“ሕዝብ የሚወድ ለባሕሪው የሚመች ሥርዐት ሲያወጡለት ነው”
ዐምስት ኾነን ባንድ ባጃጅ ታጭቀን በተቦዳደሰው መንገድ እየተጓዝን ነው፡፡ በሹፌሩ በቀኝ በኩል ያለው ሰው አንድ ጎርፍ የማይነጥፍበት ስፍራ ወዲያውም ለደኅንነት አስጊ ነው በሚባለው ስፍራ ላይ ስንደርስ፤ “አምና እኮ እዚህ ስፍራ ላይ ሌባ የለም እንጂ ይጠቀም ነበር” አለ፡፡ የተኮራረፈ የሚመስለው ተሳፋሪ እርስ በርስ ተያየ፡፡ ‘ይዘርፍ ነበር’ አላለም፡፡ ‘ይጠቀም ነበር’ ነው ያለው፡፡ አፌ ቁርጥ ይበል! አንዱ ተሳፋሪ በጎን የሚያልፈውን ጋሪ ዕያየ “ይዘርፍ ነበር አትልም?” ሲል ሾፌሩ ቀበል አድርጎ፤ “መዝረፍ ሕጋዊ ኾኗልኮ፤ አልሰማህም?”
ሰሞኑን አሜሪካ ለዐራት ዓመታት የሚዘውራትን 47ኛ መሪዋን መርጣለች፡፡ የ335 ሚሊዮን ሕዝብ እናት የኾነችው አሜሪካ፤ ከ156 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን አሳትፋ ሁለት ጊዜ ከግድያ ያመለጡትን፣ በተለያዩ ወንጀሎች ክስ የተመሠረተባቸውን ዶናልድ ትራምፕ የተባሉ አወዛጋቢ ሰውን ለሁለተኛ ጊዜ ‘ምራኝ’ ብላለች፡፡ በ2016 (ዘመኑ በሙሉ እ.ኤ.አ ነው) ድምፅ የከለከሉት ግዛቶች ሳይቀሩ ይሁንታቸውን ሰጥተዋቸዋል፡፡ ኒውዮርክ ተወልደው ያደጉት የ78 ዓመቱ አዛውንት ትራምፕ፣፤ በዚያው እትብታቸው በተቀበረበት ኒውዮርክ ከተማ 5ኛ ጎዳና ላይ፣ 68 ወለል ያለው ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ካያችሁ እሱ የትራምፕ ነው፤ የ’ትራምፕ ፎቅ’ም (Trump Tower) ይሰኛል፡፡
የናንተን ባለውቅም ከሁለትሰዓት በላይ የፈጀውን በዓለ ሲመት በቴሌቪዥን መስኮት ስመለከት በአንድ ነገር አብዝቼ ቀናሁ፤ በገነቡት ተቋም፡፡
ትራምፕ ቢወድም ባይወድም ካማላ ሃሪስ በበዓለ ሲመቱ ላይ መገኘት ነበረባት፡፡‘ የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ’ ነውና፤ በሕይወት ያሉ አሜሪካን የመሩ መሪዎች ክብራቸውን በሚመጥን መልኩ (ትራምፕ ቢወድም ባይወድም) እንዲገኙ ተጋብዘዋል፡፡ ማን የት ቦታ መቀመጥ እንዳለበት፣ማን መቼ መናገር እንዳለበት ትራምፕ መመሪያ ሊሰጡ አይችሉም፡፡ ብዝኃነትን (በሃይማኖት፣ በቆዳ ቀለም፣በሙያ፣በጾታ ወዘተ) ለማስተናገድ የሄዱበት ርቀት የሚገርም ነው፡፡ ቨርጂኒያን የመሰሉ ይሁንታቸውን ያልሰጡት ግዛቶች፣ ሰውየው ‘ይበቀለናል’ ብለው አይሰጉም፤ እሳቸውም አይሞክሩትም፤ተቋም ተገንብቷላ፡፡
ለአንድ ሀገር ዕድገት ተቋም መገንባት አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ “…ያለተቋም ግንባታ ልማትም ኾነ ዕድገት ከንቱ፣የከንቱ ከንቱ…” ብዙ ብለናል፤ደስኩረናል፡፡ ተቋም ስንል ግን ምን ማለታችን ነው?ተቋም ማለት ሕንፃ መገንባት ነው?ተቋም ማለት አዲስ ድርጅት ወይም መሥሪያ ቤት መክፈት ነው? የንባብ ሚኒስቴር ስለከፈትን ብቻ ዜጎች አንባቢ ሊኾኑ ይችላሉ? ሰክሮ ቤተሰቡን የሚበጠብጥ አባዋራ፣ የበኩር ልጁን ‘ሰላም ወይም ሰላማዊት’ ብሎ ስም ስላወጣ ቤቱ ‘ሰላም ይኾናል’ ማለት ነው?
እንደ ማኅበረሰብ ሊቆች ተቋም (Instituion)፤አንድ ማህበረሰብ ሳይነጋገር የተስማማባቸው፣ ትውልድ እየተቀባባለ ያኖራቸው፣ የጋራ አስተሳሰብ፣ ባህል፣ ዕሴቶች፣እምነቶች፣ሕጎች ወዘተ ናቸው፡፡ ቤተሰብ፣ሃይማኖትና ትምህርትን ብንወስድ፣ ትውልድ ተጠፍጥፎ የሚሠራባቸው ማኅበራዊ ተቋማት ናቸው፡፡ የምርምር ተቋማት ፣ጋዜጣ፣ሙዚየም፣የጥበብ ጋለሪ በማጎንቆል ላይ ያሉ ማኅበራዊ ተቋማት ሲኾኑ ሙዚቃ፣ሥነጽሑፍ፣ የጥበብ ሥራዎች፣ስፖርት የመሳሰሉት ደግሞ በመዝናኛ ተቋምነት የሚታወቁ ናቸው፡፡ እነዚህ ናቸው አንድን ማሰብ፣ከፍ ስንል ሕዝብን ካስማና ባላ ኾነው፣እንደ ማሰብ ሕያው ኾኖ እንዲቀጥል የሚደርጉት፡፡
አንድ መንግሥት ሕዝብን የሚያስተዳድርበት ሥርዐት /ተቋም/ ደግሞ የፖለቲካ ተቋም ይባላል፡፡ ከዛሬ 101 ዓመታት በፊት፣ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ‘መንግሥትና የሕዝብ አሥተዳደር’ በተሰኘውመጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፡-
“… ሕዝብ የሚወድ ለባሕሪው የሚመች ሥርዐት ሲያወጡለት ነው፡፡…እንሆም ሥርዐት የሚመች ይኾናል ተብሎ በብልሆች ልብ ውስጥ ተፈጥሮ አይጻፍም፤ ከሕዝቡ ልብ ይቀዳል እንጂ፤ንጉሥ ወይም ሹም በኋለኞች ትውልዶች የሚመሰገን በልቡ ፈልስፎ ደንብ ሲያወጣ አይደለም፡፡ የሕዝቡን ሃሳብ ተርጉሞ በትርጉሙ ሲሔድ ነው እንጂ፡፡ የኤሮፓ ሕዝቦች የዛሬ ሥርዐታቸው ባንድ ቀን አልተደነባም፡፡ በዘመናት ብዛት የተጣራ ነው እንጂ፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ዕውቀት እየሰፋ ሲሔድ ለወደፊት ደግሞ እንደገና እየተጣራ ይሔዳል፡፡… ትምህርት በሌለበት ሀገር ለሥርዐት የሚኾን መሠረትአይገኝም፡፡ ሥርዐት የሚፈለግ በትምህርት ነውና፤ ትምህርት የሌለው ሕዝብ ሥርዐት አይወድም፤አይጠቅመውም፡፡ …”
ዛሬ ሀብታም የምንላቸው ሀገራት፣ ሀብታም የኾኑት ለዘመናት በርትተው ተቋም ስለነገነቡ እንጂ ፈረንካ ስላካበቱ ብቻ አይደለም፡፡ ፈረንካ ሀብት ለማፍራት ያግዝ ይኾናል፡፡ ዋናው የዕድገት ምስጢር ግን ወዲህ ነው፤ በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሔድ ተራማጅ ተቋም ማቆም፡፡ ዛሬ ሀብት ማማ ላይ ተሰቅለው የምናያቸው ትናንት መሬት ላይ ሲንከባለሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ዛሬን ሳይኾን ነገን አሻግረው በማየት ጠንክረው ስለሠሩ ፤ ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ ወይም ‘እኔን ከተመቸኝ እኔ ምን አገባኝ’ ስላሉ አይደለም፡፡ ‘የአባት ዕዳ ለልጅ ነው፤ በኔ ካልደረሰ እኔ ምን ተዳዬ’ ብለው ዕዳና ፍዳን ሁሉ ለትውልድ ለማውረስ ስለተሰቀቁ፣ስላፈሩና ለመጪው ትውልድ ‘ልማትን እንጂ ልመናን አናወርስም’ ብለው ስለተጉ ይመስለኛል፡፡
ተቋም ነባር እሴቶችን፣ ባህሎችን፣ በመናድ አይመጣም፤ከቶውንም፡፡ ይልቁንም ነባሩን በማጠናከርና የላላውን በማጠባበቅ እንጂ፡፡
አሁን አፋችንን ሞልተን የ3ሺ ዘመን ታሪክ፣ባህል፣እሴት የአኗኗር ይትባህልና ሃይማኖት ያላትን ሀገር በአንድ መድረክ ንግግርወይም ፖሊሲ በመቅረጽ እቀይራለሁ ብሎ ማሰብ ልጅነት ብቻ ሳይኾን፤ ጅልነት ነው ማለት የምንችል አይመስለኝም፡፡ አሁን አፋችንን ሞልተን አንድ ልጅ ነውር ሲሠራ፣ ‘አሳዳጊ የበደለው’ ብሎ የሚያነውር ፣ አንድ መሪ ሲስት ‘አማካሪ የበደለው’ ማለት የምንችል አይመስለኝም፡፡
ተቋማት ዘብ ኾነው ነቅተው ስለሚጠብቁ (check & balance) በሀገረ አሜሪካ ነባሩን እሴት ለመንቀል፣ ነቅሎም አዲስ ለመትከል የሚችል መሪ ሊኖር አይችልም፡፡ ከዚያ ቢያልፍ የአንድ መሪ የሥልጣን ዕድሜ ዐራት ዓመት ነውና ዕዳው ገብስ ነው፡፡ አንድ መሪ ቢያንስ ለሩብ ክፍለ ዘመን ወንበሩ ላይ በሚቀመጥባት በሀገረ አፍሪካ ግን አደጋው የከፋ ይመስለኛል፡፡ ማኅበራዊ ተቋማት ጠንክረው ካልቆሙ፣ቆመውም ማኅበረሰቡን ካላቆሙ፣ በአንድም በሌላም መሪዎች ከሚቀርጹት ፖሊሲ ጀምሮ በንግግራቸው ትውልድን ማንሸዋረር ይችላሉ፡፡ ‘ካልተያዝክ በቀር ስርቆትም ሥራ ነው’ን ያስታውሷል፡፡ ይህ ንግግር አሁን ፍሬ እያፈራ ይመስላል፡፡ ለዚህ በመግቢያዬ ላይ ካነሣሁት ገጠመኝ በላይ ነፍ (ብዙ) ማሳያ ማቅረብ ይቻላል፡፡
በሥርዐት የተደራጀ ተቋም ሀገርን ይሠራል፤ ካልተደራጀ ሀገር ያፈርሳል፡፡ ተቋም ከተገነባ ማንም እስኪወቅሰው አይጠብቅም፤ማን ምን መሥራት እንዳለበት ያውቃል፡፡ማንም እስኪነግረው አይጠብቅም፡፡ በግልምጫ አይበረግግም፤ ለአጉል ውዳሴ ጭራውን አይቆላም፡፡ሥራው አለቃው ይኾናል፡፡ በተሾመ ምትክ ተፈሪ ሲመጣ ተቋሙ ትርምስምሱ የሚወጣ ከኾነ፣ ተቋም አልተገነባም፡፡ መሪው ሲታመም ተቋሙ የሚታመም ከኾነ፣ ተቋም አልተገነባም፡፡ መንግሥት እንደወንዝ ነው፤ ተቋም ግን እንደ ባሕር የረጋ በመኾኑ ወገኑ ከሀገር ነው፡፡ ተቋም ተጠሪነቱ ለሚለዋወጠው መንግሥት ሳይኾን፣ ለሀገር ከኾነ ብቻ ይዘልቃል፡፡
ከታችኛው የመንግሥት መዋቅር ጀምሮ ያሉ ተቋማትን መመልከት ያንድን መንግሥት መልክ በውል ለመረዳት ያስችላል፡፡ ላወጣው ሕግ ታማኝ ያልኾነ መንግሥት፤ ዜጎቹ ሕግን እንዲፈሩና እንዲያከብሩ መጠበቅ፣ ከበለስ ኩርንችት እንደመጠበቅ ያለ ይመስለኛል፡፡
ይሄን ካልን ዘንዳ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርጠው በነጩ ቤተ-መንግሥት (White house) ሲኖሩ ያልተለመዱ የጓዳ ልማዶቹን ጨምሮ ብዙ ያልተሰሙ ጉዳዮችን በማነሣሣት ሐተታችንን ብንቋጭስ?
በነጩ ቤተ-መንግሥት መመገቢያ ክፍል፣ 60 ኢንች ቴሌቪዥን አለ፡፡ እዚያ ቴሌቪዥን ፊት ለፊት ሰውየው (ትራምፕ) አይጠፉም፡፡ የርቀት መቆጣጠሪያውን ማን ወንድ ነው ከ’ጃቸው የሚነጥቀው? ሰውየው የዜና ሱሰኛ ነበሩ፡፡ ስብሰባ ሲኖር እንኳ የቴሌቪዥኑን ድምፅ አጥፍተው (muted)፣ ዋና ዋና ዜናዎችን ለመቃረም ዐይናቸውን ማንከራተት ልማዳቸው ነበር፡፡
አልኮል መጎንጨት አይወዱም፤የኮካ ኮላ ምርት የኾነውን ዳይት ኮክ (Diet Coke) ግን የሰጠ አይመልሳቸውም፤ በቀን እስከ 12 ጣሳ ይለጉ ነበር፡፡
የዓለም መገናኛ አውታሮች በየሁለትና ሦስት ቀን ልዩነት የእሳቸውን ስም ካላነሡ ይደብራቸዋል፡፡ (ይደብራቸዋል ብቻ ሳይኾን እጅግ ይጨንቃቸዋል)፡፡ ሰውየው ‘ሆዱን ይወዳል’ እንደሚባልለት፣ ክሊንተን አይደሉም፡፡ ለምግብ ግድ የላቸውም፡፡ እንግዶች ጎራ ሲሉ የሊንከንን መኝታ ቤትና የትሩማን ባለጌ ወንበር ካስጎበኙ በኋላ፣ ማረፊያቸው (አሻሽሎ ካሠሩት) መታጠቢያ ቤቱ ነበር፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ለመታጠቢያ ቤቱ ያላቸው ፍቅር ‘የጤና ነው?’ ያስብላል፡፡
ፈጣን ምግብ መመገብ ይወዳሉ፤በተለይ የማክዶናልድ ምርት ነፍሳቸው ነበር፡፡ ምክንያት አላቸው፡፡ የ “Fire and Fury: Inside the Trump Whitehouse ደራሲ ማይክል ወልፍ ምክንያቱን፣ “የምግብ መመረዝ በጣም ስለሚያሰጋቸው ነው” ይለናል፡፡ እጄ ሰብ እጅግ ስለሚያሰጋቸው ‘ማዘር ቤቶች’ ጋ ጎራ ብሎ መመገብ በሰውየው ዘንድ በጭራሽ አይታሰብም፡፡ ማክዶናልድ የሚያሰናዳውን ፈጣን ምግብ የሚወዱት አንድም በጥንቃቄ ስለሚዘጋጅ፣ አንድም ወደዚያ ጎራ እንደሚሉ ማንም ስለማያውቅ ነው፡፡ (ማንም ካላወቀ ማንም ሊመርዛቸው አይችልምና)፡፡
ሰውየው ከሞጃ ቤተሰብ ቢገኙም (መወልወያውን ይዘው መፀዳጃ ቤት ማጽዳት ወይም በር ላይ ቆሞ ‘ማነህ? ወዴት ነህ?’ሊኾን ይችላል) በአባታቸው ድርጅት ውስጥ ‘ዝቅተኛ’ የሚባሉ ሥራዎችን (lowest-tier jobs) እንደመሥራታቸው፣ ‘ለመረጣቸው ሕዝብ ዝቅ ብለው ያገለግሉ ይኾን?’ ወይስ የ13 ዓመት ታዳጊ እያሉ ያሳዩት ነውጠኛ ጠባይ ያገረሽባቸው ይኾን?’ ቀጣዮቹ ዐራት ዓመታት የሚነግሩን ይኾናል፡፡
Sunday, 02 February 2025 00:00
የትራምፕ ነገር…
Written by ሙሉጌታ ቢያዝን
Published in
ህብረተሰብ