የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት የሆነው ተሽከርካሪ፤ የሰዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ምቹና ቀላል በማድረግ ረገድ አይተኬ ሚና እንዳለው የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ሰዎች ያሹት ቦታ በፍጥነት እንዲደርሱ በማገዝ፣ ከጊዜና ጉልበት ብክነት ታድጓቸዋል፡፡ ንብረቶቻቸው ደህንነቱ ተጠብቆ ከቦታ ቦታ በቀለጠፈ መልኩ እንዲጓጓዝ አስችሏቸዋል፡፡ ተሽከርካሪ በአጠቃላይ የሰው ልጆች እንቅስቃሴን የተሳለጠ አድርጎታል ማለት ይቀላል፡፡
ተሽከርካሪ የሰው ልጆችን ህይወት ለማቅለልና ለማቀላጠፍ ታልሞ የተፈጠረ የአዕምሮ ውጤት ቢሆንም ታዲያ፣ አሁን ላይ በራሱ በሰው ልጅ ግዴለሽነትና ጥፋት ለሞትና ለአካል ጉዳት የሚዳረገው ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
እንደ ተባበሩት መንግስታት መረጃ በአለም አቀፍ ደረጅ በየዓመቱ ሁለት ሚሊየን ገደማ ሰዎች ሂወታቸውን በትራፊክ አደጋ ያጣሉ ከዚህ በተጨማሪም ከ30 እስከ 50 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች ለከባድና አደጋ ሲጋለጡ በተለይም እድሜያቸው ከ 5 እስከ 29 የሚደርሱ ዜጎች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው ተብሏል፡፡ የአለም ጤና ድርጅት በገዳይነቱ ከቀዳሚዎች ተርታ የመደበው ይኸው ችግር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት የከፋ ነው የተባለ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በአመት የ400 ሰዎችን ሂወት እንደሚያሳጣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት መረጃ ይጠቁማል፡፡
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የመንገድ ደህንነት አቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል በዚህም የትራንስፖርት ስረአቱን በማሻሻልና የትራፊክ አስተዳደሩ ላይ በተሰሩ ስራዎች አሁን ላይ አደጋው እየቀነሰ መጥቷል፡፡
የትራፊክ አደጋ የዜጎችን ህይወት መቅጠፍ ሳያንሰው፣ ሃብትና ንብረት በማውደም፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ የትራፊክ አደጋ ሰብዓዊም ቁሳዊም ኪሳራም ነው የሚያደርሰው፡፡
የዜጎችን ህይወት እየቀጠፈና ለአካል ጉድለት እየዳረገ የሚገኘው የትራፊክ አደጋ ዋና መንስኤዎች በጥናት ከተለዩ መካከል ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የደህንነት ቀበቶ ሳያደርጉ ማሽከርከር፣ ስልክ እያናገሩ ማሽከርከር ፣ ለሞተር ሳይክል ሄልሜት አለማድረግ ፣ የአሽከርካሪዎች ግዴለሽ አነዳድ እንዲሁም ቸልተኝነት፣ የሥነምግባር ጉድለት እና የችሎታ ብቃት ማነስ በሌላ በኩል በመንስኤነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በተጨማሪም የእግረኞች ያልተገባ የመንገድ አጠቃቀም፣ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ብቃት መጓደልና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመንገድ መሰረተ ልማቶች በተጨምሪ በመንስኤነት ይጠቀሳሉ፡፡ በቅርቡ የወጣ ጥናት ደግሞ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር የትራፊክ አደጋ ቁጥር አንድ ችግር መሆኑን አመልክቷል፡፡
ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ከጆን ሆፕኪንስ ዓለም አቀፍ የጉዳት ምርምር ክፍልና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል እንዲሁም ከብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ ዓለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት ኢኒሼቲቭ ጋር በመተባበር የአዲስ አበባ መንገድ አደጋና ሞት ቅነሳ የዳሰሳ ምልከታ ሪፖርት ይፋ ተደርጓል፡፡
በዳሰሳ ጥናቱ ከተካተቱ አሽከርካሪዎች መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት በከተማ ውስጥ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ (57 ኪሎ ሜትር በሰዓት) እንደሚያሽከረክሩ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ የዳሰሳ ምልከታ ከተደረገባቸው የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ውስጥ ደግሞ 46 በመቶ የሚሆኑት ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ እንደሚያሽከረክሩ የተመላከተ ሲሆን፤ የሞተር ሳይክሎች ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር በብዛት የሚስተዋለው በዕረፍት ቀናት ወይም (በሰንበት) እንደሆነ ጥናቱ ይጠቅሳል፡፡
በተደረገው የዳሰሳ ጥናት እንደተመለከተው፤ በአብዛኛው አደጋ የሚደርሰው ከቀኑ 6 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፤ በተለይም ሰንበት ወይም የዕረፍት ቀናት ከመንገድ መጨናነቅ ነፃ ስለሚሆኑ፣ በፍጥነት ማሽከርከር ሳቢያ የሞት ምጣኔው ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በመዲናዋ ለሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ዋነኛ መንስኤ ናቸው ተብለው ከተለዩት ውስጥ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር አንዱ ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ታረቀኝ፤ በተጨማሪም ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የደህንነት ቀበቶ አለማሰርና የአሽከርካሪዎች ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት ለትራፊክ አደጋ መንስኤ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ቢሮው በአሁኑ ወቅት ለትራፊክ አደጋ መንስኤ ይሆናሉ ተብለው በተለዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለህብረተሰቡ ስልጠናና ግንዛቤ እየሰጠ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የገፅ ለገፅ ስራዎችንም በ11ዱም ቅርንጫፎች በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከሚዲያዎችም ጋር በመተባበርም የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎችን ያከናውናል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ዋና ዋና መንገዶች ለፓርኪንግ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበርና ይህም የትራፊክ መጨናነቅ በመፍጠር ለአደጋ ሲያጋልጥ መቆየቱን ያነሱት አቶ አማረ፤ አሁን ላይ ከተማ አስተዳድሩ በኮሪደር የለሙ ቦታዎች ላይ ሰፊ ፓርኪንግ በማዘጋጀት ዋና ዋና መንገዶች ከተሽከርካሪ ክፍት እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል የህንፃ ስር ፓርኪንጎች ሙሉ ለሙሉ ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ ደንብ አፀድቆ ወደ ስራ በመግባቱ፣ አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ አደጋ ከ2010 ዓ.ም በፊት ለተከታታይ ዓመታት 6 በመቶ እየጨመረ እንደነበር የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከ6 ዓመት ወዲህ የትራፊክ አደጋ ምጣኔ ባለበት ማቆም ብቻ ሳይሆን፣ ከ5 በመቶ በላይ መቀነሱን ነው የጠቆሙት፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ ከ400 ባላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን እያጡ ነው ተብሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዲናዋ እየተስተዋለ የመጣው የትራፊክ አደጋ የመቀነስ አዝማሚያ ቀጣይነት እንዲኖረው፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶችን ያሳተፈ የመፍትሄ እርምጃዎችን በቅንጅት መውሰድ ይጠይቃል፡፡
ይህንን ታሳቢ በማድረግ በከተማ አስተዳድሩ ስር የሚገኙ 13 ተቋማትን ያካተተና በከንቲባ የሚመራ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት ተቋቁሞ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ የ5 ዓመት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ (2017-2023) ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ስትራቴጂው እስከ 2023 ዓ.ም በትራፊክ አደጋ የሚደርስ ሞትንና የአካል ጉዳትን በ25 በመቶ የመቀነስ ግብ አስቀምጧል፡፡
የትራፊክ አደጋን የመከላከል ተግባር በተወሰኑ አካላት ላይ ብቻ የሚጣል ሃላፊነት ባለመሆኑ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ነቅሶ ማረምና እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ የትራፊክ ተቆጣጣሪ አካላት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ተከታትሎ ማረምና ማነጽ ይጠይቃል፡፡ ከተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር ጋር የሚታየውን ጉድለትም በወጉ ፈትሾ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ የግድ ይላል፡፡ ከመንገድ መሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ ጉድለቶችንም አጢኖ ማረም እንዲሁም የግንዛቤ ክፍተቶችንም መሙላት እንደሚያስፈልግ አቶ አማረ ታረቀኝ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ይሄን ማድረግ በእርግጥም ዜጎችን ከሞትና ከአካል ጉድለት መታደግ ነው፡፡ የአገር ሃብትና ንብረትን ከውድመት መጠበቅ ነው። የአገሪቷንና የመዲናዋን መልካም ገጽታም መገንባት ነው፡፡ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም የድርሻውን በባለቤትነት ስሜት መወጣት ይኖርበታል፡፡ አሽከርካሪዎች፣ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች፣ መንገድ ገንቢዎች፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት አረጋጋጮች፣ እግረኞች፣ ወዘተ… በትብብርና በቅንጅት ስሟ በትራፊክ አደጋ የማይጠቀስ ከተማ ለመፍጠር በትጋት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ያኔ ከምርም ለሌሎች ጭምር አርአያ የምትሆን የአፍሪካ መዲና ይኖረናል፡፡