Sunday, 16 February 2025 00:00

ጎመን በጤና - የግሮሰሪ ጨዋታ

Written by  ሙሉጌታ ቢያዝን
Rate this item
(1 Vote)

“ወዳጄ ልቤ በዚህ ዘመን ማን፣ ምን መኾኑን ሳታውቅ አፍህን ከከፈትክ፣ ማረሚያ ቤት
ተከፍቶ ይጠብቅሃል፡፡ ለዛውም ዕድለኛ ከኾንክ፡፡ ሀገራችን መጽሐፍ ላነበበ ታራሚ የእስር
ዘመን መቀነስ እስክትጀምር አፌን አልከፍትም፡፡ ሆሆሆ… “

 

በረንዳ ላይ በአንድ ግሮሰሪ፣ ተሼና ተፌ የተሰኙ ሁለት ጓደኛሞች ወግ ይዘዋል፡፡ የቤቱ ‘ቋሚ ተሰላፊ’ ናቸው፡፡ በረንዳውን የሚመርጡት ከሙዚቃ ጩኸት ሽሽት? ሲጃራቸውን እንደልብ ለማቡነን? ማንንም ሳይገላመጡ፣ማንም ሳይገላምጣቸው ወግ ለመጠረቅ? ወይስ ሂሳብ ሳይከፍሉ ውልቅ ለማለት ? ከመጨረሻው በቀር ሁሉም ልክ ሊኾን ይችላል፡፡
ለቤቱ ጥቁር እንግዳ ሰው በመደብለቁ ምክንያት የቤቱ ቋሚ ተሰላፊ የሚባሉት ሁለቱ ጓደኛሞች ስፍራ ስፍራቸውን ይዘዋል ለማለት አይቻልም፡፡ ሙዚቃው ይጮሃል፡፡ ማንም ነገሬ ያለው ግን አይመስልም፡፡ ክላሲካል ሙዚቃዎችን የሚያዘወትረው ይህ ቤት፤ ዕድሜ ለተሼ ለድምፃውያን ቀን ወጣላቸው፡፡ ከዕለታት ባንዱ ቀን በክላሲካል ሙዚቃ ሲያዝገን፣ በነጭ ጋውን የደመቀውን የግሮሰሪውን ባለቤት ጠርቶ ምን ነበር ያለው? “ሊቀ መኳስ ደግሞ ማን ሞተ?” ባለቤቱ ከት ብሎ ስቆ ድምፃዊ የሚያዜምበት ሙዚቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያስጀመር፤ ከቤቱ ቋሚ ተሰላፊዎች ጋርም ትውውቃቸው ጀመረ፡፡
ያም ቢኾን የሚከፈቱት ሙዚቃዎች እንደ አብዛኛዎቹ ደንበኞች ዕድሜ፣ እጅግ ዝግና ስክን ያሉ፣ ልብ ላይ ሔደው ስንቅር የሚሉ ናቸው፡፡ የትዝታ ዜማ ያጠላባቸው፣ ማሰብ፣ ማሰላሰል የማይከለክሉ ሙዚቃዎች፡፡ አሁን በቀደም ዕለት የሰማሁት ዜማ ሌላ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ሰምቼው ስለማላውቅ? አይመስለኝም፡፡ ’ከዚህ ቀደም አዳምጬው ስላማላውቅ’ ብል ይሻላል፡፡ “Without music, life would be a mistake” ያለው ማ ነበር? (ሕይወት ያለሙዚቃ ከንቱ ትኾን ነበር እንበለው ይኾን? ) ድምጥ የለኝም እንጂ ለአንባቢዎቼ ባዜም ደስታውን አልችለውም፡፡ የምር! ሰው እኮ ወድዶ አይደለም የጥንት የጥዋት ዜማዎችን የሚወድደው፡፡ በተለይ ትናንቱ ከዛሬው ለደመቀለት!
ከሙዚቃው ቀጥሎ ቢራ አቀዛቀዝና መስተንግዶ እግር እስኪነቁ ቢሔዱ እንደዚህ ግሮሰሪ ‘አይገኝም’ ይባልለታል፡፡ ሁለመናው ጥርስ የኾነው የግሮሰሪው ባለቤት የሁለቱንም ጓደኛሞች እጅ ጨብጦ፣ የሚፈልጉትን ይዞላቸው ከተፍ ካለ በኋላ፣ ወደ ዋናው ባር ተመለሰ፡፡ ያቺ ልጅ ደግሞ የት ሔዳ ነው? እዚህ ቤት መቼም አስተናጋጅ አይለምድም፡፡
ዛሬ ለዚህ ቤት መቅሰፍት ኾኖለታል የሚያስብል ጥቁር እንግዳ ተከሥቷል፡፡
ግንባሩን ያልበዋል መሰል ቶሎ ቶሎ ግንባሩን በሶፍት ይጠርጋል፡፡ ቶሎ ቶሎም ስልኩን ይነካካል፡፡ መልኩ ጥቁር የኾነው ይህ ጥቁር እንግዳ፣ አልፎ አልፎ ከስልኩ ላይ ዐይኑን ነቅሎ ሁለቱን ሰዎች ለአፍታ ዐየት ያደርግና መልሶ ያደፍጣል፡፡ ጨዋታ ለመጀመር የፈለገ ይመስላል፡፡ ከዋናው ባር ሾልከው ከሚመጡ የሳቅ ርችቶች በቀር በረንዳው ያለወትሮው ዝምታ ውጦታል፡፡
የኑግ ልጥልጥ የመሰለውን ገጹን ስመለከት የአንዲት የአዝማሪ ግጥም ትዝ አለኝና ፈገግ አልኩ፡፡ (የዛሬን አያርገውና) ነሸጥ ሲያደርገኝ አንዳንድዜ የባህል ቤቶች ጎራ እል ነበር፡፡ በሚያምር ጥበብ የተሸለመችው ይቺ ድምፀ መረዋ አዝማሪ፣ የሐረርን ሰንጋ በሚያስንቁ (ሀብታም መሳይ ቀያይ) ሰዎች ፊት እየተንጎራደደች ታዜማለች፡፡ ሰዎቹ እጃቸው አልፈታ ሲል ወደኔ ዞር አለችና፤ “የዛሬውስ ሕልሜ ምነው ቀባዠረ፣ ባለመነጽሩን ያሰኘኝ ጀመረ”፡፡ ከት ብዬ ስስቅ ፍንጭቴን ዐየችና፣ አሁን ማስታወስ ያልቻልኩትን ውብ ግጥም አውርዳ፣ ከዚያ ሁሉ ሰው ከፍ አደረገችኝ፡፡ ወዲያው በረከት አልባውን (ሁለት መቶ ድፍኑን) መዥረጥ አድርጌ ግንባሯ ላይ ምርግ አደረግኩላት፡፡ ሺ ዓመት አይኖር! ይሄን ሳደርግ ወደነዛ ሀብታም መሳይ ሰዎች ዞሬ፤ ‘ዕዩኝ’ ብዬ አዋጅ አስነግሬ ነበር አሉ፡፡ (እንዲህ ነው የሚሰጥ፣ ምድረ ቋጣሪ ሁላ! በሚል ስውር መልእክት የታጀበ)፡፡
ከአፍታ ቆይታ በኋላ ገዴ ጥሩ ነው መሰል ሌላ ሰውም ምርግ ሲያደርግላት፡-
“ሀበሻ ሞኝ ነው ለቀይ ይበለጣል፣የጥቁር ሽንብራው ወጡ ይጣፍጣል”፡፡
ይሄን ጥቁር እንግዳ ሳይ ትዝ ያለኝ ግጥም ይሄ ነበር፡፡
ሁለቱ ጓደኛሞች ከያዙት መጠጥ ወሰድ፣ወሰድሰድ ካደረጉ በኋላ…
“If gin was an ocean & if I were a duck, I would swim to the bottom & never come back. ሃሃሃ…” ብሎ ወጉን የጀመረው ተሼ ነበር፡፡ በቅጽበት በረንዳው ላይ የወረደው ጸጥታ የተገፈፈ መሰለ፡፡
እዚያ ማዶ ጋዜጣ የሚያገላብጥ ሰው የተመለከተው ተፌ፤ “በወረቀት ላይ ቀረጥ መጨመሩን ሰማህ?” ሲል ወግ ጀመረ፡፡
ተሼ በግዴለሽነት “አዎን” አለ፡፡ አመላለሱ ‘እና ምን ይጠበስ?” የሚል ድምፅ የተሸከመ ይመስላል፡፡
“አንባቢ ሊጠፋ ነው፡፡ አደጋው ታይቶሃል?
“ያነበቡት ምን ሠሩ?
“አትቀልድ”
“አልቀልድም፡፡ ‘የ60ዎቹ ትውልድ አንባቢ ነበር’ በሚል መዝሙር ደንቁረናል፡፡ ግን ማንበባቸው በ’ቸ’ እና ‘ሸ’ ከመፋጀት አላዳናቸውም፡፡ ይሄው የነሱ ጦስ ለኛም ተረፈ፡፡ ‘በአፍሪካ አንድ አዛውንት ሲሞት አንድ ቤተ መጻሕፍት ተቃጠለ’ ይባላል፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ተቀዳሚ ሥራ አንድ አዛውንት አንድ ዳቦ አጥቶ እንዳይሞት መኾን አለበት”፡፡
ከዋናው ባር የተረፈው የብርሃን ስብርባሪ በዚያ ጥቁር እንግዳ ሰው ፊት ላይ ሲነሰነስ ፈገግ ማለቱን አሳበቀ፡፡
“ዐየህ ንጽጽርህ እንኳ ከመጽሐፍ ፈቀቅ አላለም፡፡ ሰው ሥጋ ብቻ ነው እያልከኝ ነው? ‘ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል’ ሲባል አልሰማህም?”
“ሰምቻለሁ፤ ሙሉ ሲያደርግ ግን ዐላየሁም፡፡ ጆሮዬን ከዐይኔ ላምን አልችልም፡፡ ይሄን የምልህ መልእክቱ የዳርዊንን ሀሳብ መሸከሙን ስቸው አይደለም፡፡”
“እንዴት ማለት?”
“ ‘ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል’ ማለት በእርሱ አምሳል የተፈጠረውን ሰው ‘ጎደሎ ነው’ ማለት አይደለምን?”
“ወዴት ወዴት?”
ተሼ ወደ ጥቁር እንግዳው ገልመጥ አለና፤ “ማንበብ ሙሉ ሰው ካደረገ ‘እጅግ አንባቢ ነው’ የሚባለው ጆሴፍ ስታሊንን ምን ልንለው ነው? ርኅራኄን የገደፈ ሰውነት ሙሉነት ነው? ስታሊን በቀን ከ300-500 ገጽ ያነብ እንደነበር ድርሳናት ይነግሩናል፡፡ ሕይወቱ ሲያልፍ በግል ላይብራሪው ውስጥ ከ25ሺ በላይ መጽሐፍት ተገኝተዋል፡፡ ልብ በል! በዘመኑ የአሜሪካ 32ኛውፕሬዚደንት በነበረው በፍራንክሊን ዲላኖ ሩዝቬልት የግል ላይብራሪ ውስጥ የተገኘው 22ሺ መጽሐፍት ብቻ ነበር፡፡ አንባቢው ስታሊን ሚሊዮችን እንደ ሳር አጭዷል፡፡ ባያነብ ኖሮ ይበልጥ ሰው በላ ይኾን ነበር ካላልን በቀር..ማንበቡ ጭካኔውን አላስጣለውም፡፡ በመሪነቱ ላይ ክርክር አለ? የለም፡፡ ሃሪ ትሩማን ‘ሁሉም አንባቢዎች መሪዎች አይኾኑም፤ ሁሉም መሪዎች ግን አንባቢዎች ናቸው’ ይለናል፡፡ ስለኾነም መልካም መሪና መጥፎ መሪ ብለን ካልከፈልን በቀር (አንድም መጽሐፍ በወጉ ማንበቡን እርግጠኛ አይደለሁም) ኢዲ አሚን ዳዳ አንባቢ ነበር ማለት ነው፡፡
ጆሮውን ጥሎ በጥሞና ሲሰማና ሲቁነጠነጥ የነበረው እንግዳ ሰው ፈገግ ለማለት ሞከረ፡፡
“ማኪያቬሊ እኮ መርዙን የረጨው፣ የዓለም አምባገነኖች መመሪያ እስከመኾን በደረሰው ልኡሉ በተሰኘው መጽሐፍ ነው”፡፡
“ሂትለር መሪ ነበር? የሚለውን ጥያቄ፤ ‘መሪ ማለት መንገዱን የሚውቅ፣ የሚሔድበትን የሚያሳይ ነው’ ሲል ጆን ማክስዌል በማያሻማ መንገድ ገልጾታል፡፡ የጀርመን መሪው ሂትለር መንገዱን ዐውቆ፣ ሔዶበትና ለተከታዮቹ አሳይቶ ሚሊዮኖችን በልቷል፤አስበልቷል፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ‘የትኛውን መንገድ አሳየ?’ የሚለው ይኾናል፡፡ ከስታሊን ቀጥሎ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ሰው በላዎች ሂትለርና ሙሶሊኒ አንባቢ ነበሩ፡፡
“ግን’ኮ” አለ ተፌ “… ግንኮ ሂትለርም ኾነ ሙሶሊኒ ግልብ አንባቢ ነበሩ፡፡ ሂትለር የሥራ ማስታወቂያን እንደሚያነብ ያለ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሙሶሊኒ በጀብዱ የታጨቁ መጽሐፍት እንደሚስቡት ታሪኩ ይነግረናል፡፡ ስለዚህ አንባቢ ነበሩ ሲባል እንዴት ያለ አንባቢ? ለምንስ ዓላማ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ አይመስልህም? …እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የሚያነበውን የማይረዳው ስንቱ ነው? ‘ንባብ ይገድላል፤ትርጉም ያድናል’ የሚለው ሀገርኛ አባባል ልከኛ ስፍራው እዚህ ጋ ይመስለኛል”፡፡
“እውነት ተናግረሃል”
ወደ ጨዋታህ ስመለስ “የሰው ልጅ የተከለከለውን ለማግኘት መቧጠጡ፣ ጥንተ ተፈጥሮው ነው ካላልን በቀር፣ በደርግ ዘመን ሳንሱር መኖሩ አንባቢን ቢያጠፋው ኖሮ እነ ኦሮማይ አይነበቡም ነበር፤ ያን ትውልድ አንባቢ ማለቱም ባልተገባ! ለያውም በእጅ በተጻፈ”፡፡ አሁንም ጥቁር እንግዳውን አጨንቁሮ ዐየና “ቀረጡንም ከዚህ ለይቼ አላየውም”፡፡
“በዚህ ከቀጠለ መጽሐፍ ይዞ የሚሔድ ሰው ማጅራት መቺ ሊከተለው ይችላል፡፡ እኔ የሚገርመኝ የመጽሐፍን ጥቅም ዐውቀው ያደጉ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ፖሊሲ ማውጣታቸው ነው”፡፡
“ብዙ አይግረምህ ‘የሰውን እውነተኛ ማንነት ለማወቅ ሥልጣን ስጠው’ ሲል ፕሌቶ ጨርሶታል፡፡ አስከትሎም “ግን’ኮ” አለ ሲጃራውን እየተረኮሰ፡፡ ገልመጥ አለና ያን ጥቁር እንግዳ ማስከፋቱን ሲገምት “ግን እኮ … በማንበባቸው ተጎድተው፣ መጽሐፍት እየጎዱን መኾኑን ተረድተው ለኛ አስበው ቢኾንስ? ማለቴ የአሁኑ ድርጊታቸው የተወለደው በማንበባቸው ከኾነስ?”
“ማንበብ ለውጥ አያመጣም እያልክ እንዳልኾነ …እንዴት እንዴት?” ተፌ በንዴት ፊቱ ቀላ፡፡
“ሩቅ ሳንሔድ ይሄን ሁሉ የምትናገረው አንብበህ አይደል?”
“አይ አስነብቤ ነው፡፡”
ይሄን ብሎ በሳቅ ፍርስ….ፍርስርስ..እንዲህ ነው እሱ፡፡
ውይይቱን በጥሞና ሲከታተል የነበረው እንግዳ ሰው ጨዋታው ሳይወሳሰብበት አልቀረም፡፡ ፊቱን ኮስኩሶ ፊቱ ላይ ያስቀዳውን መጠጥ ወደ ጉሮሮው በፍጥነት ላከና፤ “እና ምን እያልከን ነው? ቀረጥ መጣሉን ትደግፋለህ ወይስ ትቃወማለህ?”
ጥያቄ ነው ወይስ ወጥመድ?
ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ወይስ መቅሰፍት ሊኾንለት?
ተሼ ለመጀመሪያ ጊዜ አጨበጨበ፡፡ አጨብጭቦም አልቀረ፡፡ ለዛሬ አስተናጋጅነትን ደርቦ የሚሠራውን የግሮሰሪውን ባለቤት አንድ ደብል እንዲጨመርለት ብርጭቆውን በማንሣት አሳየ፡፡ መጠጡን ይዞለት እንደመጣ፡-“ሊቀ መኳስ እባክህ የፀሐየ ዮሐንስ ይኖርሃል? “
‘እንዴ ተሼ ከመቼ ወዲህ?’ በሚል አስተያየት እያየው፤
“ይኖራል፡፡ ምን የሚለው ይሁንልህ?”
“ጎመን በጤና!”
ጥቁሩ እንግዳ ብዙም ሳይቆይ ሂሳቡን ከፍሎ ውልቅ አለ፡፡
ጥቁሩ እንግዳ መራቁን እንዳረጋገጠ ተሼ፣ ለተፌ ያለው ይሄን ነበር፡-
“ወዳጄ ልቤ በዚህ ዘመን ማን፣ ምን መኾኑን ሳታውቅ አፍህን ከከፈትክ፣ ማረሚያ ቤት ተከፍቶ ይጠብቅሃል፡፡ ለዛውም ዕድለኛ ከኾንክ፡፡ ሀገራችን መጽሐፍ ላነበበ ታራሚ የእስር ዘመን መቀነስ እስክትጀምር አፌን አልከፍትም፡፡ ሆሆሆ… “

 

Read 253 times