Saturday, 01 February 2025 10:49

የብልጥ ውሻ ቡችላ ሆዷ ውስጥ ይጮሀል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አባት-ቢስ ገላ ነው፡፡ አንድ ልጅ በዚህ ቤተሰብ ይወሰዳል፡፡ ሰፈር ጎረቤት ለገንፎ ይጠራና ይበላል፡፡ ይጠጣል፡፡ እንደ አገሩ ደንብ ስም የማውጣት ልማድ የሚቀጥለው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ የተሰበሰበው ሰው ሁሉ በየራሱ ስም እያወጣ ሰጠ፡፡ በመጨረሻ ከስሞቹ መካከል  የሚወደደውን ማጽደቅ  ያለበት የቤቱ አባወራ ነውና፣ የመረጥከውን ስም ንገረን ተባለ፡፡ አባትዬው፤
“የወጣው ስም በጠቅላላ አልተስማማኝም፡፡ ስለዚህ የራሴን ባወጣ ይሻላል” አለ፡፡
የተሰበሰቡት ሰዎችም፤
“ጥሩ የአንተን እንስማ” አሉት፡፡
አባትዬውም፤
“መልካም፡፡ ብዙዎቻችሁ ያወጣችኋቸው ስሞች በተስፋ፣ በአክብሮት፣ በመልካም ምኞት እና በጀግንነት የተሞሉ ናቸው፡፡ ለቤተሰባችንና ለልጃችን ያላችሁን ልባዊ ፍቅር መግለጻችሁ ነውና ከልብ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡
በበኩሌ ግን  ላወጣ የፈለግሁት ስም በእውነት ላይ የተመሰረተ፣ ታሪክን የሚመለከትና የቤተሰባችንን የትውልድ ሀረግ የሚያጣቅስ ነውና፣ እንደምትቀበሉኝ እተማመናለሁ፡፡”
“እኔ ያወጣሁት ስም” ሲል!
የተሰበሰበው ሁሉ ማጉተምተሙንና ማንሾካሾኩን ትቶ ፀጥ፣ እረጭ አለ፡፡ ይሄኔ  አባትዬው፡- ”ጣጣህ ገና  ብየዋለሁ” አለ፡፡ የቢስ-ገላነት ችግር በዘር ይተላለፋል ይባላልና፣ ሰው ሁሉ ነገሩ ባንዴ ገብቶት በጭብጨባ ያወጣውን ስም አፀደቀለት፡፡
* * *
በኢትዮጵያ ያለውን ሥርዓት በማውገዝ፣ ዛሬ ፊት ለፊት የሚወሳው ችግር ሁሉ የዚያ ቅሪት ነው ብሎ መፈረጅ ለተወሰነ ጊዜ የሚያገለግል ዘዴ ይሁን እንጅ ቀስ በቀስ የዚህኛው ሥርዓትም የራሱ የሆኑ መሠረታዊ ችግሮች እንደ እስከዛሬው ሁሉ አፍጥጠው ብቅ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ጣጣው ያለቀ እንጂ ጣጣው ገና የሆነ ህዝብ፣ የነገ ህይወቱ አጠያያቂ ይሆናል፡፡ የነገ ተረካቢ ትውልዱ ተስፋና ራዕይም በአሉታዊነት (Negativist outlook) ተፅዕኖ ስር ይወድቃል፡፡ ተጠራጣሪ ይሆናል፡፡ ሽሽግ ይሆናል፡፡ ተመራማሪና ጠያቂ ሳይሆን በደፈናው ሁሉን ተቀባይ ወይም የሆዱን ደብቆ የተቀበለ  የሚመስል ህዝብ ይሆናል፡፡
እንኳንስ መሪዎቹን በሙሉ ልብ ሊቀበል፣ እርስ በእርሱም ሙሉ በሙሉ ለመተማመን እጅግ ረዥም ጊዜ የሚፈጅበት ይሆናል፡፡ ወይ ግፍና መከራ አንገቱን  ያስደፋው፣ አሊያም የኑሮ ጫና ለዝምታ የዳረገው ዓይነት ህዝብ ይሆናል፡፡ መሪዎቹም ቢሆኑ ቡድናዊ አስተሳሰብ የሚያጠቃቸው እንጂ በየግላቸው ነጻ የሆነ በራስ መተማመን ያዳበሩ ስላልሆኑ ቅራኔዎች ይደበቃሉ እንጂ ወደ ስብሰባው ጠረጴዛ ጎልተው አይመጡም፡፡ አንድ የሀገራችን እውቅ ፀሐፌ-ተውኔት እንደገለጸው፡-
“በተቀራረብን ቁጥር የበለጠ እንጠፋፋለን!”
አብሮ ማደግ፣ አብሮ መማር፣ አብሮ መታገል፣ አብሮ ማሸነፍ፣ አብሮ መምራት  እጅግ ጠቃሚ ነው እንዳላልን ሁሉ፣ “ከአብሮ አደግህ  አትሰደድ” ዓይነት አስተሳሰብ እየገነነ ይመጣል፡፡ አብሮ አደግ እንደ ውስጥ አዋቂ፣ እንደ ገበና አጋላጭ ይቆጠራል፡፡ ያም  ሆኖ ሁሉም በህዝብ ይምላሉ፡፡
“… በአዕምሮው ወይ በገንዘቡ፣ ወይ በሥልጣኑ ሊያውቁበት
 ጠላታቸውን ጠላቱ፣ አርገው ጠላት ሊገዙለት፣
ወዳጃቸውን ወዳጁ፣ አርገው ወዳጅ ሊሸጡለት
እምነቱን ሊታመኑበት
እድገቱን ሊታደጉበት
ውስጡን  ሆድ ለሆድ ሊስቁ
ለሆዳቸው ስላወቁ…”
እንደተባለው መሆኑ ነው፡፡ መተሳሰብ ወደ መተናነቅ ይለወጣል፡፡ “ሀ ራስህን አድን” የመመሪያዎች ሁሉ ቀዳሚ ይሆናል፡፡ አገር ወደ ፓርቲ፣ ፓርቲ ወደ ቡድን፣ ቡድን ወደ ግለሰብ ይጠብብ ይለወጥና፣ የአገር ጉዳይ ሲባል የአንድ የራስ ጉዳይ ወደ መሆን ይዘቅጣል፡፡ ይሄኔ ሪፖርቶች የራስ ቅኝት ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ፖሊሲዎች ራስን በማይጎዱበት መልክ ይቀረጻሉ፡፡ አጀንዳዎች ወደተፈለገበት አቅጣጫ ይመቻቻሉ፡፡ ዓላማ ቋሚ ፍኖት መሆኑ ይቀርና የወቅቱን ችግር ለማለፍ የተቀመረ የእሳት አደጋ መኪና ነው ይባላል፡፡ ቅዱሱን እርኩስ፣ አባዩን ሀቀኛ ማድረግ ቀላል ጉዳይ  ይሆናል፡፡ አንድ እውቅ ገጣሚ እንደተቀኘው፡-
“ሕሊናቸውን ባይሹት፣ ሀዘን የሚሸሹ እነሱ
ለሰባት እምነት ሲምሉ፣ ለሰባት ምላስ ሲያወሱ
 ባንደኛው ሲነካከሱ
በሌላው ሲሞጋገሱ
በሦስተኛው ሲካሰሱ
ሌት ዐይኑን ላፈር ያሉትን፣ ሳይነጋ የሚያወድሱ” ይሆናሉ፡፡
በሀገራን የታዩ ነጋሲዎች፣ ገዥዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ፓርቲዎች፣ ድርጅቶች፣ ማህበሮች ታሪክ አካሄድ ውስጡ ሲታይ፣ ከላይ ወደተጠቀሰው አጠቃላይ እውነታ ሲያመራ ነው የተገኘው፡፡ ማኪያቬሊያዊ የአስተዳደር ዘይቤ (ወይ ሴሜቲክ አካሄድ እንበለው ይሆን?) ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በደም ክትባት የተገኘ እስኪመስል ድረስ ተጠናውቶን መታየቱ ታሪካችንን፣ ባህላችንንና ፖለቲካችንን ወደ ኋላ  ዘልቆና ጠልቆ መመርመር ግድ መሆኑን ሳይጠቁመን አይቀርም፡፡
የአመራሩ ሂደት ድግግሞሽ፣ የአለቃና የምንዝሩ መልክ፣ የሐዋርያውና የደቀ-መዝሙሩ ባህሪ፣ የአላማጁና የመታያ አቅራቢው መመሳሰል፣ የአሮጌው ዲታ  አቆራቆዝና የአዲሱ ቱጃር አመጣጠቅ የፈጠረው የኢኮኖሚ መሪና ተመሪነት፣ አሰላለፍ ወዘተ… ህዝቡን “ያው በገሌ” ሲያሰኘው ቆይቷል፡፡ ምንም ይሁን ምን ህዝብ ከጠዲቁም  ከጠበሉም አይደርሰኝም ብሎ የማሰቡን ያህል፤ መንግስት ፈረሰ፣ ፓርቲ ተከላከለ፣ ምናልባትም አገርህ ውሃ በላው ቢሉትም፤
“ካልተነካችብኝ የደሀ ጎጆዬ
ህንፃዎች ቢናዱ እኔ ምን ተዳዬ”
እንዳለው መምህር ገጣሚ፣ አያገባኝም ማለቱን ይያያዘዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ለማንም ደግ አይደለም፡፡ አሮጌው ተሽዋሚ ጣጣህ ገና ነው፡፡ አዲሱ ተሽዋሚ  ጣጣህ ገና ነው፡፡ አሮጌው ምዕመን ጣጣህ ገና ነው፡፡፡ አዲሱ ምዕመን ጣጣህ ገና ነው፡፡ መከራ ሲፈራረቅበት “ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስኪመልሰው” እያለ ያሳልፋል፡፡ ጊዜም ለውጥ ይዞ ቢመጣ “ፊት የበቀለን ወፍ ይበላዋል…” ብሎ ሲያፈገፍግ ብልጣ-ብልጡ ይቀድመዋል፡፡ ቀድሞ መስዋዕትነት ለመክፈል የሚቆርጠው ቁጥር  እየመነመነ፣ ይመራል  የተባለው ጀሌ እየሆነ፣ መልካም ተናጋሪ እንደ አስተማማኝ አዋቂና መሪ እየተቆጠረ ወዘተ-- ሰው ሰራሽ  ማህበረሰብ (Fictious society)  ወደ መፍጠር እንዳንጓዝ  ያሰጋል፡፡  ብልጣ- ብልጦች ብቻ እየኖሩ፣ የዋሀን ከቀን ቀን እያሽቆለቆሉ የሚታዩበት ሁኔታ አሰቃቂ ነው፡፡
“ኑሮ መስዋት ነው” ሲባል የነዋሪዎቹን ምስል ያሳያልም ማለት  ነው፡፡  ይህ መስተዋት የዛሬን የአገሪቱን ጉስቁልና ብቻ ሳይሆን፣ የነገን አባዜም  ያሳያል፡፡ ሀቀኛ ሠራተኛና ባለሙያው እንደላቡ አይኖርም፡፡ ይልቁንም  አፈ-ጮማው፣ አንደበተ-ቀናው እያወለወለ የሚታይባት ሀገር እንዳትሆን መጠንቀቅ  ይገባል፡፡ የዚህ  ዓይነቱ አሰራር  ጣጣው ገና ነውና፡፡ “የብልጥ ውሻ ቡችላ ሆዷ ውስጥ ይጮሀል” የሚለውን  ተረት አለመርሳት ነው! እየወረድን ላለንበት ቁልቁለት በጊዜ ታኮ ካልተደረገ፣ “ለጥቂቶች ገነት ለብዙዎች ሲዖል” እንደመመኘት ይሆናል፡፡

Read 691 times