Monday, 03 February 2025 00:00

መንግሥታት ንባብን ሲገፉ፣ ጠመንጃ እያቀበሉ ነው!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

ዛሬ ታላቅነት ማማ ላይ የተፈናጠጠችው  እመቤት አሜሪካ የቅኝ ግዛት ቀንበሯን አሽቀንጥራ ጥላ፤ዴሞክራሲያዊና የበለጸገች ሀገር ያደረጓት መሥራች አባቶች እንቅልፍ የጠገቡ፣ዋዘኞች አልነበሩም። ይልቅስ አብዛኛዎቹ፣ መጻሕፍት ሙጢኝ ብለው ውለው የሚያድሩ፣ከንባብ ጠረጴዛቸው የማይርቁ ነበሩ።
እውነት ለመናገር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዩኒቨርስቲ ገብተው የተመረቁ አልነበሩም። ዩኒቨርስቲዎቻቸው ያነበቧቸው መጻሕፍት ናቸው።
አሌክሳንደር ሐሚልተን፣ቶማስ ጀፈርሰን፣ጆን አዳምስ፣በኋላም እነ ሊንከን፣ሳይንቲስቶቹም እነ ፋራዳይ ቶማስ ኤዲሰን በመጻሕፍት የተፈጠሩና ተልገው ያደጉ ናቸው።በሚገርም ሁኔታ አንዳንዶቹ  መደበኛ ትምህርት እንኳ አልተማሩም፤ “Self taught” ናቸው። ይህ የሚያሳየን መጻሕፍት ለአንድ ሀገር ሥልጣኔና ዕድገት በእጅጉ ወሳኝ መሆናቸውን ነው።
ጠንካራ የነፃነት ታጋዮችን እነሉተር ኪንግ፣ማኅተማ ጋንዲ፣ሔነሪ ዴቪድ ቶሩ፣እንደ ዊልያም ዌልሰር የመሳሰሉ አንቱታን የጠገቡ ታላላቅ ሐኪሞችንም ስናይ የመጻሕፍት ፍቅረኞች ነበሩ።
እንደ አሜሪካዊው ዝነኛ ዳኛ ኦሊቨር ዌንደል ሆልመስ ያሉና የተለየ ምልከታና አስተሳሰብ  የነበራቸው ፖለቲከኞች ሁሉ ከጀርባቸው ያነበቧቸው መጻሕፍት አሉ። የሰው ልጆች በመጻሕፍት ስለሚቃኑም የሠለጠኑ ሀገራት ውስጥ ባሉ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች ባነበቡት መጻሕፍት መጠን የእስር ዘመናቸው ይቀንሳል።
ጀፈርሰን ቀኑን ሙሉ ፕሮግራም አውጥቶ መጻሕፍት በማንበቡ ለአሜሪካ ነፃነትና የዴሞክራሲ መሠረት አስቀምጧል። አርክቴክትም፤ገበሬም ሆኖ ብዙ አልምቷል። የቨርጂንያ ዩኒቨርስቲን ሕንፃ ሳይቀር ነድፏል።
የፈረንሳዩ ናፖሊዮን ቦናፖርት፣ትልቁ እስክንድርና ሌሎቹም የአውሮፓ መሪዎች በአብዛኛው የንባብ ሱሰኞች ነበሩ። ወደ መንፈሳዊው ዐለም ድንኳኖች ገብተን ስናይ፣ የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት ሲሦ ያህሉን የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ እስር ቤት ሆኖ እንኳ እንዲላክለት የጠየቀው መጻሕፍትን ነበር።
ወደ ሀገራችን ጎራ ብለን የንባብና የመጻሕፍትን ጉዳይ ስንቃኝ፤...በንጉሡ ዘመን ምን ያህል ባለሥልጣናት ያነብቡ ነበር?...ካልን ጉዳዩ የአደባባይ ምስጢር ነው።ሥልጣን ላይ የተቀመጡት በአብዛኛው፣ትምህርቱም ንባቡም ያልነበራቸው፣ በአጥንት ቆጠራ ወንበር የተሰጣቸው ይበዙ ነበሩ።
ስለዚህ በኋላም የወንበራቸው እግር ሲንቋቋ እንኳ አልነቁም፤በዓለም ላይ ስለሚካሄዱት ለውጦችና አብዮቶች ፍንጭም አልነበራቸው።  ቀድመው የነቁት ጥቂቱ  ስለ ቀጣዩ ዘመን ዕጣና ነውጦች ቢነግሯቸውም፣ ለመስማትም ማወቅ ያስፈልግ ነበርና፣ ወታደሩ በዐመጽ መጥቶ ከሥር እስኪነቅላቸው ድረስ  የሚሆነውን አላወቁም ነበር።
እንደ ድንገተኛ ጎርፍ ከየካምፑ ተገልብጦ የመጣው ወታደራዊ መንግሥትም፣ ለዙፋን ሲበቃ አባላቱ ከፍተኛ መኮንኖችን እንኳ ያላካተተ ስለነበር በአብዛኛው ከዕውቀት ሩቅ ነበር። በንባብ የተሻሉ የሚባሉ ጥቂት ቢኖሩም የሚሰማቸው ስላልተገኘ፣የሰውን ጭንቅላት በዕውቀት ከማቅናት ይልቅ ማስወገድን የሚመርጡ ነበሩ። ስለዚህ የቀለም ቀንዶችን ሁሉ በጥይት አረር አነደዷቸው፤የነቃውንና የጠየቀውን ሁሉ ወደ መቃብር ሸኙት። የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ሚዛናዊነትን ያቀነቀኑ እንኳ እንደ ወላዋይ ተቆጥረው ተወገዱ።
ነገሩ “መካሪ የሌለው ንጉሥ” ሆነና የሥልጣን ዘመናቸውም በሚወድዱት ጠመንጃ ላይ የተንጠለጠለና ዕውቀት- ጠል ስለነበር አልዘለቀም። ይሁን እንጂ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም በራሱ ኪነትን ለሶሻሊዝም ግንባታና ለማኅበረሰብ ንቃተ- ሕሊና ማበልጸጊያ ይጠቀምበት ስለነበረና ለንባብ ጥሩ ግምት በመኖሩ በርካታ ቤተመጻሕፍት ተገነቡ። በወቅቱ የተጀመረው የቤተመጻሕፍት ግንባታ ቀስ በቀስ ንባብን ወደ ማኅበረሰቡ እያሰረጸ በመምጣቱ፣አርሶ አደሩ ሳይቀር  ንቃተ- ሕሊናው ከፍ ብሎ ታዬ።
ክፋቱ ግን ቀድሞ ሥልጣን ላይ የተንጠለጠለው ክፍል ባለበት ስለቆመ፣ሰላምን መከተልና ችግሮችን በንግግር መፍታትን እንደ ውርደት መመልከቱ አልቀረሜ። በመሆኑም ከታሪክ የሚማርበት ዕድል አላገኘምና ውድቀቱ ፈጥኖ ደረሰ።
ደርጉ ውስጥ ጥቂት የበሰሉ ሰዎች ቢኖሩም፤ ወደ መንግሥትነት የመጡት በመንጋ በመሆኑ ታሪክን አላነበቡም፤ አላጤኑም። ስለዚህም በታሪክ እንደምናውቃቸው አምባገነኖች ላይ የደረሰው ሁሉ ደረሰባቸው። ይህ ሁሉ የሆነው ዓለም በሥልጣኔ ማማ ላይ በወጣበት ክፍለዘመን ፤ሀገራት በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት በሚተዳደሩበት ዓለም ነበር።
ሌላው ቀርቶ “ቅይጥ ኢኮኖሚ” የሚል ሀሳብ ያቀረበውን ጓዳቸውን የጥይት ራት ያደረጉት ደርጎች፣ሥልጣናቸው ሊጨልም ደንገዝገዝ ሲል፣መልሰው “ቅይጥ ኢኮኖሚ”ቢሉም፣ ረፍዶ ስለነበረ ከውድቀት አልዳኑም። ጠመንጃ ድንበሩ አጭር፤መንገዱ ጠባብ ነበረና፤በጠመንጃ ተሰናብተው በየማረሚያ ቤቱ ታጎሩ፤በየፍርድ ቤቱ ቆሙ። ይሁን እንጂ ሁሉም የደርግ አባላት ወንጀለኛ አልነበሩም፤ መጻሕፍት የገራቸው የተለየ ሐሳብ አቅርበው ሰሚ ያጡትም፣ ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ ሆነው ዋጋ ከፈሉ።
ሁሌም የኛ ሀገር ፖለቲካ በአብዛኛው አሳዛኝ ገጹ ይበዛልና  ፖለቲካው ከሰው በላይ ይመለካል። ለፖለቲካ ተብሎ ሰው ይጠፋል፤ታሪክ ይናዳል። ሀቁ ግን እንዲያ አይደለም፤ ፖለቲካ  ለሰው ነው። ሰው የፖለቲካ ጌታ እንጂ ፤ፖለቲካ የሰው ጌታ አይደለም።የፖለቲካ ፈጣሪ ሰው እንጂ ፖለቲካ የሰው ፈጣሪ አይደለም።
ባይዘወተርም አንዳንዴ ንባብ አላቸው የሚባሉ የድሃ ሀገር መሪዎች ሳይቀር በፖለቲካ ተውጠው፣ወደ “ሰውነት” ከፍ ያለ ሰብዕናቸው በፖለቲካ ዳዋ ተውጦ፣እጃቸውን ለወንበር፣ነፍሳቸውን ለጊዜያዊ ተድላ ይሰጣሉ። ይህንን “የድህነታችን ውጤት ነው” ብንል እንኳ ንባብ በድህነት መሸነፉ አካባቢያዊ እንጂ ተፈጥሮአዊ እንዳልሆነ እንገነዘባለን።
ባለፈው ዘመነ-ኢሕአዴግ አንባቢ ከሚባሉት የዘመኑ ባለሥልጣናት አንዱን የሚቀርብ ሰው፤ “እባካችሁ ሕዝቡ እንዲያነብብ አድርጉት”ቢለው፣ “አሁን የሕዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ዳቦ ነው” እያለ ደጋግሞ አጣጣለበት። ሕዝቡ ዳቦ ካገኘ ወደ ወንበራችን አያይም ብሎ ይመስለኛል። ካነበበ ደግሞ የመብት ጥያቄ ያነሳል፤ይጠይቃል ነው ነገሩ። ግን ይህ መላ ሥልጣናቸውን  ለዘላለም አላኖረውም።
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ያነበበ ሰው ያመዛዝናል፤ ቢቃወም እንኳ እንደ ሰው እንጂ እንደ አውሬ ያገኘውን ሁሉ አይዘነጥልም። ግን ሁሌም የአፍሪካ መሪዎች ይህንን እውነት ይሸሹታል፤እነርሱም ሆኑ ሕዝባቸው በንባብና ዕውቀት ዓይናቸው እንዲበራ መሻት የላቸውም። ስለዚህ ጠመንጃን በሚያመልኩና በሚሳለሙ፣መሰሎቻቸው የሥልጣን ጥም ባሰከራቸው የዐሥርና የመቶ አለቆች በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ይወገዳሉ።
እንደዚህ ድንቁርና ከተጫጫናት አህጉር እንኳ ስናወራ፣በንባብ ልምድ የማይበልጠን ሀገር የለም። ከቅርብ ጎረቤቶቻችንን ጋር እንኳ ስንነጻጸር ልዩነታችን የትየለሌ ነው።
አዎ ብዙው የዓለም ክፍል እንደሚያምነው ማንበብ ያረጋጋል፤ያሰክናል፤በመነጋገር ወደ ማመን ያደርሳል። ንባብ ያሠለጠነው ሕዝብ ለሁሉም ነገር ወደ ጠመንጃ አይሮጥም። ለሚያነብቡ ጠመንጃ የመጀመሪያ ሳይሆን የመጨረሻ አማራጭ ነው።
ወደ ሀገራዊ ትኩረታችን ስንመለስ፣በዚህ ዘመን የንባብ ባሕላችን ለማሽቆልቆሉ  ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ።ከእነዚህ አንዱ የወረቀት መወደድና የታክስ መጨመር ሲሆን፣አሁን ደግሞ ይባስ ተብሎ ቫትም ተጀምሯል።
ይህን መስማትና ማየት ለሀገሩ ለሚያስብ ሰው የሚያምምና ግራ የሚያጋባ ነው።እንዴት አንባቢ በሌለበት ሀገር፣መጻሕፍት ላይ ጫና ይደረጋል? ሀገሩን ለማሳደግና ወደ ሥልጣኔና ብልፅግና መሥራት የማፈልግ መንግሥት “..በምን መንገድ አንባቢ እንፍጠር?” ይላል እንጂ እንዴት ንባብን ለማክሰም ሕዝብ ላይ ቀንበር ይጭናል?
የዕድል ይሁን የአጋጣሚ ነገር ሆኖ፣በዘመነ ኢሕአዴግ እነ አቶ በረከትን የመሰሉ አንባብያን በፖለቲካ ተውጠው፣ማንበብ እየወደዱ፣ለንባብ እንዳልራሩ ሁሉ፤በተራቸው እንደ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያሉ የንባብና የሥነጽሑፍ ወዳጅና ደራሲ፣ ስለ ንባብ ትንፍሽ  ያለማለታቸውና ለማገዝ አለመሞከራቸው በእጅጉ የሚገርም ነው።
ያ ብቻ አይደለም፤ጠቅላይ ሚኒስትሩስ ቢሆኑ፣ከመጻሕፍት ጋር ያላቸው ቅርርብ፣ ይህንን ያህል ንባቡ ወደ መቃብር እስኪወርድ የሚያስጨክን መሆን ነበረበት?..(እዚህ ላይ የአብርሆት ቤተመጻሕፍቱን አድናቆት ሳንረሳ)...በአጠቃላይ ሲታይ ነገሩ ግር የሚያሰኝ ነው።
ፖለቲካው የራሳቸው ጉዳይ ነው፤ የንባብ ድንኳናችን ሲደርቅ፣ጠብታ  ውሃ መንፈግ ግን ሀገርን ምድረበዳ ከማድረግ አይለይም። አሁንማ ይባስ ተብሎ መጻሕፍት የምንሸምትባቸውን መደብሮች አፍርሶ ተተኪ ቦታ ባለመስጠት፣ ንባብን መቃወም የሚመስል ድርጊት ታይቷል። ግን ማኅበረሰብን በዕውቀት  መገንባት አይጠቅምም?
በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርን የወሰደው እንቅልፍ ምን ያህል ከባድ ቢሆን ነው መጻሕፍት ቤቶች ፈርሰው፣መጻሕፍት መጠለያ ሲያጡ፣ደራስያን ነፍሳቸው ስታለቅስ ተኝቶ የሚያንኮራፋው?...ኧረ ንቁ!...ከመንግሥት ጋር መሟገት ሲገባው ማኅበሩ መተኛቱ የሚያስወቅሰው መሆኑን እኔ መናገር ያለብኝ አይመስለኝም።  ማኅበሩ የፖለቲከኞችን እጅ የመጠምዘዝ አቅም ባይኖረው እንኳ ባሉት ቀዳዳዎችና ዕድሎች ተጠቅሞ የንባብ ባሕሉን የሚያግዝበት መንገድ መፈለግ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
ለምሳሌ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ የፈረሱ የመጻሕፍት ሱቆች ከስፍራቸው ቢነሱ እንኳ፤በምትካቸው ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁና በተገጣጣሚ ሸክላዎች የሚሠሩ ሱቆችን እንኳ ከፍቶ፣ለማኅበሩ ገቢ ማስገኘት፤ ከዚያም በተጨማሪ ለአንባቢያን አቅርቦት መፍጠር የሚችል ይመስለኛል።
በአጠቃላይ ግን አንዲት ሀገር መጻሕፍት እንዳይታተሙ መንገዶችን ስታጠብብ፣መሸጫ ሱቆችን ስትዘጋ፤ ጨለማን እየጋበዘችና ድንቁርናን እያቀፈች መሆኑን ሁሉም ወገን ልብ ሊል ይገባል። ምክንያቱም የመጻሕፍትን አቅርቦት መጨመር ምክንያታዊ ትውልድን መፍጠር እንጂ ሾተል መዛዥ መቀፍቀፍ አይደለም። ስለዚህ መንግሥት፤ በተለይ የሚመለከታቸው አካላት ለነፍሳችን የሚሆን ምግብ ስለማዘጋጀትና የተዘጋጀውን ወደ ሕዝብ የምናደርስበትን ማሳለጫ በሚመለከት ሊያስቡበት ይገባል።
ቶማስ ጀፈርሰን የቤት ሠራተኛው፤ “ጌታው፤ ቤትዎ ተቃጠለ” ቢል፣ “መጽሐፎቼ ተርፈዋል?” ያለው፣ ሀገር ሠሪ ሰብዕናው  የተሠራው በመጻሕፍት እንደሆነ ስለሚያውቅ ነበረ።
****
“በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርን የወሰደው እንቅልፍ ምን ያህል ከባድ ቢሆን ነው መጻሕፍት ቤቶች ፈርሰው፣ መጻሕፍት መጠለያ ሲያጡ፣ደራስያን ነፍሳቸው ስታለቅስ ተኝቶ የሚያንኮራፋው?...ኧረ ንቁ!...”





Read 555 times