• ከተሰበሰበው ግብር 70 በመቶው ህዝብን ለሚጠቅሙ ተግባራት ውሏል
• በግማሽ ዓመቱ 111.6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተነግሯል
• አስተዳደሩ ከዕቅዱ 90 በመቶውን ማሳካቱን አስታውቋል
የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ የገመገመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ባለፉት ስድስት ወራት ጠንካራ የሥራ ባህል፣ የአመራር ቁርጠኝነትንና ቅንጅትን በማጠናከር፣ እንዲሁም የገቢ አሰባሰብን በማሳደግ፤ በርካታ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት፣ በጥራት አጠናቆ፣ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉ ተነግሯል።
በግምገማው ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም ዘርፎች አመርቂ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ የከተማ አስተዳደሩ ከዕቅዱ 90 በመቶውን ማሳካት መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡
በእነዚህ ስድስት ወራት የከተማዋን ገጽታ የቀየሩና የህዝቡን የልማት ጥያቄ የመለሱ ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ “አገልግሎት አሰጣጣችንን ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ለማድረግና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አሰራራችንን ዲጂታላይዝ ለማድረግ አቅደን የሰራናቸው ሥራዎችም ለውጦችን አሳይተዋል” ብለዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ በመዲናዋ 111.6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደራዊ ወጪንና ብክነትን በመቀነስ፣ አብዛኛው ገቢ፣ ነዋሪዎችን ለሚጠቅም ተግባር በመዋሉ፣ ፈጣን ለውጦችን ማስቀጠል መቻሉንም ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጠቆሙት፡፡
“ከህዝብ ከሰበሰብነው ግብር 70 በመቶ የሚሆነውን የነዋሪዎቻችንን እንግልት ለሚቀንሱና ህዝብን ለሚጠቅሙ ተግባራት እንዲሁም ለዘላቂ ልማት በማዋላችን፣ የፈጣን ለውጦቻችንን ቀጣይነት አስጠብቀናል” ብለዋል፤ከንቲባዋ ፡፡
“ባለፉት ስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸማችን፣ ከተማችንን ከነዋሪዎቿ ኑሮና አኗኗር ጋር አስተሳስረን ውብና አበባ የማድረግ እንዲሁም የቱሪስት መተላለፊያ ሳትሆን፣ መዳረሻ እንድትሆን ለማድረግ አቅደን እየሰራን ያለነውን ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግና ውጤታማነቱን ማስጠበቅ ችለናል” ሲሉም አክለዋል።
በተለያየ እርከን የሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች በተሳተፉበት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በመዲናዋ የተከናወኑ ጎላ ጎላ ያሉ ተግባራትንና የተገኙ ውጤቶችንና ለውጦችን ዘርዘር አድርገው አቅርበዋል፡፡ የተስተዋሉ ጉድለቶችንና ውስንነቶችንም ጠቃቅሰዋል፡፡
በመዲናዊ ሰፊ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መምጣቱን ያነሱት ከንቲባዋ፤ አዲስ አበባ 24 ሰዓት የምትሰራ ከተማ ናት ብለዋል - ቀንም ሌሊትም፡፡ መሥራት ለሚችሉና ሥራን ለማይመርጡ ሁሉ በሯን ከፍታ እያስተናገደች እንደምትገኝም ጠቁመዋል፡፡
የኑሮ ጫናን ለማቃለል የተከናወኑ ተግባራት
የከተማው ህዝብ ያለበትን የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል ታልመው የተከናወኑ በርካታ ተግባራት እንዳሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ትላልቅ የገበያ ማዕከላት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የገበያ ማዕከላት በአብዛኛው የግብርና ምርቶችን እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎችን በቀጥታ ከአምራቹ ለሸማቹ (ደላላን ከመሃል በማስወጣት) የሚቀርብባቸው ናቸው፤ በተመጣጣኝ ዋጋ፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ገበሬዎች፣ ያለአንዳች ችግር አዲስ አበባ ውስጥ ገብተው፣ ምርታቸውን ሸጠው የመውጣት ዕድል እንደከፈተላቸውም ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በተጨማሪም፣ በትራንስፖርት እንዲሁም በጤና መድህን በሚሊዮኖችና ቢሊዮኖች በጀት በመመደብ፣ ነዋሪው በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል እያደረግን ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ “ይህም ለህዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር መፈጸማችንን ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ በመዲናዋ በቀን 35ሺ የሚደርሱ ዜጎች በነጻ የሚመገቡባቸው የምግብ ማዕከላት ቁጥር 26 መድረሳቸውን ገልጸዋል፤ ሁለቱ ገና አገልግሎት አለመጀመራቸውን በመጠቆም፡፡ ዘንድሮ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ የልማት ጥያቄዎችንና የኑሮ ውድነት ጫናዎችን ማቃለል በሚቻልበት ደረጃ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት በበጎ ፈቃድ ወደ 9.2 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆን ወጪ መሸፈኑን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ይሄ የሚያስደንቅ ክንውን ነው ብለዋል፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል ታይቷል
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰጡት ማብራሪያ፤ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ “ሰራተኞቻችንን መፈተን እና መመዘን አለባችሁ ምክንያቱም ህዝቡ በአገልግሎት እየተማረረ ነው፡፡ይሄን ዕድል የሰጠን ህዝብ ስለሆነ ህዝባችንን ለማገልገል የሚያስችል ብቃትም፣ሥነምግባርም፣ተነሳሽነትም ሊኖረን ይገባል የሚል እምነት ሰራተኞቻችን ላይ መፍጠር መቻሉ አንድ እርምጃ ነዉ፡፡” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ይላሉ ከንቲባዋ፤ “ሁለተኛው እርምጃ ደግሞ ፈተና ሰጥተን ሥራና ሰራተኛን (ባለሙያን) ለማገናኘት የሄድንበት ሂደት ነው፤ በእርግጥ በደንብ እየተመዘነ መታየት አለበት፡፡ ነገር ግን ሂደቱም ለውጥ ነው” ብለዋል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ፤ “አንዴ ሰራተኛ ሆኜ ከተቀጠርኩ አልነካም የሚለው አስተሳሰብ መሰበሩ በራሱ ለውጥ ነው” ይላሉ፡፡
በርካታ አሳሪ አሰራሮች ተፈተዋል
ከዚህ ቀደም የነበሩ በርካታ አሳሪ አሰራሮችን ፈተናል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ”ቀልጣፋ አሰራርና ግልጽነት እንዲኖር ህዝቡን የሚያሳትፍና አቅሙን የሚገነባው እንዲሁም እኛን ግልጽ ለመሆን የሚያስገድዱን አሰራሮችን አውጥተን ተግብረናል” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ሦስተኛው እርምጃ ቴክኖሎጂ ነው ይላሉ፡፡ 87 ያህል የአገልግሎት ዓይነቶችን በቴክኖሎጂ አገልግሎት መስጠት ጀምረናል ያሉት ከንቲባዋ፤የስራ ቦታ ምቹ እንዲሆኑ፣አገልግሎት የሚፈልጉ ተገልጋዮች ፊት ለፊት ከሰራተኞች ጋር እየተያዩ አገልግሎት የሚያገኙበት እንዲሁም ኃላፊዎች ያለውን የስራ እንቅስቃሴ መከታተልና መቆጣጠር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲቀል እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አምና በዚህ ወቅት ስንገመግም እዚህ ከነበረው አመራር ውስጥ ረቡዕና አርብ ቁጭ ብሎ አገልግሎት የሚሰጠው 64 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባ አዳነች፤ ዘንድሮ አገልግሎት የሚሰጠው አመራር 89 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፤ይሄም ለውጥ መሆኑን በመጠቆም፡፡
በብልሹ አሰራር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በተደረገው ጥረትም፣ ባለፉት ስድስት ወራት ለመጀመሪያ ጊዜ በብልሹ አሰራር የተጠረጠሩ 78 ዳይሬክተሮችና 2ሺ46 የሚሆኑ ሰራተኞች ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በከተማችን ውስጥ የተጠረጠሩ 928 የሚሆኑ ግለሰቦች ለህግ እንዲቀርቡ መደረጋቸውንም አክለዋል፡፡
የጥንካሬያችን ምንጭ ምንድን ነው?
የእነዚህ ጥንካሬዎች መነሻ ምንድን ነው ሲሉ የሚጠይቁት ከንቲባዋ፤ የመጀመሪያው አመራር ነው ይላሉ፡፡ “አመራሩ በየደረጃው ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገው ጥረት ተነሳሽነት እንዲሁም መሰጠት እነዚህን ለውጦች ማስመዝገብ ችለዋል” ብለዋል፡፡ ሁሉም የራሱን ሃላፊነት ለመወጣት፣ የተሻሻለ የሥራ ባህል ለመፍጠር እንዲሁም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶች የዚህ ማሳያዎች ናቸው፤ ሲሉም ያብራራሉ፡፡
ሁለተኛው የገቢ አሰባሰባችን መሻሻል ነው ይላሉ፤ በዚህ ስድስት ወር ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ 50 ፐርሰንት ጭማሪ ያለው ገቢ መሰብሰብ መቻሉን በመግለጽ፡፡ የተሰበሰበው ገቢም ወደ 37 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፡፡
በርካታ የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና ማህበራዊ ውዝፍ ጥያቄዎች ያሉበት ትልቅ ከተማን ችግር ለመፍታት፣ በመንግሥት በጀት ብቻ እንደማይወጡት መገንዘብ መቻላቸውን የሚናገሩት ከንቲባዋ፤ ለዚህም “ዝቅ ብለን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ፈጥረንና አሳምነን፣ በበጎ ፈቃድ የተለያዩ የልማት ጥያቄዎች እንዲሟሉ አድርገናል” ይላሉ፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት 9 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሸፍኑ ሥራዎች መከናወን መቻላቸውን - በመግለጽ፡፡
ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የመንግሥትና የግል አጋርነትም አዲስ አበባ ላይ በደንብ እየተተገበረ መሆኑን በመጠቆም፤ በመዲናዋ የ120ሺ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡
በሌላ በኩል፤ ትልቁ የጥንካሬያችን ምንጭ የበጀት አጠቃቀማችን ነው፤ ይላሉ ከንቲባዋ፡፡ “ሩቅ ሳትሄዱ የዛሬ አራትና አምስት ዓመት የነበረው ዳታ በእጃችን አለ፡፡ ካፒታል በጀት ከ50 እጅ በታች ነው የነበረው፡፡ በዚህ ሩብ ዓመት 70 እጁ ነው ለካፒታል በጀት የዋለው፡፡” ብለዋል፤ በንጽጽር በማሳየት፡፡
ሌላው የጥንካሬ ምንጭ ደግሞ ውጤታማ የክትትልና የቁጥጥር (ሱፐርቪዥን) ሥራ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ “ቆመን ባንከታተል በዚህ ደረጃ ውጤት ሊመጣ አይችልም ነበር” ሲሉ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ የክትትልና የድጋፍ ሥርዓቱ ውጤትን የሚያመጣ ይሆን ዘንድ የሚሰራን የሚያበረታታ፣ ጉድለት ያለበትን ጉድለቱን ማሟላት የሚችልበትን አቅም እንዲፈጥር የሚደግፍ ሆኖ መቀረጽ እንዳለበትም ያስረዳሉ፡፡ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም ሱፐርቪዥንና ኦዲት የሚያደርጉት ደግሞ የተለያዩ አካላት ናቸው - ከምክር ቤት እስከ ፌደራል መንግሥት እንዲሁም እስከ ፓርቲ የሚደርሱ፡፡
ወደ ኋላ መመለስ አይታሰብም
ከንቲባዋ የተመዘገቡ ውጤቶችንና የመጡ ለውጦችን ብቻ አይደለም የዘረዘሩት፤ ጉድለቶችንና ውስንነቶችንም አንስተዋል፡፡ ውጤቶችና ለውጦች የተገኙበትን መንገድ ስናይ በብዙ ክትትል፣ በብዙ ጉትጎታና በብዙ ግምገማ ነው የሚሉት ከንቲባዋ፤ በትጋት ሰርቶ ውጤት ማስመዝገብ ገና ባህልና ልምምድ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ “ክትትልና ጉትጎታው ቀዝቀዝ ቢል የጀመርናቸው ሥራዎች ይቀዛቀዛሉ፤ ስለዚህ ወደ ባህል መቀየር አለብን” ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ አክለውም፤ “አቅዶ 24 ሰዓት መሥራትን እንዲሁም በሽፍት መሥራትን ባህል ልናደርገው ይገባል፡፡ ጽዳትና ውበት ባህል መሆን አለበት፤መቆሸሽን መጠየፍ አለብን፡፡ እኒህ የምንላቸውን አሰራሮች እንዲሁም ውጤታማነትን ባህል እያደረግን ለመሄድ ነው ማቀድ ያለብን፡፡ አዲስ አበባ ይሄን ጉዞ ጀምራለች፤ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም፤ መመለሻ መንገድም የለም፤ መሄድ ያልቻለ ይወጣል እንጂ፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በግምገማው ማጠናቀቂያም የአፈፃፀም ውስንነትን በማስተካከል፣ አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፤ፈጣን፤ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆን አሰራሮችን ይበልጥ በማዘመን፣ ብልሹ አሰራርና ጉቦኝነትን በመታገል እንዲሁም የገቢ አሰባሰብና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የተጀመሩ ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡