Monday, 17 February 2025 20:30

“አለማችን ፕላኔታዊ ውሕደት ያስፈልጋታል”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

--የመጀመሪያው ሁለንታዊ መድረክ በተዘጋጀበት አዳራሽ ውስጥ ከዓለም ሀገራት ተወክለው የመጡ ሰዎች እንዲሁም ባረኖች በረድፍ በረድፋቸው ተቀምጠዋል። የመድረኩ የአዘጋጅ ክፍል አባላት (እኔን ጨምሮ) የቅድመ አዳራሽ ሥነ ስርዓቶችን አስፈፅመናል፤ የትውውቅ፣ የቁርስ፣ የሙዚቃ፣ የፎቶና ቪዲዮ ትዕይንት… ሁሉም የቅድመ አዳራሽ መርሃ ግብር በስኬት ተከናውኗል። አሁን አዳራሹ ውስጥ ሁሉም የጥያቄና መልሱን መጀመር በብሩህ ስሜት፣ በኃይልና በንቃት ተሞልቶ እየጠበቀ ነው።
የመድረኩ ተቀማጮች ሰባት ናቸው፡ ሦስት ሰዎች፣ ሦስት ባረኖችና የሰዎች እና የባረኖች አማካይ የሆነቺው ሊሊት። ሊሊት የተቀመጠቺውም ሰዎች እና ባረኖች መካከል ነው። ሊሊትን ለማየት ያልጓጓ ማን ነው? በአፈታሪክ የተሳለልንን ያን ቁመናዋንና ቁንጅናዋን በምናባችን ይዘን ሁላችንም ሊሊትን እስክናይ ቋምጠን ነበር። እንደ ባረኖች ሁሉ እሷም ብርሃን ለብሳ ስናገኛት ግን የቆመው ልባችን ሳይረካ ቀረ። ….ሦስቱ ባረኖች ከግራ ወደ ቀኝ፡ የመጀመሪያዋ ባረን09 ትባላለች፣ ሁለተኛዋ ባረን217፣ ሦስተኛዋ ባረን199። ሦስቱም ባረኖች ፌደሬሽኑን ለመመሥረትና ለማስፋፋት ከፍተኛ ሥራ የሠሩና የሰው ልጅን በደንብ ያውቃሉ የሚባልላቸው ናቸው። ሲቆሙ ላስተዋላቸው ሴቶቹ ባረኖች ከወንዶቹ የሚረዝሙ ይመስላሉ፤ ድምፃቸው ከወንዶቹ ባረኖች ይልቅ ወፍራምና ሸካራ ነው። ብርሃናቸው ስለሚከልላቸው ፀጉራቸውን (ፀጉር ካላቸው) ያሳድጉ አያሳድጉ ባላውቅም፣ ሴቶችም ባረኖች እንደ ወንዶቻቸው ሁሉ ራሰ ከባድ ናቸው። ሰዎቹ የመድረኩ ተቀማጮች ደግሞ ከግራ ወደ ቀኝ በቅደም ተከተል በሁለንታዊ ስማቸው የመጀመሪያዋ ሂዩባረን77 ትባላለች፣ ሁለተኛዋ ሂዩባረን222፣ ሦስተኛው ሂዩባረን21። ሂዩባረን77 የጥቁር ጠይም የበሰለች ወጣት ሴት ናት፣ የሚያማምሩ ዐይኖችና ወከክ የሚያደርግ ፈገግታ ታድላለች፣ መናገር በጀመረች ቁጥር ቀድማ ፈገግታዋን እንደ መብረቅ ተግ ታደርጋለች። ሂዩባረን222 ፀጉሯ በግማሽ የሸበተ ሸንቃጣ ሴት ናት፣ ብሩህ ቡናማ ፊትና ውብ ሰማያዊ ዐይኖች አሏት። 77ቷና 222ቷ ሁለቱም ዋነኛ የትምህርትና የምርምር ዘርፋቸው በይነፕላኔታዊ ንፅፅራዊ ማህበረ-ፖለቲካዊ ምህንድስና ነው። ሂዩባረን21– የጥቁር ጠይሙ፣ ጎልማሳው፣ ሽበታሙ ሸበላ የመጀመሪያው ሁለንታዊ መድረክ ላይ የነበረው የኢንተርፕላኔታሪ ኮምንኬሽን ተቋምን የሚመራው ሰውዬ ነው።
የጥያቄና መልስ መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት ሁሉም የአዳራሹ ሰው እና ባረን ለሊሊት ክብር ለአንድ ደቂቃ ተነስቶ አጨበጨበ። ሊሊት ተነስታ ሰግዳ አመሰገነች። ያቺ ሊሊት– የመጀመሪያዋ ሴት፣ እናም የመጀመሪያዋ እብሪተኛ– ሰውነቷን (እና ሴትነቷን) በራሷ ጥረት የፈተሸቺው– የፈለገቺውን ለማግኘትና የፈለገቺውን ለመሆን ቆርጣ ከገነት የወጣቺው ሊሊት። ሊሊት ቁመቷ ከባረኖቹ ይበልጣል፣ የሰውነቷ ቅርጽ እንደ ሰው ልጅ ሴቶች ቅርጽ ነው፣ ድምጿ ትንሽ ቢሻክርም እንደ ሰው ልጅ ሴት ድምፅ ቀጭንና አባባይ ነው። እውነት ሰው ናት? እውነት ሴት ናት? እውነት እንደ ሴት ልጅ የሚታቀፍ፣ የሚለስልስ፣ የሚሞቅ፣ የሚደማ ገላ አላት? ባየኋት።
በሊሊት የጉጉት ሀሳብ ስሸመጥጥ መድረኩ ተጀምሯል። ሁለተኛው ሁለንታዊ መድረክ ለሰው ልጅ እውነተኛ ስልጣኔና ህብረት እንቅፋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። ጉዳዩ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚጠቅም በመሆኑ መዝግቤ እነሆ አንብቡት እላችኋለሁ፡
ጠያቂ፡ በአፈታሪክ የምናውቃት ሊሊት እውነት ሆና ወደ ምድር በመመለሷ የተሰማኝን ስሜት የምገልፅበት ቃል የለኝም። የሁለቱ ፕላኔቶች እንዲሁም የሰው እና የባረን አማካይ እንደመሆኗ እኔ የመጀመሪያ የሆነውን ጥያቄዬን ማቅረብ የምፈልገው ለሊሊት ነው። ምድር ላይ ይሄን ፌደሬሽን የመሠረቱት ሰዎች እና ባረኖች አበክረው ሰዋዊና ፕላኔታዊ አንድነት ስለመመሥረት ይናገራሉ። የተወደድሽው እህታችን፣ ስለዚህ ጉዳይ ምን ትያለሽ?
ሊሊት፡ በመጀመሪያ አንድ አሳዛኝ እውነታ ልንገራችሁ፡ እስካሁን በሁለንታው ውስጥ ከማውቃቸው የአእምሮና የማሰብ ችሎታ ካላቸው ፍጡራን ውስጥ ዘራዊና ፕላኔታዊ አንድነት የሌለው የሰው ልጅ ብቻ ነው። ሌሎቹ የሰለጠኑ ፍጡራን ምንም ያህል ለሌሎች ለማይመስሏቸው ፍጡራን ክፉ ቢሆኑም እንኳን እርስ በርስ ግን አይጠፋፉም። የዚህ መሠረታዊ ምክንያቱ የሰው ልጅ ሰዋዊ አንድነት ከዚያም ፕላኔታዊ አንድነት አለመገንባቱ ነው። የሰው ልጅ ሰዋዊ አንድነት እንዳይኖረው ያደረገው ዋናው ምክንያት ደግሞ ራሱን በትናንሽ ማንነቶች ማጠሩ ነው። የሰው ልጅ አንድነት ጠላቶቹ ትናንሽ ማንነቶቹ ናቸው። እነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ከሰው ልጅ መሠረታዊ ተፈጥሮ ያልመነጩ፣ የሰው ልጅ በሂደት በራሱ ላይ የጫናቸው ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ለአብዛኛው የሰው ልጅ ችግር፣ መከፋፈልና ጦርነት መነሻዎች ናቸው። የሰው ልጅ የህዋ ስልጣኔን በጀመረበት በዚህ ዘመን እነዚህን ትናንሽ የማንነት ድርቶች አውልቆ መጣል አለበት። ስለ እነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ዝርዝር በጉዳዮቹ ላይ ጥናት ያደረጉ ሰዎች እና ባረኖች እህት ወንድሞቼ የበለጠ የሚነግሩን ይሆናል።
ሊሊት ስትናገር ልክ እንደ ባረኖች ቃላቶቿ የአፏን እንቅስቃሴ ቀድመው ይወጣሉ፣ ተናግራ ስትጨርስ ወይ መሐል ላይ እልባት ስታደርግ ደግሞ ድምጿ ከአፏ እንቅስቃሴ ቀድሞ ያቆማል። እንግሊዝኛውን ታቀላጥፈዋለች። ከመቼው?
ጠያቂ፡ የሰው ልጅ ትናንሽ ማንነቶች የምትሏቸው የትኞቹን ማንነቶች ነው? ለስልጣኔና ለሰዋዊ አንድነት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉትስ እንዴት ነው?
ሂዩባረን77፡ የሰው ልጅ ትናንሽ ማንነቶች ከፋፋይ ሃይማኖት፣ ጎሳ ነገድ ወይም ብሄረሰብ፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም፣ የታሪክ ቅራሪ፣ የሀገር ድንበርና ብሔርተኝነት እንዲሁም የሰው ልጅን ውጫዊ አካላዊ ሁኔታን ወይም ቀለምን መሠረት ያደረጉ ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ማንነቶች ከሰው እውነተኛ ተፈጥሮ ውጭ የሆኑ ሰው ሠራሽ ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ማንነቶች የተቀባቡ የውሸት ሥሪቶች ናቸው፣ የሰው ልጅን በየቦታው እኛ እና እነሱ እያሉ ስለሚሸነሽኑ የሰዋዊ መስተጋብር ጋሬጣዎች ናቸው። እነዚህ ትናንሽ ማንነቶች የግብዝነት፣ የድንቁርና፣ የራስ ወዳድነት፣ የኢፍትሐዊነት፣ የመናቆርና የጦርነት መነሻዎች ናቸው። የሰው ልጅ በእነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ውስጥ ሆኖ ዐይኑን ገልጦ እውነትን ለማየት አይችልም።
ሂዩባረን222፡ የሰው ልጅ ሲወለድ ንፁህ ነው፣ ሰው ብቻ ነው። እያደገ ሲሄድ በትናንሽ ማንነቶች ይቆሽሻል። መጀመሪያ በሃይማኖት ጣሳ ውስጥ ያስገቡታል፤ ከዚያ በጎሳ፣ በብሔረሰብና በሀገር ብሔርተኝነት ገመድ ይተበትቡታል፤ ከዚያ የታሪክ፣ የፖለቲካና የርዕዮተዓለም ሸክም ይጭኑታል። አደግሁ፣ በሰልሁ ሲል እውነቱን በእነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ውስጥ አጥሮ ይገነባል። በዚህ አጥር ውስጥ እንደኳተነ በመጨረሻም እውነተኛ ማንነቱን ሳያውቅ ያልፋል። በከንቱ ማለፍ ብቻ አይደለም እነዚህ ትናንሽ ማንነቶቹን ለቤተሰቡና በዙሪያው ላሉት አውርሶ ነው የሚያልፈው። ሂደቱ አዙሪት ነው። እነዚህ ትናንሽ ማንነቶች እንደ ወሳኝ እውነታ ተቆጥረው በመሠረቱ አንድ አይነት ተፈጥሮና ፍላጎት ያለውን ሰው ከፋፍለው ሲያፋጁት ይኖራሉ።
ባረን199፡ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ስለሆኑት የሰው ልጆች የምናውቀውን ያህል በቅንነት እንናገራለን። የምንናገረው በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ መግባት ስለምንፈልግ አይደለም፣ የምንናገረው ከሰው ልጅ ጋር ያለን ህብረት እንዲሰምር ነው። በህብረቱ እኛም የሰው ልጅም ተጠቃሚ ነን። ህብረታችን እንዲሰምር ታዲያ የሰው ልጅ ለእውነተኛ ስልጣኔው እንቅፋት የሆኑበትን ችግሮች መቅረፍ አለበት። እነዚህ ችግሮች እንዲቀረፉ ከሰዎች እህት ወንዶሞቻችን ጋር ተባብረን እንሠራለን፣ በገባን ልክ እንናገራለን። ከፋፋይ ሃይማኖት፣ ዘር ነገድ ወይም ጎሳ፣ ንዑስ ወይም ብሔረሰባዊ ብሔርተኝነትና የሀገር ብሔርተኝነት፣ ትናንሽና ትላልቅ የፖለቲካ ርዕዮተዓለሞች፣ ያለፈና የማይለወጥ ታሪክንና ትርክትን እየሳቡ እያመጡ በእሱ መነታረክና መከፋፈል… እነዚህና የመሳሰሉት ነገሮች በሰዎች መካከል የተሰነቀሩ ሰው ሰራሽ ድንበሮች ናቸው። የሰው ልጅ እውነተኛ ሞራላዊና ቁሳዊ ስልጣኔ ላይ የሚደርሰው እነዚህን የውሸት ድንበሮቹን አፍርሶ ሰዋዊና ፕላኔታዊ አንድነት ከፈጠረ ብቻ ነው።
ሂዩባረን21፡ ከሌላው የሰው ልጅ የሚለየንን ማንኛውንም ስብከት ልንቀበል አይገባም። በሰዎች መካከል የሚደረገውን ጋብቻ ከዝምድና በስተቀር የትናንሽ ማንነቶች አጥር ሊያግደው አይገባም። የጥላቻና የፖለቲካ ቀውስ አንዱ መነሻ ዘረኝነት ነው። የዘረኝነት መነሻችን አንዱ የመልካችን መለያየት ነው። የቀለማችንና የመልካችን ይሄን ያህል መለያየት አንዱ ምክንያት ደግሞ ቀደምቶቻችን ጋብቻቸውንና ዝምድናቸውን በጠባብ የማንነት ክበቦች ውስጥ አጥረው መኖራቸው ነው። የሰው ልጆች በነዚህ የውሸት ድንበሮች ሳንወስን እንገናኝ፣ እንተሳሰብ፣ እንጋባ እንዋለድ እንዛመድ። ያን ጊዜ ድንበሩና አጥሩ መፍረስ ይጀምራል፣ እውነተኛ ማንነታችን ይገለጣል፣ የሰላምና የፍትሕ መንገድ ይሰፋል። እርግጥ ነው ብዙ ሰዎች እነዚህን የውሸት አጥሮች እየዘለሉ ሲገናኙና ሲዛመዱ ኖረዋል። ሆኖም አጥሮቹ ተዘለሉ እንጂ ገና አልፈረሱም።
ጠያቂ፡ ሃይማኖት ሰው ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበት መንገድ ነው። ይሄን መንገድ እንዴት ይፍረስ ትላላችሁ?---
ከአዘጋጁ፡- በአብርሃም ገነት
ከተጻፈውና ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው “ሳላዛት” የተሰኘ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ የተቀነጨበ ነው፡፡

 

Read 165 times