(ከፍል ሁለት)
የዛሬ ሁለት ሳምንት በወጣው የዚህ ጽሁፍ ክፍል አንድ፣ የአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሴት ተማሪዎች ሒጃብ አድርገው እንዳይገቡና እንዳይማሩ መከልከሉንና የተፈጠረውን ችግርና ውዝግብ በመጠኑም ቢሆን አውስቻለሁ፡፡ ጥቂት የሃይማኖት ወይም ለሃይማኖቱ የቀረብን ነን የሚሉ ልሂቃን ችግሩን ካላባባሱት በስተቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሌም ተቻችሎ የሚኖር መሆኑ የማያጠያይቅ ነው፡፡ በእርግጥም፣ አኗኗሩም፣ ማሕበራዊ ኑሮውም፣ ተቀራራቢ የሆነ፤ አመለካከቱም ተቻችሎ የሚኖር መሆኑ ይታወቃል፡፡
ለምሳሌ በአክሱም ከተማ አንዱ ክርስቲያን (ቄስም ሊሆን ይችላል) ልጁን ድሮ ሙስሊም ወዳጁን ቢጠራ ሙስሊሙ ከሚስቱ ጋር ሙሽሮችን ለመመረቅ የሚሄደው ወንዱ ኮፍያውንና ጥምጣሙን አድርጎ ሚስቱም ሒጃቧን (ጉፍታዋን፣ ሙጸን) አድርጋ ነው፡፡ ማንም ‹‹ተመለሱ›› የሚላቸው የለም፡፡ እንዲያውም የሙስሊም ምግብ ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህ በሁሉም የትግራይ ግዛት የሚተገበር ነው፡፡ በወሎና በጎንደርም እንደዚሁ፡፡ በተመሳሳይም ሙስሊም ልጁን ቢድር ለክርስቲያኖች ምግብ አዘጋጅቶ ይጠብቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ቄስ እስከ መስቀላቸው፣ መነኩሴ እስከ ቆባቸው ገብተው ሙሽሮችን መርቀው ይሰናበታሉ፡፡
ይህም ሆኖ በሰላምና በጸጥታ ተስማምቶና ተቻችሎ ከሚኖረው ሕብረተሰብ ውስጥ ጥቂት ቡድኖች ይህንን ለዘመናት የኖረ ማሕበራዊ ሕይወታችንን ለማደፍረስ ጥረት ሲያደርጉ መስተዋላቸው አልቀረም፡፡ አንዳንዶቹ ስለ ሰላም ሲነገር፣ ስለ መቻቻል ጥረት ሲደረግ፣ በሰላም አብሮ ስለ መኖር ሲነሳ የሚከፋቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም እነሱ ባሉት መንገድ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ሌላ መንገድ የሌለ የሚመስላቸው አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እነሱ የሚሉት በራሳቸው ሰው ካልተባለ በቀር የማይጥማቸውና የማይቀበሉ አያ ደቦልቧሌዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡ ስለ ሰላም እያወሩ ጸረ-ሰላም ድርጊት የሚፈጽሙም አሉ፡፡ በሰላማዊ መንገድ ሲጨብጧቸው በመርዝ የሚወጉም አይጠፉም፡፡ «ነገሩ በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል?» እንደሚባለው ሆኖ የሚገኝበት ሁኔታም አለ፡፡ ስለዚህ ምን መደረግ አለበት? አንዱ መፍትሔ ችግሮቻችንን በመፈተሽ ለማስተካከል መሞከር ነው፡፡ በበኩሌ ማንሳት የምፈልገውም በርእሱ ላይ እንደተመለከተው ለመቻቻል፣ በሰላምና በፍቅር አብሮ ለመኖር- የሃይማኖት ሕግጋት ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን በሚመለከት ነው፡፡
እርግጥ ነው፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11፤ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ በዚሁ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ አንድም፤ መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይተዋል፡፡ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ የመንግሥት ሃይማኖት የለም ይላል፡፡ ንዑስ አንቀጽ ሦስት፤ መንግሥት በሃይማኖቶች ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ይገልጻል፡፡
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27 ደግሞ የሃይማኖት፣ የእምነትና የአስተሳሰብ ነጻነት እንደተረጋገጠ ያመለክታል፡፡ የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አንድ፤ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነጻነት እንዳለው አስቀምጧል፡፡ ይህ መብት የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት መያዝን ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር የመግለጽ መብትን አካቷል፡፡ ንዑስ አንቀጽ ሦስትም አማኙ የመረጠውን እምነት እንዳይዝ ሊያግደው ወይም በሌላ መንገድ ሊከለክለው እንደማይችል ይናገራል፡፡ ንዑስ አንቀጽ አራት፤ ወላጆችና ሕጋዊ ሞግዚቶች በእምነታቸው መሠረት የሃይማኖታቸውንና የመልካም ስነምግባር ትምህርት በመስጠት ልጆቻቸውን የማሳደግ መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል፡፡ አንቀጽ አምስት ወይም ሃይማኖትን ወይም እምነትን የመግለጽ ነጻነት የሚገደበው ሕጋዊና አስፈላጊ ነው ተብሎ በሕግ በተደነገገው መሠረት የሕዝብ ደህንነትን፣ ሰላምን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብ ሞራልን፣ መሠረታዊ መብቶችን፣ የሌሎች ነጻነትን፣ የመንግሥት ከሃይማኖት ነጻ መሆንን የሚጻረረ ከሆነ ነው፡፡ በአንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ትምህርት ከሃይማኖታዊ፣ ከፖለቲካዊ ቡድኖች (ፓርቲዎች)፣ ከትምክህተኛ የባህል ተጽእኖ ነጻ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የእኩልነት መብትን የሚያረጋግጠው አንቀጽ 25፣ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ሲሆን ያለአንዳች ልዩነት የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል ይላል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ሕጉ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ ወይም በተገኘበት ማሕበረሰብ፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በአመለካከት፣ በሀብት፣ ከሌላ አገር በመወለድ በትውልድ ሳይለይ ለሁሉም ሰው በሕግ የተጠበቀ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡
ይሁንና የሃይማኖቶች እኩልነት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በማያሻማ መንገድ መቅረቡ ትልቅ ነገር ሆኖ፣ ሕገ መንግሥትን እየጠቀሱ ብቻ ዳኝነት መስጠት ስለሚያስቸግር አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን በተለይም በፍታብሔሩ፣ በወንጀለኛ መቅጫው፣ በቤተሰብ ሕጉና በሌሎችም ሕግጋት ያልተካተቱ ጉዳዮችን በሕግ መደንገግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በምዕራፍ 27 ንዑስ አንቀጽ አምስት፤ ሃይማኖትን ወይም እምነትን የመግለጽ ነጻነት የሚገደበው ሕጋዊና አስፈላጊ ነው ተብሎ በሕግ በተደነገገው መሠረት የሕዝብ ደህንነትን፣ ሰላምን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብ ሞራልን፣ መሠረታዊ መብቶችን፣ የሌሎች ነጻነትን፣ የመንግሥት ከሃይማኖት ነጻ መሆንን የሚጻረረ ከሆነ ነው» ሲል ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለት መንግሥት «ትክክለኛ አካሄድ አይደለም» ብሎ ባመነበት ሁሉ እየተነሳ «የሕዝብ ደህንነትን፣ ሰላምን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብ ሞራልን፣ መሠረታዊ መብቶችን፣ የሌሎች ነጻነትን ነክተሃል» እያለ ችግር ሊፈጥር ይችላል ወይም በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ይገባል ማለት ነው? መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ትብብር ቢፈልግ ወይም የሃይማኖት ተቋማት ከመንግሥት ትብብር ቢፈልጉ አያገኙም ማለት ነው? የኢስላማዊ ምክር ቤቱ ወይም ሲኖዶሱ ወይም ሌላ እውቅና ያለው ሃይማኖታዊ ተቋም ከመንግሥት ጋር በመወያየት ቢሠራ ተለጣፊ ሃይማኖት ተደርጎ ይወሰዳል ወይስ ለሕልውናዬ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ «በልከከኝ ልከክህ ዓይነት» አብረን ልንቆም እንችላለን እንደማለት ሊሆን ይችላል? የሃይማኖት ተቋም ነጻ በመሆኑ ምክንያት ከሀገሪቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ፖሊሲ እውቅና ውጭ በመንቀሳቀስ ሃይማኖታዊ ጉዳዩን ማከናወን ይችላል ማለት ነው? በሃይማኖት መሠረት ለምዕመናኑ የሚወጡ ሕግጋት መንፈሳዊ፤ ለዜጎች የሚወጡ ሕግጋት ዓለማዊ ሆነው እስከተቀረጹ ድረስ ልዩነት ሊኖራቸው ቢችል አስማምቶ መዳኘት የሚቻለው እንዴት ነው? የሃይማኖትን ነጻነትን በተግባር ለማዋል ወይም የሃይማኖት ነጻነትን ለማስከበር የሚያስችሉ ሕጎችን ለማውጣት ምን ያህል ስለሃይማኖት ነጻነት ተረድተናል? ስለሃይማኖት ነጻነት ሳንረዳ የምናወጣቸው ሕጎችስ ምን ያህል ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ? ትክክል ካልሆንን ቀኑ እየገፋን ነው ወይስ እኛ ቀኑን እየገፋነው ነው? የመቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ጥያቄ በሆነበት ዘመን ችግሮቻችንን ሕጋዊ በሆነ መንገድ በመፍታት ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት እናዞራለን ወይስ በውስጣችን ተቀብሮ በሚኖረው የራስ ወዳድነት አባዜ ተወጥረን እንቀጥላለን? በሀገሪቱ በሕግ ላይ የተመሠረተ መቻቻል ቢኖር ባይኖር ምን ቸገረን ብለን የግል ጥቅማችንን እናሳድዳለን ወይስ በብሔራዊ ስሜት ተሞልተን ለሕዝብ እንሠራለን? በዕውቀት ተሞልተን ወደፊት እንገሰግሳለን ወይስ በጨለማ እውር ድምብሱን እንደናበራለን? ወይስ አቤ ጉበኛ «ገብላንድ» ብሎ እንደቀረጸው ገጸ ባህርይ አጭበርባሪ ጦጣ እየመሰልን እንኖራለን?... በዚህ ረገድ በርካታ ጥያቄዎችን ልናነሳ እንችላለን፤ ነገር ግን አንድ አድርገው የሚያስተሳስሩን ሕጎቻችን በተለይም ሃይማኖት ነክ ሕጎቻችን ፍትህና ርትዕ የሚያሰፍኑ ሆነው እንዲገኙ ማድረግ ወይም ህጎቻችን በዚህ ረገድ ያላቸው ብቃት ሕብረተሰቡ እንዲገነዘባቸው ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ከቶ አይደለም፡፡ ስለሆነም የሃይማኖታዊ ሕጎች አስፈላጊትን በሚመለከት የሚከተሉትን ነጥቦች ማንሳት ጠቃሚ ይመስላል፡፡
ቤተሰብን በተመለከተ
ቤተሰብ የሕብረተሰብ መሠረት እንደመሆኑ በብዙ መልኩ መንግሥታዊ ትኩረት የሚሰጠው ማሕበራዊ ተቋም ነው፡፡ ይሁንና ቤተሰብ ማሕበረሰባዊ ብቻ ሳይሆን እራሱን ችሎ የሚቆም አካል በመሆኑ ደግሞ ሌላውን የሕብረተሰብ ክፍል ሳይጎዳ የራሱን ማሕበራዊ ሕይወት የሚመራበት ማህበራዊ ህግ ያስፈልገዋል፡፡
ትምህርት
ሃይማኖታዊ ጉዳይ፣ ግለሰባዊ የዜግነት ጉዳይ፣ መንግሥታዊ እንዲሁም ብዙ ሃይማኖቶችን፣ እምነቶችን፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን፣ አመለካከቶችን አስተባብሮ የሚመለከት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ነገረ ግን ግለሰብ በሕብረተሰብ አካልነቱ ብቻ ሳይሆን በግል እምነቱ ምክንያት የሚያሳያቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ሙስሊምም፣ ክርስቲያንም፣ ይሁዲም፣ ሌላ እምነት ያለቸውም አብረው ሊማሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ሙስሊሟ ሒጃብ፣ ክርስቲያኗ ማተብ ከዚያም ጋር አነስተኛ መስቀል አድርጋ፤ ሌላዋ ደግሞ አማልክቷ ጨሌ የሚወዱ ልትሆን ብትችል እንደዚሁ አንገቷ ላይ ወይም ሌላ ቦታ አድርጋ ልትታይ ትችላለች፡፡
ሦስቱም የእምነት መለያዎች በሚሆኑበት ሁኔታ (ለውበት ወይም ለሌላ ጉዳይም ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ) አሁን ባለው ሁኔታ አንዳንድ የመለያ ምልክቶች ሲፈቀዱ አንዳንድ ደግሞ አይፈቀዱም፡፡ አንዳንዶቹ የማይፈቀዱት በጉልህ ስለሚታዩ ሲሆን አንዳንዶቹ የሚፈቀዱት በትንሹ ስለሚታዩ ነው፡፡ በወንዶችም በኩል ቢሆን በጉልህ ባይሆንም የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ የሙስሊሙም ሆነ የክርስቲያኑ ሕይወት ከመስጊድና ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ ከብዙ አገሮች በተለየ ሁኔታ ልትታይ ትችላለች፡፡ ወጣቶች መንፈሳዊ አመለካከትና ፈሪሃ ፈጣሪ በውስጣቸው ከኖረ ከብዙ ጥፋቶች ሊቆጠቡ እንደሚችሉም ይታመናል፡፡ ነገር ግን ሁሉም እምነቶች በተለይም በታላላቅ የትምህርት ተቋሞች የሚስተናገዱት እንዴት ነው? አመጋገባቸው፣ አኗኗቸው፣ ማሕበራዊ ሕይወታቸው ከእምነታቸው ጋር የተሳሰረ ነው? በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶች በየሀገሩ እየተስፋፉ ያሉ ይመስላል፡፡ ከነዚህ አገሮች ተምረው የሚመጡና በዜግነታቸው ወደ ሀገራቸው መጥተው የሚማሩት ወጣቶች ጉዳይስ እንዴት ይያዛል?
የትምህርት ቤቶች መሠረታዊ ተልእኮ በአንድነት ውስጥ ስላሉት ልዩነቶችና በልዩነት ውስጥ ስላሉ አንድነቶችን ለመረዳት የሚያስችሉ፣ የመቻቻል ባህልን የሚያጎለብቱ፣ ግልጽነት የሰፈነባቸው እንዲሆኑ፣ የሚማሩት ትምህርት ከሕዝባዊ ተጠያቂነት ጋር የተቀናጀ መሆኑንና ማሕበረሰባዊ ክብን የሚያጎናጽፍ መሆን ይኖርበታል፡፡
ኢስላማዊ መድረሳዎችና የቄስ ትምህርት ቤቶች
በኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት ታሪክ ኢስላማዊ መድረሳዎችና የቄስ ትምህርት ቤቶች መሠረታዊ ሃይማኖታዊ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን መሠረተ ትምህርት በማስፋፋት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ተቋማት ናቸው፡፡ ስለዚህም ከመደበኛው ትምህርት በተለየ ሁኔታ ትኩረት አግኝተው የበለጠ ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ሕጋዊ ድጋፍ ቢኖራቸው ሀገራችንን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማሳደግ ለምንሻው ብሔራዊ ዓላማ ሊውሉ ይችላሉ፡፡ ይልቁንም ኢስላማዊ መድረሳዎችና የቄስ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም የማይጠይቁ ከመሆናቸውም በላይ ልጆች ተሰባስበው በሚገኙባቸው ቦታዎች (ለምሳሌ በእረኝነት ለተሰማሩ ልጆች፤ እሁድና ቅዳሜ እቤታቸው ለሚውሉ፤ ባለው ትርፍ ጊዜ ቤተሰብና ጎረቤት የሆኑ ልጆች) ሁሉ መሠረታዊ ትምህርትን ለማስፋፋት አመቺ ናቸው፡፡
የፕሬስ ውጤቶችና ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት
የፕሬስ ውጤቶች ማለትም የሕትመትና የኤሌክትሮኒክስ (እንደ ጋዜጣ፣ መጽሄቶች፣ ጆርናሎች፣ ብሮሹሮች፣ በራሪ ጽሑፎች፣ ፖስተሮች፣ ቢል ቦርዶች፣ የሬዲዮ፣ የቴሌቪዥን፣ የሲኒማ፣ የድምጽ፣) ውጤቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገዶች የሕብረተሰቡን ተቻችሎ የመኖር ባህል እንዳይንዱ የሚከለክል፤ ሁሉንም ሃይማኖቶችና እምነቶች መሠረት ያደረገ ሕግ እንዲኖረን ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የመገናኛ ብዙሃን የመንግሥትንም ጨምሮ ወደ አንድ በኩል ያጋደለ መስሎ ስለሚታይም፣ ይህም የፕሬስ ውጤት በሕግ የታገዘ ሥራ እንዲያከናውን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያስተዳድራቸው የፕሬስ ውጤቶች በውስጡ የተለያዩ የሃይማኖት ጉዳዮች የሚመለከቱ ክፍሎች እስከ ሌሉት ድረስ በግልጽም ሆነ በረቀቀ ሁኔታ የሕብረተሰቡን መብት የሚጻረሩበት ሁኔታ እንዳይኖር ከሰው ኃይል አቀጣጠርና አመዳደብ ጀምሮ ማካተት ያለበት ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
እንደ ፕሬሱ ሁሉ በሌሎችም አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት ለምሳሌ በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ በፖሊስ፣ በሀገር መከላከያ ሃይል ወዘተ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ስለ ሃይማኖት መግለጫ በሚሰጡበት ጊዜ እነርሱን ከሃይማኖታቸውና ከአመለካከታቸው ውጭ ማየት ስለማይቻል የሕብረተሰቡን ውክልና ማስተዋል ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
የሃይማኖት ስነምግባር
ምንም እንኳን ሁሉም ሃይማኖትና እምነት የራሱ የሆነ ስነምግባር ያለው ቢሆንም ሁሉም ሃይማኖቶች በጋራ የሚስማሙባቸው፣ የሃይማኖት ስነምግባራት በማውጣት የሃይማኖቱ ሕግ አካል ማድረግ ይቻል እንደሆነ መመካከር ያስፈልጋል፡፡ የጋራ ስነምግባራዊ መመሪያ ወይም ሕግ የሚያስፈልግበት መሠረታዊው ምክንያት እየአንዳንዱ ትኩረት የሚሰጠው ለራሱ ብቻ ከመሆኑም በላይ የጋራ የሆኑት ስነምግባሮች ለአማኞች እንዳስፈላጊነቱ የማይሰራጩ በመሆናቸው ነው፡፡ የሃይማኖት የጋራ ስነምግባር መመሪያዎች መኖር በጭፍን «ትክክሉ የኔ ነው» ከሚል አመለካከት አውጥቶ «ለካስ ሌሎችም እንደኛ ትክክል የሆነ የስነምግባር መመሪያ አላቸው» የሚል አዎንታዊ አመለካከት ሊያሰፍን እንዲሁም ሕዝብ ለመቻቻል፣ በፍቅርና በሰላም አብሮ ለመኖር የሚያደርገውን ጥረት የበለጠ ሊያጠናክሩ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ ደረጃ በደረጃም ለዘመናት የነበረውን አንዱ ሌላውን እንዳያውቅ ይከለክል የነበረውን አስተሳሰብ በማስቀረት፣ አንዱ ስለሌላው እንዲያውቅ ያስችለዋል፡፡ ሃይማኖት በማወቅ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማገዝም ሀገር በዕውቀት የሚመራ ዕድገት እንዲኖራት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሊያግዝ ይችላል፡፡
«ስህተት እንደነበረ ሊቀጥል የማይችለው» ወይም «ስህተት መብት የለውም» የሚባለውም ዕውቀት በሂደት ትክክለኛውን ለማሳወቅ ስለሚችል ነው፡፡
ማጠቃለያ
ሀገራችን እንደ ሩቅ ምሥራቅ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ ሀገሮች የቅኝ ግዛት ስላልነበረች በሌሎች ቅኝ ግዛት እንደነበሩ አገሮች ሆን ተብሎ በሚፈጠር የዘር፣ የጎሳ፣ የጂኦግራፊያዊ አሰፋፈር፣ የሃይማኖት ክፍፍል አልደረሰብንም፡፡ በውስጣችን በገዥ መደቦች ውስጥ የመናናቅ ነገር የነበረ ቢሆንም፣ ሰፊው ሕዝብ ባልተራራቀ ማሕበረሰባዊ ኢኮኖሚ ሕይወት ስለነበረ ጎልቶ የሚታይ ችግር አልነበረም፡፡
ወይም እንደ አሜሪካውያን ከየትም ተጠራቅመን የተሰባሰብን ሕዝቦች ባለመሆናችን የተራራቀ የስነባሕርይ አመለካከት የለንም፡፡ በሃይማኖት፣ በብሔር ብሔረሰብ የተለያየን ብንሆንም፣ ለብዙ ሺህ ዓመታት አብረን የኖርን ብቻ ሳንሆን አንዳችን ከሌላችን ጋር በጋብቻና በአሰፋፈር እየተሰናሰልን የመጣን ነኝ፡፡ ይሁንና የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስሩ እየተጠናከረ ሲሄድ ተጋቦቱም ሊኖር ስለሚችል በወንጀለኛ መቅጫችንና በፍታብሔር ሕጋችን ያልተካተቱ ሃይማኖታዊ ሕጎችን ማውጣት ያስፈልጋል፡፡
Sunday, 16 February 2025 00:00
የአክሱም ተማሪዎች የሒጃብ ጥያቄ የፖለቲካ ህመሙ ምልክት ወይስ እራሱ ህመሙ ነው?
Written by ከተሾመ ብርሃኑ ከማል
Published in
ነፃ አስተያየት