ይህን ካልኩ በኋላ ስለ “ቅኔ” ላውሳ። ከላይ እንደተወሳው ቅኔ “ሥነ-ቃል” ነው፡፡ በጽሑፍ ያልሰፈረ ድርሰት “ሥነጽሑፍ” ባይባልም፣ ያን ዓይነት ስያሜ ተሰጥቶት በአንዳንድ አካባቢ ቢታወቅም፤ በ”ሥነ-ቃል” እና በ”ሥነ-ጽሑፍ” መኻል ያለው ልዩነት በጽሑፍ የሰፈረው በቃል ከሚነበነበው ከ”ሥነ-ቃል” በላቀ ሁኔታ ሳይዛነፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ በመቻሉ ብቻ ነው፡፡ ያም የድርሰቱን፣ የፈጠራውን ይዘት አይቀይረውም፡፡ ስለሆነም እንደ ጽሑፍ ሁሉ በልሳን የተነደፈውም እኩል እውቅና ሊሰጠው ይገባል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ በዚህች ጽሑፍ “ሥነ-ቃል”ን እንደ”ሥነ-ጽሑፍ” እኩል አድርጌ ወስጄዋለሁ፡፡
በኢትዮጵያ አንዱ ዋና የሥነ-ቃል አካል የግዕዝ ቅኔ ነው፡፡ ቅኔ ይቆጠራል፣ አንዳንዴም ይዘረፋል እንጅ፤ አይሰነድም፡፡ የግዕዝም ሆነ የአማርኛ ቅኔ (ምንም ጥቂት ግለሰቦች የአማርኛ ግጥም ቅኔ አይባልም ቢሉም) በብዙ ቃላት መገለጥ ያለበትን ሐሳብ ተግባሩን አጥልሎ፤ ጨምቆ፤ በጥቂት ቃላት፣ በረቀቀ ስልት መድረስ (መፍጠር) ነው፡፡ አካሄዱም በጠላ ዘመራ ወይም በማር ወለላ ሊመሰል ይችላል፡፡ ድርሰት (ተጻፈም፤ አልተጻፈም፤ ይኸውም በአገራችን ማንበብ እና መጻፍ የማይችሉ ብዙ የአማርኛ ስንኝ ፈጣሪዎች አሉ) የከፍተኛ ፈጠራ ችሎታ ገላጭ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የኢትዮጵያን የጥንት የድርሰት ፈጠራን የማቀርበው በዚህ ግንዛቤ ላይ ተመስርቼ ነው፡፡ ፈጠራው እስካለ ለድረስ ኢትዮጵያም የሥነ-ጽሑፍ ደሃ ሆና መታየት አይገባትም፡፡
ቀድም ብዬ በሌላ ጽሑፍ እንደገለጥኩት፤ የቅኔ (ሥነ-ቃል) አባት በመባል የሚታወቀው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ፣ የተለያዩ ድርጊቶችን ገላጭ የሆኑ ፈርጀ ብዙ ቅኔዎችን በ6ተኛው ክፍለ ዘመን እንደተቀኘ ይታወቃል፡፡ ከዚያም ከሺ ዓመት ገደማ በኋላ በ15ኛው ክፍለ ዘመን በሊቀሊቃውንት ከፍተኛ ተደናቂነት ያተረፈውና ከቅዱስ ያሬድ ቀጥሎ እውቅና የተሰጠው ባለቅኔ አባጊዮርጊስ ዘጋስጫ ነበር፡፡ ከዚያም ቀጥለው የቅኔን ይዘት፣ ውበት፣ ጥልቀት፣ ምጥቀት በተለያዩ ዘመናት እንዳጐሉት የሚወሱ የገብላው (ዋድላ ደላንታ) ዮሐንስ እና የጎጃሙ ተዋናይ ናቸው፡፡
ከእዚህ በመቀጠል፤ በጣም ውስን የሆኑ ቅኔዎችን በስማበለው ወደ አማርኛ ተርጉሜያለሁ፡፡ ቅኔዎቹን ያገኘሁት፣ የቅርብ ጓደኛዬ ኃይሉ ሃብቱ በቅርብ ጊዜ በእንግሊዝኛ ካሳተመው፤ በጽሑፌ መጀመሪያ ከጠቀስኩት መጽሐፍ ነው፡፡ አጠቃላይ በግዕዝ የተሰነዱን ጽሑፎች ቢያንስ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ፣ ለዘመኑ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች ማበርከት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ጥቂት ሊቆች ይህንን ተግባር በመጠኑም ቢሆን አስተናግደዋል፤ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፡፡
የቅኔን የረቀቀ ይዘት በጨረፍታ ለመዳሰስ፣ በስማበለው የተተረጐሙ ቅኔዎች እነሆ፡፡ በመጀመሪያ ስለ አንድ ረቢ ጉዳይ ላውሳ፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት እንደሰፈረው፤ አንድ የታወቀ ረቢ (የይሁዲ የሃይማኖት ሊቅ) ክርስቶስን ሲሰብክ ሰምቶ እና ተአምር ሲሠራም ዐይቶ ኖሮ፤ ክርስቶስን ለመጐብኘት ሻተ። ያንን ሲያደርግ ግን፤ ውርደት እንዳይሆን፤ ሰው እንዳያየው፤ በመንፈቀ ሌሊት ወደ ክርስቶስ ሄዶ ሰገደለት፡፡ ‘ረቢ ’የሚለው ቃል የይሁዲ እምነት ልሂቅ ከመሆን በተጨማሪ፤ የዓለምጌታ (እግዚአብሔር) የሚል ትርጉምም አለው፡፡ በዓረብኛ‘ አልሃምዱሊላሂ’ (እግዚአብሔር ይመስገን) ከተባለበኋላ፤‘ ረቢ አልአላሚን’ (የዓለምጌታ) በሚል ይታጀባል፡፡
ረቢ ሰገደ፤ በመንፈቀ ሌሊት ለረቢ፣።
አኮኑ አጽባእት፤ እምአጽባእት የዐቢ፡፡
***
ረቢ ለረቢ በመንፈቀ ሌሊት ሰገደ።
አንዱ ጣት ከሌላው ጣት፣ በመላቁ ተምሳሌነት ተገደደ፡፡
ይህችን ቅኔ መሰል አንድ የአማርኛ ግጥም ላውሳ፡፡

ወሌ ወሌ ወሌ ቢሏችሁ፣...
የወረባቡ አይምሰላችሁ፣
የ’ሳቱ ቁራጭ መርጦ አለላችሁ፡፡...
(ለእቴጌ ጣይቱ ታናሽ ወንድም ለራስ ወሌብጡል የተገጠመ)፡፡
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ቆላ ጋይንት ጨጭሆ ተራራ አናት ላይ ሆኖ ወደታች (ቁልቁል) ሲመለከት፣ ዝናብ አዘል  ደመና ሲከንፍ አየ፣ ያየውን፤ ሳይንሳዊ ይዘት ባላት ቅኔ ገለጠ፤   እነሆ፡፡

በተነ ጊሜ ረቂቅ ዘየአቊሮ ለማይ
ዘየአርጎ እም ቀላይ፣
ወዘ ያወርዶ እምኑኀ ሰማይ፡፡
***
ትነትን ከባህር ገጽታ ዘረፈ፣
ክብደት አልባ አድርጐ በሰማየ ሰማያት አንሳፈፈ፣ አከነፈ፣
ከዚያም ዝናብ በመሬት ላይ ጎረፈ፡፡
በዚህች ሳይንሳዊ ይዘት ባላት ቅኔ የእኔን ስንኝ ላክልባት፡፡

የተነነን ውሃ፣ የትነው የምትዘንበው? ብለህ አትጠይቀው፤
የወቅቱ ነፋስ ነው፣ ቦታውን       የሚያውቀው፡፡

መደምደሚያ
ያለንን የአገርቤት ዕውቀት ቋት ለማወቅ አለመሻት ብሎም አለማወቅ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በዚያ ምክንያት የውጭ ሰዎች አውቀውም ሆነሳያውቁ የተዛቡ ትረካዎችን ይነዙብናል፡፡ እንዲያውም ከዚያ ይባስብሎ፣ የኛም ምሁራን፣ የውጭ እይታዎችን ተቀብለው፤ አምነው፤ የተዛቡ ግንዛቤዎች እነሱም በጽሑፎቻቸው ውስጥ በብዛት በማንፀባረቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህች እይታ አንድ ትርክት  አለች፡፡ በአንድ ዕለት ባል ተደብድቦ፤ ተፈንክቶ፤ ወደ ቤቱ ሲገባ፤ ባለቤቱ ደንግጣ “ምን ሆንክ ብላ ጠየቀችው? “ከእገሌ ጋርተጣልቼ ደበደበኝ” ብሎ መለሰላት፡፡ ከዚያም “በዱላው ነው?፣ ብላ ሌላ ጥያቄ ስታቀርብለት፤ ባል”ዱላ መቼ ያዘና፣ ያማ ወንድንት ነው፤ የኔኑ ዱላ ቀምቶ ነው እንጅ የደበደበኝ” ብሎ መለሰላት ይባላል፡፡ እኛን ይህን ሁኔታ በጥሞና ፈትሸን፤ አነኝህን የተዛቡ ትረካዎችን አቃንተን፤ ለዓለም ማሳወቅ ይገባናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
የዚህ ችግር አንዱ እና ዋናው መንስዔ፣ ዘመናዊ ትምህርት ሲመሠረት ከውጭ እንዳለ ተቀድቶ፤ በአገርቤት ላይ መለጠፉ ነው፡፡ የአገራችን ዘመናዊ ትምህርት መሠረት-አልባ ነው፤ በድቡሽት ላይ እንደተገነባ ነው የምገነዘበው፡፡ ያለውን፤ ማንነቱን የማያውቅ ማኅበረሰብ ምንጊዜም ሌሎችን ለመምሰል የሚጥር፤ እሱነቱን ያልተረዳ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡ በዚህ ዓይነት የትምህርት ሥርዓት ያለፉትን ነው ታዋቂው ፈላስፋ ‘ጃን ፖል ሳርትር’ “አውሮፓ የነደፈችው ዓላማ ግቡንመቷል” ያለው። በእስያ፣ በደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ ባህላቸውን ደምስሳ የሷን ባህል በዚያ ቦታ ተክታለች፤ እሷን መሰል ለመሆን የሚጥሩ ጥራዝ ነጠቆች (በቶክሲዶ ላይ በርኖስእንዲሉ) አፍርታለች፤ ባህላቸውን ደምስሳ ባህሏን አከናንባቸዋለች፡፡ አገር ቤትም ይህን ጉዳይ የምትነካካ ቅኔ አለች፤ እነሆ፡፡
ቀራንብት ኀቤሁ እንዘ ቅሩባን፣
ቀራንብተ ኢይኔፅር ዓይን፡፡
በኃይሉ ሃብቱ
ቅንድብ፣ ለዓይን ቅርቡ ሳለ፤
ዓይን፣ ቅንድብን አላየ።
ትርጉም በከበደ ሚካኤል ስልት (ሽብሩ ተድላ)፤

ዓይንና ቅንድቦች ሆነው ጎረቤት፣
እንዳለ መታደል እንደምትሃት፣
ዓይኖች ቅንድቦችን ወይ አለማየት?

እኔንም ይህ ጉዳይ ስለሚከነክነኝ፤አንድ ሁኔታ ገላጭ የሆነች ስንኝ አለችኝ፡፡

ይህ የዛሬው ትምህርት፣
መሠረት አልባ ነው የውሃ ላይ ኩበት፡፡
ይዘቱ ዲቃላ፣ስሙ የከበረ፤
ብጥስጣሽ፣ ጥቃቅን፣ የተመነዘረ፣ የተሸረሸረ፤
መቋጫው ወረቀት፤
ምስክር ሰጭነት፤
ለተወሰነ ዕውቀት፤
የማወቅ ጥልቀቱ፣ በጥበቱ መጠን፤
አጮልቆ እያዬ፣ አድማሱ ሲወሰን፤
አድማሱ ሲሸፈን፡፡
ግዕዝ አንዱ ዋናው የነባር ዕውቀት ቋት ስለሆነ፤ በግዕዝ የተደረሱ መጻሕፍትን ማደራጀት፡፡ ከዚያም ወደ የተለያዩ የአገር ቤት ቋንቋዎች መተርጐም፤ ያንን ማድረግ ካልተቻለም፤ ለጊዜው ወደ አማርኛ መተርጐም ያስፈልጋል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ ይህን ተግባር የሚያከናውን በመንግሥት ተቋም ደረጃ (ኮሚሽን) ማቋቋም ያስፈልጋል፤ ያን ማድረግ ካልተቻለም፤ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የግዕዝ ሊቃውንት ጉባዔ ማቋቋም (መመሥረት) ተገቢ ነው እላለሁ፡፡ ይህ የዕውቀት ቋት የአገር ሀብት ስለሆነ፤ ለጉዳዩ በአገር ደረጃ ማሰብ ይገባል፡፡ ይህን ማድረግም ማንነታችንን ያሳውቀናል፤ ከጥራዝ ነጠቅነትም ያላቅቀናል፤ የሚል እምነት አለኝ፤ እንደሌሎች ብዙ ግለሰቦች ሁሉ፡፡




Read 408 times