የአሜሪካ እርዳታ ነበር መተማመኛቸው። እርዳታው አሁን ሲቋረጥ፣ ምንድነው የሚደረገው? ምንድነው የሚሻለው?
የአውሮፓና የአሜሪካ እርዳታ ወደፊትም እየደረቀና እጃቸው እየራቀ መምጣቱ አይቀርም - ኢኮኖሚያቸው ተዛብቷል፤ የዜጎች ቅሬታ በዝቷል። ፖለቲካቸው ተበውዟል። እየተለወጡ ናቸው። መንገዳቸው የመሻሻልም የመበላሸትም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ተጨማሪ እርዳታ ወደ መስጠት የሚያመራ መንገድ አይደለም።
የአሜሪካና የአውሮፓ አየር ሲጨፈግግ፣ ኢትዮጵያና ሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ይጨልምባቸዋል። ዘንድሮ የአሜሪካ የእህል እርዳታ ሲቋረጥ፣ አገሬው ምን እንደሚሆን እንጃ። ከ2 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ምን እንደሚውጣቸው እንጃ። ከ10 ሚሊዮን በላይ የገጠር ነዋሪዎች ከዓመት እስከ ዓመት የሚያደርስ ምርት የላቸውም። በእርዳታ ነው የሚኖሩት - ከሞላ ጎደል በአሜሪካ እርዳታ።
የቱን ያህል አስጨናቂ ችግር እየመጣ እንደሆነ ብዙ ሰው የተረዳው አይመስልም። “ምን ይሻላል?” የሚል ሐሳብ ብዙ አይታይም። ደግሞም የምግብና የእህል እርዳታ ብቻ አይደለም ችግሩ። የኤችአይቪ መድሃኒት እንዲሁም የወባ መከላከያና ሕክምናም በአብዛኛው በአሜሪካ እርዳታ ላይ የተመሠረተ ነው። በUSAID የሚመጣው እርዳታ ብቻ ሲሰላ በየዓመቱ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው። ጦርነትና የዝናብ እጥረት በተባባሰበት በ2022 ደግሞ በUSAID የመጣው እርዳታ ከ2 ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል።
አሁን እርዳታው ድንገት ተቋርጧል። ለኢትዮጵያ የሚመደበው እርዳታ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ በUSAID በኩል ለበርካታ አገራት የሚሰራጨው እርዳታ በሙሉ ነው የታገደው።
በእርግጥ፣ የነፍስ አድን እርዳታዎች እንዳይታገዱ እናደርጋለን ብለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩብዮ ተናግረው ነበር። ነገር ግን፣ በቀላሉ የሚሳካ አይመስልም። እያንዳንዷን የእርዳታ ዓይነት አንድ በአንድ እየመረመርን ፈቃድ እንሰጣለን ነው የሚሉት። ግን እልፍ አእላፍ የእርዳታ ዓይነቶችን እየለቀሙ ለመመርመር ዓመት አይበቃቸውም። እንዴት ሊለቅሙት? እነማንስ ሊመረምሩት? የUSAID ቢሮዎች ተዘግተዋል። ሠራተኞችም ታግደዋል።
ለነገሩ በርካታ ሠራተኞች ከመንግሥት የመጣውን ውሳኔ በተቻለ መጠን ከመፈጸም ይልቅ፣ ለማንገራገርና በጎንዮሽ እንዳሰኛቸው ለመቀጠል መሞከራቸውም ነው ችግሩን ያባባሰው። ለዚያም ነው ድርጅቱን የመዝጋትና ሠራተኞችን የማገድ አጣዳፊ ትዕዛዝ የተላለፈው።
የእገዳ ትዕዛዞችን ለማስለወጥ ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡ ክሶች፣ እንዲሁም ከፍርድ ቤት የተሰጡ ጊዜያዊ ውሳኔዎች አሉ።
ቢሆንም ግን፣ የክስና የሙግት ምልልሶሽ፣ እዚያው አሜሪካ ውስጥ ተቀናቃኛ ፓርቲዎች የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር ሊጠቀሙበትና ለብሽሽቅ ሊገለገሉበት ይችሉ እንደሆነ እንጂ፣ ለነ ኢትዮጵያ ብዙም የተጨበጠ ፈጣን ለውጥ አያመጣም።
እና ምን ተሻለ? ምናልባት በኢትዮጵያ በኩል፣ የእርዳታ ዓይነቶችን በነጠላና በዝርዝር እየተገለጸ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለማቅረብ መሞከር፣ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ጋር የወዳጅነት ዝንባሌ ያላቸው ሁለት ሦስት ሴናተሮችን ለማነጋገርና ለማስረዳት መሞከር ያስፈልጋል - ሳይዘገይ፣ ሳይውል ሳያድር። በአንዳች ተአምር ነገሩ መፍትሔ እንደሚያገኝ መጠበቅና እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አያዋጣም። ተአምረኛና ፈጣን መፍትሔ ከተገኘ ጥሩ! ተአምር ይመጣል ብሎ መተማመን ግን ወይ ሞኝነት ወይ ስንፍና ነው።
የUSAID ነገር በቀላሉና በአጭር ጊዜ መፍትሔ እንደማያገኝ የገመቱ የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት፣ ለጊዜው ቢያንስ ቢያንስ የ1.8 ቢሊዮን ዶላር የእህል እርዳታ ለማስፈቀድ የሚረዳ ሕግ ለማርቀቅ እየሞከሩ ነው።
በUSAID ተመድቦ ከነበረው 45 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ እርዳታ ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ማስፈቀድ እንደ ትልቅ ለውጥ ላይቆጠር ይችላል። ነገር ግን፣ ለኢትዮጵያ ትልቅ ለውጥ ይኖረዋል። የእርዳታ እህል ዋና ተቀባይ አገር ኢትዮጵያ ናት። ለነገሩ በጦርነት ምክንያት ትልቅ እርዳታ ከተመደበላት ከዩክሬን በመቀጠል፣ የUSAID ትልቋ እርዳታ ተቀባይ አገር ኢትዮጵያ ናት። የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት የእህል እርዳታ ለማስፈቀድ ከቻሉ ለኢትዮጵያ አንድ እፎይታ ይሆናል።
ለዘለቄታው ግን፣ አስተማማኙ መፍትሔ “እርዳታ” አይደለም። ጦርነትንና ግጭትን ማስወገድ፣ ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው መመለስና ማቋቋም፣ በአጠቃላይም ኢኮኖሚን ማረጋጋትና ማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና የሥራ ዕድሎች እንዲበራከቱ የቢሮክራሲ ዕንቅፋቶችን ማስወገድ ነው - ሁነኛው መፍትሔ።
ሁነኛ መፍትሔ አንፈልግም ብንል እንኳ፤ ዋናዎቹ ለጋሽ አገራት፣ በተለይ አሜሪካ እንዲሁም የአውሮፓ አገራት እንደድሯቸው አይደሉም።
የኢኮኖሚ ሁኔታቸውና የፖለቲካ ድባባቸው እንደድሮ አይደለም - የአውሮፓና የአሜሪካ።
ተድላና ደስታ የበዛላቸው ይመስሉ የነበሩ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት ውስጥ፣ የኑሮ ቅሬታ እየተዛመተባቸው ነው። ፖለቲካቸው እየተበወዘ ነው።
አውሮፖና አሜሪካ ውስጥ፣ የነባሮቹ ፓርቲዎችና የባለሥልጣናት ነገረ ሥራ ለብዙ ዜጎች የሚያስደስት አልሆነም።
በፓርላማ ምርጫ ከ30 በመቶ በላይ ድርሻ የሚያሸንፍ ፓርቲ እየጠፋ ነው - ከእንግሊዝና ከአሜሪካ በስተቀር። ለነገሩ፣ “በሰፊ ብልጫ አሸንፈዋል” ተብለው ስልጣን የያዙት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር፣ ገና አንድ ዓመት ሳይሞላቸው አብዛኛው ሰው ጠልቷቸዋል። በዜጎች ዘንድ ያላቸው ድጋፍ 30 በመቶ አይሞላም። ከእንግሊዝ ዜጎች መካከል 60 በመቶ ያህሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደሚቃወሙ ይገልጻሉ።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ ቀስ በቀስ ተቀባይነታቸው እየቀነሰ ወደ 25 በመቶ ከወረደ በኋላ፣ ስልጣን ላይ የመቆየት ተስፋቸው እንደከሰመ ገብቷቸዋል። ስልጣን ለመልቀቅ ወስኛለሁ ብለዋል።
ከ20 በላይ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት ውስጥ የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ከስዊዘርላንድና ከአሜሪካ በስተቀር ሌሎቹ አገራት መሪዎች በሙሉ በዜጎች ተጠልተዋል። ከሚደግፋቸው ይልቅ የሚቃወማቸው ሰው ይበዛል።
የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ትንሽ ይሻላሉ - ወደ 40 በመቶ ገደማ ድጋፍ አላቸው።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደለን፣ የስልጣን ዘመናቸውን ያጠናቀቁት በአሜሪካ ምድር ታይቶ በማይታወቅ ከፍተኛ ተቃውሞ በማስተናገድ ነው። የነበራቸው ድጋፍ 37 በመቶ ብቻ ነበር።
የጀርመኑ ቻንስለርና የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ግን ከሁሉም የባሰባቸው ሆነዋል። በዜጎች ዘንድ ያላቸው ድጋፍ 20 በመቶ አይሞላም። ከዚያም በታች ወርዷል እንጂ። ከፈረንሳይ ዜጎች መካከል 75 በመቶ ያህሉ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን እንደሚቃወሙ ይገልጻሉ። የሚደግፉ ደግሞ 18 በመቶ ብቻ።
የጀርመኑ ቻንስለር 19 በመቶ ዜጎች ይደግፏቸዋል። 75 በመቶ ዜጎች ይቃወሟቸዋል።
ምንድነው ነገሩ? የመኪና ፋብሪካዎች መዘጋት፣ የበሽታውን ምልክት ይጠቁመናል።
የኑሮ ጉዳይ ነው ብዙዎቹን የሚያማርራቸው። እ.ኤ.አ በ2008 ከፈነዳው የኢኮኖሚና የፋይናንስ ቀውስ ወዲህ የአውሮፓና የአሜሪካ ኢኮኖሚ ላለፉት 20 ዓመታት ምንም ጤና አላገኘም። ከዚያ በኋላ ደግሞ የኮቪድ ወረርሽኝ ተደረበበት። ዓመት ሙሉ ቤት ቆልፎ ፋብሪካዎችን ዘግቶ በመቀመጥ መፍትሔ የሚመጣ ይመስል ኢኮኖሚያቸውን ይብሱኑ አመሳቀሉት። በዚያ ላይ እንደዘበት ገንዘብ እያተሙ አገሬውን በድጎማ ማንበሻበሽ ጨመሩበት። በዋጋ ንረት የዜጎችን ኑሮ አናጉት።
የኢኮኖሚ በሽታው ሥረ መሠረት ግን ዕድሜው ረዥም ነው። በቀስ በቀስ ከእግራቸው ሥር እየተሸረሸረ በትንሽ በትንሹ ሲሸሽ ወዲያውኑ መዘዙ ጎልቶ ላይታይ ይችላል። እየተቦረበረ እየተናደ ሲመጣ ነው በግላጭ የሚታየው። ለተመልካች ያስደንቃል። ለደረሰባቸው ደግሞ ያስቆጣል።
የዛሬን አያድርገውና ከ65 ዓመት በፊት፣ ዋናዎቹ የመኪና አምራች አገራት፣ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን ነበሩ።
እ.ኤ.አ 1960 የመኪኖች ምርት ብዛት
1 አሜሪካ 8 ሚ.
2 ጀርመን 2 ሚ.
3 እንግሊዝ 1.8 ሚ.
4 ፈረንሳይ 1.4 ሚ.
5 ጣሊያን 0.6 ሚ.
በዓለም ዙሪያ 16 ሚ.
16 ሚሊዮን መኪኖች መካከል 14 ሚሊዮን ያህሉ በአምስቱ አገራት ውስጥ ነበር የተመረቱት። 85 በመቶ ያህል መሆኑ ነው። የአሜሪካ ድርሻ ብቻ ሲታይ፣ 50 በመቶ ገደማ ነበር።
ምን ዋጋ አለው? የአሜሪካና የአውሮፓ ሩጫ እንደ አጀማመራቸው አልቀጠለም። ካልጠበቁት አቅጣጫ አስደንጋጭ ተፎካካሪ መጣባቸው - የጃፓኑ ቶዮታ።
በ1960ዎቹ ነው ቶዮታ የመኪና ገበያውን መቆጣጠር የጀመረው። ጃፓን በ1970 ብዙዎቹን የአውሮፓ አገራት በመቅደም ከአሜሪካ በመቀጠል የምትጠቀስ ሆነች።
እ.ኤ.አ 1970 የመኪኖች ምርት ብዛት
(በሚሊዮን)
1 United States 8.3
2 Japan 5.3
3 Germany 3.8
4 France 2.8
5 United Kingdom 2.1
6 Italy 1.9
World 29.4
አሜሪካና አውሮፓ በጃፓን የደነገጡት ያነሰ ይመስል፣ እንደገና የደቡብ ኮሪያ ፉክክር ተጨመረባቸው።
የዛሬ 25 ዓመት በፈረንጆች አዲስ ሚሌኒየም በመላው ዓለም የተመረቱት መኪኖች 58 ሚሊዮን ናቸው። ጣሊያንና እንግሊዝ ወደ ታች እየተንሸራተቱ በቦታቸው ደቡብ ኮሪያ እየገነነች የመጣችበት ዘመን ነው - በሃዩንዳይ መኪኖች።
እ.ኤ.አ 2000 የመኪኖች ምርት በሚሊዮን
1 United States 12.8
2 Japan 10.1
3 Germany 5.5
4 France 3.3
5 South Korea 3.1
World 58.4
በዚህ አላበቃም። እ.ኤ.አ በ2005 የአውሮፓ አገራትን ወደ ታች የምታወርድ ሌላ አገር መጣች - ቻይና።
በእርግጥ፣ በቻይና የሚመረቱት መኪኖች የሌሎች አገራት ሞዴሎች ናቸው። በጃፓንና በደቡብ ኮሪያ እንደታየው አይደለም። እንደ ቶዮታና እንደ ሃዩንዳይ፣ ከቻይና ምድር የበቀለ ዝነኛና ተወዳጅ የመኪና ሞዴል ለጊዜው ጎልቶ አልወጣም። ቢሆንም ግን፣ የቻይና ግሥጋሤ ቀላል አይደለም። በመኪኖች ምርት ብዛት ቻይና ከቀዳሚዎቹ አገራት ተርታ የተሰለፈችው የዛሬ 20 ዓመት ነው።
እ.ኤ.አ 2005 የመኪኖች ምርት በሚሊዮን
1 United States 11.9
2 Japan 10.8
3 Germany 5.8
4 China 5.7
5 South Korea 3.7
World 66.5
የአሜሪካና የአውሮፓ ፋብሪካዎች ወደ ቻይና የሸሹት ወደው አይደለም!
የዓለማችን ዋና ዋና የመኪና ሞዴሎች በሙሉ ቻይና ውስጥ በርካታ ፋብሪካዎችን ከፍተዋል። አውሮፓና አሜሪካ ውስጥ የሠራተኞች ደሞዝ ከፍተኛ ነው። በዚያ ላይ በየዓመቱ የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግ ያለ እረፍት የሚቀሰቅሱና ለአድማ የሚያነሳሱ ማህበራት አሉ።
በርካታ ፖለቲከኞችም ሠራተኞችን የጠቀሙ እየመሰላቸው ለሠራተኛ ማህበራት ወግነው በመኪና ኩባንያዎች ላይ ጫና ያሳድራሉ።
እጠቅማችኋለሁ እያለ መጉዳት፤ አድናችኋለሁ እያለ መግደል እንዲህ ነው። ተጨማሪ ደሞዝ አስገኝላችኋለሁ እያለ ሥራ አሳጣቸው።
ኩባንያዎቹ በጠንካራና በትክክለኛ አቋም መከራከር አልቻሉም፤ “የሥራ ብቃትን እያየን እንጂ በጅምላ ደሞዝ አንጨመርም” ብለው የመከራከር ድፍረትና ፍላጎት አልነበራቸውም። በአቋራጭ መንገድ ከችግር ማምለጥ ቀለላቸው።
የአውሮፓና የአሜሪካ ፋብሪካዎችን እየዘጉ፣ በቻይና አዳዲስ ፋብሪካዎችን በብዛት ከፈቱ።
በእርግጥም ያሰቡት ነገር ለጊዜው ተሳክቶላቸዋል። ቻይና ውስጥ በአነስተኛ ደሞዝ መኪኖችን በብዛት ለማምረትና ትርፋማ ለመሆን ችለዋል። ግን ለጊዜው ብቻ ነው። በቻይና ሕግ መተማመንና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እየፈጠሩ መሥራት አልቻሉም። እናም ቀስ በቀስ መዳከማቸውም አልቀረም።
በዚሁ መሀል ግን፣ ቻይና ዋናዋ የመኪና ፋብሪካ የመሆን ዕድል አገኘት። በእርግጥ ከአሜሪካና ከአውሮፓ መኪኖች (ከፎርድ ወይም ከቮልስ ጋር፣ ከቶዮታና ከሃዩንዳይ ጋር በጥራት ሊፎካከሩ የሚችሉ የመኪና ሞዴሎች በቻይና አልተፈጠሩም። ቢሆንም በብዛት ሁሉም ዓይነት መኪኖች የሚመረቱባት አገር ሆናለች።
እ.ኤ.አ 2015 የመኪኖች ምርት በሚሊዮን
1 China 24.5
2 United States 12.1
3 Japan 9.3
4 Germany 6.0
5 South Korea 4.6
World 90.8
የቅርብ ዓመታት መረጃዎችን ስንመለከትም፣ የአውሮፓ አገራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁልቁል የሚንሸራተቱበት ፍጥነት ጨመረ እንጂ አልቀነሰም። መጀመሪያ በጃፓን፣ ከዚያ በደቡብ ኮሪያ ተበለጡ። ከዚያም ቻይና መጣችባቸው። አሁን ደግሞ ህንድ ተጨመረችበት።
እ.ኤ.አ 2023 የመኪኖች ምርት በሚሊዮን
1 China 30.2
2 United States 10.6
3 Japan 9.0
4 India 5.9
5 South Korea 4.2
World 93.5
በብዛት እየተፈበረኩ ያሉት መኪኖች በአብዛኛው የአሜሪካ፣ የጀርመንና የፈረንሳይ፣ እንዲሁም የጃፓንና የደቡብ ኮሪያ ሞዴሎች ናቸው። 75 በመቶ እስከ 80 በመቶ ድረስ።
የሚመረቱበት ቦታ ግን ወደ ቻይናና ወደ ሕንድ፣ እንዲሁም ወደ ሜክሲኮና ብራዚል በብዛት እያዘነበለ ነው የመጣው።
ይህም ብቻ አይደለም። ባለፉት ዐሥር ዓመታት እየተበራከቱ የመጡት የኤሌክትሪክ መኪኖች ላይ የአውሮፓ አገራት ወደ ኋላ ቀርተዋል። ዋናዎቹ የኤሌክትሪክ መኪና ሞዴሎች ቴስላና ቢዋይዲ ናቸው። አንደኛው ከአሜሪካ ሌላኛው ከቻይና።
ቴስላና ቢዋይዲ? የአውሮፓ ኩባንያዎችስ የት ጠፉ?
በ2024 ቴስላ ቀዳሚነቱን ይዞ ለማጠናቀቅ የቻለው በትንሽ ብልጫ ነው። 1.8 ሚሊዮን የኤሌክትሪክ መኪኖችን አምርቷል። ቢዋይዲ ደግሞ 1.7 ሚሊዮን የኤሌክትሪክ መኪኖች። የአውሮፓ ድርሻ ከቁጥር የሚገባ አይደለም።
በብዙ የኢንዱስትሪ ዘርፎች፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ድርሻ ባለፉት 30 ዓመታት በእጅጉ አሽቆልቁሏል። የፋብሪካ ሠራተኞች ቁጥር በጣም ቀንሷል። በ25 በመቶ ገደማ።
ታዲያ አውሮፓው ውስጥ የኑሮ ቅሬታ ቢበረታ፣ ዜጎች ፖለቲከኞችን በጥላቻ ስሜት ቢጠምዷቸው አይገርምም።
አኗኗርን የሚያሻሽል የሥራ ዕድል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ ብቻ አይደለም ዜጎች የሚማረሩት።
መንግሥት ከዜጎች የሚወስደው ታክስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ኢንዱስሪ በፍጥነት እየተስፋፋ በነበረበት ዘመን፣ መንግሥት ከዜጎች ዓመታዊ ገቢ ውስጥ በአማካይ ከ10 በመቶ የሚበልጥ ታክስ አይወስድም ነበር።
ዛሬ ግን፣ አማካይ ገቢ የሚያገኝ ዜጋ፣ በተለያየ የታክስ ዓይነት 50 በመቶ ያህል ገቢው በመንግሥት ይወሰድበታል። ቅሚያ ብንለው ይሻላል።
በወር 4 ሺ ዩሮ ገቢ ቢያገኝ፣ 2 ሺ ዩሮ መንግሥት ይነጥቀዋል።
መንግሥት እንዲህ የሚሰበስበውን ገንዘብ “ስደተኞችን ለመንከባከብና ለመርዳት አዋለው” ተብሎ ሲዘገብ ደግሞ የዜጎች ንዴት እንዴት እንደሚቀጣጠል አስቡት።
የአውሮፓ ፖለቲከኞችና ባለሥልጣናት ላይ የዜጎች ጥላቻ ቢበረታ ምኑ ይገርማል?
ታዲያ በዚህ ሁኔታ የድሮው ዓይነት እርዳታ ወደፊትም የሚቀጥል ይመስላችኋል?