“ይህ በየቦታው ሊነገር የሚገባ ድንቅ ታሪክ ነው”
በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የሚገኘውና በተለምዶ ዋንዛ ሰፈር እየተባለ ይጠራ የነበረው መንደር አሁን አዲስ ስያሜ አግኝቷል - ”የበጎነት“ መኖሪያ መንደር የሚል፡፡ ስያሜውን ያገኘው ደግሞ በከተማዋ በስፋት እየተለመደ በመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ቀና ልብ ባላቸው ባለሃብቶች በተገነቡ በርካታ መኖሪያ ቤቶች በመሞላቱና መኖሪያና መጠጊያ ያጡ አቅመ ደካሞች መጠለያ ያገኙበትና የዘመነ አኗኗር የጀመሩበት በመሆኑ ነው፡፡
በ2015 ዓ.ም በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሲጀመር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ ወደ ዋንዛ ሰፈር ጎራ ብለው ነበር፡፡ የነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ ከጎበኙ በኋላም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሻለ የመኖሪያ ሥፍራ እንደሚሸጋገሩ ቃል ገቡላቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ባህል እየሆነ በመጣው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የበርካታ ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ተቃሏል፡፡ ነዋሪዎች ክብር ያለው ኑሮ ይገባቸዋል የሚል ጽኑ እምነት ያለው የከተማ አስተዳደሩ፤ ዜጎች ከደቀቁና ለኑሮ ምቹ ካልሆኑ ቤቶች ወጥተው የተሟላ የመሰረተ ልማት ወዳላቸው ዘመናዊ ቤቶች እንዲሸጋገሩ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም የአዲስ አበባ አስተዳደር ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመተባበር በበጎነት መንደር የገነባቸው ሁለት ባለ 9 ወለል የመኖሪያ ህንጻዎች ተጠናቀው በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመረቁ ሲሆን፤ መኖሪያ ቤቶቹም ለነዋሪዎች ተላልፈዋል፡፡
በዚህ የመኖሪያ መንደር የእንጀራ ማእከል ህንፃ ተገንብቷል፣ የወንዶችና የሴቶች የውበት መጠበቂያ፤ ፀጉር ቤት፣ የልብስ ስፌት ማሽን ተሟልቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ለእናቶችና ለህፃናት አገልግሎት እንዲሆን ተቀናጅቶ የተሰራ የልማት ስራ ተካቶበታል፡፡ በእንጀራ ማእከሉ ያሉ እናቶች ከክፍለ ከተማው የተደራጁና ሰልጥነው ወደ ስራ የገቡ ናቸው፡፡
በፀጉር ቤቱ፣ በውበት መጠበቂያዎቹ፣ በህፃናት እንክብካቤዎችና በልብስ ስፌት ላይ የሚሰማሩት የነገዋ ሴቶች ሰልጣኝ እህቶቻችን ናቸዉ፡፡
የመኖሪያ ቤቶቹ ተጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች ቤታቸውን ከተረከቡና ገብተው ከጎበኙ በኋላ በሰጡት አስተያየት፤ በከተማ አስተዳደሩ የተሰጣቸው መኖሪያ ቤት ከግምታቸውና ከጠበቁት በላይ እንደሆነባቸው በመግለጽ፤ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አቶ ገብረመድህን አያሌው አካል ጉዳተኛ የአካባቢው ነዋሪ ሲሆኑ፤ የቀድሞ ቤታቸው ሊወድቅ የደረሰና ዝናብ የሚያስገባ እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የመጸዳጃው ሩቅ መሆን ለእርሳቸው ዓይነት በዊልቼር ለሚጠቀም አካል ጉዳተኛ አስቸጋሪ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አሁን የተሰጣቸው መኖሪያ ቤት ግን በቃላት ከሚገልጹት በላይ ምቹና ያልጠበቁት እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡
“የበፊቱ መኖሪያ ቤት የግድ ሆኖ ነው እንጂ ለእንደ እኔ ያለው አካል ጉዳተኛ አመቺ አልነበረም፡፡ አሁን ዊልቼሩ ቤት ድረስ ገብቶ ሶፋ ላይ ቁጭ ያደርገኛል፡፡ ሁሉም ነገር ምቹ ሆኖልኛል” ብለዋል፤ አቶ ገብረመድህን፡፡ በቃላቸው መሰረት አዲስ መኖሪያ ቤት ገንብተው ለሰጧቸው ከንቲባ አዳነች አቤቤም፤ “የሥራ ጊዜያቸውን የተባረከ ያድርግላቸው” ሲሉ አመስግነዋል፡፡
ሌላዋ በአዲሱ መኖሪያ ቤታቸው የተደሰቱት ወ/ሮ እልፍነሽ ሰንበቴ፤ “ከንቲባዋ በ3 ወር ውስጥ ቤት ሰርቼ እሰጣችኋለሁ ስትለኝ እንደዚህ ዓይነት ቤት ሰርታ የምትሰጠኝ አልመሰለኝም ነበር” ብለዋል፡፡ የቀድሞው ቤታቸው ምን ይመስል እንደነበር ሲናገሩም፤ “አስር ሆነን ነበር አንድ ቤት ውስጥ የምንኖረው፤ እኔ እግሬ ስለማይታጠፍልኝ መጸዳጃ ቤት ወንበር ተቀምጦልኝ ነበር የምጠቀመው” ያሉት ወ/ሮ እልፍነሽ፤ “ወደ አዲሱ ቤት ስገባ በደስታም በድንጋጤም እግሬ መሬት መርገጥ አቅቶት ነበር፡፡” ሲሉ የተፈጠረባቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡
የቀድሞ ቤታቸው በክረምት ሃይለኛ ጎርፍ የሚሄድበትና የሚቸገሩበት እንደነበር የሚናገሩት ሌላዋ የቤት ተጠቃሚ ወ/ሮ አረጋሽ ቱሉ፤ እንደዚህ ጽድት ያለ ራሱን የቻለ መኖሪያ ቤት ይሰጠናል ብለን አልጠበቅንም ነበር ብለዋል፡፡ ከበፊቱ የተሻለ ይሆናል ብለን ነው የጠበቅነው እንጂ በዚህ ደረጃ አልጠበቅንም ያሉት ወ/ሮ አረጋሽ፤”እግዚአብሄር ይመስገን የእጥፍ እጥፍ አድርገው ነው የሰጡን“ ሲሉ ጥልቅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በበጎነት መንደር የመኖሪያ ህንጻዎች የምርቃት ሥነስርዓት ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር፤ “ይሄንን ለመሥራት ብዙ ርቀት መሄድ አላስፈለገንም፤ መንግሥት ቦታውንና አንዳንድ ተጨማሪ የሚላቸውን ግብአቶች በማቅረብ፣ ባለሃብቱ ደግሞ ገንዘቡን ይዞ በጋራ በመተባበር ለወገኖቻችን የሰራናቸው ቤቶች ናቸው” ብለዋል፡፡
ልማታችን ሁሉንም በየደረጃው የሚያካትት እንዲሆንና ማህበራዊ ፍትህ እንዲነግስ እየተጋን ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ይሄንን ደግሞ ብቻችንን በመንግሥት በጀት ብቻ ልንወጣው ስለማንችል እንደ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ያሉትን የግል ተቋማት አስተባብረን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
“መንግሥት ካስተባበረ የሚተባበር ህዝብ አለ፤ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው” ሲሉም አክለዋል፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ የሚለውን ብሂል የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ ከተባበርን ሃብት አናጣም፤ ብዙ መሥራት እንችላለን፤ ብዙ ስንሰራ ደግሞ የብዙዎችን ህይወት እንለውጣለን፤ ብለዋል፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ የሰው ተኮር መርሃ ግብር፣ ባለሃብቱ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ እያገዘው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለወገን ተብሎ የሚከናወን ተግባር በረከት እንጂ የሚያጎድል ነገር የለውም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጀማል አህመድ፤ በዚህ እምነታችን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 72ሺውም ሠራተኛ መግባባት ላይ ደርሶ፣ 10 ከመቶ ትርፋችንን በየክልሉ ለበጎ ተግባር እያዋልን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በበጎነት መኖሪያ መንደር ምርቃት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶ/ር ሳም ዱ፤ በዚህ እየተመለከትነው ባለው ተግባር እኔ በግሌ ከልብ ተነክቻለሁ ሲሉ የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡
“ልማት ማለት የከበረ ጉዳይ ነው፤ ልማት ማለት የትብብር ጉዳይ ነው፤ ልማት ማለት ሰዎች ትርጉም ያለው ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ ነው” ያሉት ዶ/ር ሳም፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ማየት ጀምረናል ብለዋል፡፡
“ዩኤንዲፒ በኢትዮጵያ ለ10 ዓመታት ቆይቷል፤ አሁን ላይ ግን አዲስ ታሪክ ማየት ጀምረናል፡፡ የከተማ አስተዳደሩና የግሉ ዘርፍ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን ዜጎች ኑሮ ለማሻሻል በጋራ የሰሩትን ታሪክ እየተመለከትን ነው” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
አክለውም ሲናገሩ፤“የግል ተቋማትና መንግሥት ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን ህይወት ሲቀይሩ እየተመለከትን ነው፤ ይህ ለእኔ በየቦታው ሊነገር የሚገባ ድንቅ ታሪክ ነው፡፡” ብለዋል፤ ዶ/ር ሳም ዱ፡፡
Published in
ባህል