Saturday, 08 February 2025 20:40

“መንግሥት የዝርፊያ ቡድን ነው” ብለዋል - ሃቭየር ሚሌ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

በኮቪድ ዘመን የተጀመረው “ቤት ሆኖ መሥራት” የሚሉት ፈሊጥ እስከ ዛሬ አልተቋረጠም። በርካታ ኩባንያዎች አሠራራቸውን አስተካክለዋል። ሠራተኞች ወደ ሥራ ቦታ እንዲመለሱ አድርገዋል። ብዙ የመንግሥት ሠራተኞች ግን፣ ዛሬም ድረስ ወደ ቢሮ አይመጡም።
ዶናልድ ትራምፕ ይህን የመታገሥ ፍላጎት እንደሌላቸው የተናገሩት ገና ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ነው። “ከቤት ሆኖ መሥራት” የሚባል ነገር ካሁን በኋላ አይኖርም ብለዋል።
ነገር ግን፣ “ቢሮ የማይገባ ሠራተኛ ይባረራል” አላሉም።
ይልቅስ፣ ወደ ቢሮ መመለስ የማይፈልግ ሠራተኛ፣ በነጻ ደሞዝ እንደሚከፈለው ቃል ገብተዋል።
ለስምንት ወር በነጻ ደሞዝ ይወስዳል። ከዚያ በኋላ በዚያው ከሥራ ይሰናበታል።
በዚህ ዘዴ፣ ከ100 ሺ በላይ የመንግሥት ሠራተኞችን ለመቀነስ አስበዋል - ጋሽ ትራምፕ። ሠራተኞች ወደ ቢሮ ሳይመጡ በዚያው እንዲቀሩ መገፋፋት ይቻላል የሚል ተስፋ አድሮባቸዋል።
በእርግጥ የመከላከያና የፖሊስ ተቋማት የዚህ “ዕድል” ተጠቃሚ አይሆኑም ተብሏል። ወይም ደግሞ “የቅነሳ ኢላማ” አይሆኑም ብለን ልንገልጸው እንችላለን።
“ቀኝ ዘመም ፖለቲካ” ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ብቅ ከሚሉ የሐሳብ ዝንባሌዎች መካከል አንዱ፣… “መንግሥትን መቀነስ” የሚል ሐሳብ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ፣ “የመንግሥት ሠራተኞችን የመቀነስ ፍላጎት” ይመጣል።
መንግሥት ከልክ በላይ ተለጥጧል፣ አብጧል፤ ደልቧል… ብለው ያስባሉ እነ ዶናልድ ትራምፕ፣ በተለይ እነ ሃቭየር ሚሌ።
መንግሥት አለቅጥ ሲስፋፋና ሲንሰራፋ፣ መዓት ቢሮዎችንና ቅርንጫፎችን ሲያቋቁም፣ ሠራተኞችን በገፍ ሲቀጥር… የዕለትና የዓመት ወጪው ለከት ያጣል። በዜጎች ላይ የታክስ ሸክም እየጫነ ኪሳቸውን ያራቁታል። ታክስ አልበቃ ሲለው ከዓመት ዓመት እየተበደረ አገሬውን ለዕዳ ይዳርጋል። በየዓመቱ ለወለድ ይገብራል።
የአሜሪካ መንግሥት በየዓመቱ ለወለድ ብቻ 800 ቢሊዮን ዶላር እስከመክፈል ደርሷል።
ለነገሩ እስከ ዓምና ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ለወለድ ብቻ እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ሲከፍል አልነበር? በኢትዮጵያ አቅም አስቡት።
መንግሥት ሲንሰራፋና ወጪው ሲያብጥ፣ በታክስ ጫና ዜጎችን ከማራቆት አልፎ፣ ያለ ሐሳብ እየተበደረ ተጨማሪ ወጪ ይፈጥራል - በብድር ወለድ አገርን ያደኸያል።
መቼም የትኛውም መንግሥት ቢሆን፣ በዚህ መንገድ ብዙ መቀጠል አይችልም።
የሚያብጥ መንግሥት፣ በገፍ የሚቀጠር ቢሮክራሲ፣ እንደ አሸን የሚፈለፈል ወጪ፣ በየዓመቱ የሚቆለል በጀት… በአንድ ወገን ዜጎችን በታክስ እያራቆተ፣ በሌላ ወገን በብድር ብዛት የወለድ ወጪ እየጨመረ… በዚሁ መንገድ መቀጠልና መዝለቅ ሲያቅተው ሌላ ምን አማራጭ አለው?
የገንዘብ ሕትመትን በላይ በላዩ ማጧጧፍ ይጀምራል። የአገሪቱ ዓመታዊ ምርት ሳያድግ የአገሪቱ ገበያ በገንዘብ ሕትመት እንደጉድ ሲጥለቀለቅ፣ የዋጋ ንረት ይግለበለባል። ኢኮኖሚው ይቃወሳል፤ የዜጎች ኑሮ ይናጋል። የአገር ኢኮኖሚ መቃወሱ አይገርምም። ኑሮ መናጋቱ አይደንቅም።
የኢኮኖሚ ችግርንና ድህነትን በገንዘብ ሕትመት መፍታት ቢቻል ኖሮ፣ የዕውቀት ችግርና መሃይምነትን በዲግሪ ሕትመት መፍታት ይቻል ነበር ይላሉ - የአርጀንቲናው ፕሬዚዳንት ሃቭየር ሚሌ።
በእርግጥ የግዙፍ መንግሥታት ሀጢአት፣ በታክስ ብዛት ኢኮኖሚ ማዳከማቸው ወይም በገንዘብ ሕትመት ሳቢያ የዋጋ ንረት እየፈጠሩ የዜጎችን ኑሮ ማጎሳቆላቸው ብቻ አይደለም።
መንግሥት ራሱ የሥራ እንቅፋት ነው፤ ለዜጎችም ምቀኛ ነው ብለው የሚያምኑት ሃቭየር ሚሌ፤ የመንግሥት ሀጢአት ለቁጥር እንደሚያስቸግር ይገልጻሉ።

መፍትሔው “የመንግሥት ቅነሳ” ነው።
የመንግሥት ቅነሳ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ማፍረስና ቁጥራቸውን መቀነስ ነው። የመንግሥት ሠራተኞችንና የመንግሥት ወጪዎችን መቀነስም ነው!
ዶናልድ ትራምፕ ብዙ ለመቀነስ አስበዋል። ለመነሻ ያህል ግን፣ ቤት መዋል የለመዱ ሠራተኞች በዚያው እንዲቀሩ በማበረታታት ከ100 ሺ በላይ ሠራተኞችን ለመቀነስ ተስፋ አድርገዋል።
የመንግሥት ወጪም ይቀንሳል። በየዓመቱ በትንሹ 100 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለመቀነስ የሚረዳ ዕቅድ ነው ተብሎለታል።
“ከቤት ሆነው ሲሠሩ” የነበሩ ብዙ የመንግሥት ተቀጣሪዎች፣ አሁን በየዕለቱ ወደ ቢሮ መግባት ሊያስጠላቸው ይችላል። ስንቶቹ ሠራተኞች የ8 ወር ነጻ ደሞዝ፣ እንዲሁም የጡረታ ክፍያዎችን ተቀብለው በዚያው ለመሰናበት ይወስኑ ይሆን? እስጀ ኀሙስ ድረስ የተገኘው መረዳ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ 40 ሺ ሠራተኞች ወደ ቢሮ ሳይመጡ በዚያው ለመቅረትና ከሥራ ለመሰናበት መርጠዋል። እንደታሰበው ባይሆንም ብዙ ናቸው። ግን ለዶናልድ ትራምፕ በቂ አይደለም።
ብዙ ሺ ሠራተኞች ከሥራ ቢሰናበቱም እንኳ፣ ሌሎች ከ2 ሚሊዮን በላይ ሠራተኞች ወደየ ቢሯቸው ማምራታቸው አይቀርም። ወደዱም ጠሉም… ከሥራ ለመሰናበት ካልወሰኑ በቀር፣ ቢሮ መግባት የግድ ነው ተብለዋል።
ለሠራተኞች የተሰራጨው ኢሜይል፣ ረዥም የማሰቢያ የማሰላሰያ ጊዜ አይሰጥም። የመንግሥት ሠራተኞች በዐሥር ቀን ውስጥ ውሳኔያቸውን ማሳወቅ እንደሚኖርባቸው ይገልጻል።
እና ደግሞ፣ “ከሥራ የመሰናበት ዕድል እንዳያመልጣችሁ!” የሚል የማበረታቻ ስሜት ይዟል። ወይም የማስፈራራያ!
ቢሮ ለመግባት ብትወስኑም እንኳ “ከቅነሳ ነጻ ትሆናላችሁ” ማለት አይደለም ይላል - ለሠራተኞች የተሰራጨው ማስጠንቀቂያ።
ቢሮ ገብተን ለመስራት ፍቃደኞች ነን ብትሉም እንኳ፣ “ቅነሳ አይነካችሁም” ማለት አይደለም። የተቀጠራችሁበት ተቋም አይፈርስም ብለን ቃል አንገባላችሁም ይላል - ደብዳቤው።
“At this time, we cannot give you full assurance regarding the certainty of your position or agency but should your position be eliminated you will be treated with dignity and will be afforded the protections in place for such positions” ይላል የትራምፕ አስተዳደር ማሳሰቢያ።
ማሳሰቢያው መንታ ዓላማዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ማለት ይቻላል።
“ከቤት ሆኖ መሥራት” የምትሉት ጨዋታ ከእንግዲህ አይሠራም። የቢሮ መግቢያና መውጫ ሰዓት እቆጣጠራለሁ። ቢሮ ካልገባችሁ… ደሞዛችሁንና ሥራችሁን ታጣላችሁ። ይሄ የመጀመሪያው መልእክት ነው። ዋናው መልእክት ግን ይሄ አይደለም።
“ሥራችሁን እንድትለቅቁ አበረታታለሁ። ሥራ ለመልቀቅ ከወሰናችሁ፣ ቢሮ ሳትገቡ ለ8 ወራት ደሞዝ እከፍላችኋለሁ። ቢሮ ለመግባት የሚወስኑ ብዙ ሠራተኞችንም ግን አሰናብታለሁ። ከመደበኛው ክፍያ ውጭ ሌላ ጥቅም አያገኙም። አሁን ከወሰናችሁ ግን፣ የ8 ወር ደሞዝ ተጨማሪ ክፍያ ይኖራችኋል። አሁኑኑ ብትወስኑ ይሻላችኋል። ይሄ ሁለተኛውና ዋናው መልዕክት ነው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የመንግሥት ሠራተኞችንና የመንግሥት ተቋማትን ለመቀነስ የፈለጉት፣ “ወጪ ለመቆጠብ” ብቻ አይደለም። ወጪዎችን መቀነስ አንድ ቁምነገር ነው።
ነገር ግን፣ መንግሥት አለልክ ሲስፋፋና ሲንሰራፋ፣ የዜጎችን ሥራ ያደናቅፋል። ኪሳራውም ዕጥፍ ድርብ ይሆናል ብለው ያስባሉ።

መንግሥት የስራ እንቅፋት! ለዜጎችም ምቀኛ!
ሁሉም የመንግሥት ዐይነት አይደለም ለዜጎች “አደናቃፊ ምቀኛ” የሚሆንባቸው። የዜጎችን ነጻነትና መብትን በማስከበር ላይ ብቻ ያተኮረ መንግሥት፣ የአገር በሽታ አይሆንም፤ ለዜጎችም የጎን ውጋት አይሆንባቸውም።
ትክክለኛ ሥራውን ትቶ አለቦታው ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር አገር ምድሩ ላይ የሚንሰራፋ ግዙም መንግሥት ግን፣ በሽታ ነው።
ግዙፍ መንግሥት፣ ወጪው ብዙ ስለሆነ፣ በታክስ ጫና የዜጎችን ኪስ ያራቁታል።
እንደገና ተመልሶ፣ አላስፈላጊ እልፍ አእላፍ ቁጥጥሮችን እያወጀ የዜጎችን ሥራ ያደናቅፋል።
በተንዛዛ ቢሮክራሲ አምራቾችን ሌት ተቀን ይነዘንዛል።
ውኃ ቀጠነ እያለ ክስና ቅጣት ይጭንባቸዋል።
በአጭሩ፣ ግዙፍ መንግሥት የአገር ኢኮኖሚን የሚረብሽ፣ የዜጎችን ኑሮ የሚሸረሽር የእድገት ጠላት፣ መድኃኒት የሌለው ነቀርሳ ነው።
በፕሬዚዳንት ትራምፕ ዘንድ አድናቆትንና ሙገሳ ያገኙት የአርጀንቲናው ፕሬዚዳንት ሃቭየር ሚሌ በዚህ ይስማማሉ።
እንዲያውም መንግሥት የዝርፊያ ቡድን ነው፤ መፍትሔውም መንግሥትን የሚገዘግዝ ኀይለኛ መጋዝ ነው ይላሉ። መንግሥት ማለት፣ “ታክስ” በሚሉት የዝርፊያ ዘዴ ጡንቻውን እያፈረጠመ ዜጎች ላይ የሚፈነጭ ወንጀለኛ ቡድን ነው በማለት መንግሥትን ያወግዛሉ። ምን ይሄ ብቻ!
መንግሥት አለቅጥ የሚያትመው ገንዘብ “ከፎርጅድ ገንዘብ” አይሻልም የሚል ሐሳብ አላቸው - ሃቭየር ሚሌ።
ፎርጅድ ደግሞ “የውሸት” ነው። ወንጀል ነው። ጉዳት እንጂ እውነተኛ ጥቅም የለውም። ይህን ለማስረዳትም፣…
“ገንዘብ በማተም መበልጸግ ቢቻል፣ ዲግሪ በማተም ሞኝነትን ማጥፋት ይቻል ነበር” ይላሉ የአርጀንቲናው ፕሬዚዳንት ሃቭየር ሚሌ። በአውሮፓና በአሜሪካ መንግስታት ላይ ለማሾፍ አይደለም። ገንዘብ በማተም አርጀንቲና ብዙዎቹን አገራት ታስከነዳለች። ለዚያም ነው አርጀንቲና በዋጋ ንረት ከዓለም አገራት ቀዳሚ እየሆነች የነበረችው።
ሃቭየር ሚሌ የመጡት ይህን ሁሉ ቀውስ እንደሚያስወግዱ በመዛት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የገንዘብ ሕትመትን ለመግታት፣ የመንግሥትን በጀት ለመቀነስ፣ ኢንቨስትመንትን የሚያደናቅፉ የመንግሥት ቁጥጥሮችን ለማስወገድ ቃል በመግባት ነው የዛሬ ዓመት በምርጫ ያሸነፉት።

የሃቭየር ሚሌ ምልክት - ባለ ሞተር መጋዝ!
ለአገር ችግርና ለዜጎች መከራ መንግሥት መፍትሔ አይሆንም ባይ ናቸው - ፕሬዚዳንት ሃቭየር ሚሌ። ይልቅስ፣ “መንግሥት ነው ችግር የሆነብን” ይላሉ። መንግሥትን ለመገዝገዝና ጎራርደው ለመጣልም ዘወትር ይዝታሉ። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን አፈርሳለሁ ብለው ዝተዋል፤ ቃል ገብተዋል።
ለምርጫ ቅስቃሳ የተጠቀሙበት ትልቁ ምልክት “መጋዝ” ነው። እንደ ሞተር ብስክሌት የሚያጓራ ኦቶማቲክ መጋዝ።
እንዲያም ሆኖ፣ “ነገር ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆናል” ብለው አልተናገሩም። የአገር ችግሮችን የሚያስወግድ አንዳች ተዓምር እፈጥራለሁ ብለው ዜጎችን ለማሳመን አልሞከሩም። ይልቅስ፣…
የአርጀንቲና የኢኮኖሚ ቀውስ በእሽሩሩና በማባበያ መፍትሔ አያገኝም። የሚያስደነግጥ የሚያንዘፈዝፍ ሕክምና ያስፈልገዋል ሲሉ ነው ለዜጎች ቃል የገቡት። እኔ የማመጣው የኢኮኖሚ ሕክምና ያሳምማል እያሉ ነው ለምርጫ የቀሰቀሱት።
መንግሥት የአገርን ችግር ማቃለል ይችላል ብለው የምርጫ ዘመቻ አላካሄዱም። ይልቅስ፣ መንግሥት ነው የአገር ኢኮኖሚን የሚገድለው። መንግሥት ነው የዜጎችን ኑሮ የሚያመሳቅለው። መንግሥት ነው ጠላታችን እያሉ ነው የሰበኩት።
በምርጫ አሸንፈው ይሄውና መንግሥት ሆነዋል። ሥልጣን ይዘዋል። በመንግሥት ላይ ያላቸው ጥላቻ አሁን በርዶላቸው ይሆን?
ምኑም አልተነካም።
“በመንግሥት ላይ ያለኝ ጥላቻ ስፍር ቁጥር የለውም” የሚል መልስ ሰጥተዋል - ስልጣን ላይ አንድ ዓመት ሊሞላቸው በዋዜማው።
ዓመት ከሞላቸው በኋላም ሃቭየር ሚሌ ሐሳባቸውን አልቀየሩም። መንግሥት ዜጎችን የሚዘርፍ ወንጀለኛ ቡድን ነው። የኔ ስራ መንግስት መገገዝ ነው ብለዋል።
ለመሆኑ የታጠቁት መጋዝ ሰርቶላቸዋል? መንግሥትን ገዝግዘው ገንድሰው ጨረሱ? ገና ምኑም አልተነካም።
ከዓመት በፊት 18 የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ነበሩ። ሃቭየር ሚሌ ስልጣን ከያዙ በኋላ ግማሾቹ ፈርሰዋል። አሁን 9 የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ቀርተዋል። የመንግሥት በጀት በ30 በመቶ ተቀንሷል።
ነገር ግን አሁንም የመንግሥት አጥፊ እጆች ገና አልተሰበሰቡም ባይ ናቸው - ሃቭየር ሚሌ።
መንግሥት በእልፍ ዓይነት ቁጥጥሮች የአገሪቱን እጅና እግሮች አሳስሮ ይዟል። መተንፈሻ መላወሻ አሳጥቷቸዋል - ይላሉ ፕሬዚዳንቱ።
“የመንግሥት አጥፊ ሕጎች እልፍ ናቸው” ብለው ሲናገሩ እንዲሁ በደፈናው እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። አንድ ሁለት ተብለው በጽሑፍ እየዘረዘሩ 4000 ሕጎችንና ደንቦችን ቀድዳደው ለመጣል ነው የዛቱት።
እና ስንቱን ቀደዱ? ወይስ ስልጣን በያዙ ማግስት፣ በፊናቸው አዳዲስ ሕጎችንና ደንቦችን መፈልፈል ጀመሩ? “የመንግሥት የጥፋት እጆች” ተብለው ከተዘረዘሩት 4000 ሕጎችና ደንቦች መካከል፣ እስካሁን 900 ያህሉ ላይ “እርምጃ” ተወስዶባቸዋል። ነገር ግን፣ ገና ምኑም አልተነካም። 3100 ሕጎችን ለመደምሰስ ከጊዜ ጋር ሩጫ ይዘዋል - ሃቭየር ሚሌ። በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ለመጨረስ ነው የሚሮጡት።
ለምዕተ ዓመት የተጠራቀሙ የመንግሥት የጥፋት መዘዞችና የኢኮኖሚ ቀውሶች በአንድ ዓመት ውስጥ መፍትሔ አግኝተው አገሬው ከጉዳት አያገግምም። በአንድ ዓመት ወደ ብልጽግና መምጠቅ አይቻልም። ነገር ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ ከቁጥጥር ውጭ እየጦዘ የነበረው የዋጋ ንረት፣ ከ230 በመቶ ወደ 90 በመቶ ገደማ እየቀነሰ መጥቷል። በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ 40 በመቶ ይወርዳል ተብሏል።
በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ የአገሪቱ የዋጋ ንረት ከ10 በመቶ በታች ይሆናል ተብሎ እንደሚገመት የአይኤምኤፍ መረጃ ያመለክታል። ትልቅ ስኬት ይሆንላቸዋል። እስከዚያው የአርጀንቲናውያን ትዕግሥት ካላለቀ ነው ታዲያ። እስካሁን የፕሬዚዳንት ሃቭየር ሚሌ ተቀባይነት አልቀነሰም። እንዲያውም እየጨመረ ነው የመጣው። 60 በመቶ ዜጎች የፕሬዚዳንታቸውን ጥረት ይደግፉሉ ይላል - የሞርኒንግ ኮንሰልት የጥናት ሪፖርት።
ዶናልድ ትራምፕም በተወሰነ ደረጃ መንግሥትን ለመገዝገዝ እየጣሩ ነው። በዮኤስኤአይዲ ጀምረዋል። ከዚያም የትምህርት ሚኒስቴርን ለማፍረስ አቅደዋል።
በአዲስ ሹመት ለትምህርት ሚኒስትርነት የተዘጋጁት የትራምፕ ባለስልጣን፣ የመጀመሪያና የመጨረሻ ተግባራቸው ትምህርት ሚኒስቴርን መዝጋት ነው ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ ዘንድሮ አምርረው ነው የመጡት። ነገር ግን የአርጀንቲናው ፕሬዚዳንት ላይ የሚደርሱባቸው አይመስሉም። የትና የት!
ሃቭየር ሚሌ በመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ቀናት ውስጥ ነው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ግማሽ በግማሽ ያፈረሷቸው- (አፍራሽ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በማቋቋም)። ዶናልድ ትራምፕ ገና ብዙ ትግል ይጠብቃቸዋል።

Read 647 times