በፐርሺያ ስለፐርሺያ የጥንት ንጉሥ የሚነገር አንድ አፈ - ታሪክ አለ፡፡
እንዲህ ይላል፡፡
አንድ ጊዜ የንጉሡ ሁለት ባለሟሎች ባጠፉት ጥፋት ዙፋን ችሎት እንዲቀርቡ ይታዘዛሉ፡፡ ከዚያም ያጠፉት ጥፋት ፍርዱ እንደሚከተለው ተነገራቸው፡፡
ንጉሱ፤ ተደላድለው ዙፋናቸው ላይ ከተቀመጡ በኋላ፡-
“ያጠፋችሁት ጥፋት ፍፁም ምህረት የማይደረግለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለታችሁም በሞት እንድትቀጡ ተወስኗል፡፡ ይግባኝ ማለት ወይም የመሰላችሁን አስተያየት መስጠት ትችላላችሁ” አለ፡፡
ከሁለቱ ፍርደኞች አንደኛው ንጉሱ ከልብ የሚወድዱት ፈረስ እንዳላቸው ስለሚያውቅ፤
“ንጉስ ሆይ! አንድ ዓመት ይሰጠኝና የሚወድዱት ፈረስዎን በአየር ላይ እንደ ወፍ መብረር ላስተምረው፡፡ ይህንን ካደረግሁኝ ነብሴን ይምሩልኝ ከሆነ ማስተማሬን ልቀጥል” አለና ተማጠነ፡፡
ንጉሱ፤ በአንድ ወገን የሚወድዱት ፈረሳቸው መብረር መቻል፣ በሌላ በኩል የጥፋተኛውን ፍርድ መሻር፣ በጣም ካማለላቸው በኋላ፣ በአለም ላይ የሚበር ፈረስ ያለው ንጉስ እሳቸው ብቻ መሆናቸውን አሰቡና ልባቸውን ሞቅ አላቸው፡፡ በመጨረሻም፤
“ይሁን፤ ፈረሴን በአየር ላይ መብረር አስተምርልኝ! አንድ ዓመት ሰጥቼሀለሁ” አሉት፡፡
ይህን ወስነው እንደሄዱ ሁለቱ ሰዎች መወያየት ጀመሩ፡፡
ሁለተኛው ፍርደኛ - “ስማ፤ አብደሃል እንዴ? ፈረስ በአየር ላይ በምንም አይነት እንደማይበር ታውቃለህ፡፡ በምን ተአምር ፈረሱን በአየር መብረር ልታስተምረው ነው? አንድ አመት እሩቅ መሰለህ? የማይቀረውን ነገር ቀኑን ማስተላለፍስ ለምን ይጠቅምሀል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
አንደኛው ፍርደኛም፤
“ይህንን ያደረግሁት በአራት መንገድ ነፃ እወጣለሁ የሚል ተስፋ ታይቶኝ ነው” አለና መለሰ፡፡
“አራት መንገድ? ለመሆኑ ንጉሱን የሚያሳምን አንድስ መንገድ ይገኛል? ስማ፤ ንጉሱ የሚለቅቁህ ፈረሳቸውን ለማብረር ከቻልክ ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ ምን ምን መንገድ ታይቶህ ነው?”
አንደኛው ፍርደኛም እንዲህ ሲል መለሰ፡-
“አንደኛ፤
በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ንጉሱ እራሳቸው ሊሞቱ ይችላሉ፡፡
ሁለተኛ፤
እኔ እራሴ ልሞት እችላለሁ፡፡
ሦስተኛ፤
ፈረሱ ሊሞት ይችላል፡፡
አራተኛ፤
ማን ያውቃል፤ ምናልባት ፈረሱን በአየር ላይ መብረር ላስተምረው እችል ይሆናል” አለ፡፡
* * *
ከእንዲህ ያለ አጣብቂኝና ውጥረት ሀገራችንን ይሰውራት፣ ማለት ደግ ነው፡፡ በማንኛውም ጉዳይ አማራጭ ማግኘት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ አማራጮች ሌላ አማራጭ ቢፈልጉም እንኳ የሚቻለውን ጥረት አድርጎ መፈለጉን መቀጠሉን ሁኔታዎች ግድ ይላሉ፡፡ ከአማራጮች መካከል መደራደር አንዱ መንገድ ነው፡፡ ብዙ ነገሮች እጅግ በተወጣጠሩ ሰአት ረጋ እና ሰከን ብሎ የሚያስብና መውጫ መንገዶችን የሚያሰላ ግለሰብ ወይም ቡድን ማግኘት መታደል ነው፡፡ በጣም አስፈላጊም ነው፡፡
የመጨረሻ ውጥረት ቢኖርም እንኳ ማረጋጋትና ማርገብ ሁሌም ከአማራጮች መካከል የማይቀር ነው፡፡
ዛሬ ሀገራችን ባለችበት ሁኔታ ሀገርና ህዝብን የማረጋጋት ሂደት ተቀዳሚ ነው፡፡ ሰላም የሁሉ ማሰሪያ ነው፡፡ ምንም እንኳን ግጭትና ፍጭት የሰፈነበት የአሁኑ ሁኔታ፣ የህዝቡን ብሶትና ምሬት የፈጠሩት ሁኔታዎች የነባራዊና ህሊናዊ መንስኤዎች ጥምርና ድምር ቢሆንም፣ ህዝብ የሚለውን ሳይታክቱ መስማትና የልብ - ትርታውን ማዳመጥ፣ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ሀሳብን መግለፅ የህዝብ መብት ነው፤ የሚለውን ቋሚ መርህ ከልብ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ህዝብ መቼም ቢሆን መች “ላይ ላዩን ይነጋገራሉ፣ ልብ ለልብ ይተዛዘባሉ” እያለ ጀምሮ፣ ከሮና መርሮ የብስጭትና ምሬቱ ጫፍ ላይ እስኪደርስ መጠበቅ ኋላ ማጣፊያው እንዲያጥር ያደርጋል፡፡
የህብረተሰብ ድርና ማግ በረዥም ሂደት ውስጥ የተሸመነ እንደመሆኑ፤ የተጠራቀሙ ብሶቶች ያልተፈቱ ችግሮች፣ መናቅና መግፋት፣ እንዲሁም ሁኔታዎችን እንደማያድጉ አድርጎ ማሰብ፤ ውሎ ሲያድር ውሉ ከማይታወቅ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊከት እንደሚችል ከዛሬው ሁኔታ ሌላ አስተማሪ አይኖርም፡፡ ዴቪድ ፖል ቴሩ የህዝብ አልታዘዝ ባይነት በሚለው ታዋቂ ፅሁፉ፤ “የህዝብ አልታዘዝ - ባይነት ማለት የሲቪል ህግጋት ወይም ድንጋጌዎች አልቀበል ወይም አልታዘዝም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ተቃውሞ የሰላማዊ ተቃውሞን ወይም የሀይል - አልባ ተቃውሞን ቅርፅ የያዘ ነው፡፡ ይህ አይነት ተቃውሞ የሚያካሂዱ ዜጎች ህግን የማያከብሩት ኢ-ፍትሀዊነት አለ ብለው ከልብ ሲያምኑና እንለውጠዋለንም ብለው ተስፋ ሲያደርጉ ነው” ይላል፡፡
እስከዛሬ በነበረችው ኢትዮጵያ “ባለቤቶች ሲሸሹ፣ ባለቆዳዎቹ ይዋጋሉ” የሚባለው አይነት ሁኔታ ውስጥ የቆየው ህዝብ ወደፊት አምርቶ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ራሱ ወደ ማወቅ ሲጓዝ መታየቱ ታሪካዊ ነው፡፡ ልዩ እመርታም ነው፡፡ ይህ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ቀና ብሎ መብቴን ነፃነቴን ስጠኝ የሚልበት ብቻ ሳይሆን መብቱም ነፃነቱም የእኔ ነው፡፡ የሚልበት ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል እያንዳንዱ ፓርቲ ሊገነዘበው ይገባል፡፡
በተደጋጋሚ በዓለም ያየነው የፖለቲካ ታሪክ “ሰው እስኪጠላህ እድሜ አይስጥህ” በሚለው ተረት የሚጠቃለል እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ በዚህ እረገድ ሁሉም እራሱን ቢፈትሽ መልካም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እርጋታ ያስፈልጋል፡፡ በጥሞና የሄዱበትንና የሚሄዱበትን ሁሉ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ካጠፉ ለመታረም፣ ከተቃረኑ ለመደራደር የፀና ልቦና የሰለጠነ አእምሮ ያስፈልጋል፡፡
ህዝብ የታሪክ ወንዝ ነው፡፡ መንግሥታት ይለወጣሉ፡፡ መሪዎች ይቀየራሉ፡፡ የሀገሪቱ ነገ በህዝቡ ዛሬ የሚወሰን ነው፡፡
የህዝቡ ዛሬ ደግሞ በሁላችንም እጅ ላይ ነው፡፡ ህዝቡን ማዳመጥ ፣ ጎንበስ ብሎ የልብ-ትርታውን ማወቅ እና መረዳት ግዴታችን ነው፡፡ “ጠላ እጠጣለሁ ብለህ ወንዝ እረግጠህ አትሻገር” መባሉ ለዚህ ነው፡፡ ሰላም የዚህ ሁሉ ቁልፍ ይሁን፡፡