Saturday, 15 February 2025 21:09

“ለብቻዬ ስንጥር ከምሆን ከሀገር ጋር እርፍ ልሁን”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ ልዑል ከቤተ-መንግስት ራቅ ብሎ ወደሚገኝ አንድ ትልቅ ጫካ ሄዶ አደን ሲያድን ውሎ ወደ ቤተ-መንግሥቱ ሲመለስ አንድ ባላገር ያገኛል፡፡ ባላገሩ ልዑሉ ማን እንደሆነ አያውቅም ነበርና አንዳችም እጅ- ሳይነሳ፣ ሰላምታም ሳይሰጥ ዝም ብሎ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ልዑሉም የባላገሩ ነገር ገርሞት፣
“ሰማህ ወይ ወዳጄ፣ ለመሆኑ እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቃለህ ወይ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ባላገሩም፤ “በመንደራችን ባለው ጫካ ውስጥ በገዛ-ፈቃድህ ገብተህ አደን ስታድን እንደቆየህ አይቻለሁ፡፡ በሰላም የተቀመጡትን አዕዋፋት ስትረብሻቸው፣ እንስሳቱንም መጠጊያ ስታሳጣቸው የነበርክ ሰው መሆንህንም ተመልክቻለሁ” አለው፡፡
ልዑሉም፤ “ምን ስሰራ እንደቆየሁ ማወቅህ መልካም፡፡ ማንነቴንስ አውቀሃል ወይ?”
ባላገር፤ “አላውቅም፡፡”
ልዑሉ፤ “እንግዲያው ና ፈረሴ ላይ ውጣና አብረን ወደ ከተማ እንሂድ፡፡ ንጉሥ ማለት ምን እንደሆነ እዚያ ታውቃለህ” አለው፡፡
ልዑሉ ባላገሩን አፈናጦት ወደ ከተማ ይዞት ሄደ፡፡ በመንገድ ላይም “ንጉሥ ማለት የተከበረ፣ በሄደበት ቦታ ሁሉ ህዝብ እጅ የሚነሳው፣ መንገደኛው ሁሉ ቆሞ የሚያሳልፈው ትልቅ ሰው” ነው አለው፡፡
ከተማ ሲደርሱ፤ ህዝቡ ልዑሉን ሲያይ እየቆመ፣ እጅ እየነሳ አሳለፈው፡፡ ግማሹም አቤቱታውን አሰማ፡፡
ይሄኔ ልዑሉ ወደ ባላገሩ ዞሮ፤ “አሁንስ ንጉሡ ማን እንደሆነ አወቅህ?” ንጉሡ ማን ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ባላገሩም፤ “እንግዲህ፤ ወይ እኔ ወይ አንተ መሆናችን ነዋ” ሲል መለሰ፡፡
“ቡመራንግ” ማለት ይሄው ነው - ለሌላው የወረወሩት ቀስት ተመልሶ ወደ ራስ!
* * *
ህዝቦችና መሪዎች ሲጠፋፉ የሚፈጠረው ግራ-መጋባት አይጣል ነው! የክልል፣ የቀጠና፣ የወረዳና የቀበሌ መስተዳድር. የቢሮና የሚኒስቴር ኃላፊዎች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች ከህዝብ ሲርቁ ከላይ እንደተጠቀሰው ባላገር ማንነታቸው ብቻ ሳይሆን ምንነታቸውም ለህዝብ ግራ የሚገባበት ደረጃ ይደርሳል፡፡ ህዝቡ ልቡ ክፍት ነው፡፡ ህዝብ የነገሩትን ይሰማል፡፡ የተረጎሙለትን፣ እውነት ብሎ ይቀበላል፡፡ ያወጁለትን አዋጅ፣ ይበጀኝ ብሎ ያከብራል፡፡ የደነገጉለትን ህግ፣ በወጉ ሊተዳደርበት ይነሳል፡፡ ያወጡለትን መመሪያ እመራበታለሁ ብሎ ይስማማል፡፡ እቅዶች አምረው ሲያያቸው ሰምረው አገኛቸዋለሁ ብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ችግር የሚፈጠረውና ፀብ የሚመጣው፣ አንድም በተግባር ሲተረጎሙ በመዛባታቸው፤ አንድም ባወጣቸው ክፍል በራሱ በቃል-አባይነት እንደሌሉ ሲካዱ (ሲሻሩ) ነው፡፡ “Law-maker Law-breaker” እንዲል ፈረንጅ፡፡ ያስቡልኛል ያላቸው መሪዎችና ኃላፊዎች “አንተና አንቺ” ብለው ከናቁት፣ ያወጡትን መመሪያዎች በሱው ላይ መጠቀሚያ ካደረጓቸው፣ በግልፅ-ወገናዊነት “ሁሉም ህዝቦች እኩል ናቸው ካሉት፣ አንዳንዶቹ ግን የበለጠ እኩል ናቸው” ካሉት፣ አዋጅም፣ ህግም፣ መመሪያም እንደ ብዙዎቹ ተግባር-አልባ የፕሮጄክት ጥናቶች ያማሩ ወረቀቶች ሆነው ነው የሚቀሩት፡፡
እቅድ በሥራ ላይ መዋሉን ለማየት በሚል “የግምገማ” ስብሰባ፣ ጥንት የሚታወቀው “ድርጅታዊ አሰራር” ከተንፀባረቀ፣ “በእኔ አስተያየት” በሚል የግል ካባ ቡድናዊ ስሜት የሚያስተጋባ ከሆነ አመራርና ተመሪ መራራቁ የማይቀር አባዜ ይሆናል፡፡ ህዝብን በግምገማ ማረቅ አይቻልም! መሪዎችንና መመሪያዎችን እንጂ! እነሱም በጄ ካሉ! ግምገማውም የዕውነት ከሆነ! በአንድ ወቅት ስለ ሂስና ግለ-ሂስ ሲወሳ፤ ”ሂስ እያሉ ሌላውን መዘርጠጥ፣ ግለ ሂስ እያሉ ራስን ማዋረድ አይገባም!” ያሉ እንደነበሩ ያስታውሷል፡፡ መታረም መተራረም፣ መቻል፣ መቻቻል የሚቻለው ትክክለኛ ሂስ ማቅረብ ሲቻል ነው፡፡ እዚህ ጋ ድክመት አለ ተብሎ ሲጠቆም ነው፡፡
እርግጥ ነው መማማር ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ትምህርቱ መታወቅ፣ አስተማሪና ተማሪውም አስቀድሞ መለየት አለበት፡፡ ገጣሚው ኦማር ካህያም እንዳለው፤ “እኔስ ማነኝሳ ቁጭ ብዬ እምማር፤ አንተ ማነህ እሱን የምታስተምር፤” ሳንባባል ለመቀጠልና ለመማማርም መቻቻል አለብን፡፡ አለበለዚያ አንድ አዋቂ የሀገራችን ፀሐፌ-ተውኔት ባንደኛው ቴያትራቸው ውስጥ እንደፃፉት ይሆናል፡፡
አንዱ ገፀ-ባህሪ፤ “ምነው ተጠፋፋን ጓድ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ጓዱም ሲመልስ፤ “የአብዮት ጊዜ አይደለም እንዴ? መጠፋፋት መች ገደደ?!” ነበር ያለው፡፡
ይህን መሰል የፖለቲካ ሰዎች ፈሊጥ ህዝብ ውስጥ እንዲገባ መደረግ የለበትም፡፡ ህዝቦች እንዲኖሩ እንጂ እንዲጠፋፉ፣ እንዲቻቻሉ እንጂ እንዲናቆሩ መሆን የለባቸውም፡፡ ቅን ልቦና፣ ፅናትና ለሀገር ማሰብ ሲኖር መቻቻል ይቻላል፡፡ መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ መቻቻል ይችላሉ፡፡
ዋናው፤ “ለብቻዬ ስንጥር ከምሆን ከሀገር ጋር እርፍ ልሁን!” ማለት ብቻ ነው፡፡

Read 851 times