“ዝክረ አድዋ ኢትዮጵያዊነት” የተሰኘ ልዩ የኪነ-ጥበብ መርሃ ግብር፣ በመጪው ሳምንት አርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በአድዋ ሙዚየም ይካሄዳል፡፡
የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይንመንት እንደገለጸው፣ በአድዋ ድል ዋዜማ በሚካሄደው በዚህ የኪነጥበብ መርሃ ግብር፤ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ዝክረ አድዋ” የተሰኘ ጥናታዊ ፅሁፍና ዲስኩር በምሁራን የሚቀርብ ሲሆን፤ የግጥም ምሽትና የስታንዳፕ ኮሜዲም እንደተሰናዳ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ፖለቲከኞች በሰላምና አንድነት ዙሪያ አነቃቂ ንግግር፣ እንዲሁም ጀግኖች አርበኞች ሽለላና ፉከራ በባህላዊ ባንድ ታጅበው ያቀርባሉ ተብሏል።
በመርሃ ግብሩ ደራሲ፣ ገጣሚና ፀሀፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ አምባሣደር ዲና ሙፍቲ፣ ዶ/ር ወዳጄነህ ማህረነ፣ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ መምህር ዲያቆን ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ፣ መጋቢ ቸርነት በላይነህ (ፓስተር ቸሬ)፣ አርቲስት ተስፋዬ ሲማ፣ አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤልና ሌሎችም እንደሚሳተፉ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን ብሎም የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት በሆነው የአድዋ ድል ዋዜማ ላይ በሚካሄደው መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚታደሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመግቢያ ዋጋ መደበኛ 300 ብር፣ VIP ደግሞ 500 ብር ሲሆን፤ ትኬቱ በቴሌ ብር፣ በጃፋር ቤተ-መፅሐፍት፣ በ2 ሺህ ሐበሻ የባህል ምግብ አዳራሽ እንደሚገኝ አብርሃም ግዛው ኢንተርቴንመንት ጠቁሟል፡፡