፩. ኆኅተ ነገር
ማኅበረሳባችን የሥነግጥም ባህሉ አንድ የሕይወቱ አካል ሆኖ የኖረ ነው። ታሪኩን በግጥም ይሰንዳል፤ ኃዘኑን በግጥም ይሸኛል፤ ብሶቱን በግጥም ያተናል፤ ፍቅሩን በግጥም ያጣጥማል፤ ትዝብቱን በግጥም ይቀኛል፤ እልሁን በግጥም ይወጣል፤ ጥያቄውን በግጥም ያቀርባል፤ ወዘተ፤
አስረጂዎች
ታሪክን በግጥም መዘከር- ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፣ በእስራት ከሀገር ሀገር ሲንከራተቱ እንዲህ ብለው ገጥመዋል፤
ሰው በድዬ ኖሮ እንዲህ እንደዋዛ
ቁናው ቁናዬ ነው ዙሩ የኔ በዛ።
ኃዘንን መሸኘት፡- ሙሾ አውራጅ እንዲህ ተቀኝታለች፤
መቼም አይረሳ የልጅነት ነገር
ትዝ አለህ መሰለኝ የምትፈጨው አፈር።
ብሶት ሲናጥ እንዲህ ያለ የቅኔ ቅቤ ይወጣዋል፤
የዘንድሮ እንጃ ለመሚጣው በጋ
ብረትህ ከሰው እጅ ሚስትህ ከሰው አልጋ።
መሣሪያውን አውጡት ይገዙታል አሁን እየተሳሳቁ
የእሱ ገንዘብ ገበ,ፊ መሆኑን ሳያውቁ።
የተለመደው ረሃባችን ይህን መሰል የቅኔ ቅርስ አውርሶናል፤
ናሴ ሰንሰለቱ
መስከረም ዳገቱ
ጥቅምት ቁልቁለቱ
ሕዳር ገደርዳሬ
ታሳስ ሆይ ቀብራሬ
እንጀራውን ይዘህ ምነው እስከ ዛሬ
ይህን ጨዋታ ለምን አመጣኸው … በሉኝ። ስለመሠረት ግጥሞች ላወጋችሁ ነው።
የመሠረት አበውና እማት ከላይ የጠቃስናቸውን በመሳሰሉ ስንኞች ነው በየዘርፉ ላለው ሕይወታቸው ጣዕም ሲሰጡ የኖሩት። እሷም ከባለቅኔ አበው አብራክና እማት ማኅፀን እንደመገኘቷ፣ በስንኞች ፈርጥ ያጌጡ ሐሳቦችን ተቋደሱ ብትለን፣ እኔ እጹብ-ድንቅ የምላት የወረሰችውን አሸጋገረች ብዬ ነው፤ እንደ አባቶቿ እንደ እናቶቿ በቅኔ አነጋግራናለችና።
እንደመነሻ ይህን ያህል ካልኩ፣ ቀጥዬ ሺ ጊዜ እንዳፈቅር የተሰኘችዋን መድበሏን የተመለከተ ዳሰሳዬን ላቅርብ።
፪. የሺ ጊዜ ፍቅር ምስክርነት
የመሠረት አዛገ ሺ ጊዜ እንዳፈቅር በዘንድሮው ዓመት (2017 ዓ.ም.) የታተመች የግጥም መድበል ናት። 92 ገጾች አሏት። በጠቅላላው በስንኞች ቅመም ከሽና ያቀረበችልን ግጥሞች 46 ናቸው። ከነዚያ መካከል እንዷ «ሺ ጊዜ እንዳፈቅር» በሚል ርእስ የቀረበችው የስንኞች ክሽን ናት።
ከመነሻዬ እንዳልኩት፣ ምንም እንኳን መሠረት፣ የጥበብ ሐረጓ ከቅኔ ዘር ቢመዘዘም፣ እንደገጣሚ የሚያስመሰግኗትን የግል አሻራዎችን በስንኞቿ አትማለች። ሁለቱን መጥቀስ ይቻላል፤ የዘመናዊ ገጣሚነት አሻራና የጭብጥ ስርጸት።
በዚህ ዳሰሳ ሁለቱን መሠረት እያደረግሁ አወጋለሁ። ከዘመናዊ ገጣሚነቷ ልነሳና፣ አስቀድሜ ስለዘመናዊ ግጥም ጥቂት ፍንጭ ልስጥ።
፪. ዘመናዊ ግጥም
ታሪካዊ ዳራው
ጥበቡን የፈጠረው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጋር ተያይዞ የመጣው የሰው ልጆች ተመክሮና የአኗኗር ዘይቤ አዲስ ቅርጽ ይዞ መከሰቱ ነው። በተከታታይ የተካሔዱት ጦርነቶች የሰው ልጆችን ለሥነልቡናዊ ምስቅልቅል ዳርገዋል። ኢ-አማኒነት፣ ቀቢጸተስፋ፣ ባይተዋርነት፣ ወለፌንዳዊነት፣ የመሳሰሉት ሥነልቡናዊ ቀውሶች በዓለም ላይ ያመጡት የአስተሳሰብ ለውጥ፣ መጠኑ በምንም መመጠኛ የሚመጠን አልነበረም። ከዚያ ትይዩ፣ የዓላማ የሥልተ ምርት ሥርዓት በአመራረት፣ በምርት ክፍፍልና በአኗኗር ዘይቤ ላይ ፋታ የሚነሳ (ድራስቲክ) ለውጥ አስከተለ። ሕይወት ከባህላዊ አመራረት ወደ ኢንደስትሪ ሥልተ ምርት ሲቀየር፣ የሰው ልጀች አስተሳሰብም ልማዳዊውን ፈለግ ሽሮ አዲስ ቅኝት ፈጠረ።
ሥነልቡናዊ አዝማሚያውንና ሥልተ ምርቱን ተከትሎ የመጣው ሁለንትናዊው ለውጥ በጥበቡም ላይ ተጽዕኖ ፈጠረ። ጥበብ (በጠባይዋ) ዘመኗን የማዘመን ልማድ አላትና፣ ዘመኗን ለመምሰል፣ ዘመኗን ለመዋጀት፣ የዘመናዊነት ኩል ተኩላ ተከሰተች። ሥነግጥምም፣ እንደ ጥበብ ቤተሰብነቱ፣ ያንኑ የጥበብን ጠባይ ተከትሎ ግበሩን ሊወጣ፣ አዲሱን ዓለም ተቀላቀለ። የሥነግጥምን አዲሱን ይትባህሉን አስተዋወቁት የሚባሉት እዝራ ፓውንድን፣ ቲ. ኤስ. ኢሊየትን፣ በትለርን፣ ይትስን፣ የመሳሰሉት ገጣምያን ብዕራቸውን ቀርጸው፣ አዲሲቱን የሥነግጥም ሙሽሪት በስንኝ ሊኩሏት ደንገጡሯ ሆነው (ሴትም ባይሆኑ ግድ የለም) ተሰየሙ።
ባሕርያቱ
ዘመናዊ ግጥም ለትውፊታዊው የግጥም ይትበሃል አይገዛም። ይህም ሲባል፣ ክርክም ያለ ምጣኔን ለዘመናዊ ገጣሚ ከላንቃ የሚላከክ ጉዳይ አይደለም። ስሜትን በሚጠቃ የተጠናቀቀ ወለለት ቤት መምታት/መድፋት ለዘመናዊ ገጣሚ ጊዜው ያለፈበት ፋሽን ነው። የወላዊ ምነባን ወግንም ሲጥስ ለነገዬ አይልም። በተቀነጣጠሱ ወይም በተንዘላዘሉ ስንኞች ሲሰነኝ እንመለከታለን። አንዳንዴ ግጥም ሳይሆን፣ እጅ እንዳመጣ በወረቀት ላይ የተበተነ ዝርው ሐሳብ የመሰለ ግጥም ካጋጠመን እሱ ዘመናዊ ለመሆን የቃጣው ነው። በዚህ ጠባዩ ከአቤ ጉበኛ፣ ከከበደ ሚካኤል፣ እንዲሁም ከዘመናችን ወጣት ገጣምያን ጋር ሆድና ጀርባ መሆኑ አይቀርም፤ ከትውፊታዊው የግጥም ጥበባችን ጋርም እንዲሁ። ለዚህ ነው አቤ ጉበኛ በዘመን አጋጣሚ ብቅ ያሉ ዘመናዊ ገጣሚዎቻችንን «አቦል ጀባቴም ግጥም ሆነና …» ሲል የወረፋቸው።
በቋንቋው አጠቃቀሙ ቀላል፣ ግልጽና ለተርታው ተደራሲ ቅርብ የሆነ ነው። ፈረንጆቹ ዘለለታዊ ቋንቋ ለግጥም አይሆንም የሚል ብሂል አላቸው፤ ከዚህም አያይዘው ምርጥ ቃላት በምርጥ አደራደር ይሉናል። ይህ ብሂል ለዘመናዊ ገጣሚ አይሠራም። ምክንያቱም ዘመናዊ ገጣሚ ገና ለገና ግጥም አሳምራለሁ ብሎ ምርጥ ቃላት ፍለጋ፣ ከአጽናፍ-አጽናፍ ሲባትል አይውልም። የእሱ ቋንቋ የሰላምታ ያህል ቀላል ነው።
ውስብስብ ሐሳቦች፣ እስቦችና የስሜት ውልብልቢቶች ፍንትው ባለ ምነባና በክሱት ምሰላ ይሰነኛሉ። ሆኖም፣ በቀላል ቃላት፣ በግልጽ ምነባና በክሱት ምሰላ የሚቀርቡት ጭብጦች ረቂቅ ናቸው፤ ገጣሚው እንደዘበት የወረወራቸው ቃላት ውስጠ ምሥጢራቸው ሩቅ ነው፤ ለተደራሲ አይገራም። ቀላል የተባሉት ቃላት ጥልቅ የሆኑ የስሜት ውልብልቢቶች ይውለበለቡባቸዋል።
ዘመናዊ ገጣሚ፣ የሚያተኩረው ለእኛ ተራ በሚመስሉን ጉዳይና ፋይዳዎች ላይ ነው፤ ግን በጥልቅ ስሜት ነው የሚገልጻቸው። እያንዳንዱ ጭብጥ በነባራዊ ዓለም ላይ ያተኩራል። በተጨባጭ የታችኛውን መደብ የሰው ልጆች ጥያቄ ፈጥጦ እንዲታይ በማድረግ ሰብአዊነትና ዲሞክራሲ ያላቸውን ቦታ ያሳያል።
፫. የመሠረት መሠረቶች
የመሠረት ግጥሞች ሁለት የብቃት መሠረቶች እንዳላቸው አስቀድሜ ጠቁሜአለሁ፤ ዘመናዊነትና የጭብጥ ስርጸት። ከዘመናዊ ባሕርያቸው እንጀምር።
ብዙዎቹ ስንኞች ከለመድንው ሥልተ ምታዊ ፈሰሳና ወለለታዊ ውበት ወጣ ይላሉ። ስናነባቸው፣ ጎምቱ ገጣሚዎቻችን ሰለሞን ዼሬሳ፣ ሰይፉ መታፈሪያ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ትዝ ይሉናል። የነዚህ ገጣምያን ሥራዎች፣ ዐማርኛ ካኖረው የሥልተ ምት ሰንሰለት ራሳቸውን ነፃ በማውጣት፣ የግላቸውን ሕቡዕ የፈሰሳ ጅረት ቀየሰዋል። በዚህ የተነሳ፣ ስንኞቻቸው ወግ-ሰብር (ነውጠኛ) ተባሉ፤ ለዚህ ነው አቤ ጉበኛ «አቦል ጀባቴ» ማለቱ፤ ግጥም እሱ የሚገብርለትን የግጥም ከራማ ትውፊት ስለሰበረበት።
መሠረት የስሜት መብረቅ ሲበርቅባት፣ የሚቀጣጥልባት የምናብ ትንታግ ሲፈጃት በሚፍለቀለቁ ቃላት ታተነዋለች፤ ትንታጉን መቋቋም ሲሳናት። እኔ ያ ስሜት ነው በወረቀቱ ላይ ሲንበለበል የማየው። እነሆ አስረጂ፤
ገበር ምጣድ የሚተክነው፣
እቶን ዋዕይ የሚበላው፣
ለዳቦው፡፡
ደግሞም ለሌላው፡፡
አይቆርሰው ቢሉ፣ አይቀምሰው፤
አያሸተው፣ አያውቀው፤
ሕይወቱ ሕይወት መክፈል ነው
ለሌላው።
ይህን የመሰለ የስሜት ትንታግ የሚተገትጋት ነፍስ ቃላት ለመቀሸር፣ ስንኝ ለማሳመር የሚያስችል ቀልብ የላትም!? በምጥ የተያዘች ሴት ገና ስለሚወለደው ልጅ ጌጣጌጥ ማሰላሰል ይቻላታልን!? እንዴት ተብሎ …!? ፈረሰኛ ውኃ የወሰደውን ሰው አሰብሁ፤ እሱ ለውኃው ግስጋሴና የፈሰሳ ዜማ ለማፍለቅ እንዴት ይቻለዋል…!?። እንዴት ሆኖ …!? ድንገት በሚንቀለቀል እሳት ውስጥ የተጣለን ሰው ደግሞ አሰብሁ፤ እሳቱ የሚተገትገው ሰው ስለነበልባሉ ቅርጽ ለመጠበብ በምን አቅሙ ይችላል…!? አይሞከርም!
ፈረሰኛ ስሜት እንደዚያ ነው፤ የግጥም ስሜትም ትንታግ ነው፤ ትንታግን የሚያውቅ ያውቀዋል። ለምሳሌ ዮፍታሔ ንጉሤ ያውቀዋል፤ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ያውቀዋል፤ ሰይፉ መታፈሪያም ያውቀዋል። ባጭሩ፣ ገጣሚዋ ጎምቱ ገጣሚዎቻችንን በስንኞቿ ልትዘክራቸው የጥበብ ዘመን መልሶ ከሰታት ልብል።
አንብበን እንፍረድ!
ሁለተኛ አስረጂ እናምጣ።
በኖርኩበት ዘመን፣ ባለፍኩበት ሁሉ፣ ጥበቃህ ከሁሉ፤ በረከትህ ሙሉ፡፡
ቸርነት፣ ይቅርታህ ከባህር የሰፋ. . .
. . . ጥልቅ ከውቅያኖስ፤
ስጦታህ የማያልቅ፣
. . . ለሁሉ የሚደርስ፡፡
ሁለተኛውን ጉዳይ ላንሳ፤ ጭብጣዊ ፋይዳ …
ብዙዎቹን ግጥሞች ሳነብ የመጣልኝ ሐሳብ፣ ገጣሚዋ የትዝታ ራሮት (nostalgia) እንጉርጉሮ በልቡናዋ ጅረት የሚፈስ መሆኑ። ይህም (ለምሳሌ) ትናንትን በማድነቋ፣ የእናትን ቱባ ብሂል በማቀንቀኗ እንዲሁም ድንግል (rustic-styled) ሰብእናን በግጥሞቿ ውስጥ በማጉላቷ ይንጸባረቃል።
በኩታሽ ከልዪኝ፤ በሰፊው ቀሚስሽ፤
ከማንም ከምንም፤ ልከለል በቀልብሽ።
ከኋላሽ ልከለል፣ከፊት ቆመሽ ጋርጂኝ፤
ማን አባቱ ደግሞ? ምን የቆረጠው ነው የሚነካ ልጄን?»
ብለሽ ሁኚኝ ምሽግ፤
እያለ ከሚከለበሰው የስንኝ ጅረት ውስጥ የምንዋኘው እናትን የሞገሷ ድባብ የሆነውን ቀሚሷንና መጎናጸፊያዋ የሆነውን ኩታዋንም የዋናችን መቅዘፊያ አድርገን ነው፤ ከቱባ ምልዓቷ ጋር። ዋናው የእናቶቻችን አንጡራ ዐውደ ዓለም ይመልሰናል። ነገሬን ከሌላ ግጥም ስለእናት በተዜሙ በእነዚህን የመሠረት ስንኞች ቅምሻ አጣጥሙልኝ፤
ከእናት ሆድ ከእምዬ፣ ጭንቅ ጥብብ ታይቶ፣
የህይወት መቁጠሪያው፣ ሲጀምር ከዜሮ፤
በሌላ ገጽ ስሜቴን የሚፈታተኑ ሌሎች ስንኞች ተቀብለው ወለፈንዴነቴን ነገሩኝ፤
በጩኸት፣ በእሪታ. . . የትም በማያደርስ፣
የአቅም መፍጨርጨር፣ ላንቃ እስከሚበጠስ!
በሰፊው ጎዳና፣ የጀመርነው ጉዞ፣
ዜሮ ብሎ ሲቆጥር፣ ፍርሃትን አርግዞ፡፡
ይኸው በእናት ውለታ የሚጀምረው ግጥም፣ ዝቅ ሲል፣ የወለፈንዴነቴን ዶሴ ይመዘዋል። የዶሴው መዘዝ የሚመዘዘው ደግሞ ግጥሙ እንዲህ ብሎ ሲቋጭ ነው፤
የመጨረሻችን፣
ለህፃን፣ ለወጣት፣ ለአዛውንት፣ ለጀግና. . .
ለሁሉም ያስፈራል፣ መኖር ውብ ነውና፡፡
የመሠረት ግጥሞች ጭብጥን ለማስረጽ አጥብቀው ይተጋሉ። ጭብጦቹ በአብዛኛው አብነታዊነት የሚታይባቸው ናቸው፤ በሌላ አገላለጽ ክላሲክ አተያይ ላይ ይመሠረታሉ። በዚህ ደግሞ ከበደ ሚካኤልን ታመጣብኛለች።
«ሺ ጊዜ እንዳፈቅር» የሚለውን ግጥም ዋቢ እንጥራ። መጽሐፍ፣ «ከሁሉ ፍቅር ይበልጣል» እንዳለ፣ ፍቅር ሥነመለኮታዊ ፍልስፍናም (በክርስትና፣ በእስልምና፣ በቡድሐ፣ …) ያጸደቀው የነገር ሁሉ ማዋቀሪያ አምድ ነው። መሠረት ይህን አብነታዊ ፍልስፍና በስንኞቿ ለማስረጽ ነው «ሺ ጊዜ እንዳፈቅር» የምትለን።
አምጣ-ድገም ብባል፣ «ብርር. . . በይ!» የሚለውን ሌላ ግጥም ዋቢ ጠቅሼ፣ ምስክርነቴን አጠናለሁ። ይኸው የግጥሙ መቋጫ፤
ብርር. . . በይ ወደላይ፤
ከጥላቻ በላይ፡፡
ከጥላቻ በላይ ምን አለ፤ የፍቅር አዝመራ…! የፍቅር መንፈስ፤ የፍቅር እልልታ፤ በቃ …!
ገጣሚዋ፣ በሌላ ግጥሟ እንዲህ በማለት አርኬዎቿን ትደመድማለች፤
ዛሬን የለገሱን፣
እልፍ ነፍሶች አሉ፡፡
መምህሩ «ዋኖቻችሁን አስቡ» ሲል መልካም አለ። መሠረት እንዳለችው፣ ዛሬ የቆምነው ዋኖቻችን ባቆሙት አምድ ላይ ተዋቅረን ነው፤ ዋኖቻችን በከሰሙት ካስማ ተቆላልፈን ነው። ዋኖቻችን በገረገዱት ግርግዳ ተማግረን፣ እነሱ ባዋቀሩት ጣራ ሥር ተጠልለን እኮ ነው፤ ምሰሶው እነሱ፤ ዋልታውም እነሱ … እንደ ሰዎችማ ቢሆን፣ ባለቅኔው መንግሥቱ ለማ፣ «ፈጣሪህን ፈጣሪ ብታደርገው ኖረ፣ በአንድ ቀን ጀምበር ባለቅነው ነበር» ብሎ እንደጠቀሰ፣ እንኳን በጅስማችን በአጽማችንም የለንም ነበር፤ እንኳን በሩሐችን በስማችንም የለንም ነበር። አኒባልን የመሰለ ጀግና አስከብሮ ያኖራት ከታርጎ ዛሬ በዓለሚቱ ካርታ ላይ ስሟ ተጽፎ አይገኝም። ትሮይ እኮ ከዓለም ካርታ ስሟ ተፍቆ የአሻራዋ ደብዛ የተገኘው ከሰባተኛው ከርሰ ምድር ውስጥ ነው፤ በሥነምድር አጥኚዎች ተቆፍሮ።
እናጠቃለው፤
የመሠረትን ግጥሞች ሁለት አቅጣጫዎችን ለማየት ሞከርን። አንዱ አሰነኛኘቷ ነው። በወጥ ሥልተምታዊ ፈሰሳና በድምፆች ወለለት (በቤት መምቻ/መድፊያ) እየተቃኘን ያደግንና የኖርን ነንና፣ ከመሠረት ግጥም ይህን ግጥማዊ ምሱን ሲያጣ፣ ሥነግጥማዊ ቀልባችን ቆሌው መሳቀቁ አይቀርም። ግን ባለ ራእዩ «ጆሮ ያለው ይስማ …» እንዳለው፣ ለሙዚቃዊ ቅርጽ መንሰፍሰፍ ልማዳዊ አባዜ እንጂ፣ ሥነግጥማዊ ግዴታ አይደለም የሚለውን እናስምርበት፤ ዘመን ወልዶታልና።
ሁለተኛው አቅጣጫ ጭብጣዊ ፋይዳው ነው። አልፎ-አልፎ፣ ነባር ፍልስፍናዎቻችንን የሚሞግቱ ጭብጦች ቢታዩም፣ የገጣሚዋ የጭብጥ አሻራ የታተመው ግን አብነታዊነት ካላቸው ቀለሞቻቸን እያረመደ መሆኑን እናጤናለን።
ጉዳዩ በዚህ ልክ ብቻ የሚነገር አልነበረም። ሆኖም፣ መጽሐፍ፣ «አብዝኆተ ነገር ያዘነግህ ልብ» እንዲል፣ ለፍንጭ ያህል ይህቺን ፍጭጭ ካደረግሁ፣ አንባብያን ደግሞ ከእኔ የላቀውን ይጨምሩበት።
አንብቦ ነው መፍረድ …!