Saturday, 22 February 2025 11:23

ለመጥፎም ዘመን ባለጊዜ አለው

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በሞንጎላውያን አፈ-ታሪክ ውስጥ የሚከተለው  አንድ ታዋቂ ተረት ይገኛል፡፡
“ስለ ዓለም ዕጣ-ፈንታ ሦስት የተለያዩ አስተሳሰቦች አሉ፡፡
የመጀመሪያው የሳንሳ ግልባጭ መኪና (crane) አስተሳሰብ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ መኪና በወንዝ ውስጥ ባሉ ቋጥኝ ድንጋዮች መካከል እንዴት በቀላሉ ያለሀሳብ እንደሚሄድ አይታችኋል፡፡ ጭንቅላቱን ሽቅብ አያጎነ እንደገና እንዴት ወደ ኋላ እንደሚቆለመም አይታችሁልኛል? ይሄ ክሬን የተባለ የሳንሳ - ገልባጭ- መኪና አንድ ሁነኛ እርምጃ ቢወስድ ተራሮች ተደረማምሰው እንደሚወድቁ፣ መሬት እንዴት አርዕድ አንቀጥቅጥ እንደሚይዛትና ለዘመናት የቆሙት ዛፎች እንዴት እንደሚብረከረኩ ያስባል፡፡
ሁለተኛው አንበጣ ነው፡፡ የአንበጣ አስተሳሰብ ደግሞ የተለየ ነው፡፡ አንበጣ ሆዬ አንዲት ጠጠር ላይ ቀጥ ብሎ ያስባል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የጥፋት ውሃ መጥቶ ዓለምን እንደሚያጥለቀልቃትና ሁሉም ህይወት ያላቸው ፍጥረታት በጎርፍና በማዕበል እንደሚጠፉ ያሰላስላል፡፡ በዚህ ምክንያት ይኸው እስከዛሬ ከተራሮች ጫፍ ላይ የሚጠራቀመውን ዝናብ-አዘል ዳመና በዓይነ-ቁራኛ ያስተውላል፡፡
ሦስተኛዋ የሌሊት ወፍ ናት፡፡ የሌሊት ወፍ አንድ ቀን ሰማይ ወድቆ ብትንትኑ እንደሚወጣ ታምናለች፡፡ ከዚያም ህይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ድምጥማጣቸው ይጠፋል፡፡ በዚህ ምክንያት ይኸው እስከዛሬ የሌሊት ወፍ አንዴ ወደ ሰማይ ተወንጭፋ ትሄዳለች፤ አንዴ ደግሞ ወደ መሬት ትወርዳለች - ይህን የምታደርገው ሰማይና መሬት ሰላም መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነው ይባላል፡፡
****
አለምንም ሆነ ሀገርን በገልባጭ ጉልበታቸው እንዳሻቸው የሚያደርጉ አያሌ ነገሥታትና  መሪዎች አጋጥመውናል፡፡ ከቶውንም ቋጥኝ በፈነቀሉ ግንድ በጣሉና ተራራ በናዱ ቁጥር ቀጥሎ ደግሞ መሬትን አንቀጠቅጣታለሁ የሚል የሳንሳ - ግልባጩ መኪና አስተሳሰብ ያላቸው አይተናል፡፡ ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ ያሉ ሹሞቻቸው፣ አፈ-ንጉሶቻቸው፣ አዝማቾቻቸው፣ አፈ ቀላጤዎቻቸው፣ ሰብቀኞቻቸው፣ ካድሬዎቻቸው ወዘተ ሁሉ ዛሬ ቋጥኝ አቀበቱን መደረማመስ ከተቻለ ነገ ሰማይና መሬትን ቀውጢ ማድረግ አያቅትም የሚለውን አስተሳሰብ ይጋራሉ፡፡ “የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ”፣ “የአጣቢ ልጅ አለቅላቂ” እንዲል መፅሐፍ፡፡
ነገ የጥፋት ውሃ እንደሚመጣና እከሌ ከእከሌ ሳይል አገር ምድሩን የሚጠራርግ ማዕበል እንደሚያጥለቀልቀን የሚያስቡ - የአንበጣው አስተሳሰብ ያላቸው አያሌ ናቸው፡፡ እኒህኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥፋቱ የሚመጣው ገልባጩ እንደሚያስበው ከውስጥ ሳይሆን ከውጪ ነው፡፡ ጥፋቱ ከውጪ ይመጣል ብለው ግን እንደ መዳኛ የሚያስቡት ስፍራ እንደ አንበጣው - ጠጠር ያለ ነው፡፡ ምሽግ አልፈጠሩም፡፡ የኖኀ-መርከብ መስራት አልጀመሩም፡፡ መሣሪያ አላዘጋጁም፡፡ መአቱን እየለፈፉ፣ ስለመጪው የፍዳ ዘመን እየተናገሩ፣ ጠጠር-አናት ላይ ቆመው ጎርፍ ይጠብቃሉ፡፡
ከፊሎቹ ደግሞ ሰማይ ወድቆ እንክትክቱ እንደሚወጣ በዚያም ሰበብ ፍጥረት ሁሉ እንደሚንኮታኮት ያስባሉ፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ አንዴ ወደ ስልጣኑ መንበር ይወጣሉ፤ አንዴ ደግሞ ታች ወደ ታደመው ህዝብ ይወርዳሉ፡፡ እንደዋዠቁ ይኖራሉ፣ እንደዋዠቁ ይሞታሉ - እንደ ሌሊት ወፏ ናቸው፡፡
በሀገራችን የጉልበተኛው ገልባጭ መኪናም፣ የአንበጣውም፣ የሌሊት ወፏም አመለካከት የሚበጅ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በእኔው ተጀምሮ በእኔው ይለቅ የሚል አስተሳሰብ ማን-ያህሎኝነትን ብቻ ነው የሚጠቁመው፡፡ እንደ አንበጣ ቅንጣት ታህል ቦታ ብቻ ስለያዙም ከመዓቱ እንድናለን ብለው የሚያስቡም ጎደሎ-መፍትሄ በማሰብ ደህንነት የሚታያቸው ናቸው፡፡ እንደሌሊት ወፍ ከስልጣኑም ከህዝቡም እየቀሰምኩ እኖራለሁ የሚለውም አስተሳሰብ ከዚህ ቀደም ደጋግመን እንዳየነው የአድር-ባዮችን ዥዋዥዌ ከመጠቆሙ በስተቀር የሚፈይደን ነገር የለውም፡፡
ይልቁንም ከኃይል ይልቅ በዲሞክራሲና በመተማመን፣ በቅንጣት የሥልጣን ምሽግ ሳይሆን በብዙኃኑ የተረጋጋ የስልጣን ባለቤትነት፣ በመዋዠቅ ሳይሆን አግባብነት ባለው ፅናት የምትመራ አገር ናት የሁላችን ማረፊያ መሆን ያለባት!
እንዲህ አይነት አገር እንድትኖረን የምንሻ ከሆነ ስለ ባለጊዜ እያወራን ጊዜያችንን አለማባከን ይጠበቅብናል፡፡ አንዱን ስንጥፍ አንዱ እየተቀደደ እንደሚያስቸግር ቦላሌ አልጨበጥ ያለውን የሀገራችንን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር በጊዜ የምንነጋገርበት ሁነኛ መድረክ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ ተወያይቶ፣ ችግር ለችግር ተግባብቶ፣ ሁሉ ቢተባበርስ ችግራችን በዋዛ የሚፈታ ነወይ ብሎ ማሰብ ዋና ነገር ነው፡፡ መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር፣ ለመጥፎም ዘመን ባለጊዜ እንዳለው ነው!!

Read 889 times