Wednesday, 19 February 2025 19:43

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

#በዛሬዋ_ዕለት
ከ 88 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን በአብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም መሪነት በኢጣልያኑ የጦር አዛዥ ጄነራል ግራዚያኒ ላይ በቦንብ ያደረጉት የግድያ ሙከራ ምክንያት የኢጣሊያን ወታደሮች በቂም በቀል በመነሳት በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለ 3 ተከታታይ ቀናት ዘግናኝ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በህዝቡ ላይ ጭፍጨፋ ያደረሱበት ዕለት ነበር።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በፋሺስት ኢጣሊያ በግፍ የተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት ሲታወሱ......
የካቲት 12 ቀን በኢትዮጵያ ታሪክ የተለየ ቀን ነው፡፡ የኢጣሊያዋ ኔፕልስ ግዛት ልዑል ልጅ መውለዱን ለመዘከር ግራዚያኒ በዚህ ቀን የአዲስ አበባን ደሃዎች ሰብስቦ ለመመጽወት ባደረገው ጥሪ መሰረት ከ 3ሺ የሚበልጡ አቅመ ደካሞች በጥዋቱ በ 6 ኪሎው ቤተመንግስት ተገኝተዋል፡፡
በዚህ ቀን ኢትዮጵያውያን ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚለው መረጃ እስከ ሮም በመሰማቱ የቤተመንግስቱ ውስጥና ዙሪያ መትረየስ በታጠቁ ልዩ ወታደሮች እንዲጠበቅ ተደርጓል፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ይህንን ጠንካራ ጥበቃ አልፈው ውስጥ ገብተዋል፡፡
ከቀኑ ለስድስት ሩብ ጉዳይ አካባቢ ሲሆን ከፍተኛ ፍንዳታ በቤተ መንግስቱ ተሰማ፡፡ ከፍ ወዳለው የቤተመንግስቱ ደረጃ የተወረወረው ቦምብ ደግሞ ግቢውን በጩሀት አናጋው፡፡ የመጀመሪያው ቦምብ ባለመትረየስ ጠባቂውን አስወገደው፡፡ 2ኛው ቦምብ ከግራዚያኒ አጠገብ የነበረውን ምሰሶ አፈራረሰው፡፡ ግራዚያኒ ወደ ውስጥ ሲሸሽ ጀርባው፣ ትከሻውና የቀኝ እግሩን ከ 350 በሚበልጥ የቦምብ ፍንጣሪ ቆሰለ፡፡ የካሜራ ባለሙያውና ወታደሮች ግራዚያኒን ከወደቀበት አንስተው በመኪና በመጫን ወደ ሆስፒታል ይዘውት በረሩ፡፡
ሶስተኛው ቦምብ ፖጊያሊ ፊት በመውደቅ ፍንጣሪው አቡነ ቄርሎስን ሲያቆስላቸው ጃንጥላ ያዣቸውን ደግሞ ገደለው፡፡ የኢጣሊያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ሊዮታ በቦምብ እግሩን አጣ፡፡ የፋሺስት ፓርቲ ዋና ጸሀፊና የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች በድንጋጤ ለምጽዋት በ6 ኪሎ በተሰበሰበው ህዝብ ላይ እሩምታ በመተኮስ ከ1ሺ የሚበልጡትን ገደሉ፡፡ የጥቃቱ ዋና ፈጻሚዎች ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ ከጊቢው በመውጣት ተሰወሩ፡፡
በቀጣይ ሰአታት ጥቁር ከነቴራ ለባሽ የኢጣሊያ ልዩ ወታደሮች የቴሌፎንና የፖስታ አገልግሎትን ዘጉ፡፡ ወዲያው መሃል ፒያሳ አራዳ ባለው የፋሽስት ዋና ጽ/ቤት የነበረው ጎዶ ኮርቴሌ የፋሽስት ወታደሮች ለሚቀጥሉት 3 ቀናት ኢትዮጵያውያንን እንዲጨፈጭፉ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በዚሁ ምሽት አዲስ አበባ የእርድ ቄራ ሆነች፡፡
ነዋሪዎቿ ቤት ከውጭ እየተቆለፈባቸው ከውጭ በሚለኮስ እሳት እንዲነዱ ተደረገ፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የተገኙት ደግሞ እየታፈሱ በመኪና ተጭነው ተወስደው በግራዚያኒ ዋና መምሪያ ተረሸኑ፡፡ ከሚነዱት ቤቶች አምልጦ ለመውጣት እድል ያገኘውን ደግሞ የኢጣሊያ ወታደሮች ከደጅ ሆነው በጥይት ለቀሙት፡፡
የጥቃቱ አቀናባሪዎችንና አድራሾችን ለመያዝ ጥብቅ ምርመራና አሰሳ ተጀመረ፡፡ የኢጣሊያ ደህንነቶች ከምሽቱ በ 2 ሰአት የአብረሃ ደቦጭን ቤት ሰብረው ሲገቡም እጀታው አረንጓዴ፣ቢጫ እና ቀይ በሆነው የኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት በተቀባ ሳንጃ የኢጣሊያ ባንዲራ ተቦጫጭቆ አገኙ፡፡ በመቀጠል የሞገስና የአብርሃ ጓደኞችን ማደን ተጀመረ፡፡
አብርሃና ሞገስ ከምሽቱ 1:00 ሰአት አካባቢ ወደ ጀርመን ሚሽን በመሄድ ጓደኛቸው ስብሀትን በአጥር ቢያስጠሩትም ስብሀት አብሯቸው ለመሄድ ዝግጁ ስላልነበር ብቻቸውን ከተማውን ለቀው ሸሹ፡፡ ከጥቂት ሰአታት በኋላ የኢጣሊያ ወታደሮች የጀርመንን ሚሽን በመክበብ ስብሀትን እያዳፉ ወሰዱት፡፡ አርበኛ ሸዋ ረገድ ገድሌንም በማታ ወስደው በኤሌክትሪክ ንዝረት ቢያሰቃይዋትም ሚስጥር ሳታወጣ ቀረች፡፡
ቅዳሜ ጥዋት በድንጋጤ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሲሯሯጡ የተገኙ ነዋሪችም ታፍሰው ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ አጠገብ ተረሸኑ፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ ተሸሽገው የነበሩ በ 100ዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ኤምባሲው አሳልፎ እንደሰጣቸው ኤምባሲው በር ላይ እንደ ውሻ እየተቀጠቀጡ ተገደሉ፡፡
ይህ ለአሜሪካ ህዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር እና ኢትዮጵያ የሚገኘው አምባሳደር ዜናውን በማግስቱ አስተባበሉ፡፡ ምኒልክ አደባባይ አቅራቢያ ሆኖ ይህንን ግፍ ይመለከት የነበረው ወጣቱ ልጅ እምሩ ዘለቀም ከሰአታት በኋላ ቤቱን ሰብረው በገቡ የኢጣሊያ ወታደሮች ከእናቱና 2 እህቶቹ ጋር ተይዞ ታሰረ፡፡
እሁድ እለት የ 3 ቀኑን ጭፍጨፋ ለማስቆም በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች የሚከተለው አዋጅ ተለጠፈ፣
“ ሞሶሎኒ እንደ ፈጣሪ ሃያል ነው፡፡ ፈጣሪም ሆነ ሞሶሎኒ ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው፡፡ ሞሶሎኒ ተበሳጭቶባችሁ ነበር፡፡ አሁን ግን ቁጣው በርዷል፡፡ ወደ የቤታችሁ በመሄድ እለታዊ ተግባራችሁን ቀጥሉ፡፡”
ይሁን እንጂ ከዚህ አዋጅ በኋላም ግድያው ቀጥሎ ነበር፡፡ የበቀል ቅጣቱን ለማምለጥ ከቤታቸው ከወጡት ወደ 5ሺ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ ብዙዎቹ የአርበኞችን ትግል ተቀላቀሉ፡፡ በሁለት ቀን ተኩል በኢጣሊያ የግፍ ጭፍጨፋ የተገደሉትን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር አንዳንድ ወገኖች እስከ 30ሺ እንደሚደርስ ሲገልጹ ሌሎች ደግሞ ቁጥሩን ከላይ 17ሺ - 18ሺ ያደርሱታል፡፡
©️ የአርበኞች ጀብዱ፣ Jeff Pearce እንደጻፈው፣ ኤፍሬም አበበ እንደተረጎመው፣ ገጽ 205-212
ክብና ዘላለማዊ ዕረፍት ለሰማዕታት ????
#ታሪክን_ወደኋላ

Read 415 times